መንግሥት እና ፋኖን ለማቀራረብ የሚጥረው የሰላም ካውንስል “ውጤት ማምጣት አልቻልኩም” አለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአማራ ክልል በመንግሥት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል እየተካሄደ አንድ ዓመት የሆነውን ግጭት በንግግር ለማስቆም በሚል ዓላማ የተቋቋመው የሰላም ካውንስል እንቅፋቶች እንደገጠሙት አስታወቀ።
ከአዲስ አበባ እና ከአማራ ክልል የተለያዩ ዞኖች የተወጣጡ “የማኅበረሰብ ክፍሎች ተወካዮች እና ተጽዕኖ ፈጣሪዎች” የተካተቱበት የሰላም ካውንስሉ ሰኔ 18/2016 ዓ.ም. በባሕር ዳር ከተማ በተካሄደው ‘የሰላም ጉባኤ’ ላይ ነበር የተቋቋመው።
አስራ አምስት አባላት ያሉት የሰላም ካውንስሉ በክልሉ ያለውን ግጭት ለማስቆም ለሁሉም ወገኖች የሰላም ጥሪውን አቅርቦ እንቅስቃሴ ከጀመረ ሁለተኛ ወሩን ሊደፍን በተቃረበበት ጊዜ ነው ጥረቱ እንቅፋቶች እንደተጋረጡበት ያሳወቀው።
መንግሥት እና የፋኖ ኃይሎች “ያለ ቅድመ ሁኔታ፣ በየትኛውም ቦታ፣ በማንኛውም አደራዳሪ” እንዲነጋገሩ ለማስቻል የአመቻችነት ሚናን ይዞ የተነሳው ካውንስሉ፤ በአማራ ክልል “እርስ በርስ ጦርነት” እየተደገ መሆኑን በመጀመሪያ መግለጫው ገልጾ ነበር።
ነገር ግን ሁለቱ ወገኖች ለንግግር እንዲቀመጡ ለማመቻቸት እያደረገው ባለው ጥረት በተለይም የፋኖ አደረጃጀት ወጥ አለመሆን ለሚያደርጉት ጥረት ፈተና እንደሆነ የካውንስሉ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ እያቸው ተሻለ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“ከአንዱ አዎንታዊ [ምልሽ] ሲገኝ፤ ከሌላኛው አሉታዊ ይሆናል። . . . አንደኛው ጋር ጥሩ ነገር ሲገኝ ሌላኛው ጋር ደግሞ ተቃራኒ መግለጫ ሲሰጥ ይሰማል” ያሉት ኃላፊው፤ ወጥ አደረጃጀት አለመኖር የፋኖ ኃይሎች ለድርድር እንዲቀመጡ ለማመቻቸት እንቅፋት ሆኗል ብለዋል።
እስከ ወረዳ ድረስ ባሉ መዋቅሮች የሰላም ካውንስሉ አካል የሆኑ ውይይቶች እንደተደረጉ የጠቀሱት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው፤ ለድርድሩ ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር ማኅበረሰቡ “እገዛ እንዲያደርግ” ተልዕኮ ሰጥተናል ብለዋል።
“እደራደራለሁ ለማለት ቀርቶ አልደራደርም ለማለትም ተቋም እና መሪ ያስፈልጋል፤ በጋራ መሆን ያስፈልጋል” ሲሉ በክልሉ ያለው የሰላም ችግር በቶሎ መፍትሄ እንዲያገኝ ለሚያደርጉት ጥረት እንቅፋት የሆነውን ጉዳይ የሚወገድበትን መንገድ አመልክተዋል።
ካውንስሉ ከመቋቋሙ በፊት ጀምሮ የፋኖ አደረጃጀት ወጥ አለመሆኑ ስለሚታወቅ ካውንስሉ ምን አማራጭ መንገድ አስቀመጠ? በማለት ቢቢሲ ላነሳው ጥያቄ “የፋኖ ኃይሎች ወደ አንድ ይመጣሉ የሚል ተስፋ ነበረን” ብለዋል አቶ እያቸው።
“ለእኛም መቋቋም ዋናው ምክንያት የአደረጃጀት ወጥ አለመሆን ነው። እኛም ያኔ ሊፈትነን እንደሚችል ገምግመናል። ግን ስንገመግም ምናልባት ድርድር መባሉን ተከትሎ [የፋኖ ኃይሎች] በፍጥነት ወደ ድርድር ይመጣሉ የሚል ተስፋ አድርገን ነበር። በእርግጥ አሁንም ቢሆን ሁለት ወደሚመስል አደረጃጀት ለመምጣት እሞከሩ ነው” በማለት አሁንም ተስፋቸው እንዳልተሟጠጠ ተናግረዋል።

የፎቶው ባለመብት, Amhara Communication/FB
በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከፋኖ ኃይሎች ጋር መንግሥታቸው ይፋዊ ያልሆነ “ንግግር” ከጀመረ መቆየቱን አስታውቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአንድ ስብሰባ ላይ በአገሪቱ ሰላም መስፈን አስፈላጊ መሆኑን ባወሱበት ጊዜ በአማራ ክልል ከሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ጋር “ንግግር ከተጀመረ ውሎ ያደረገ” ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰዋል። ነገር ግን የሰላም ካውንስሉ እንደሚለው የቡድኑ ወጥ ያልሆነ አደረጃጀት እክል እንደሆነ ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እየተደረገ ነው ያሉት “ንግግር” ካውንስሉ እያደረገ ያለው ጥረት ጋር የሚገናኝ አለመሆኑን የጠቀሱት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው፤ ይህም “መንግሥት በራሱ እየሄደበት ያለ መንገድ ይኖራል ብለን ነው የምናስበው” በማለት በተለያዩ አቅጣጫዎች ጥረት እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።
አቶ እያቸው የሰላም ካውንስሉ እያደረገ ላለው የማቀራረብ ጥረት የፋኖ እንቅስቃሴ አንድ ወጥ የሆነ አደረጃጀት አለመኖሩ እንቅፋት ከመሆን ባሻገር፣ ገጠመን ያሉት “ቅድመ ፍረጃ” ፈተና እንደሆነባቸውም ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“ካውንስሉ የተቋቋመው ምህረት ለመጠየቅ፣ የሸፈተን በምህረት አስገቢ አድርጎ መፈረጅ አለ። በተደጋጋሚ በግልጽ እንደተናገርነው እኛ ጥረት መደበኛ የሆነ ድርድር እንዲደረግ እንጂ አንዳንዶቹ እንደሚሉት የሽምግልና ሂደት አይደለም። ስለዚህ አንድ [አደረጃጀት] አለመሆን እና በአንዳንድ ቡድኖች ፍረጃ ውስጥ መገባቱ ለካውንስሉ እንቅፋት ነው” ብለዋል።
ፍረጃው “በሁሉም የፋኖ አደረጃጀት አልገጠመንም” የሚሉት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው፤ የገለልተኝነት ጥያቄ ከተነሳብን ለፋኖ ኃይሎች ይህንን ማቀራረብ ተግባር የሚያከናውን ሌላ አካል ይተካ ማለት እንደሚችሉ ማሳወቃቸውን ገልጸዋል።
“ምናልባት [የፋኖ ኃይሎች] በመርኅ ደረጃ ድርድሩን የሚፈልጉት ከሆነ እና ካውንስሉ ላይ ከሆነ ቅሬታ የሚነሳው፤ ካውንስሉ ማስተካከል ይችላል። ሌላ ተቋም መተካት እንደሚቻል በግልጽም ተናግረናል” ብለዋል።
አክለውም “እንዳልነው ሚናችን አመቻችነት ነው። በአመቻችነቱ ላይ እንኳ የገለልተኝነት ጥያቄ የሚነሳብን ከሆነ ‘እገሌ የሚባል የፈለጋችሁት አካል ይተካልን፤ እናንተ ላይ ጥርጣሬ አለን’ ማለት ይቻላል ብለናቸዋል” በማለት አስረድተዋል።
ካውንስሉ እስካሁን በገጠሙት አንድ ወጥ የፋኖ ቡድን አለመኖር እና በፍረጃ ምክንያቶች ዋነኛ ፈተናዎች ስለገጠሟቸው “እዚህ ግባ የሚባል የታየ ውጤት የለም” ሲሉ የእስካሁን ጥረቱን በሚመለከት ያሳቡትን ማሳካት አለመቻላቸውን አመልክተዋል።
ነገር ግን ካውንስሉ በመንግሥት እና በታታቂዎቹ መካከል ንግግር እንዲጀመር ለድርድር እንዲቀመጡ የማመቻቸት ጥረቱን እንደሚቀጥል በመግለጽ እሳካሁን በገጠማቸው እንቅፋት ተስፋ አለመቆረጣቸውን ተናግረዋል።
“[የፋኖ ኃይሎች] ምላሽ እስኪሰጡን ከመጠበቅ ውጭ ሌላ ምንም ምርጫ የለም። እኛ ከመጠየቅ ውጪ የምናስገድድበት መንገድ የለንም።. . . ሰላም እስኪመጣ ድረስ ያለመሰልቸት እንሠራለን ብለን ነው ያሰብነው። መቼ ነው ያሰብነው ዓላማ የሚሳካው? እኛም አናውቅም” ብለዋል።
መንግሥት ባለፈው ዓመት በአማራ ክልል የሚገኘውን ልዩ ኃይል ለመበተን እና የፋኖ ታጣቂዎችን መሳሪያ ለማስፈታት መወሰኑን ተከትሎ ነበር በሁለቱ ኃይሎች መካከል ይፋ የወጣ ግጭት የተቀሰቀሰወቅ።
አንድ ዓመት ካስቆጠረው በጦር መሳሪያ የተገዘ ግጭት ጋር በተያያዘ በክልሉ ለ10 ወራት የቆየ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተደንግጎ የነበረ ቢሆንም ያለውን ግጭት ለመቆጣጠር ሳይቻል አሁን ድረስ አብዛኛው የክልሉ ክፍል ባለመረጋጋት ውስጥ ይገኛል።
ይህ ክልሉን ለከባድ ቀውስ የዳረገው ግጭት ተጠናክሮ በተለያዩ አካባቢው የየራሳቸው መሪዎች ያሏቸው የፋኖ ቡድኖች ከመንግሥት ኃይሎች ጋር እስካሁን የዘለቀ ግጭት ውስጥ ናቸው። በዚህም ሳቢያ በክልሉ ውስጥ ዘርፈ ብዙ ችግሮች መካሰታቸውን ነዋሪዎች ይናገራሉ።
የፌደራል መንግሥቱ እና የአማራ ክልል መስተዳደር በተደጋጋሚ ግጭቱን በሰላም የመፍታት ፍላጎት እንዳላቸው ሲገልጹ የቆዩ ሲሆን፣ እስካሁን ግን ይህ ነው የሚባል ተጨባጭ ውጤት አልተገኘም።












