የህወሓት ጉባኤ “የበላይነት አለኝ በሚል ኃይል ተጠልፎ ወደ አደገኛ ሁኔታ እያመራ ነው”

የህወሓት ቁጥጥር ኮሚሽን ሊቀመንበር አቶ ተኽለብርሃን አርአያ እና የህወሓት አርማ

የፎቶው ባለመብት, TPLF/FB

የምስሉ መግለጫ, የህወሓት ቁጥጥር ኮሚሽን ሊቀመንበር አቶ ተኽለብርሃን አርአያ እና የህወሓት አርማ

ህወሓት በቅርቡ ሊያካሂደው ያቀደው የ14ኛው ጉባኤ ሂደት እና ዓላማ የበላይነት ባለው ኃይል ተጠልፎ ወደ አደገኛ ሁኔታ እያመራ መሆኑን የድርጅቱ የቁጥጥር ኮሚሽን ሊቀመንበር ገለጹ።

የኮሚሽኑ ሊቀመንበር አቶ ተኽለብርሃን አርአያ ይካሄዳል የተባለው የህወሓት ጉባኤ በመከፋፈል እና በመጠቃቃት ችግር ውስጥ መሆኑን አመልክተዋል።

ጨምረውም “ጉባኤው ከአዘጋጅ ኮሚቴው እውቅና ውጪ እየተመራ ነው። ይህም የበላይነት አለኝ በሚል ኃይል ተጠልፎ ወደ አደገኛ ሁኔታ እያመራ ነው” ሲሉ ስጋታቸውን ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ኮሚሽኑ ረቡዕ ባወጣው መግለጫ ለጉባኤው ዝግጅት ካለፈው የሚያዝያ ወር ጀምሮ ሲሠራ እንደነበረ በማስታወስ “በማዕከላዊ ኮሚቴው ውስጥ ያደጉ” ያላቸው ቡድኖች እንቅፋት ሆነውብኛል ብሏል።

በከፍተኛ የአመራሮች መከፋፈል እና መገፋፋት ውስጥ እንደወደቀ የሚነገርለት ህወሓት በምርጫ ቦርድ ሳይመዘገብ ማካሄድ አይገባውም የሚባለውን ጠቅላላ ጉባኤ ለማካሄድ ዝግጅት እያደረገ መሆኑ ይታወቃል።

የጉባኤው ዓላማ “ድርጅቱ ውስጥ በተደራጁ ከፍተኛ አመራሮች ተጠልፏል” የሚለው የህወሓት ቁጥጥር ኮሚሽን አባላቶቹ ከአዘጋጅ ኮሚቴው ራሳቸው እንዲያገሉ ምክንያት መሆኑን ባወጡት መግለጫ አመልክቷል።

የኮሚሽኑ ሊቀመንበር አቶ ተኽለብርሃን “ጉባኤው መካሄድ አለበት፤ ግን ዴሞክራሲያዊ እና ግልጽ መሆን አለበት። የቁጥጥር ኮሚሽኑ የሚታዩ ችግሮች እንዲፈቱ ጥያቄ ሲያቀርብ ቆይቷል። ሊታረሙ ግን አልቻሉም” ሲሉ ለቢቢሲ ትግርኛ ተናግረዋል።

“በተሳሳተ መንገድ መሄድ የሚፈልግ ኃይል ስላለ፣ ይሄንን አውግዘናል። የጉባኤው ዝግጅት ግልጽነት ይጎድለዋል። አዘጋጅ ኮሚቴው በነጻነት መሥራት አልቻለም። ጉባኤው በኮሚቴው መመራት ሲገባው መምራት አልቻለም” ብለዋል።

ዘጠኝ አባላት ያሉት የህወሓት ጉባኤ አዘጋጅ ኮሚቴ ጉባኤውን ለማካሄድ ኃላፊነት የሚወስድ አካል ቢሆንም “አሁን ያለው አካሄድ ግን እንደዚያ አይደለም። ከመጋረጃ ጀርባ የሚፈጸም ነገር ሆኗል፤ በተለይ ድርጅቱ በከፍተኛ የአለመተማመን ችግር ውስጥ በሚገኝበት ጊዜ ግልጽነት አስፈላጊ ነው” ብለዋል አቶ ተኽለብርሃን።

በከፍተኛ የህወሓት አመራሮች ውስጥ ከባድ የመከፋፈል ችግር መፈጠሩን ያመለከቱት አቶ ተኽለብርሃን፣ “የሁሉም ነገር መነሻ ውስጣዊ ችግር እንጂ ከውጪ የመጣ አይደለም” ሲል ተናግረዋል።

“የቆየ ችግር አለ፤ ይህም የሥርዓት ችግር ነው። አመራር ከአላማው ሲርቅ ድርጅቱን ይበክለዋል። አመራሩ ትኩረቱን ጥቅም እና ሥልጣን ላይ አድርጓል። በድርጅቱ ውስጥ የሚታይ ሁለት የጥቅም ትስስር ተፈጥሯል። ይህ ደግሞ ሁሉንም ነገር አበላሽቶታል” ሲል አብራርተዋል።

ነገር ግን በህወሓት ውስጥ ተፈጥሯል ስላሉት ቡድን እና ስለሚመሩት ሰዎች ከመናገር ተቆጥበዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ህወሓት (ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ) ከሳምንት በፊት በመቀለ ለቀናት ሲያካሂድ የነበረውን የከፍተኛ አመራሮች ጉባኤ ካጠናቀቀ በኋላ ባወጣው መግለጫ የግል ጥቅምን ማስቀደም የፓርቲውን ህልውና አደጋ ላይ እንደጣለ እና “በ50 ዓመት ታሪኬ ከባዱ ፈተና ተጋርጦብኛል” ማለቱ ይታወሳል።

ፓርቲው ማክሰኞ ሐምሌ 9/2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ “በማዕከላዊ ኮሚቴው ውስጥ ከሕዝባዊ ወገንተኝነት ያፈነገጠ እና ለግል ጥቅም መሰባሰብ” በተደራጀ መልኩ መሥራት እንዳላስቻለው ገልጿል።

ህወሓት በማዕከላዊ ኮሚቴው ውስጥ ያጋጠመው የችግር ምንጭ “ቡድናዊነት፣ ፀረ-ዴሞክራሲያዊነት፣ ጎጠኝነት፣ ሕዝበኝነት እና ሙስና” ናቸው ብሏል።

ፓርቲው ከፌደራል መንግሥት ጋር ግጭት ውስጥ ከገባ በኋላ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ተቀስቅሶ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት “አሸባሪ ድርጅት” ተብሎ ተፈርጆ እንደነበር ይታወሳል።

ከዚህ በኋላም ፓርቲው ንብረቱ ተወርሶ እንዲሁም በምርጫ ቦርድ ሕጋዊ እውቅናው መሰረዙ የፓርቲው ህልውና ያበቃለት አስመስሎ ነበር።

ይሁን እንጂ ፓርቲው ለሁለት ዓመታት የተካሄደውን ደም አፋሳሽ ጦርነት ለማስቆም ከፌደራል መንግሥቱ ጋር የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት ከተፈራረመ በኋላ የትግራይ ክልልን እያስተዳደረ ይገኛል።

ፓርቲው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተጥሎበት የነበረው “የአሸባሪ ቡድንነት” ፍረጃም ተነስቶለታል።

ከዚህ በተጨማሪም በቅርቡ ሕጋዊ ፓርቲ ሆኖ በምርጫ ቦርድ እንዲመዘገብ የፍትሕ ሚኒስቴር ምርጫ ቦርድን መጠየቁ ይታወሳል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ባደረጉት ውይይት ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ጉባኤ ከማካሄዱ በፊት “በሕጋዊ መንገድ መመዝገብ እንዳለበት” አሳስበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ባሉ ማግስት ህወሓት ባወጣው የጉባኤ መርሃ ግብር በ14ኛው ድርጅታዊ ጉባኤ ላይ የሚሳተፉ ጉባኤተኞች ምርጫ በዚህ ሳምንት መጨረሻ እንደሚጀምር አስታውቋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ህወሓት ከዚህ ቅደም ተከተል ውጪ ጉባኤ የሚያካሂድ ከሆነ ሊከሰት የሚችለውን ነገር ለተቃዋሚ ፓርቲ ተወካዮች ገልጸዋል።

“[ህወሓት] ያንን ባያደርግ እኔ ብፈልግም ባልፈልግም ዋጋ የለውም ምርጫ ቦርድ ካልተቀበለው፣ ህወሓትን ሕጋዊ ፓርቲ ካላለው በምርጫ ሊሳተፍ አይችልም መንግሥት ሊሆን አይችልም፣ ምን ማለት ነው ተመልሰን ደግሞ ጦርነት ውስጥ እንገባለን ማለት ነው” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) በፖለቲካዊ ውሳኔ የነበረው ሕጋዊ ሰውነት እንዲመለስለት እንጂ እንደ አዲስ መመዝገብ እንደማይፈልግ የፓርቲው ቃል አቀባይ አቶ አማኑኤል አሰፋ ለቢቢሲ መናገራቸው ይታወሳል።

አቶ አማኑኤል ባለፈው ግንቦት ወር በምርጫ ሕጉ ላይ የተደረገው ማሻሻያ፤ “የተሰረዘውን [የህወሓት] ሕጋዊ ሰውነት ለመመለስ የሚያስችል ሳይሆን በልዩ ሁኔታ እንደ አዲስ ለመመዝብ የሚያስችል ነው” ብለዋል።