በአላማጣ ከተማ ከፌደራል ኃይሎች ውጪ የጦር መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስ እና ሰልፍ ማድረግ ተከለከለ

የአላማጣ ከተማ አውራ መንገድ

የፎቶው ባለመብት, Youtube Screenshot

በአላማጣ ከተማ ከመከላከያ ሠራዊት እና ከፌደራል ፖሊስ ውጪ የሚገኙ ሌሎች አካላት የጦር መሳርያ ይዘው እንዳይንቀሳቀሱ ክልከላ መጣሉን ሦስት የከተማዋ ነዋሪዎች እና በአማራ ክልል የተሾሙት የአላማጣ ከንቲባ ለቢቢሲ ተናገሩ።

በከተማዋ ውስጥ ሰልፍ መውጣት እና ከፀጥታ ኃይሎች እውቅና ውጪ ማንኛውንም ስብሰባ ማድረግ ላይም እገዳ እንደተጣለ ተገልጿል።

የአማራ እና ትግራይ ክልሎች ከሚወዛገቡባቸው የራያ አካባቢዎች አንዷ በሆነችው አላማጣ ይህ “የኮማንድ ፖስት ትዕዛዛት” የተላለፈው ረቡዕ ሰኔ 26/2016 ዓ.ም. እንደሆነ ነዋሪዎች ተናግረዋል።

እንደ ነዋሪዎች ገለጻ፤ ስምንት ክልከላ እና ትዕዛዛትን የያዘው ይህ ክልከላ የተላለፈው ከሚያዝያ ወር አንስቶ ከተማዋን እየተቆጣጠሩ ባሉት የመከላከያ ሠራዊት እና የፌደራል ፖሊስ ነው።

ሁለቱ የፌደራል መንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በአላማጣ ከተማ በተለይም የፀጥታ ሁኔታን መቆጣጠር የጀመሩት ከሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በኋላ በአማራ ክልል ስር ከተማዋን ሲያስተዳድሩ የነበሩት ኃላፊዎች ከከተማዋ ከወጡ በኋላ ነው።

የፌደራል ፖሊስ አባላት፤ በትናንትናው [ረቡዕ] ዕለት የተላለፉትን ትዕዛዛት ለከተማዋ ነዋሪዎች ያሳወቁት “ከተማዋ ውስጥ በፓትሮል እየዞሩ” ክልከላዎችን በማንበብ እንደሆነ አንድ ነዋሪ ለቢቢሲ አስረድተዋል።

በዚህ ዓይነት መልኩ ከተገለጹት ክልከላዎች መካከል “ከአገር መከላከያ ሠራዊት እና ከፌደራል ፖሊስ ውጪ የጦር መሳርያ ይዙ የተገኘ ማንኛውም ሰው ሕጋዊ እርምጃ ይወሰድበታል” የሚለው እንደሚገኝበት ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ገልጸዋል።

ከጦር መሳሪያ በተጨማሪ ስለታማ የሆኑ ድምጽ አልባ መሳሪያዎችንም ይዞ መንቀሳቀስም እንደተከለከለ ተነግሯል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ይህ ትዕዛዝ መጣሉን ለቢቢሲ ያረጋገጡት በአማራ ክልል የተሾሙት የከተማዋ ከንቲባ አቶ ኃይሉ አበራ፤ ክልከላው የተላለፈው “በከተማዋ የሚንቀሳቀሱት የትግራይ ኃይሎች እንዲወጡ ሊደረግ” ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ነው ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።

አቶ ኃይሉ፤ “የታጠቀው ኃይል እስከ ነገ አርብ እንዲወጣ ተነግሮታል። በዚህ መካከል ጥፋት እንዳይጠፋ ሊሆን ይችላል” ሲሉ ክልከላው የተጣለበትን ግምታቸውን አስቀምጠዋል።

ከፌደራል ፖሊስ እና ከመከላከያ ሠራዊት እውቅና ውጪ ማንኛውንም ስብሰባ ማድረግ እንዲሁም በቡድን መንቀሳቀስ እንደማይቻል መነገሩን ነዋሪዎቹ ለቢቢሲ ገልጸዋል። ሰልፍ መውጣትም ክልከላ ከተጣለባቸው ጉዳዮች መካከል እንደሆነም ጠቅሰዋል።

እንደ ነዋሪዎቹ ገለጻ ሰልፍ ማድረግ የተመለከተው ክልከላ የመጣው ለመጪው እሁድ የተቀጠረ ሰላማዊ ሰልፍ እንደተሰረዘ ከተነገረ በኋላ ነው። ሰልፍ ሊካሄደ የነበረበት አንዱ ምክንያት “በአካባቢው ከመንግሥት ኃይሎች ውጪ ያሉ ታጣቂዎች እንዲወጡ ለመጠየቅ” እንደሆነ አንድ የከተማዋ ነዋሪ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በመከላከያ ሠራዊት እና የፌደራል ፖሊስ የተጣለው ክልከላ በከተማዋ የነዋሪዎች፣ የተሽከርካሪዎች እና የንግድ ተቋማት እንቅስቃሴ ላይም የሰዓት ገደብ ያስቀመጠ እንደሆነ ነዋሪዎቹ ገልጸዋል።

ባለ ሶስት እግር “የባጃጅ” ተሽከርካሪዎች ከምሽቱ 12 ሰዓት በኋላ እንዳይንቀሳቀሱም ትዕዛዝ መሰጠቱ ተገልጿል።

እንደ ሆቴል እና መጠጥ ቤቶች ያሉ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እና ነዋሪዎች ደግሞ ከምሽቱ ሁለት ሰዓት በኋላ በከተማዋ ውስጥ ከፍት መሆን እና መንቀሳቀስ እንደማይችሉ መከልከሉ ተነግሯል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች እንደሚያስረዱት ረቡዕ ዕለት ከተላለፉት ትዕዛዛት ውስጥ ክልከላን ያልያዘው ተፈናቃዮዎችን የሚመለከተው ትዕዛዝ ነው። የከተማዋ ነዋሪዎች በጦርነቱ ምክንያት ተፈናቅለው የነበሩ ተመላሾችን “በኢትዮጵያዊነት ስሜት እንዲቀበሉ” እንደተነገራቸው ተገልጿል።

ሁለቱ ክልሎች በይገባኛል በሚወዛገቡባቸው አካባቢዎች ከሦስት ዓመት በፊት ጦርነት መቀስቀሱን ተከትሎ የተፈናቀሉ ሰዎችን ለመመለስ በክልሎቹ እና በፌደራል መንግሥቱ አማካይነት ጥረት እየተደረገ መሆኑ ይታወቃል።