ከሊባኖስ መውጣት ያልቻሉት አፍሪካውያን፡ ‘ከአገር መውጣት እፈልጋለሁ ግን አልቻልኩም’

በሌባኖስ በተከሰተው የፋይናንስ ቀውስ ምክንያት በርካታ ኢትዮጵያውያን ሴቶች ስራቸውን አጥተዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በሌባኖስ በተከሰተው የፋይናንስ ቀውስ ምክንያት በርካታ ኢትዮጵያውያን ሴቶች ስራቸውን አጥተዋል።

ኬንያዊቷ ኤውሊት ጄሮፕ ላለፊት 14 ወራት ከሊባኖስ መዲና ቤይሩት ወጣ ብሎ በሚገኝ ስፍራን መኖሪያዋ አድርጋ ቆይታለች።

ኤውሊት ባለፉት ሳምንታት ከዚህ ቀደም ሰምታ የማታውቀው አሁን ላይ በተደጋጋሚ የምትሰማው ፍንዳታ የሚመስል ድምጽ በጣም ሲረብሻት ቆይቷል።

“በጣም ነው የሚያስፈራው። ቦምብ እንዳልሆነ ይነግሩናል። የአውሮፕላን ድምጽ ነው ይላሉ። ድምጹ ግን በጣም አስፈሪ ነው” ትላለች።

በሊባኖስ መዲና የሚሰማው የፍንዳታ ድምጽ የጦር ጀቶች አየሩን ሰንጥቀው ሲበሩ የሚፈጥሩት ከፍ ያለ ጩኽት ነው።

ከመስከረም 26ቱ የሐማስ ድንገተኛ ጥቃት በኋላ መቀመጫውን በሊባኖስ ባደረገው ሔዝቦላህ እና እስራኤል መካከል በየትኛው ጊዜ ጦርነት ሊያፈነዳ የሚችል ከፍተኛ ውጥረት ተከስቷል።

በኢራን የሚደገፈው ሔዝቦላህ ለፍልሰጤማውያን ድጋፉን ለማሳየት እስራኤል ላይ ጥቃት እያደረሰ መሆኑን ይገልጻል።

ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው የወጭ ዜጎች

በቀጣናው የተፈጠረውን ውጥረት ተከትሎ አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ አውስትራሊያ፣ ፈረንሳይ እና ካናዳ በሊባኖስ የሚገኙ ዜጎቻቸው በአስቸኳይ አገሪቱን ለቅቀው እንዲወጡ ማሳሰቢያ አውጥተዋል።

ይሁን እንጂ በጦርነት ሰጋት ውስጥ ከምትገኘው አገር መውጣት ለአብዛኛዎቹ ቀላል ነገር አይደለም።

ኤውሊት እንደምትለው ከሆነ የቤት ሠራተኞች ሊባኖስ እንደደረሱ አሠሪዎቻቸው ፓስፖርታቸውን እንደሚቀበሏቸው ትናገራለች።

የቤት ሠራተኞች ፓስፖርታቸው እንኳ እጃቸው ላይ ቢኖር ከአገር መውጫ ቪዛ በአገሪቱ መንግሥት ይጠየቃሉ። ከአገር የመውጫ ቪዛው ደግሞ በአሰሪዎቻቸው ይሁንታ ላይ የሚመሠረት ነው።

ይህ አሠራር ወደ 250 ሺህ የሚጠጉ የውጭ አገር ሠራተኞችን በሚያስተዳድረው “ካፋላ” የተባለ ሥርዓት ላይ ተደንግጓል።

የካፋላ ሥርዓት የሠራተኞችን መብት በመገደብ፤ የአገሪቱ ዜጎች ወይም ድርጅቶች የውጪ ዜጎችን እንዲቀጥሩ ያስችላል።

ምንም እንኳ በዚህ ሥርዓት ላይ ማሻሻያ እንዲደረግ ተደጋጋሚ ጥሪዎች ቢቀርቡም የካፋላ ሥርዓት በሌሎች የአረብ አገራት ጭምር ተግባራዊ እየተደገ ይገኛል።

የእስራኤል ጦር ወደ ሌባኖስ ሲተኩስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የእስራኤል ጦር ወደ ሌባኖስ ሲተኩስ

ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (አይኦኤም) ባልደረባ የሆኑት ዳንኤላ ሮቪና በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት የዜጎችን መብት ከሚያስከብሩ መርሆች መካከል አንዱ የትኛውም ሰው ወደ ትውልድ አገሩ እንዲመለስ ከየትኛውም አገር ለቅቆ እንዲወጣ መፍቀድ ነው ይላሉ።

ዳንኤላ ከዚህ በተጨማሪ አንድ ሰው እየኖረ ባለበት አገር ግጭት የሚያጋጥም ከሆነ የጄኔቫው ኮንቬንሽን የሰብዓዊ መብቶች ዓለም አቀፍ ሕግ ተግባራዊ ይደረጋል ይላሉ። አገራት በጄኔቫ ኮንቬንሽን በአንድ አገር ግጭት ሊከሰት ሲል ወይም ከተከሰተ ሰላማዊ ሰዎች ከአገር እንዲወጡ ተስማምተዋል።

በእስራኤል እና በሔዝቦላህ መካከል ውጥረት የተፈጠረው ከ40 ዓመታት በፊት እስራኤል በደቡባዊ ሊባኖስ በሰፈረችበት ወቅት ነው።

በሁለቱ ጎረቤት አገራት መካከል እአአ 2006 ላይ ጦርነት ተከስቶ ነበር። በወቅቱ ሔዝቦላህ ድንበር ተሻጋሪ ጥቃቶችን እስራኤል ላይ ሲፈጸም ነበር።

በአሁኑ ወቅትም በመካከለኛው ምሥራቅ ያለው ውጥረት ወደለየለት ጦርነት መቀየሩ አይቀርም እየተባለ ነው።

ይሁን እንጂ የኤውሊታ ቀጣሪዎች ኬንያዊቷ በሥራዋ እንድትቀጥል ይፈልጋሉ።

“አሁን ያለው ዓይነት ሁኔታ ለበርካታ ዓመታት የኖረ ነው በማለት ምንም የሚያሰጋ ነገር የለም ይሉኛል” የምትለው ኤውሊታ፤ አሁን ያለው ውጥረት እና የምትሰማው የፍንዳታ ድምጽ ግን በጣም እንደሚረብሻት ተናግራ፤ “እኔ የምፈልገው ወደ አገሬ መመለስ ነው” ትላለች።

ዋጋው የማይቀመሰው የአየር ቲኬት

አውሊታ እና ሌሎች የቤት ሠራተኞች ከሊባኖስ የሚያስወጣቸውን ፓስፖርታቸውን እና ቪዛ ቢያገኙ እንኳ ሌላ ችግር ከፊታቸው አለ።

“ያሉት በረራዎች በጣም ትንሽ ከመሆናቸው በላይ በጣም ውድ ናቸው” ትላለች።

ከሊባኖስ ወደ ኬንያ ለሚደረግ በረራ 1000 የአሜሪካ ዶላር ይጠየቅበታል። ይህ ደግሞ ለአውሊታ እና መሰሎቿ በጣም ውድ ነው።

በሊባኖስ የኢትዮጵያውያን ሠራተኞች መብት ለማስከበር የሚጥር የመረዳጃ ማኅበር ያቋቋመችው ባንቺ ይመር አማካይ የቤት ሠራተኞች ደሞዝ 150 ዶላር ነው ትላለች።

ይሁን እንጂ በሊባኖስ ባለው የከፋ ምጣኔ ሀብታዊ ቀውስ ጨርሶ ደሞዝ ያመይከፈላቸው በርካቶች ናቸው ትላለች።

ሌላኛዋ ኬንያዊት ቺኩ ወደ ትውልድ አገሯ ለመመለስ የአየር ቲኬት መግዛት ሳትችል መቅረቷን ትናገራለች።

ቺኩ በምዕራብ ሊባኖስ በምትገኘው ባብዳ በተባለችው ከተማ አንድ ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ እየሠራች ቆይታለች።

“ወደ አገሬ መመለስ እፈልጋለሁ። ግን የአየር ቲኬት ዋጋ በጣም ውድ ነው። እናት እና አባቴ ቲኬቱን እንዳይገዙልኝ አቅም የላቸውም” ትላለች።

ልክ እንደ አውሊታ ሁሉ፤ ቺኩ አሠሪዎቿ ከአገር እንድትወጣ እንደማይፈቅዱላት ትናገራለች።

“የገባሽውን ውል ስላልጨረስሽ መሄድ አትችይም ይሉኛል” የምትለው ቺኩ፤ “ነገር ግን ይህ ኮንትራት ከሕይወቴ በላይ ነው?" ስትል ትጠይቃለች።

ቢቢሲ የሊባኖስ የሠራተኛ ሚኒስቴር በዚህእ ጉዳይ ላይ አስተያየት እንዲሰጥ ያቀረበው ጥያቄ ምላሽ አላገኘም።

ሐምሌ 2016 ላይ እስራኤል ሔዝቦላን ዒላማ ያደረገ በሌባኖስ ከተማ ላይ ጥቃት አድርሳ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ሐምሌ 2016 ላይ እስራኤል ሔዝቦላን ዒላማ ያደረገ በሌባኖስ ከተማ ላይ ጥቃት አድርሳ ነበር።

የአፍሪካ መንግሥታት ዜጎቻቸውን "ለማስወጣት ዝግጁ ናቸው"

በኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥ የሥራ ኃላፊ የሆኑት ሮስሊን ንጆጉ መንግሥት ፓስፖርት ለሌላቸው ዜጎች የአስቸኳይ ጊዜ የጉዞ ሠነድ ማዘጋጀት ይችላል ይላሉ።

እንደ ሮስሊን ከሆነ የኬንያ መንግሥት አስፈላጊ ሆኖ ካገኘው ዜጎች በአስቸኳይ ከሌባኖስ ለማስወጣት በረራዎችን ማዘጋጀት የሚያስችል ዕቅድ አለን ብለዋል።

"ወደ 26ሺህ የሚጠጉ ኬንያውያን በሌባኖስ ይገኛሉ። እስካሁን ድረስ ከሌባኖስ ለማስወጣት ወደ 1ሺህ 500 የሚጠጉ ዜጎችን መዝግበናል" ብለዋል።

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዲሁ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ዜጎችን ከሌባኖስ ለማስወጣት እቅድ መነደፉን ተናግረዋል።

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ነብዩ ተድላ "አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ዜጎችን እና ዲፕሎማቶችን ከሎባኖስ ለማውስጣት እቅድ ተነድፏል" ብለዋል።

ባንቺ ይመር ግን ከእስራኤል እና ጋዛ ግጭት በፊት እንኳ ከሌባኖስ መውጣት ፈልገው መውጭ አጥተው በአገሪቱ የሚገኙ በርካታ ኢትዮጵያውያን መኖራቸውን ትናገራለች።

እአአ 2020 ሌባኖስ ያጋጠማት ምጣኔ ሃብታዊ ቀውስ በርካታ ኢትዮጵያውያንን ከሥራ አስወጥቶ ነበር።

በአሁኑ ወቅት በርካታ ምዕራባውያን መንግሥታት ዜጎቻቸውን ከሌባኖስ ለማስወጣት እየጣሩ በሚገኙበት ወቅት አንዳንዶች በሰው አገር እንደተረሱ ያስባሉ።

ቺኩ ወደ ኬንያ የሚያስገባትን የአየር ቲኬት ለመግዛት ገንዘብ መቆጠብ ከጀመረች ሰነባብታለች።

"ሰርተው ገንዘብ መቆጠብ የማይችሉትስ ዕጣቸው ምንድን ነው የሚሆነው" ትላለች።