ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ህወሓት ሕጋዊ ሰውነቱን መልሶ ሳያገኝ ጉባኤ እንዳያካሂድ አስጠነቀቁ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከተቃወሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሲሰጡ

የፎቶው ባለመብት, Abiy Ahmed Ali/FB

የምስሉ መግለጫ, ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ውይይት ያደረጉት በሳምንቱ መጀመሪያ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ባደረጉት ውይይት ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ጉባኤ ከማካሄዱ በፊት “በሕጋዊ መንገድ መመዝገብ እንዳለበት” አሳሰቡ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰኞ ሐምሌ 13/2016 ዓ.ም. በሰጡ ማግስት ህወሓት ባወጣው የጉባኤ መርሃ ግብር በ14ኛው ድርጅታዊ ጉባኤ ላይ የሚሳተፉ ጉባኤተኞች ምርጫ በዚህ ሳምንት መጨረሻ እንደሚጀምር አስታውቋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማስጠንቀቂያውን የሰጡት ህወሓት “ጠቅላላ ጉባኤ እንዳናደርግ የሚከለክለን ምድራዊ ኃይል የለም የሚል መግለጫ እያወጣ ወደ ትናንትና ፉከራው፣ ወደ በሽታው እየገባ ባለበት ሁኔታ የጊዜያዊ አስተዳደሩ መከለስ የለበትም ወይ?” የሚል ጥያቄ አቶ ከበደ አሰፋ በተባሉ የትንሳዔ 70 እንደርታ ፓርቲ ተወካይ ከቀረበላችው በኋላ ነው።

አቶ ከበደ ከዚህ ጥያቄ በተጨማሪ የትግራይ ክልል ጊዜያው አስተዳደር እና የፕሪቶሪያው ስምምነትን የተመለከቱ ጥያቄዎችንም አንስተዋል።

ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ በምላሻቸው “ከስምምነቱ [ከፕሪቶሪያ] አንጻር 99 በመቶ ተሳክቶልናል” ብለዋል። ለዚህም ጦርነቱ መቆሙን፣ አገልግሎት በትግራይ ክልል መጀመሩን፣ የጊዜያዊ አስተዳደር መቋቋሙን እና የተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው መመለስ በማሳየነት ጠቅሰዋል።

ከህወሓት ጉባኤን በተመለከተ ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ቀላል ምክር” ሰጥተዋል።

ከአራት ዓመታት በፊት “በምርጫ መራዘም” ሳቢያ የተከሰተውን “ቀውስ” ያስታወሱት ዐቢይ፤ “ምን ያህል ሰው እንደወደመ፣ ምን ያህል ሀብት እንደወደመ መገመት ትችላላችሁ” ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ “ያ የወደመ ሀብት እና የወደመ የሰው ሕይወት በትክክል ሳይገመገም፣ እንዴት ጠፋ ሳይባል ሌላ ጥፋት ማምጣት ጥሩ አይደለም” ሲሉ አክለዋል።

አክለውም የህወሓት ሕጋዊ ሰውነት እንዲመለስ መንግሥታቸው ያከናወናቸውን ሥራዎች ለተቃዋሚዎቻቸው አስታውሰዋል።

“እና ባለፈው እናንተ የምታውቁት ሕግ ያሻሻልነው ህወሓት እና መሰል ፓርቲዎች በሕጋዊ መንገድ ተመዝግበው ሕጋዊ ፓርቲ እንዲሆኑ [ነው]” ብለዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጠቀሱት የሕግ ማሻሻያ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጸደቀው ባለፈው ግንቦት ወር መጨረሻ ነው። የምርጫ ሕጉን ያሻሻለው ይህ የአዋጅ ማሻሻያ ኃይልን መሠረት ባደረገ የአመጽ ተግባር ተሳትፎ የነበረ የፖለቲካ ቡድን በፓርቲነት የሚመዘገብበትን ሂደት በዝርዝር ያስቀመጠ ነው።

ማሻሻያው የፖለቲካ ቡድኑ “ሕገ መንግሥታዊ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን አክብሮ ለመንቀሳቀስ መስማማቱ በሚመለከተው የመንግሥት አካል ከተረጋገጠ፣ የፖለቲካ ቡድኑ በልዩ ሁኔታ እንደ ፖለቲካ ፓርቲ ሊመዘገብ ይችላል” ሲል ይደነግጋል።

ከማሻሻያ አዋጁ መጽደቅ በኋላ ንግግሮች መደረጋቸውን ያስታወሱት ዐቢይ “ምርጫ ቦርድ ሥራውን ሠርቶ፣ የሚያጣራውን አጣርቶ በተሟላ መንገድ እንዲፈቅድላቸው።ዐቃቤ ሕግ ለምርጫ ቦርድ [ደብዳቤ] መጻፍ ነበረበት ጽፈናል” ብለዋል።

“የአስፈጻሚውን ሥራ መቶ ፐርሰንት ሰርተናል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “ህወሓት አሁን ማድረግ ያለበት ምርጫ ቦርድ ጋር ሂዶ በሁለት እና ሦስት ሳምንት ውስጥ የሚጠበቅበትን ሰነዶች አሟልቶ በሕጋዊ መንገድ ተመዝግቦ ወይም ፈቃዱን reinstate [መልሶ አግኝቶ] ነው ጉባኤ ማካሄድ ያለበት” ሲሉ በአጽንኦት ተናግረዋል።

ዐቢይ ይህን ቢሉም ግን የህወሓት ቃል አቀባይ አቶ አማኑኤል አሰፋ፤ “ይህ የአዋጅ ማሻሻያ የተሰረዘውን ሕጋዊ ሰውነት ለመመለስ የሚያስችል ሳይሆን እንደ አዲስ ለመመዝገብ የሚያስችል” መሆኑን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አቶ አማኑኤል አክለውም፤ “ወደ ምርጫ ቦርድ አመልክተን በዚያ አዋጅ መሠረት እንድንስተናገድ ነው የሚፈልጉት። እኛ ወደ ምርጫ ቦርድ ቴክኒካል ወደ ሆነው ጉዳይ እንደ አዲስ ለመመዝገብ ማመልከት ሳይሆን ፖለቲካሊ የተሰረዘውን ሕጋዊ ሰውነት ለማስመለስ የሚያስችል ፖለቲካዊ ውሳኔ በሚመለከተው የመንግሥት አካል እንዲሰጠን ነው የምንፈልገው” ሲሉ የፓርቲያቸው ውሳኔ አስረድተዋል።

“የፕሪቶሪያውን ስምምነት ተከትሎ ምርጫ ቦርድም የተሰረዘውን ሕጋዊ ሰውነታችንን እንዲመልስ ነው የምንጠብቀው” ያሉት አቶ አማኑኤል ምርጫ ቦርድ ቀርቦ እንደ አዲስ ምዝገባ እንደማይፈልግ ጠቁመዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ህወሓት ከዚህ ቅደም ተከተል ውጪ ጉባኤ የሚያካሂድ ከሆነ ሊከሰት የሚችለውን ነገር ለተቃዋሚ ፓርቲ ተወካዮች ገልጸዋል።

“[ህወሓት] ያንን ባያደርግ እኔ ብፈልግም ባልፈልግም ዋጋ የለውም ምርጫ ቦርድ ካልተቀበለው፣ ህወሓትን ሕጋዊ ፓርቲ ካላለው በምርጫ ሊሳተፍ አይችልም መንግሥት ሊሆን አይችልም፣ ምን ማለት ነው ተመልሰን ደግሞ ጦርነት ውስጥ እንገባለን ማለት ነው” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ዐቢይ አክለውም “የቀረች ጉዳይ አሟልቶ በሕጋዊ መንገድ ጉባኤ አካሂዶ ፓርቲውን መልሶ ወደ ፖለቲካ ሥርዓት መመለስ ከሁሉ በላይ ህወሓትን፣ ከህወሓት ቀጥሎ የትግራይ ሕዝብን ከዚያ ቀጥሎ ሁላችንንም ይጠቅመናል” ሲሉ መክረዋል።

“የምርጫ ቦርድ ጉዳይ ስለሆነ ከእኛ ጋር ምንም አያገናኘውም” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስተሩ “አውዱ ተመችቶ ሳለ፣ ሕግ ተመልሶ እያለ፣ በሰላም መፍታት የሚያስችል ነገር እያለ፣ ያንን ወደ ጎን ትቶ መሄድ ጥሩ አይደለም። ለትግራይ ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ ጥፋት ስለሚያመጣ ቆም ብለው አይተው ወደ ሰላማዊ መንገድ ይሄዳሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ” ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ይህን ቢሉም ግን ሕወሓት በ14ኛው ድርጅታዊ ጉባኤው ጠቅላላ ጉባኤውን ለማካሄድ ዝርዝር መርሃ ግብሮችን አውጥቷል።

በዚህም መሠረት ዛሬ ረቡዕ ሐምሌ 17 በወረዳ ደረጃ ለጉባኤ አዘጋጅ ኮሚቴ ኦሬንቴሽን ይሰጣል። በሚቀጥለው ሳምንት ሐምሌ 23/2016 ዓ.ም. ደግሞ በወረዳ ደረጃ ጉባኤ ተሳታፊዎች እንደሚመርጥ ባወጣው መረሃ ግብር ላይ አመልክቷል።