በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱት የፋኖ ቡድኖች መሪዎች እነማን ናቸው?

[ከላይ ጀምሮ ከቀኝ ወደ ግራ] እስክንድር ነጋ፣ ምሬ ወዳጆ፣ ዘመነ ካሴ፣ ሐብቴ ወልዴ፣ መከታው ማሞ እና ባየ ቀናው
የምስሉ መግለጫ, [ከላይ ጀምሮ ከቀኝ ወደ ግራ] እስክንድር ነጋ፣ ምሬ ወዳጆ፣ ዘመነ ካሴ፣ ሐብቴ ወልዴ፣ መከታው ማሞ እና ባየ ቀናው

የትግራይ ጦርነት ማብቃትን ተከትሎ የፌደራል መንግሥቱ በአማራ ክልል ውስጥ ያሉትን የታጣቁ ኃይሎች ትጥቅ ለማስፈታት እና የክልሉን ልዩ ኃይል ለመበተን መወሰኑን ተከትሎ የተቀሰቀሰው ግጭት ክልሉን ቀውስ ውስጥ አስገብቶታል።

የመንግሥትን ውሳኔ የተቃወሙ የልዩ ኃይል አባላት እና የፋኖ ኃይሎች ባለፈው ዓመት ሐምሌ ያደረጉት እንቅስቃሴ ያልተጠበቀ ሁኔታን ፈጥሮ ነበር። በዚህም የክልሉ አስተዳደር ታጣቂው ኃይል ከአቅሙ በላይ መሆኑን በመግለጽ የፌደራል መንግሥቱን ጣልቃ እንዲገባ መጠየቁ ይታወሳል።

ይህ በአማራ ክልል በመንግሥት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል የሚካሄደው ግጭት ከጀመረ አንድ ዓመት ሆኖታል። የፌደራል መንግሥቱ የፋኖ ኃይሎችን ለመቆጣጠር ለ10 ወራት የቆየ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደንግጎ ሠራዊቱን አሰማርቶ ቆይቷል።

የፋኖ ኃይሎችም አደረጃጀታቸውን በበርካታ የክልሉ አካባቢዎች በማስፋት በተለያዩ አካባቢዎች የየራሳቸውን አደረጃጀት በመፍጠር ከመንግሥት ኃይሎች ጋር ከባድ የሚባሉ ወታደራዊ ግጭቶችን እያካሄዱ ይገኛሉ። በዚህም የክልሉ ነዋሪ ለጉዳት ከመዳረጉ በተጨማሪ የተለያዩ ችግሮች አጋጥመውታል።

የፋኖ ኃይል በተለያዩ የክልሉ ክፍሎች ውስጥ በየአካባቢው የተደራጀ ሲሆን፣ ሁሉም የየራሱ መሪ ያለው ስብስብ ነው። ይህንን ኃይል አንድ ወጥ አመራር እንዲኖረው ለማድረግ ባለፉት ወራት ጥረቶች መደረጋቸው የተሰማ ቢሆንም እስካሁን የተሳካ ውጤት ላይ አልደረሱም።

በቅርቡ በተካሄደ የውህደት ጥረት ወቅት እስክንድር ነጋ በመሪነት መሰየሙ ቢነገርም፣ ይህንን የሚቃወሙ የፋኖ ቡድኖች እንዳሉ አሳውቀዋል። ስለዚህም አንድ ወጥ የፋኖ አመራር እና መዋቅር ለመፍጠር የተሞከረው ሂደት ሁሉም በሚቀበለው መልኩ ሳይጠናቀቅ ቀርቷል።

በተጨማሪም በሸዋ አካባቢ ከሚንቀሳቀሱ የፋኖ ቡድኖች መካከል አንዱ የነበረው ኮሎኔል አሰግድ መኮንን በመንግሥት እጅ ሥር መግባቱን በመገናኛ ብዙኃን ቀርቦ ተናግሯል። ይህ ሁኔታም በፋኖ ቡድኖች መካከል መወነጃጀል ማስከተሉን በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ከሚተላለፉት መልዕክቶች መረዳት ይቻላል።

ለመሆኑ እነዚህን በየአካባቢው ያሉ የተለያዩ የፋኖ ኃይሎችን የሚመሩት እነማን ናቸው?

እስክንድር ነጋ፡ የአማራ ሕዝባዊ ሠራዊት

እስክንድር ነጋ
የምስሉ መግለጫ, እስክንድር ነጋ
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

እስክንድር ነጋ አዲስ አበባ ውስጥ የተወለደ ሲሆን፣ በ1980ዎቹ ወደ አሜሪካ በማቅናት የኮሌጅ ትምህርቱን እዚያ ተከታትሏል።

ከደርግ ሥርዓት ውድቀት በኋላ ወደ ኢትዮጵያ በመመለስ በጋዜጠኝነት ሙያ ተሰማርቶ የተለያዩ ጋዜጦችን በባለቤትነት እና በዋና አዘጋጅነት በማሳተም የሠራ ሲሆን፣ ከዚህ ሥራው ጋር በተያያዘ በተደጋጋሚ ለእስር ተዳርጎ ነበር።

እስክንድር ከወራት እስከ ዓመታት በተደጋጋሚ በእስር ላይ ቆይቷል። ረዘም ያሉት ከምርጫ የ1997 ምርጫ ቀውስን በኋላ ከአንድ ዓመት በላይ ታስሯል። በ2004 ዓ.ም. ደግሞ ከአንድ ዓመት የፍርድ ሂደት በኋላ የ18 ዓመት እስር ተፈርዶበት ነበር።

የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ መንግሥት ወደ ሥልጣን መምጣቱን ተከትሎ በአገሪቱ ያሉ የፖለቲካ እስረኞች ሲፈቱ እስክንድር ከአራት ዓመት እስር በኋላ ከእስር ወጥቶ ወደ ጋዜጠኝነት ሥራው ተመለሰ።

ነገር ግን ብዙም ሳይቆይ የአዲስ አበባ ጉዳይን ዋነኛ አጀንዳው ያደረገውን “የባላደራ ምክር ቤትን” በማቋቋም፣ በሂደት “ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ” የተባለ ፓርቲ መሥርቶ ከመንግሥት ጋር ከፍተኛ እሰጥ አገባ ውስጥ ገባ።

በ2012 ዓ.ም. ደግሞ በድጋሚ ታስሮ ሁለት ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ በእስር ቤት ቆይቶ ከተፈታ በኋላ ወደ ጋዜጠኝነት ሙያውም ሆነ ወደ ፓርቲ እንቅስቃሴው አልተመለሰም፤ ለወራት በአማራ ክልል ውስጥ ከቆየ በኋላ “የአማራ ሕዝባዊ ግንባር” የሚል የትጥቅ እንቅስቃሴ የሚያደርግ ቡድን መመሥረቱን ይፋ አደረገ።

ግንባሩ ብዙም ሳይቆይ መክሰሙ እና ከወራት በኋላ ደግሞ “የአማራ ሕዝባዊ ሠራዊት” በሚባል መተካቱ ተሰማ። ከሳምንታት በፊት በተለያዩ የፋኖ ቡድኖች አማካይነት “የአማራ ፋኖ ማዕከላዊ ዕዝ” የተባለውን አንድ ወጥ የፋኖ አደረጃጀት ለመመሥረት በተደረገው ጥረትም እስክንድር መሪ ሆኖ መሰየሙ ተነግሯል።

ነገር ግን ይህ የእስክንድር ነጋ በመሪነት መመረጥን ያልተቀበሉ የፋኖ ቡድኖች አዲስ ለተመሠረተው እና በእስክንድር ለሚመራው ማዕከላዊ መዋቅር እውቅና እንደማይሰጡት በመግለጽ ራሳቸውን አግልለዋል።

ምሬ ወዳጆ፡ የአማራ ፋኖ በወሎ

ምሬ ወዳጆ
የምስሉ መግለጫ, ምሬ ወዳጆ

ምሬ ወዳጆ ተወልዶ ያደገው ራያ ቆቦ ነው። የምሬ ስም ከፋኖ ቡድን ጋር መነሳት የጀመረው የትግራይ ኃይሎች ወደ አማራ ክልል ዘልቀው መግባታቸውን ተከትሎ በተካሄዱት ደም አፋሳሽ ጦርነት ወቅት ጀምሮ ነው።

በራያ አካባቢ ነዋሪ ዘንድ እንደተለመደው የግል የጦር መሳሪያ የነበረው ምሬ፣ የፀጥታ ኃይሎች መሳሪያውን ለመንግሥት እንዲያስረክብ በጠየቁት ጊዜ ፈቃደኛ ባለመሆኑ ተፈላጊ ሆኖ ነበር። በዚህም ሳቢያ ወደ ሳዑዲ አረቢያ ተሰደደ።

ወደ ሳዑዲ በሕገወጥ መንገድ ያመራው ምሬ እዚያ ከአንድ ዓመት በላይ መቆየት አልቻለም። በአገሪቱ ፖሊስ ተይዞ ወደ ኢትዮጵያ የተመለሰ ሲሆን፣ በቀየው ተፈላጊ በመሆኑ ብዙም ሳይቆይ ተመልሶ ወደ ሳዑዲ አረቢያ በድጋሚ ተሰደደ።

እዚያም እስከ 2010 ዓ.ም. ቆይቶ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን መምጣትን ተከትሎ ወደ አገር ቤት ተመለሰ።

በወቅቱ የፋኖ እንቅስቃሴ በተለያዩ የአማራ ክፍሎች ውስጥ እየተጠናከረ ስለነበረ፣ ምሬም ከሌሎች ጓደኞቹ ጋር በመሆን የፋኖ ቡድንን በትውልድ አካባቢው ራያ ቆቦ ማደራጀት ጀመረ። በተጨማሪም ከራያ ቆቦ ባሻገር በጎንደር፣ በጎጃም እና በሸዋ ከሚገኙ የፋኖ ቡድኖች ጋር ግንኙነት ፈጥሯል።

በ2013 ዓ.ም. የተቀሰቀሰው የትግራዩ ጦርነት ተባብሶ የትግራይ ኃይሎች ወደ አማራ ክልል ዘልቀው ሲገቡ እና በራያ ቆቦ አካባቢ የተደራጀው ፋኖ በውጊያዎች በመሳተፍ ልምድ እና ትጥቅን ለማግኘት መቻሉ ይነገራል።

ጦርነቱ ከቆቦ አካባቢ እየሰፋ ወደ ሰሜን እና ደቡብ ወሎ አካባቢዎች ሲዛመት የቡድኑ የእንቅስቃሴ አድማስም እየሰፋ ሄደ። በዚህም ምክንያት በምሬ ወዳጆ የሚመራ ሰፊውን የወሎ አካባቢዎችን የሚያካልል “የምሥራቅ አማራ ፋኖ” የሚል ኃይል ተፈጠረ።

ጦርነቱ ሰፍቶ የትግራይ ኃይሎች ወደ ሰሜን ሸዋ ሲገቡም የምሥራቅ አማራ ፋኖ እና መሪው ምሬ ወዳጆ ከወሎ አካባቢዎች ውጪም በሸዋ ውስጥ በሚካሄዱ ውጊያዎች ተሳትፈዋል።

ለሁለት ዓመት የቆየው አውዳሚ ጦርነት በፕሪቶሪያው ስምምነት ከተጠናቀቀ በኋላ፣ ምሬ ወዳጆ እና የፋኖ ቡድኑ በአንድ ስፍራ ላይ ለመሰባሰብ እና ወደ ሰላማዊ ሕይወት ለመመለስ ተስማምተው ነበር።

መንግሥት የክልል ልዩ ኃይሎችን ለማፍረስ እና ሌሎችን ትጥቅ ለማስፈታት መወሰኑን ተከትሎ በራያ ቆቦ ሰፍሮ የነበረው የምሥራቅ አማራ ፋኖ በአካባቢው ከነበረው የመከላከያ ሠራዊት ጋር ግጭት ውስጥ ገብቶ ነበር።

በአካባቢው በፋኖ ኃይሎች እና በመንግሥት ኃይሎች መካከል የተፈጠረውን ግጭት እና ውጥረት ለማርገብ በአካባቢው የአገር ሽማግሌዎች አማካኝነት በተደረገ ሽምግልና ከስምምነት ሲደረስ ምሬ የፋኖ ኃይሎችን ወክሎ እርቅ ፈጽሟል።

ነገር ግን እርቁ ብዙም ሳይቆይ በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በፋኖ እና በመንግሥት ኃይሎች መካከል ይፋ የወጣ ግጭት መካሄድ በመጀመሩ፤ ምሬ ወዳጆም አባላቱን ይዞ ወደ ጫካ ገባ።

በዚህ ጊዜም የምሥራቅ አማራ ፋኖ የእንቅስቃሴ አድማሱን አስፍቶ “የአማራ ፋኖ በወሎ” የተሰኘ ዕዝ በማዋቀር ምሬ ወዳጆን ዋና አዛዥ ሲያደርግ፣ ኮሎኔል ፈንታሁን ሙሃባውን ደግሞ ምክትል አድርጓል።

ዘመነ ካሴ፡ የአማራ ፋኖ በጎጃም

ዘመነ ካሴ
የምስሉ መግለጫ, ዘመነ ካሴ

በአማራ ክልል ሰሜን ጎጃም ዞን መርዓዊ ውስጥ ተወልዶ ያደገው ዘመነ ካሴ የአማራ ፋኖ በጎጃም ሰብሳቢ ነው።

ከሐሮሚያ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪውን ያገኘው ዘመነ፣ በተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በባለሙያነት እና በኃላፊነት የሠራ ሲሆን፣ በተጨማሪም የአማራ ክልል ወጣቶች ፕሬዝዳንትም ነበረ።

ከ1997 ዓ.ም. የምርጫ ቀውስ በኋላ የግንቦት ሰባት ንቅናቄ በወቅቱ በነበረው መንግሥት ላይ የትጥቅ እንቅስቃሴን ጨምሮ ዘርፈ ብዙ ትግል ለማካሄድ ሲመሠረት ዘመነም ወደ ኤርትራ በመሄድ ቡድኑን ተቀላቅሎ ነበር።

ከዚያም በኋላ ወደ ተለያዩ አገራት የሄደው ዘመነ፣ በአገሪቱ አስተዳደራዊ ለውጥ ከተካሄደ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ የአማራ ክልል መስተዳደር ለተቃዋሚዎች ሥልጣን ሲያጋራ ዘመነ ሥልጣን ከተሰጣቸው መካከል አንደኛው ነበር።

በዚህም በክልሉ የአካባቢ ጥበቃ መሥሪያ ቤት የአማካሪነት ቦታ ተሰጥቶት የነበረ ሲሆን፣ ነገር ግን በሰኔ 15/2011 ዓ.ም. በክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ላይ የተፈጸመውን ግድያ ተከትሎ በተፈጠረው ግርግር ሳቢያ ዘመነ ኃላፊነቱን ለቆ ተሰወረ።

የክልሉን ፕሬዝዳንት ጨምሮ ከፍተኛ አመራሮች ከተገደሉበት ጥቃት ነጻ መሆኑ ከተገለጸ በኋላ ዘመነ እንደገና ወደ ፖለቲካው ብቅ ማለት የጀመረው የሰሜኑ ጦርነት ተስፋፍቶ ወደ መሃል አገር ዘልቆ በገባበት ወቅት ነው።

በወቅቱ የህወሓት ኃይሎች በርካታ የአማራ አካባቢዎችን መቆጣጠራቸውን ተከትሎ ጎጃም ላይ ከሌሎች ጓደኞቹ ጋር በመሆን “የአማራ ሕዝባዊ ኃይል” የሚል ቡድን አቋቁመው በሰብሳቢነት ተመረጠ።

ምንም እንኳን የትግራይ ኃይሎች ወደ ጎጃም አካባቢ ዘልቀው ባይገቡም ይህ ኃይል ወደተለያዩ የአማራ አካባቢዎች በመንቀሳቀስ በተለይም በምዕራቡ የወሎ ክፍል ከመከላከያ ሠራዊት ጎን ተሰልፎ እንደተዋጋ ይነገራል።

ነገር ግን የሰሜኑ ጦርነት ሳይጠናቀቅ የክልሉ መንግሥት "ሕግ ማስከበር" በሚል ዘመነ እና የሚመራው ኃይል በሚንቀሳቀስበት አካባቢ ዘመቻ በመክፈት ዒላማውን የቡድኑ መሪ ላይ አድርጎ የነበረ ቢሆንም፤ ብዙም ሳይቆይ ችግሩ መፈታቱ ተገልጾ ነበረ።

ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ግን የክልሉ ፖሊስ ዘመነ ካሴን ባሕር ዳር ከተማ ውስጥ በቁጥጥር ሥር አዋለው። እዚያም ለወራት ከታሰረ በኋላ ተፈትቷል።

ባለፈው ዓመት የፋኖ ታጣቂዎች ከመንግሥት ኃይሎች ጋር ጦርነት ውስጥ ሲገቡ ዘመነ “የአማራ ሕዝባዊ ኃይል” በሚል ያደራጀውን ቡድን ይዞ ወደ ጫካ ገባ።

ይህ ኃይል በአንድ ዓመት ውስጥ በተለያዩ የጎጃም አካባቢዎች ከሚንቀሳቀሱ የፋኖ ታጣቂዎች ጋር በመዋሃድ የሚንቀሳቀስበትን አካባቢ እና የሰው ኃይሉን ሲያሰፋ “የአማራ ፋኖ በጎጃም” ሆኖ በመዋቀር ዘመነ ካሴ ዋና ሰብሳቢ ሆነ።

ሐብቴ ወልዴ፡ የአማራ ፋኖ የጎንደር ዕዝ

ሐብቴ ወልዴ
የምስሉ መግለጫ, ሐብቴ ወልዴ

በጎንደር ተወልዶ ያደገው ሐብቴ ወልዴ በጎንደር ከሚገኙ ሁለት የፋኖ ዕዞች መካከል አንዱ የሆነውን የአማራ ፋኖ የጎንደር ዕዝን ይመራል።

ሐብቴ በአማራ ክልል የተካሄደውን ሕዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ የመንግሥት ለውጥ ከመጣ በኋላ በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የፋኖ እንቅስቃሴ ከመጠናከሩ በፊት በየትኘውም የፖለቲካም ሆነ የትጥቅ እንቅስቃሴ ውስጥ አልነበረም።

ነገር ግን ከአማራ ክልል ውጪ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ በአማራ ተወላጆች ላይ የሚፈጸሙ ግድያዎች እና ጥቃቶች እንዲቆሙ በሚጠይቁ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ከሌሎች ወጣቶች ጋር ተሳትፏል።

ከ2012 ዓ.ም. ወዲህ ደግሞ እነዚህ ጥያቄዎች ምላሽ የሚያገኙት በትጥቅ በታገዘ እንቅስቃሴ ነው በሚል በአካባቢው የፋኖ እንቅስቃሴ ማስተባበር ጀመረ።

በትግራይ የተጀመረው ጦርነት ተስፋፍቶ ወደ አማራ ክልል ሲዛመት መንግሥት በክልሉ ያለው ነዋሪ አካባቢውን በመከላከል በጦርነቱ እንዲሳተፍ ባቀረበው ጥሪ መሠረት ሐብቴ በሥሩ ያሉትን ፋኖዎች በመምራት በተለያዩ ግንባሮች ላይ ተሰልፏል።

በጦርነቱም የቡድኑ አባላት፣ በጦር መሳሪያ እና በልምድ እንዲጠናከር ዕድልን እንደፈጠረለት የሚነገር ሲሆን፣ ባለፈው ዓመት የመንግሥት ኃይሎች በክልሉ በሚገኙ ታጣቂዎች ላይ ዘመቻ ሲከፍት በሐብቴ የሚመራው የጎንደር ፋኖም ዒላማ በመሆኑ ወደ ግጭት ገብቷል።

ከጥቂት ዓመታት በፊት በውስን አባላት የተጀመረው ይህ እንቅስቃሴ ባለፉት ወራት በተለያዩ የጎንደር አካባቢዎች መዋቅሩን አስፍቷል። በዚህ ወቅትም ይህ በሻለቃ ኃይል ደረጃ የነበረው ቡድን እየተጠናከረ ሄዶ በአሁኑ ወቅት የአማራ ፋኖ ጎንደር ዕዝ በመሆን በሐመብቴ ወልዴ ይመራል።

መከታው ማሞ፡ ሸዋ ጠቅላይ ግዛት ዕዝ

መከታው ማሞ
የምስሉ መግለጫ, መከታው ማሞ

የሸዋ ጠቅላይ ግዛት ዕዝ የሚባለው የፋኖ ኃይል በሰሜን ሸዋ ጣርማ በር ወረዳ የተወለደው መከታው ማሞ የሚመራ ነው።

መከታው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በሸዋ ሮቢት ከተማ ተምሮ ካጠናቀቀ በኋላ ፊቱን ወደ ንግድ ሥራ አዙሮ ቆይቷል። መከታው እዚያው ሸዋ ሮቢት ከተማ ውስጥ በተለያዩ የንግድ ሥራዎች ላይ ተሰማርቶ ሕይወቱን ሲመራ ነበር።

መከታው ከትምህርት እና ከንግድ ሥራው ውጪ በየትኛውም የፖለቲካም ሆነ የትጥቅ እንቅስቃሴ ውስጥ ገብቶ እንደማያውቅ ይናገራል። ነገር ግን ባለፉት ዓመታት በቅርብ በሚያውቃት በአጣዬ ከተማ እና በአካባቢዋ በተደጋጋሚ በተፈጸሙ ጥቃቶች ምክንያት ጓደኞቹን በማስተባበር ወደ ትጥቅ እንቅስቃሴ ገብቷል።

ይህንን ተከትሎም ወደ አማራ ክልል በዘለቀው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ውስጥ ከመከላከያ ሠራዊት ጋር በመሆን በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ውስጥ በተካሄዱ ውጊያዎች ውስጥ ተሳትፏል።

ጦርነቱ ካበቃ በኋላ ደግሞ መከታው እና የሚመራው የፋኖ አባላት በሚንቀሳቀሱባቸው አካባቢዎች ተደጋጋሚ ግጭት ቀጥለው፣ ቡድኑ ከሸዋ ሮቢት በመውጣት በአዋሳኝ አካባቢዎች ሲንቀሳቀስ ቆይቷል።

በአማራ ክልል የነበረው ውጥረት ፈንድቶ በመንግሥት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ግጭቶች ሲባባሱ በመከታው የሚመራው የፋኖ ቡድንም በአካባቢያቸው በሚካሄደው ግጭቶች ውስጥ ተሳታፊ ሆኗል።

በሸዋ አካባቢ ከሚንቀሳቀሱ የፋኖ ቡድኖች መካከል አንዱ የሆነው በመከታው ማሞ የሚመራው ቡድን እየተጠናከረ በመሄድ “ሸዋ ጠቅላይ ግዛት ዕዝ” የሚል ስያሜን ይዞ መሪውም ራሱ መከታው ሆኖ ቀጠለ።

ባየ ቀናው፡ የአማራ ፋኖ በጎንደር

ባየ ቀናው
የምስሉ መግለጫ, ባየ ቀናው

ባየ ቀናው በጎንደር አካባቢ ካሉ የፋኖ ቡድኖች መካከል አንዱ የሆነው “የአማራ ፋኖ በጎንደር” መሪ ነው። የ42 ዓመቱ ጎልማሳ ባየ የዕድሜውን ግማሽ የሚሆነውን ያሳለፈው በጫካ ውስጥ ነው።

በሰሜን ጎንደር ዞን ወገራ ወረዳ እንቃሽ በምትባል ቦታ የተወለደው ባየ ወደ ጫካ የወጣው በ1993 ዓ.ም. ነው።

ለዚህም ምክንያቱ የቀድሞው አስተዳደር ባለሥልጣናት ቤተሰቦቹን በፖለቲካ አቋማቸው ምክንያት ማሳደዳቸው እና ማሰራቸው በፈጠረበት ቁጭት እንደሆነ ይናገራል። ባዬ፣ ለአራት ዓመታት በጫካ ውስጥ ከቆየ በኋላ በእርቅ ወደ ሰላማዊ ሕይወት ተመልሶ ነበር።

ነገር ግን ብዙም ሳይቆይ በ1997 ዓ.ም. ባየ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውሎ ለእስራት ተዳረገ። ሁለት ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ በእስር ካሳለፈ በኋላ በ1999 ዓ.ም. ከእስር ተፈታ።

ባየ ከእስር ከተፈታ በኋላ ግን ወደ መደበኛ ሕይወቱ አልተመለሰም። በቀጥታ ወደ ጫካ በማምራት በመንግሥት ላይ ሸፈተ።

ከዓመታት በኋላ ጎንደር ላይ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ በፌደራል ፖሊስ መከበባቸውን ተከትሎ በተፈጠረው ግርግር የሚመራቸውን ታጣቂዎች ይዞ ተሳትፏል። ከዚያ ግጭት በኋላም ተመልሶ ወደ ጫካ በመግባት እስከ 2013 ዓ.ም. ድረስ ቆይቷል።

በጥቅምት ማብቂያ ላይ 2013 ዓ.ም. በትግራዩ ጦርነት ተጀምሮ ወደ አማራ ክልል በተስፋፋበት ጊዜ መንግሥት በጫካ ለነበሩ ታጣቂዎች ጥሪ ሲያቀርብ፣ ባየ ለዓመታት ከቆየበት ጫካ በመውጣት ከመከላከያ ሠራዊት ጎን በመሰለፍ ወደ ክልሉ ከገባው የህወሓት ኃይል ጋር በተካሄዱ ጦርነቶች ተሳትፏል።

ጦርነቱ በስምምነት አብቆቶ መንግሥት በክልሉ ያሉ ታጣቂዎችን ትጥቅ ለማስፈታት መወሰኑን ተከትሎ ባለፈው ዓመት ሐምሌ መጨረሻ በክልሉ በተከሰተው በፋኖ ታጣቂዎች እና በመንግሥት ኃይሎች መካከል ግጭት ውስጥ በጎንደር አካባቢ ተሳትፏል።

ባየ ቀናው በአሁኑ ወቅትም በደቡብ ጎንደር፣ በማዕከላዊ እና ሰሜን ጎንደር አካባቢዎች የሚንቀሳቀሰውን የአማራ ፋኖ በጎንደር ኃይልን በአዛዥነት ይመራል። [ይህ ዘገባ ከተሰናዳ በኋላ የአማራ ፋኖ በጎንደር አዲስ የአመራር ሽግሽግ ማድረጉን የሚገልጽ መግለጫ በማኅበራዊ ሚዲያ አጋርቷል]

መደምደሚያ

በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱትን የፋኖ ኃይሎች በአንድ አመራር ሥር ለማደራጀት ጥረቶች ሲደረጉ የቆዩ ሲሆን፣ ከሳምንታት በፊት እነዚሁ ቡድኖች ባደረጉት ውይይት አንድ ዓላማ እና መሪ ለመሰየም የተደረገው ጥረት የተሳካ አይመስልም።

ምንም እንኳይ ይህ አመራር ለመሰየም የተደረገው ውይይት በመጨረሻ እስክንድር ነጋን በመሪነት መምረጡ ቢነገርም በሁሉም የፋኖ ቡድኖች በኩል ተቀባይነትን አለማግኘቱ እየተነገረ ነው። ተከትሎ የተሰማው መወቃቀስም የፋኖ እንቅስቃሴን ወደ አንድ ከማምጣት ይልቅ ልዩነታቸውን እያጎላው መሆኑ እየታየ ነው።

ለአንድ ዓመት ያህል በክልሉ ውስጥ በመንግሥት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል እየተካሄደ ባለው ግጭት በበርካታ ስፍራዎች የመንግሥት አግልግሎቶች፣ የትምህርት እና የጤና አቅርቦቶች፣ ንግድ እና የሰዎች እንቅስቃሴዎች ክፉኛ ተስተጓጉለዋል። በዚህም ሳቢያ ክልሉ ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኝ አመራሮቹ እየተናገሩ ነው።

ከሁሉ የከፋው ደግሞ በሁለቱ ወገኖች መካከል በሚካሄዱ ግጭቶች እና በሚፈጸሙ ጥቃቶች ምክንያት ሰላማዊ ነዋሪዎች ሰለባ እየሆኑ መሆናቸውን በተደጋጋሚ የሚወጡ ሪፖርቶች ያመለክታሉ።

የክልሉ አስተዳደር እና የፌደራል መንግሥቱ ችግሩ ሰላማዊ መፍትሄ ለማግኘት ፍላጎት እንዳላቸው በተደጋጋሚ የገለጹ ቢሆንም እስካሁን የታየ ተጨባጭ እርምጃ የለም።

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በአንድ ስብሰባ ላይ በሰጡት ፍንጭ መንግሥታቸው ከፋኖ ታጣቂዎች ጋር ውይይት እያደረገ መሆኑን ተናግረው፤ ነገር ግን በክልሉ የሚንቀሳቀሱት የፋኖ ቡድኖች የተለያዩ በመሆናቸው ከስምምነት ለመድረስ አዳጋች እንደሆነ ገልጸዋል።