የፓኪስታን ፓርላማ “ድመቶች እንኳ በሚፈሯቸው” ግዙፍ አይጦች ተወረረ

የፓኪስታን ፓርላማ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የፓኪስታን ፓርላማ

የፓኪስታን ፓርላማ ችግር ገጥሞታል።

የችግሩ ምንጭ ታዲያ የምክር ቤት አባላቱ አይደሉም። ችግሩን የፈጠሩት የምክር ቤት አባላትን እያሸበሩ ያሉት እና የፓርላማውን ሕንጻ መፈንጫቸው ያደረጉት አይጦች ናቸው። ግዙፍ አይጦች።

የምክር ቤቱ ሕንጻ በከፍተኛ መጠን በአይጥ መወረሩ የታወቀው አንድ የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ ከዓመታት በፊት የተካሄደ የስብሰባ ማስታወሻ ቅጂ እንዲወጣለት ከጠየቀ በኋላ ነው።

ይህ ሠነድ እንዳይሆን ሆኖ በአይጦች ተበልቶ ተገኘ።

“እዚህ ወለል ላይ ያሉት አይጦች በጣም ትልቅ ከመሆናቸው የተነሳ ድመቶች እንኳ ይፈሯቸዋል” ሲሉ የብሔራዊ ምክር ቤት ቃል አቀባይ ዛፋር ሱልጣን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ውርዬ የማትደፍራቸውን አይጦች ለማስወገድ ምክር ቤቱ 4,300 ዶላር በጀት በመመደብ ጨረታ አውጥቷል።

አይጦቹ በርካታ የቋሚ ኮሚቴ ስብሰባዎች የሚካሄድባቸው እና የመመገቢያ አዳራሽ የሚገኝበትን የምክር ቤቱን የመጀመሪያ ወለል ተቆጣጥረዋል።

እንደ ቃል አቀባዩ ዛፋር ሱልጣን ከሆነ፤ አይጦቹ ቀን ላይ ድምጻቸውን አጥፍተው ይቆያሉ። “ሁሉም ወደቤቱ ሲገባ ጠብቀው ምሽት ከያሉበት ይወጡና የማራቶን ሩጫ ይመስል በወለሉ ላይ ይርመሰመሳሉ” ብለዋል።

“አሁን ላይ አብዛኛው ሠራተኛ አይጦቹን ተላምዷል። ለመጀመሪያ ጊዜ ወደዚህ የሚመጣ ሰው ግን በጣም ይፈራቸዋል” ሲሉ ዛፋር ጨምረው ተናግረዋል።

የአገሪቱ ፓርላማ አሁን ላይ አይጦቹን የሚያጠፋለት ድርጅት ፍለጋ በፓኪስታን ጋዜጦች ላይ ማስታወቂያ አስነግሯል።

ይሁን እንጂ እስካሁን ድረስ ግዙፎቹን አይጦች ለማጥፋት ፍላጎት ያሳዩ ኩባንያዎች ሁለት ብቻ ናቸው ተብሏል።