የአዲስ አበባ ሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት “በከተማዋ መግቢያ” ቦታዎች ሊከናወን ነው

የፎቶው ባለመብት, Mayor office of Addis Ababa
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሁለተኛውን ምዕራፍ የኮሪደር ልማት እንደ ኮዬ አደባባይ፣ ጎሮ እና ሰሚት ባሉ “የከተማዋ መግቢያ” እና “ማስፋፊያ ላይ በሚገኙ” አካባቢዎች ሊያከናውን ነው።
43 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ሁለተኛው ምዕራፍ ግንባታ፤ ከሸገር ከተማ የኮሪደር ልማት ጋር “በማስተሳሰር” እንዲከናወን ታቅዷል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር “የኮሪደር ልማት” ሲል የጠራውን ዋና ዋና መንገዶችን የማስዋብ፣ የእግረኛ መንገድን የማስፋት፣ መዝናኛ ቦታዎችን የመገንባት እንዲሁም የመንገድ ዳር መብራት እና ቴሌኮሚዩኒኬሽን መስመሮችን በዘመናዊ መንገድ የመዘርጋት ሥራ የጀመረው በዚህ ዓመት የካቲት ወር ላይ ነበር።
የከተማዋን ታዋቂ እና ነባር አካባቢዎችን የሸፈነው የመጀመሪያው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት፤ አምስት መስመሮችን የያዘ ነው። በመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታ ከተከናወነባቸው አካባቢዎች መካከል ፒያሳ፣ አራት ኪሎ፣ ቦሌ፣ መገናኛ፣ ሜክሲኮ እና ሲኤምሲ ይገኙበታል።
የኮሪደር ልማቱ ሲከናወን ተለይም በፒያሳ አካባቢ ጥንታዊ ኪነ ሕንጻዎችን ጨምሮ በርካታ ቤቶች የፈረሱ ሲሆን፣ በዚሁ ግንባታ ምክንያት 11 ሺህ ገደማ ነዋሪዎች ከአካባቢው መነሳታቸውን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ አስታውቀው ነበር።
የከተማ አስተዳደሩ፤ በድምሩ 48 ኪሎ ሜትር ለሚሸፍነው ለመጀመሪያው ዙር የኮሪደር ልማት፤ 33 ቢሊዮን ብር ወጪ ማድረጉንም መግለጻቸውም ይታወሳል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ግምገማ እየተደረገበት የተካሄደው ይህ የኮሪደር ልማት፤ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወ/ሮ አዳነችን ጨምሮ ከፍተኛ የከተማዋ ኃላፊዎች ግንባታ የሚከናወንባቸውን መስመሮች ተከፋፍለው ሥራውን መርተውታል።
ከኮሪደር ልማቱ መስመሮች ውስጥ ቀድሞ የተመረቀው በከንቲባዋ ክትትል ስር የነበረው ከአራት ኪሎ ፒያሳ የሚደርሰው መንድ ሲሆን፣ ባለፈው ሳምንት ሰኞ የተመረቀውን ከመገናኛ ሲኤምሲ የተዘረጋውን ልማት ጨምሮ ሌሎቹ መስመሮች በተለያዩ ጊዜያት ክፍት ሆነዋል።

የፎቶው ባለመብት, Office of the Prime Minister
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፤ በመጀመሪያው ምዕራፍ የገነባቸውን እነዚህን “መሃል ከተማ” የሚገኙ መስመሮች፤ “የከተማዋ መግቢያ ተብለው ከተለዩ ቦታዎች እና በማስፋፊያ [ላይ] ከሚገኙ አካባቢዎች ጋር ለማስተሳሰር” ማቀዱን ቢቢሲ ከከተማ አስተዳደሩ ጥናት ተመልክቷል።
በምዕራፍ ሁለት የሚከናወኑ የኮሪደር ልማት ሥራዎች ላይ የተደረገው ይህ ጥናት በከተማዋ የፕላን እና ልማት ቢሮ የተዘጋጀ ነው። በአጠቃላይ 43 ኪሎ ሜትር ርዝመት የሚኖረው የምዕራፍ ሁለት የኮሪደር ልማት፤ ቦሌ፣ ለሚ ኩራ እና አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተሞችን እንደሚያካትት የጥናት ሰነዱ ያሳያል።
ሁለተኛው ምዕራፍ ግንባታ በአምስት መስመሮች ላይ የሚከናወን ነው። ከእነዚህ መስመሮች ውስጥ ከፍተኛ ዝርመት ያለው “ከአንበሳ ጋራዥ - መብራት ኃይል - ጎሮ - ኮዬ አደባባይ” የሚደርሰው መንገድ ነው። ይህ መስመር 14.8 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ነው።
“ከቦሌ ካርጎ - ቡልቡላ - ኮዬ አደባባይ” የሚደርሰው ሁለተኛው ረጅም መስመር ደግሞ 12.8 ኪሎ ሜትር ርዝመት አለው። በሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ውስጥ የተካተተው ሌላኛው መስመር “ከቦሌ ድልድይ” ተነስቶ “በቦሌ ሆምስ - በአየር መንገድ ቪአይፒ መግቢያ” አድርጎ መዳረሻው “ጎሮ” አካባቢ ነው።
“ከጎሮ አደባባይ” የሚነሳው አራተኛው መስመር አምስት ኪሎ ሜትር ርዝመት እንደሚኖረው በጥናት ሰነዱ ላይ ሰፍሯል። ይህ መስመር “ከጎሮ አደባባይ - በሰባ ሁለት አካባቢ - ሰሚት ለስላሳ ፋብሪካ አካባቢ - ፍየል ቤት - ሲ ኤም ሲ አደባባይ” አካባቢዎችን ይሸፍናል።
“ከፍየል ቤት - ፊጋ - ሰሃሊተ ምህረት አደባባይ - ጃክሮስ” የሚደርሰው አምስተኛው መስመር ደግሞ 5.9 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ነው።
በከተማዋ የአስተዳደር ወሰን ማብቂያ አካባቢ የሚገኙ አካባቢዎችን ያካተተው ሁለተኛው ምዕራፍ ግንባታ፤ “በትግበራ ላይ ከሚገኙ የሸገር [ከተማ] የልማት ኮሪደሮች ጋር በማስተሳሰር የሚከናወን” እንደሆነ የጥናት ሰነዱ ያመለክታል።
በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚገኙ አምስት ከተሞችን በአንድ የከተማ አስተዳደር ስር በማድረግ ባለፈው ዓመት የተመሠረተው የሸገር ከተማ፤ ሰኔ ወር ላይ “ዘጠኝ የልማት ኮሪደሮችን” በመለየት ወደ ሥራ ለመግባት በዝግጅት ላይ መሆኑን አስታውቆ ነበር።
የአዲስ አበባ ከተማ ፕላን እና ልማት ቢሮ ያዘጋጀው የጥናት ሰነድ፤ ከኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ ጋር በሚዋሰኑ አካባቢዎች የሚገኙ የኮሪደር ልማት ሥራዎች ከአጎራባቹ ከተማ ጋር “ወጥ የሆነ ዲዛይን ተዘጋጅቶላቸው በጋራ የሚለሙበትን ማዕቀፍ መፍጠር” እንደሚያስፈልግ አስፍሯል።
በሁለተኛው ምዕራፍ ውስጥ በተካተቱት አካባቢዎች ላይ የሚከናወነው የኮሪደር ልማት እንደ መጀመሪያው ምዕራፍ ሁሉ የእግረኛ መንገድን የማስፋት ውጥን ያለው ነው። በዋና መንገድ (አስፓልት) ጠርዝ የሚገኙ አካባቢዎች የአስር ሜትር ስፋት እንዲኖራቸው እንደታሰበ በጥናቱ ላይ ተጠቅሷል።
አምስት ሜትሩ የሚውለው ለእግረኛ መንገድ ሲሆን፤ የሳይክል መስመር ደግሞ ሦስት ሜትር ስፋት ይኖረዋል። በአስፓልቱ በኩል የሚኖረው ቀሪው ሁለት ሜትር ለአረንጓዴ ልማት ቦታ እንደሚውል ጥናቱ ያስረዳል።

የፎቶው ባለመብት, Bole communication
በአምስቱ መስመሮች የሚገነባው የኮሪደር ልማት በሌሎች አካባቢዎች እንደተሠራው ሁሉ፤ የታክሲ ማቆሚያ ቦታዎችን፣ የሕዝብ መፀዳጃ፣ የመዝናኛ ቦታዎች እንዲሁም በከተማ፣ ክፍለ ከተማ እና ወረዳ ደረጃ የሚገነቡ ፓርኮችን እንደሚያካትት ጥናቱ ገልጿል።
የመኖሪያ ቤቶች ግንባታም የዕቅዱ አካል እንደሆነ የሚያመለክተው ጥናቱ፤ “ከቦሌ ሆምስ - አንበሳ ጋራዥ -አይሲቲ ፓርክ” ባለው አካባቢ ውስጥ “የማስፈሪያ ቦታ” (relocation site) እንደሚኖር ያስረዳል። በዚህ ስፍራ ላይ “ቅይጥ የመኖሪያ ቤቶች” (mixed residence) ይገነባሉ ተብሏል።
በኮሪደር ልማቱ ምክንያት “ሙሉ በሙሉ የሚነሱ” ቦታዎች ጉዳይ በሰነዱ ላይ “ውሳኔ” እንዲሰጥባቸው ከተዘረዘሩ ነጥቦች መካከል ነው። ነባር ግንባታዎች “በልማቱ ውስጥ የሚካተቱበት መንገድ” መፈጠር እንዳለበት የሚያስገነዝበው ሰነዱ፤ የኮሪደር ልማቱ በሚከናወንባቸው መስመሮች ላይ ለሚገኙ ሕንጻዎች ሁለት አማራጮችን አስቀምጧል።
“ከሁለት ወለል በላይ” ላላቸው ሕንጻዎቸ የተቀመጠው አማራጭ “ታዛ (Arcade) እንዲያካትቱ ማድረግ” የሚል ነው። ይህ ዓይነቱ አማራጭ የመጀመሪያው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት በተካሄደባቸው አካባቢዎች በሚገኙ ሕንጻዎች ላይም የተተገበረ ሲሆን፣ የህንጻዎቹ የምድር ወለል የፊት ለፊት ገጽታ ፈርሶ ቦታው ለእግረኛ ክፍት እንዲሆን ተደርጓል።
ከሁለት ወለል በታች ላሉ ግንባታዎች የተቀመጠው አማራጭ፤ “በጥናቱ መሠረት ወደ ልማት ውስጥ ማስገባት” የሚል ነው። በምዕራፍ ሁለት በተካተቱ ቦታዎች ለሚገኙ “ይዞታዎችን የመለየት፣ የመተንተን፣ ግምት እና የምትክ አገልግሎቶችን የመለየት ሥራ” እየተከናወነ መሆኑን ጥናቱ ይጠቅሳል።
በሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ውስጥ ከተካተቱት መስመሮች መካከል በቦሌ ክፍለ ከተማ የሚገኙት ሦስት ግንባታዎች “በቅርቡ” እንደተጀመሩ የክፍለ ከተማው የኮሚዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ለቢቢሲ አረጋግጧል።
በለሚ ኩራ ከፍለ ከተማ የሚገኙት መስመሮች ላይ ደግሞ ሥራውን ለማስጀመር “ከሕብረተሰቡ ጋር ውይይት እየተደረገ” መሆኑን የክፍለ ከተማው የኮሚዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት አስታውቋል።















