የአላማጣ እና አካባቢው ተፈናቃዮች “ትምህርት ቤት ውስጥ እረፉ” በመባላቸው ወደ መጡበት ቆቦ ከተማ ተመለሱ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ወደ መኖሪያቸው ለመመለስ ከቆቦ የተነሱ የአላማጣ ከተማ እና አካባቢው ተፈናቃዮች፤ ወደ ከተማዋ ሲደርሱ “ትምህርት ቤት ውስጥ እረፉ” በመባላቸው ወደ መጡበት መጠለያ ካምፕ መመለሳቸውን ነዋሪዎች እና በአማራ ክልል የአላማጣ ከተማ ከንቲባ ተናገሩ።
ተፈናቃዮቹ ወደ መጡበት የተመለሱት “የፀጥታ ስጋት ችግሮች እንዳይከሰቱ” የፌደራል የፀጥታ ኃይሎች ያቀረቡት አማራጭ ላይ ባለመስማማታቸው እንደሆነ በከተማዋ የሚገኘው የፌደራል ፖሊስ ሬጅመንት ዋና አዛዥ ዋና ኢንስፔክተር አብርሃም ከበደ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በአማራ እና በትግራይ ክልሎች የይገባኛል ጥያቄ የሚነሳባት የአላማጣ ከተማ ነዋሪዎች ከመኖሪያቸው ሸሽተው በሰሜን ወሎ ዞን ቆቦ እና ወልዲያ ከተሞች የተጠለሉት በሚያዝያ ወር ላይ ነበር።
ነዋሪዎቹ ከከተማዋ የሸሹት “በትግራይ ታጣቂዎች” እና “በአካባቢው ሚሊሻዎች” በተደረጉ የተኩሰ ልውውጦች የትግራይ ኃይሎች ከሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ወዲህ በአማራ ክልል ስር ወደነበሩ የራያ አላማጣ ወረዳ አካባቢዎች ከገቡ በኋላ ነበር።
ይህንንም ተከትሎ በአማራ ክልል የተሾሙ የራያ አካባቢዎች አስተዳዳሪዎችን ጨምሮ ነዋሪዎች በተለይም በአቅራቢያ በምትገኘው ቆቦ ከተማ ተጠልለው ቆይተዋል።
አላማጣ ከተማን ጨምሮ ከሌሎችም የራያ አካባቢዎች በቆቦ ከተማ የተጠለሉ ሰዎች ብዛት 42 ሺህ ገደማ እንደሆነ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ እርዳታ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት በወቅቱ አስታወቆ ነበር።
ወደ ቆቦ ከተማ የገቡት ተፈናቃዮች በቴክኒክ እና ሙያ ማሠልጠኛ ተቋም ቅጥር ግቢ እንዲሁም ከከተማዋ ሦስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ የኢንዱስትሪ መንደር ላይ መጠለላቸው ተገልጾ ነበር።
ከአላማጣ እና በዙሪያው ከሚገኙ የራያ አላማጣ ወረዳ አካባቢዎች ከተፈናቀሉት ነዋሪዎች መከካል ባለፉት ወራት ውስጥ ወደ መኖሪያቸው የተመለሱ ነዋሪዎች የሚናገሩት በአማራ ክልል የተሾሙት የአላማጣ ከተማ ከንቲባ አቶ ኃይሉ አበራ፤ አሁንም “በአስር ሺህ” የሚቆጠር ተፈናቃዮች በቆቦ ከተማ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
እነዚህን ተፈናቃዮች ወደ መኖሪያቸው ለመመለስ አላማጣ ከተማን ከሚቆጣጠረው የመከላከያ ሠራዊት አመራሮች ጋር “ንግግር ተደርጎ” እንደነበር ገልጸዋል። በዚህም መሠረት ትናንት ረቡዕ ሐምሌ 17/2016 ዓ.ም. በመጠለያ ካምፕ እንዲሁም “በሕብረተሰቡ ውስጥ” ተጠልለው የነበሩ ተፈናቃዎች እንዲመለሱ መንገድ ተጀምሮ እንደነበር አስረድተዋል።
ተፈናቃዮችን ለመመለስ በተደረገ ስምምነት ከቆቦ ወደ አላማጣ ከተማ የተንቀሳቀሱት ተሽከርካሪዎች ብዛት “ከ30 በላይ” እንደሆነ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የራያ ቆቦ ወረዳ ኃላፊ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በዚህ መልኩ ጉዞ የጀመሩት ተፈናቃዮች ወደ አላማጣ ከተማ ያመሩት “ባንዲራ እያውለበለቡ እና መዝሙር እየዘመሩ” እንደነበር ከተመላሾች መካከል የሆነ አንድ ነዋሪ ገልጿል። ወደ አላማጣ ሲቃረቡም የከተማዋ ነዋሪ በተመሳሳይ መልኩ እንደተቀበላቸው ጠቅሷል።
ነዋሪዎች ተፈናቃዮችን ለመቀበል የወጡት በከተማዋ ነዋሪዎች አስተባባሪነት እንደሆነ ሌላ የከተማዋ ነዋሪ ለቢቢሲ ተናግሯል።
ተፈናቃዮቹን የያዙት ተሽከርካሪዎች አላማጣ ከተማ መግቢያ ላይ የሚገኝ “ድልድይ” የተባለ ቦታ ሲደርሱ “በመከላከያ ሠራዊት አባላት” እንዲቆሙ እንደተደረጉ ቢቢሲ ያነጋገረው ተመላሽ ተናግሯል። “አላማጣ መግቢያው ላይ ስንደርስ ሕዝቡን አግደው ወደ እድገት ፋና ትምህርት ቤት ግቡ ነበር የተባልነው” ሲል ሁኔታውን አስረድቷል።
ከንቲባው አቶ ኃይሉም በተመሳሳይ፤ “ወደ ከተማዋ እየገባን ነው የነበረው። የከተማዋ መግቢያ ላይ ስንደርስ ጫፍ ላይ እድገት ፋና የሚባል ትምህርት ቤት አለ። ‘ወደዚያ እንድትገቡ እና እዚያ ከገባችሁ በኋላ ነው [ተመላሽ] የሚበታተነው’ የሚሉ ሀሳቦች ቀረቡ” ሲሉ ከመከላከያ ሠራዊት በኩል ቀርቧል ያሉትን አማራጭ አስረድተዋል።
ወደ ከተማዋ እየገቡ የነበሩት ተፈናቃዮች በመጀመሪያ ትምህርት ቤት ውስጥ እንዲያርፉ የተነገራቸው ተመላሾቹ ወደ ከተማዋ ሲገቡ ከነበረው እንዲሁም አቀባበል ከሚያደርጉ ነዋሪዎች ሁኔታ ጋር በተያያዘ እንደሆነ አቶ ኃይሉ እንዲሁም ተመላሽ እና የተመላሾች አስተባባሪው ተናግረዋል።
ተፈናቃዎች በአንጻሩ ወደ ከተማዋ መግባት እንደሚፈልጉ በመግለጽ ይህንን ሀሳብ እንዳልተቀበሉትም አክለዋል።
አቶ ኃይሉ፤ “ወደ ቤታችን ነው የምንገባው፤ የመብት ጉዳይ ነው። ወደ ራስ ቤት ለመግባት ምንም ዓይነት ገደብ ሊጫን አይገባም። ምክንያቱም [ተፈናቃዮች ሲገቡ] የተፈጸመ ምንም ችግር የለም። ለምን በረሃ ላይ ወርደን ወደ ቤት ግቡ እንባላለን?” ሲሉ ከመከላከያ ሠራዊት በኩል የቀረበውን አማራጭ ለምን እንዳልተቀበሉት ገልጸዋል።
በተፈናቃዎች በኩል የነበረው ፍላጎት ተሽከርካሪው ከተማው ውስጥ “አደባባይ ላይ ሲደርስ” ተመላሾቹ ወደየመኖሪያቸው ይበተኑ የሚል እንደነበርም ጠቅሰዋል።
“ሕዝቡ [ወደ ከተማ] ካልገባሁ እመለሳለሁ የሚል አቋም” እንደያዘ የሚናገሩት አቶ ኃይሉ በዚህም ምክንያት “ይህንን አጋጣሚ ተጠቅሞ ችግር ቢፈጠር ሌላ ቀውስ ይመጣል” በሚል ተፈናቃዮች ወደ መጡበት ቆቦ ከተማ እንዲመለሱ እንደተደረገ ተናግረዋል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው የራያ ቆቦ ወረዳ ኃላፊ ተፈናቃዮቹ ትናንት [ረቡዕ] ወደ ቆቦ ከተማ ተመልሰው መግባታቸውን አረጋግጠዋል። “[አላማጣ] ያለ ኃይል ‘ወደ ካምፕ ትገባላችሁ’፤ [ተፈናቃዮች ደግሞ] ‘ወደቤታችን ነው የምንገባው’ በሚል አለመግባባት ተመልሰው ወደ ቆቦ መጥተዋል” ሲሉ ተመሳሳይ ምክንያት ጠቅሰዋል።
በድጋሚ ወደ ቆቦ ከተማ የገቡት ተፈናቃዮች፤ በከተማዋ በሚገኘው የቴክኒክ እና ሙያ ማሠልጠኛ እንደሁም በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ እንዲያርፉ መደረጉንም ገልጸዋል።
ወደ አላማጣ እየተመለሱ የነበሩት ተፈናቃዮች ወደመጡበት መመለሳቸውን በአላማጣ ከተማ የፌደራል ፖሊስ ሬጅመንት ዋና አዛዥ ዋና ኢንስፔክተር አብርሃም ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
የከተማዋን ፀጥታ የሚቆጣጠሩት ፌደራል የፀጥታ ኃይሎች ተመላሾቹ በትምህርት ቤት እንዲያርፉ የተፈለገው “ተረጋግተው” ወደ ከተማዋ እንዲገቡ በማሰብ እንደሆነ ዋና ኢንስፔክተር አብርሃም ገልጸዋል።
ተፈናቃዮች ወደ ከተማዋ እየመጡ የነበረበት ሁኔታ “በጣም በኃይለኛ እና በብዛት” እንደሆነ የተናገሩት ዋና አዛዡ፤ በከተማዋ የሚገኙት የፌደራል የፀጥታ ኃይሎች “እንደዚህ ሆነው ይመጣሉ ብለው እንዳልገመቱ” አስረድተዋል።
በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ከከተማዋ የተፈናቀሉ የትግራይ ተወላጅ ነዋሪዎች ባለፈው ሳምንት ወደ ከተማዋ ሲገቡ “አንዳንድ ችግሮች” እንደነበሩ ያስታወሱት ዋና ኢንስፔክተር አብርሃም፤ ቆቦ የተጠለሉ ተፈናቃዮች ሲደርሱ “የነበረው ጭፈራ እና ሁኔታዎች ምናልባት ወደ ግጭት ሊያስገባ ይችላል” የሚል ስጋት መፈጠሩን ጠቅሰዋል።
“በዚህ አጋጣሚ መሳሪያ፣ በቦንብ ጥቃት” እንዳይፈጸም ለመከላከል ሲባል ተፈናቃዎች ወደ ትምህርት ቤት እንዲገቡ ሀሳብ መቅረቡን ተናግረዋል። “በሰከነ መንገድ ፌደራል ፖሊስም መከላከያ ሠራዊትም ቦታውን ይዞ፤ እኛ ባለንበት እንዲገቡ ነበር ፍላጎታችን። ከተማ ሲገቡ ሌላ ሁከት እና ብጥብጥ እንዳይፈጠር በሚል ስጋት ነው” ሲሉም ይህ አማራጭ የቀረበበት ምክንያት አስረድተዋል።
ዋና አዛዡ፤ በዚህም አለመግባባት የተነሳ በድጋሚ ወደ ቆቦ የሄዱት ተፈናቃዮች ወደ መኖሪያቸው እንዲመለሱ ለማድረግ “ፕሮግራም ተይዞ ንግግር” ሊደረግ እንደሚችል ጠቁመዋል።












