በአላማጣ አራት ወጣቶች “በትግራይ ታጣቂዎች” ታግተው መወሰዳቸውን ቤተሰቦቻቸው ተናገሩ

አላማጣ ከተማ

የፎቶው ባለመብት, sm

“በማንነት ጥያቄ ላይ እንቅስቃሴዎች ላይ የሚሳተፉ” አራት የአላማጣ ከተማ ነዋሪዎች በከተማዋ በሚገኙ “የትግራይ ታጣቂዎች ታግተው መወሰዳቸውን” ቤተሰቦቻቸው እና ከተያዘ በኋላ የተለቀቀ እማኝ ለቢቢሲ ገለጹ።

በትግራይ ክልል የአላማጣ ከተማ ከንቲባ በበኩላቸው “ረብሻ በመፍጠራቸው” ምክንያት የሚሊሻ አባላት ተይዘው ለፌደራል የፀጥታ ኃይሎች ከተላለፉ ግለሰቦች ውጪ “የታገተም ሆነ የታፈነ” ሰው እንደሌለ ተናግረዋል።

የአማራ እና ትግራይ ክልሎች ከሚወዛገቡባቸው የራያ አካበቢዎች አንዷ በሆነችው አላማጣ ከተማ፤ ነዋሪ የሆኑት አራት ወጣቶች በታጣቂዎች የተያዙት ባለፈው ሳምንት አርብ ሐምሌ 12/2016 ዓ.ም. እንደሆነ ስድስት የቤተሰብ አባላት እና የዐይን እማኝ ገልጸዋል።

የቤተሰብ አባላቱ እንደሚናገሩት፤ በማኅበር ተደራጅተው የተሽከርካሪ ጭነት በማራገፍ እና በመጫን ሥራ ላይ የተሰማሩት ወጣቶች በታጣቂዎች የተያዙት በከተማዋ “04 ቀበሌ” በተባለ አካባቢ ነው።

አባዲ ፈንታው፣ አምባቸው ኃይሌ፣ ከድር ኑርአዲስ እና ሞገስ መለሰ የተባሉትን አራት ወጣቶች ያገቱት “የትግራይ ታጣቂዎች” እንደሆኑ ሦስት የግለሰቦቹ የቤተሰብ አባላት እና የዐይን እማኙ ገልጸዋል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች እንደሚገልጹት የትግራይ ታጣቂዎች ወደ ከተማዋ መግባታቸው የተነገረው ከሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት አንስቶ ከተማዋን ሲያስተዳድር የነበረው በአማራ ክልል የተቋቋመ አስተዳደር አመራሮች አካባቢውን ለቅቀው መውጣታቸውን ተከትሎ ነበር። ከዚህ ክስተት በኋላ የከተማዋን የፀጥታ ሁኔታ እየተቆጣጠሩ የሚገኙት የመከላከያ ሠራዊት እና የፌደራል ፖሊስ ናቸው።

አርብ ዕለቱ ክስተት ሲፈጠር አራቱ ወጣቶችን ጨምሮ በጠቅላላው ዘጠኝ ግለሰቦች በአካባቢው የቤት እቃዎችን ከጭነት ተሽከርካሪ ላይ እያራገፉ እንደነበር አብሮ በሥራው ላይ የነበረ የዐይን እማኝ ተናግሯል። ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈቀደው የዐይን እማኝ፤ “[ጭነት] አራግፈን እንደጨረስን [...] ‘የሚመጣ አካል አለ፤ ቆዩ፣ ቁጭ በሉ’ ተባልን። ስልካችንን ተቀማን፤ ቁጭ ብለን ጠበቅናቸው። ከዚያ [ታጣቂዎች] መጡ” ሲል ሁኔታውን ገልጿል።

ወደ አካባቢው የመጡት “ክላሽ የያዙ ቢያንስ ስድስት ታጣቂዎች እና ሁለት አመራሮቻቸው” እንደሆኑ የሚናገረው የዐይን እማኙ፤ ወጣቶቹ አምስት እና አራት ሆነው በሁለት ቡድን መለየታቸውን አስረድቷል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በአንዱ ቡድን ውስጥ የተካተቱት አራቱ ወጣቶች “የማንነት ጥያቄ ሰልፍ ላይ ሲንቀሳቀሱ ፎቶ እየተነሱ ፌስቡክ ላይ ይለጥፉ ነበር” የሚለው የዐይን እማኙ፤ በዚሁ ምክንያት ለብቻ ተለይተዋል የሚል እምነት እንዳለው ገልጿል።

የተወሰዱት ወጣቶች ቤተሰብ የሆኑ ሦስት ምንጮችም ወጣቶቹ በዚሁ ዓይነት እንቅስቃሴ ላይ በነበራቸው ተሳትፎ ምክንያት በታጣቂዎች ተለይተዋል ብለው እንደሚያስቡ ገልጸዋል። ሌሎች ሦስት የቤተሰብ አባላት በበኩላቸው ወጣቶቹ በምን ምክንያት እንደተለዩ እንዳማያውቁ ተናግረዋል።

ዘጠኙን ግለሰቦች በሁለት ቡድን የተከፈሉት ታጣቂዎች፤ በአቅራቢያው ወደሚገኝ የቴክኒክ እና ሙያ ማሠልጠኛ ተቋም እንደወሰዷቸው የዐይን እማኙ አስታውሷል። የተቋሙ ቅጥር ግቢ፤ ከሚያዝያ ወር ጀምሮ ወደ “ከተማዋ መግባት የጀመሩት ትግራይ ታጣቂዎች ካረፉባቸው” አካባቢዎች ውስጥ አንዱ እንደሆነ ከዚህ ቀደም የከተማዋ ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።

ዘጠኙ ግለሰቦች ወደ ማሠልጠኛ ተቋሙ መወሰዳቸው ሲታወቅ የአካባቢው ነዋሪዎች ጉዳዩን በከተማዋ ለሚገኙት የመከላከያ ሠራዊት እና የፌደራል ፖሊስ አባላት እንዳሳወቁ አንዱ ወጣት ቤተሰብ ተናግረዋል። በዚህ ጥቆማ መሠረትም የፌደራል ፖሊስ አባላት ወደ ቦታው ማምራታቸውን ጠቅሰዋል።

ወደ ተቋሙ ቅጥር ግቢ የሄዱት የፌደራል ፖሊስ አባላት በአንድኛው ቡድን ውስጥ የነበሩት አምስት ግለሰቦችን ይዘው እንደወጡ በዚያ ቡድን ውስጥ የነበረው የዐይን እማኝ ገልጿል። የተለቀቁት ግለሰቦች በቅጥር ግቢው ወስጥ የቀሩ አራት ወጣቶች እንዳሉ ለፌደራል ፖሊስ አባላቱ ቢገልጹም “ምላሽ እንዳላገኙም” ጠቅሷል።

ከዚህ ክስተት በኋላ አራቱ ወጣቶች በምን ዓይነት ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ እንደማያውቁ ቢቢሲ ያነጋገራቸው ስድስት የቤተሰብ አባላት ገልጸዋል።

ለወጣቶቹ ውስጥ የአንዱ እናት የሆኑ ግለሰብ፤ “[ልጅሽ] ‘ቴክኒክ እና ሙያ አካባቢ ነው ያለው’ ሲሉኝ ሄጄ ሳለቅስባቸው እኔንም ገፈተሩኝ። ከዚያ በኋላ ልጄን የማገኝበት መንገድ የለም” ሲሉ ያደረጉትን ጥረት ተናግረዋል።

የወጣቶቹን በታጣቂዎች መያዝ ተከትሎ አርብ ዕለት ከሰዓት ላይ ነዋሪዎች “አደባባይ” በተባለ የከተማዋ አካባቢ ሰልፍ ለማድረግ ወጥተው የነበረ ቢሆንም በመከላከያ ሠራዊት አባላት እንዲበተኑ መደረጉን አራት ነዋሪዎች ተናግረዋል። በዚህ ወቅት የፀጥታ ኃይሎች “በወሰዱት እርምጃ” ሰዎች መጎዳታቸውንም አክለዋል።

የወጣቶቹን ጉዳይ በከተማዋ ለሚገኙ የፌደራል የፀጥታ ኃይሎች ማሳወቃቸውን የተናገሩ ሁለት የቤተሰብ አባላት፤ “እየተከታተልን ነው” የሚል ምላሽ እንዳገኙ ገልጸዋል።

በትግራይ ክልል በኩል የአላማጣ ከተማ ከንቲባ የሆኑት አቶ ዝናቡ ደስታ፤ አራት የከተማዋ ወጣቶች “በትግራይ ክልል ታጣቂዎች ተይዘዋል” መባሉን አስተባብለዋል።

ይሁንና፤ “ከተፈናቃይነት የተመለሱ የከተማዋ ሚሊሻዎች በሚገኙበት ካምፕ” አካባቢ “ረብሻ ተፈጥሮ፣ ሽጉጥም ክላሽም ተተኳኩሰው” የነበሩ አምስት ግለሰቦች በሚኒሻዎች አማካኝነት ተይዘው በከተማዋ ለሚገኙት የፌደራል የፀጥታ ኃይሎች መተላለፋቸውን ተናግረዋል።

አቶ ዝናቡ ሁኔታውን ሲያስረዱ፤ “የተያዙት አምስት ሰዎች ናቸው። ‘አራት ነው’ ብለው ጠየቋቸው። ‘አይደለም ተሳትታችኋል። አምስት ናቸው፤ ተረከቡ’ ተብለው ፌደራል ፖሊስ ተረክቦ ሄዷል” ብለዋል።

በአካባቢው የነበሩ ሚሊሻዎች ከዚህ ቀደምም “ስርቆት የፈጸሙ” ሰዎችን በተመሳሳይ መንገድ ይዘው ማስረከባቸውን ያስታወሱት ከንቲባው፤ ከዚህ ውጩ ግን “የታገተም ሆነ የታፈነ ሰው የለም” ሲሉ አስተባብለዋል።