ባለፉት ቀናት ውጥረት ውስጥ የገቡት አንዳንድ የአማራ ክልል ዋና ዋና ከተሞች ሰሞናዊ ሁኔታ

ካለፈው ሳምንት ማብቂያ ወዲህ ባሉት ቀናት በአማራ ክልል አንዳንድ ከተሞች የትራንስፖርት እና ሌሎች እንቅስቃሴዎች መስተጓጎላቸውን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናገሩ።
በክልሉ በመንግሥት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ሲካሄድ አንድ ዓመት የሞላውን የትጥቅ ግጭት ተከትሎ አንዳንድ ከተሞች አሁንም መረጋጋት እንደራቃቸው ነው።
ከሰሞኑም ‘የፋኖ ታጣቂዎች መልዕክት አስተላልፈዋል’ በሚል የክልሉ መቀመጫ የሆነችውን ባሕር ዳር ከተማን ጨምሮ በሌሎች ዋና ዋና ከተሞች የዕለተ ተዕለት እንቅስቃሴዎች መስተጓጎላቸውን ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ተናግረዋል።
በአንዳንድ ከተሞችም የተኩስ ልውውጥ እንደነበር ቢቢሲ ከነዋሪዎች ሰምቷል።
ነዋሪዎች የእንቅስቃሴ መስተጓጎሉ የደኅንነት ስጋት እንደደቀነባቸው እና በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው ላይ ከባድ ተፅዕኖ እያስከተለ እንደሆነ ተናግረዋል።
ቢቢሲ ባሕር ዳር፣ ወልዲያ፣ ሸዋ ሮቢት እና ደብረ ማርቆስ ከተሞች ዛሬ ሰኞን ጨምሮ ባለፉት ቀናት እንዴት እንደሰነበቱ ነዋሪዎችን በማናገር ቃኝቷል።
ባለፉት ቀናት እና ዛሬ ሰኞ ነሐሴ 13/2016 ዓ.ም. በከተሞቻው ስላለው ሁኔታ ለቢቢሲ የተናገሩ የየከተሞቹ ነዋሪዎች ለደኅንነታቸው ሲሉ ስማቸው እንዲጠቀስ አልፈቀዱም።
በተጨማሪም ቢቢሲ የሚመለከታቸውን የክልሉን እና የከተሞቹን ኃላፊዎች ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።
ባሕር ዳር ከተማ
የክልሉ ዋና መቀመጫ በሆነችው ባሕር ዳር ከተማ አዲስ ውጥረት ከነገሰ ዛሬ አራተኛ ቀኑን ይዟል።
ባሳለፍነው ሳምንት አርብ ‘ከፋኖ ታጣቂዎች መልዕክት ተላልፏል’ በሚል የንግድ ተቋማት ተዘግተው የነበሩ ሲሆን፣ የመንግሥት እና ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማትም በፀጥታ ሥጋት ምክንያት ዝግ ሆነው እንደነበር ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገልጸው ነበር።
ቢቢሲ አርብ ዕለት ያነጋገራቸው አንድ ነዋሪ፣ ማንነታቸውን ከማያውቋቸው ሰዎች አምስት የሚደርሱ የጽሑፍ መልዕክቶችን እንደደረሳቸው ተናግረዋል።
የደረሳቸው መልዕክትም ‘ፋኖ አርብ 7፡00 ላይ ወደ ከተማዋ ሊገባ ስለሆነ፤ ቤታችሁ በመቀመጥ ትብብር እንድታደርጉልን፣ ካልሆነ ለሚደርስባችሁ አደጋ ኃላፊነቱን አንወስድም” የሚል ነው ይላሉ።
ሌላ የከተማዋ ነዋሪም እንዲሁ አርብ ዕለት ከቀኑ 7፡00 ጀምሮ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ አለመኖሩን እና በከተማ ውስጥ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ይታዩ እንደነበር ተናግረዋል።
ይህ ከመሆኑ ቀደም ብሎም በከተማዋ አንዳንድ አካባቢዎች የቦምብ ፍንዳታዎች እንደነበሩ ነዋሪዎቹ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
የክልሉ ባለሥልጣናት የዚያኑ ዕለት በሰጡት መግለጫ ከተማዋ ውስጥ ለስጋት የሚዳርግ ምንም ነገር እንደሌለ ገልጸው፣ የክልሉ የፀጥታ ኃይል ከፌደራል መንግሥት ጋር በመሆን ወታደራዊ እርምጃ ለመውሰድ በቂ ኃይል እንዳለው አስታውቀው ነበር።
ከቦምብ ፍንዳታው ጋር በተያያዘም የተጠረጠሩ የተወሰኑ ሰዎች መያዛቸውን እና ሌሎችን ለመያዝ እየተሠራ መሆኑንም በክልሉ ኮሚዩኒኬሽን የማኅበራዊ ገጽ ላይ የተጋራው የሰላም እና ፀጥታ ቢሮ መግለጫ አመልክቷል።
ሆኖም ግን በባሕር ዳር ከተማ አጋጥመዋል ስለተባሉት የቦምብ ፍንዳታዎች መግለጫው ዝርዝር መረጃ አልሰጠም።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ቅዳሜ እና እሑድ የተወሰነ የሰዎች እንቅስቃሴ እንደነበር ገልጸው፣ እሑድ ከቀ7፡00 ሰዓት በኋላ ግን በከተማዋ ሦስት አቅጣጫዎች የተኩስ ልውውጥ እንደነበር ተናግረዋል።
በዘንዘልማ፣ በበላይ ዘለቀ አውሮፕላን ማረፊያ አቅራቢያ፣ እንዲሁም በሰባት አሚት ማረሚያ ቤት አቅጣጫ በከባድ መሣሪያ የታገዙ የተኩስ ልውውጦች እንደነበሩ ነዋሪዎቹ ገልጸዋል።
አባይ ማዶ አካባቢ ነዋሪ እንደሆኑ የተናገሩ አንድ ነዋሪ በዘንዘልማ አካባቢ ሲሰማ የነበረው ተኩስ እስከ ሌሊቱ 8፡00 ድረስ እንደነበርና በአውሮፕላን ማረፊያው አቅራቢያ ያለው ደግሞ እስከ እሁድ ምሽት 3፡00 ድረስ መቆየቱን ተናግረዋል።
ዛሬ [ሰኞ ነሐሴ 13/2016] የተወሰኑ ባለሦስት እግር ተሽከርካሪዎች (ባጃጆች) እና ጥቂት ታክሲዎች እንዲሁም ሰዎችም በእግራቸው ሲንቀሳቀሱ አልፎ አልፎ እንደሚታዩ አንድ ሌላ ነዋሪ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ሆኖም የንግድ ተቋማት እና የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችም ሙሉ በሙሉ ወደ አገልግሎት አልተመለሱም ብለዋል።
እሁድ ዕለት በከተማዋ ቀበሌ 11 አካባቢ ከፍተኛ የተኩስ እንደነበር የገለጹት ነዋሪው፣ “ውጥረቱ አሁንም እንዳለ ነው” ብለዋል።
የመከላከያ ሠራዊት እና የአድማ ብተና አባላትም በፓትሮል መኪና ሲንቀሳቀሱ መመልከታቸውን ነዋሪው ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ወልዲያ ከተማ
ከሰሜኑ ጦርነት ጀምሮ የፀጥታ ስጋት ተለይቷት የማያውቀው የሰሜን ወሎ ዞን መቀመጫ በሆነችው ወልዲያ ከተማ ዛሬ [ሰኞ] የትራንስፖርት እንቅስቃሴዎች መቋረጣቸውን ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሁለት ነዋሪዎች ገልጸዋል።
ነዋሪዎቹ ከወልዲያ ተነስተው ወደ ቆቦ፣ ወደ ደሴ እና ወደ ጎንደር መስመር የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ዛሬ ጠዋት ጀምሮ ተቋርጧል ብለዋል።
ጠዋት ላይ ወደ መናኸሪያ ሄደው እንደነበር የጠቀሱ አንድ ነዋሪ፣ ከከተማዋ ወደ ሌሎች ከተሞች የሚሄዱ ተሽከርካሪዎች እየተሰማሩ አለመሆናቸውን ተናግረዋል።
“አሽከርካሪዎቹን ስንጠይቃቸው ትናንት [እሁድ] ከመርሳ በኩል ሲመጡ ‘ነገ እንዳትመለሱ’ እያሉ በታጣቂዎች ትዕዛዝ እንደተሰጣቸው ነው የነገሩን፤ በአንዳንድ አካባቢዎችም መልዕክቶች ተለጥፈው ተመልክተናል።” ብለዋል ነዋሪው።
የትራንስፖርት እንቅስቃሴ እንዲቆም 'በፋኖ ትዕዛዝ ተላልፏል' የሚል መረጃ ከተሠራጨ በኋላ እንቅስቃሴው መቆሙንም ነዋሪዎቹ አስረድተዋል።
በከተማው ውስጥ አልፎ አልፎ ከሚታይ የባጃጅ እና የአምቡላንስ አገልግሎት በስተቀር የወትሮው እንቅስቃሴ እንደማይታይ ተናግረዋል።
ሌላ ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪም ከከተማዋም ሆነ ወደ ከተማዋ የሚገባ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ አለመኖሩን ጠቅሰው፤ ምክንያቱን ግን አላውቅም ብለዋል።
“ቢራ እና ማዳበሪያ ጨምሮ ሌሎች ምርቶችን የጫኑ ከባድ ተሽከርካሪዎችም እንቅስቃሴያቸው ተገድቦ ከተማዋን አጨናንቀው ነው ያሉት” ብለዋል ነዋሪው።
በወልዲያ ከተማ በፋኖ ታጣቂዎች እና በመንግሥት ኃይሎች መካከል ግጭት ከተፈጠረ አንስቶ በተደጋጋሚ የተኩስ ልውውጦች ተካሂደዋል። በከተማዋ የሚገኙ ፖሊስ ጣቢያዎች እና ማረሚያ ቤቶች ላይም በተደጋጋሚ ጥቃት ተሰንዝሮባቸዋል።
ሸዋ ሮቢት
በክልሉ፣ ሰሜን ሸዋ ዞን ውስጥ በምትገኘው ሸዋ ሮቢት ከተማም ከዛሬ [ሰኞ] ጠዋት ጀምሮ እንቅስቃሴ አለመኖሩን ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ገልጸዋል።
ከአዲስ አበባ ወደ ደሴ እንዲሁም ከደሴ ወደ አዲስ አበባ የትራንስፖርት አገልግሎትም ተቋርጧል ብለዋል።
እንደ ነዋሪዎቹ ከሆነ በከተማዋ ውስጥ አልፎ አልፎ ከሚታዩ ከባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪዎች (ባጃጆች) እና የፈረስ ጋሪዎች በስተቀር የወትሮው እንቅስቃሴ የለም።
“ጠዋት ስነሳ ነገሮች ተዘጋግተው ተመለከትኩ” የሚሉት አንድ ነዋሪ፣ ባንኮች ክፍት መሆናቸውን፤ ነገር ግን የሰዎች እንቅስቃሴ አለመኖሩን ተናግረዋል።
በከተማው የክልሉ የአድማ ብተና ኃይሎች ሲንቀሳቀሱ መመልከታቸንም እኝሁ ነዋሪ ገልጸዋል።
ሌሎች ሁለት ነዋሪዎችም በከተማዋ የወትሮው የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ መስተጓጎሉን ገልጸው፣ ይህ የሆነው “የፋኖ ሸዋ ጠቅላይ ግዛት በነሐሴ 13 እና 14/2016 ዓ.ም. ምንም ዓይነት የትራንስፖርት እንቅስቃሴ እንዳይኖር ትዕዛዝ አስተላልፏል” የሚል መረጃ ከተሠራጨ በኋላ መሆኑን ገልጸዋል።
ነዋሪዎቹ በከተማዋ ውስጥ የጥይት ድምጽ ባይሰማም “ድባቡ ደስ አይልም” ብለዋል።
ደብረ ማርቆስ
በምሥራቅ ጎጃሟ ደብረ ማርቆስም ከነሐሴ 7/2016 ዓ.ም. ጀምሮ ብዙም እንቅስቃሴ አለመኖሩን ሦስት ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገልጸዋል።
እስከ ትናንት [እሁድ] ድረስ ባጃጆች በከተማዋ ይንቀሳቀሱ እንደነበር የገለጹት ነዋሪዎቹ፣ “ከዛሬ ጀምሮ ግን የእነርሱም እንቅስቃሴ ቆሟል፤ ከአንዳንድ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች እና ባንኮች በስተቀር ሁሉም አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ዝግ ናቸው” ብለዋል።
ነዋሪዎቹ እንዳሉት ከአዲስ አበባ ወደ ባሕር ዳር እንዲሁም ከባሕር ዳር ወደ አዲስ አበባ እንዲሁም ወደ ሌሎች የወረዳ ከተሞች የሚደረግ የትራንስፖርት እንቅስቃሴም የለም።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሁለት ነዋሪዎች ይህ እንቅስቃሴ የተቋረጠው “ከነሐሴ 7/2016 ዓ.ም. ጀምሮ ላልተወሰነ ጊዜ ፋኖዎች እንቅስቀሴ እንዲቆም መግለጫ ሰጥተዋል” የሚል መረጃ ከተሰራጨ በኋላ መሆኑን ገልጸዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ዛሬ [እሁድ ለሰኞ አጥቢያ] ሌሊት 6፡30 አካባቢ ማረሚያ ቤት እና መምህራን ኮሌጅ አካባቢ፣ ምክንያቱን ባያውቁትም ለ10 ደቂቃ ገደማ የቆየ የተኩስ ልውውጥ እንደነበር ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።
ሌላኛው ነዋሪም ዛሬ [ሰኞ] ከጠዋት ጀምሮ በከተማዋ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ አለመኖሩን ገልጸው፣ ንጋት 11፡30 ገደማ በተለምዶ ቦሌ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ለ30 ደቂቃ የዘለቀ የተኩስ ለውውጥ እንደነበር ገልጸዋል።
ነዋሪው የትራንስፖርት እንቅስቃሴ የተቋረጠበትንም ሆነ የተኩስ ልውውጡ ምክንያት ምን እንደሆነ አላውቅም ብለዋል።
በከተማዋ ከወትሮው የተለየ ባይሆንም የአድማ ብተና ኃይሎች እና የመከላከያ ሠራዊት አባላት በፓትሮል ሲንቀሳቀሱ እንደሚታዩ አልፎ አልፎም ሰዎች በእግራቸው ሲንቀሳቀሱ እንደሚታዩ ነዋሪዎቹ ገልጸዋል።
የከተማዋ አስተዳደር ግን ከተማዋ በመደበኛ እንቅስቃሴ ላይ ናት ብሏል።
የክልሉ ወቅታዊ ሁኔታ
በአማራ ክልል፣ ከአንድ ዓመት በፊት የፌደራል መንግሥት የክልሉን ልዩ ኃይል ትጥቅ ለማስፈታት እና እንደ አዲስ ለማዋቀር የወሰደውን እርምጃ ተከትሎ የፋኖ ታጣቂዎች እና የመንግሥት ኃይሎች መካከል ግጭት ውስጥ መግባታቸው ይታወሳል።
በተደጋጋሚ በተለያዩ አካባቢዎች የሚከሰቱ ግጭቶችን ተከትሎም ሕጻናትን ጨምሮ በርካታ ሰላማዊ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል። በሺዎች የሚቆጠሩ ትምህርት ቤቶችም ከአገልግሎት ውጪ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በቅርቡ ባወጣው ሪፖርት ገልጿል።
በክልሉ ያለው እንቅስቃሴ በመስተጓጎሉም በመድኃኒት እና መሠረታዊ አቅርቦት ላይ እጥረት እና የዋጋ ንረት መከሰቱን ነዋሪዎች ሲገልጹ ቆይተዋል።
ግጭቱን ለመፍታት የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን በተለያየ ጊዜ ሲገለጽ ቢቆይም እስካሁን ያስገኘው ውጤት አልታየም።
የፋኖ ታጣቂዎችን ከመንግሥት ጋር ለማቀራረብ በቅርቡ በክልሉ የተቋቋመው የሰላም ካውንስልም ‘ፋኖ ወጥ አደረጃጀት ባለመኖሩ ‘ዓላማዬን ላሳካ አልቻልኩም’ ሲል ለቢቢሲ ገልጿል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድም በቅርቡ በተካሄደ አንድ ስብሰባ ላይ “በአማራ ክልል ከሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ጋር ንግግር ከተጀመረ ውሎ ያደረ ጉዳይ” መሆኑን ቢጠቁሙም፣ ስለንግግሩም ሆነ ስላለበት ደረጃ በዝርዝር ያሉት ነገር የለም።






![[ከላይ ጀምሮ ከቀኝ ወደ ግራ] እስክንድር ነጋ፣ ምሬ ወዳጆ፣ ዘመነ ካሴ፣ ሐብቴ ወልዴ፣ መከታው ማሞ እና ባየ ቀናው](https://ichef.bbci.co.uk/ace/ws/660/cpsprodpb/4360/live/aac27780-50c7-11ef-aebc-6de4d31bf5cd.jpg.webp)








