በባሕር ዳር ከተማ የሰዓት እላፊ እና የተለያዩ ገደቦች ተጣሉ

በአማራ ክልል ዋና ከተማ ባሕር ዳር በነዋሪዎች እና በተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ ላይ የሰዓት እላፊ ገደብ እና የተለያዩ ክልከላዎች ተጣለ።
አንድ ዓመት ሊሆነው የተቃረበውን የአማራ ክልል የፀጥታ ችግርን ተከትሎ የተዋቀረው የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር የፀጥታ ምክር ቤት እሁድ ሐምሌ 21/2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው የሰዓት እላፊውን እና ገደቦቹን የጣለው ያሉ የፀጥታ ችግሮችን ለመፍታት ነው ብሏል።
በዚህም መሠረት በባሕር ዳር ከተማ ውስጥ ከምሽቱ ሦስት ሰዓት አንስቶ እስከ ንጋት 12 ሰዓት ድረስ የሚቆይ የሰዓት እላፊ ደገብ በሰው እና በተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ ላይ ተጥሏል።
ይህ የሰዓት እላፊ ገደብ የፀጥታ አካላት ተሽከርካሪዎችን፣ አምቡላሶችን እና የእሳት አደጋ መኪኖችን የማይመለከት መሆኑን የገለጸው የፀጥታ ምክር ቤቱ ጨምሮ በእነዚህ ተሽከርካሪዎች እና በሌሎችም ላይም በማንኛውም ጊዜ በፀጥታ ኃይሎች ፍተሻ አንደሚደረገ አሳወቋል።
የጦር መሳሪያ አያያዝን በተመለከተም ከፀጥታ ኃይል አባላት እና ለፀጥታ ሥራ ተሰማርተው የመንቀሳቀሻ ፈቃድ ከተሰጣቸው ውጪ የጦር መሣሪያ ይዞ መንቀሳቀስ ተከልክሏል። በተጨማሪም ከስምሪት ውጪ የሆኑ የፀጥታ ኃይል አባላት የጦር መሳሪያ ይዘው መንቀሳቀስ እንደማይችሉ ተገልጿል።
የባሕር ዳር ከተማ ፀጥታ ምክር ቤት ባወጣው መግለጫ ጨምሮም በከተማዋ አሉ ያላቸውን ችግሮች ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ውስጥ “አባባሽ” ምክንያቶችን መለየቱን ጠቅሶ “አብዛኞቹ ችግሮች የሚፈጸሙት በባጃጅ ተሽከርካሪዎች በመታገዝ” ነው ብሏል።
ስለዚህም በባሕር ዳር ከተማ በስፋት የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡት ባለሦስት ጎማ ባጃጅ ተሽከርካሪዎች ከሌሎች ተሽከርካሪዎች በተለየ ከአመሻሽ 12 ሰዓት እስከ ንጋት 12 ሰዓት ድረስ እንዳይንቀሳቀሱ ክልከላ ተጥሎባቸዋል።
በተጨማሪም ባጃጆች ውስጣቸውን የሚሸፍኑባቸውን መጋረጃዎች እንዲያነሱ፣ በተመደቡበት የስምሪት ቦታ ብቻ እንዲንቀሳቀሱ እና ከከተማዋ ትራንስፖርት ቢሮ የሚሰጣቸውን አዲስ መለያ እንዲለጥፉም አዟል።
እንዲሁም የባጃጅ ባለ ንብረቶች በሹፌር እና በኪራይ የሚያሠሩ ከሆነ የውል ስምምነታቸውን ለፖሊስ እና ለከተማዋ የትራንስፖርት ጽህፈት ቤት እንዲያሳውቁ ግዴታ ተጥሎባቸዋል።
የከተማዋ ፀጥታ ምክር ቤት የባሕር ዳር ከተማን ፀጥታ እና ደኅንነት የበለጠ ለማጠናከር በሚል ባወጣው የሰዓት እላፊ እና የእንቅስቃሴ ገደብ ላይ ሞተር ሳይክሎች ላልተወሰነ ከእንቅስቃሴ ውጪ እንዲሆኑ መወሰኑን አስታውቋል።
የተጣሉትን የሰዓት እላፊ ገደቦች እና ክልከላዎችን ተላልፈው በሚገኙ ሰዎች እና ተሽከርካሪዎች ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ እና የሕግ ተጠያቂነትም እንደሚከተል አመልክቷል።
እንዲሁም ከተጣለው ክልከላ በተቃራኒ የጦር መሣሪያ ይዘው የሚገኙ ሰዎች የጦር መሳሪያቸው እንደሚነጠቅ ምክር ቤቱ ገልጿል።
በበርካታ የአማራ ክልል አካባቢዎች ውስጥ በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል የሚካሄደው ግጭት ከተቀሰቀሰ አንድ ዓመት ሊሞላው የተቃረበ ሲሆን፣ ባለፈው ዓመት መጨረሻ ላይ የፋኖ ታጣቂዎች ባሕር ዳርን ጨምሮ በክልሉ ያሉ ከተሞችን ለመቆጣጠር ተቃርበው እንደነበር ይታወሳል።
በወቅቱ የክልሉ አስተዳደር ጥያቄን ተከትሎ የፌደራል መንግሥቱ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመደንገግ መከላከያ ሠራዊት በአማራ ክልል ተሰማርቶ ከተሞቹን በመቆጣጠር ሥርዓት በማስከበር ላይ እንደሚገኝ ሲገልጽ ቆይቷል።
በክልሉ ለ10 ወራት ተግባራዊ ሆኖ የቆየው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ባለፈው ግንቦት ወር ላይ ያበቃ ሲሆን፣ አሁንም በተለያዩ የአማራ ክልል አካባቢዎች በመንግሥት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል የሚካሄደው ግጭት እንደቀጠለ ነው።
የባሕር ዳር ከተማ የፀጥታ ምክር ቤት የተጣሉትን የሰዓት እላፊ እና ሌሎች ገደቦችን ይፋ ባደረገበት መግለጫው “በፌደራል፣ በክልል እና በከተማዋ የፀጥታ ኃይሎች ብርቱቱ ተጋድሎ” የከተማዋ ሰላም እና ፀጥታ እየተሻሻለ ነው ብሏል።
ነገር ግን ምክር ቤቱ ከእሁድ ሐምሌ 21/2016 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆኑትን የሰዓት እላፊ እና ክልከላዎች ለመጣል ምክንያቱ ምን እንደሆነ በግለጽ ያለው ነገር የለም።












