“መፈንቅለ መንግሥት ኢትዮጵያ ውስጥ አይሳካም” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

የፎቶው ባለመብት, pm office
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ “መፈንቅለ መንግሥት ኢትዮጵያ ውስጥ አይሳካም፤ እኛ ወታደሮች ነን መፈንቅለ መንግሥት እንዳይሳካ አድርገን ነው ተቋማት የሠራነው” ሲሉ ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ “አንዳንድ አባቶች” ሲሉ የጠሯቸው ነገር ግን በስም ያልጠቀሷቸው ግለሰቦች “በቅርቡ እንዳንድ ቦታ ላይ መፈንቅለ መንግሥት እናካሂዳለን” የሚል “ውይይት ያካሂዳሉ” ብለዋል።
ዐቢይ ይህን ያሉት ዛሬ ሐሙስ ሰኔ 27/2016 ዓ.ም. ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ እና ማብራሪያ ላይ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተሳተፉበት እና ለግማሽ ቀን ያህል በዘለቀው የዛሬው የፓርላማ ስብሰባ ላይ 16 የፓርላማ አባላት ጥያቄዎችን አቅርበዋል። አብዛኛዎቹ ጥያቄዎች የኢኮኖሚ እንዲሁም የሰላም እና ደኅንነት ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ነበሩ።
ከጥያቄዎቹ መቅረብ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ በምሳሌ እና በተረት እያስደገፉ ምላሽ እና ማብራሪያቸውን ሰጥተዋል።
የሰላም እና ደኅንነት ጉዳይን በሚመለከተ በሰጡት ማብራሪያ ላይ “በቅርቡ እንዳንድ ቦታ ላይ መፈንቅለ መንግሥት እናካሂዳለን ብለው አንዳንድ አባቶቻችን ውይይት ያካሂዳሉ” ሲሉ ተደምጠዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አክለውም፤ “መፈንቅለ መንግሥት ኢትዮጵያ ውስጥ አይሳካም፤ እኛ ወታደሮች ነን መፈንቅለ መንግሥት እንዳይሳካ አድረገን ነው ተቋማትን የሠራነው” ሲሉ ይካሄዳል ያሉት ውይይት ፍሬ እንደማያፈራ በፓርቲያቸው የበላይነት ለተያዘው ምክር ቤት አስረግጠዋል።
በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ “ኢትዮጵያ ውስጥ መፈንቅለ መንግሥት አንዴ የተሳካው የዛሬ 50 ዓመት ከሃምሳ ዓመት በኋላ ብዙ የሚረቡ እና የማይረቡ ሙከራዎች ነበሩ አልተሳኩም አሁን ጭራሽ አይሳካም” ሲሉ ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም “እንበልና ይሄ የማይሳካው ነገር ተሳካ እንበል። አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ የሆነ ሰው ገድለን መፈንቅለ መንግሥት ብናደርግ፤ ኢትዮጵያን ሌላ ሱዳን እናደርጋት እንደሆን እንጂ አገር ሆና፣ እኛም መንግሥት ሆነን አንቀጥልም” ብለዋል።
ዐቢይ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ በዛሬው የምክር ቤት ስበሰባ ላይም መንግስታቸው ለሰላም “ዝግጁ” መሆኑን አስረግጠው ተናግረዋል።
“ሶማሊን እንደ ኢትዮጵያዊ ቆጥረን ‘ኢምፓወር’ ያደረግነው እኛ ነን”
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በዲፕሎማሲያው እና ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገራት ጋር ስላላት ግንኙነትም ማብራሪያ ሰጥተዋል። በዚህ ማብራሪያቸው በዋነኛነት ያተኮሩት ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በገቡበት ውዝግብ ላይ ነው።
ከሰባት ወራት በፊት ኢትዮጵያ ነጻነቷን ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር የመግባቢያ ስምምነት ከተፈራረመች ወዲህ የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ ግንኙነት ሻክሯል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ታኅሣሥ 22/2016 ዓ.ም. በስምምነት ሰነዱ ላይ ፊርማቸውን ያኖሩት “በሶማሊያ አንድነት ላይ ጥያቄ ፈጥረን አይደለም” ሲሉ ተናግረዋል።
ከስምምነቱ መፈረም በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባደረጓቸው ንግግሮች በተደጋጋሚ የኢትዮጵያ መንግሥት “ለሶማሊያ አንድነት” ከፈለ የሚሉትን “መስዋዕትነት” ሲዘረዝሩ ይደመጣሉ።
ዛሬም በተመሳሳይ፤ “ለሶማሊ ሰላም [እና] አንድነት ሞተናል፤ ለሶማሊ ያለንን ክብር ብልጽግና ከማንም መንግሥታት በላይ አሳይቷል” ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በዛሬው ንግግራቸው የኢትዮጵያ መንግሥትን “መስዋዕትነቶችን’ በመዘርዘር ብቻ አላበቁም፤ “ሶማሊን እንደ ኢትዮጵያዊ ቆጥረን ‘ኢምፓወር’ [ያበቃነው] ያደረግነው እኛ ነን” ሲሉ ተደምጠዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሶማሊላንድ ጋር የተደረገውን ስምምነት ተከትሎ፤ “የሶማሊያ መንግሥት እኛን ከማናገር በየሰፈሩ እየዞረ እኛን መክሰስ መርጧል” በማለት ወቅሰዋል።
በተጨማሪም “እኛን ለመክሰስ አገር ለአገር መሄድ አያስፈልግም፤ አዲስ አበባ መምጣት ይቻላል ለመነጋገር ዝግጁ ነን። ሶማሊያ እንድትጎዳ፣ እንድትፈራርስም፣ እንድትበተንም የሚፈልግ መንግሥት አይደለንም፤ ቢሆን ልጆቹን ልኮ እዚያ አይሞትም” ብለዋል።
የመግባቢያ ስምምነቱን በተመለከተም “ለሁሉም ጎረቤቶቻችን ያቀረብነው ጥያቄ ሁሉንም ጠይቀን፣ ለምነን ምላሽ ስናጣ የመለሰልን አካል ጋር ተፈራረምን እንጂ በሶማሊያ አንድነት ላይ ጥያቄ ፈጥረን አይደለም” ሲሉ አብራርተዋል።
ከሶማሊያ በተጨማሪ የሱዳንን የእርስ በርስ ጦርንት በተመለከተ የመንግሥታቸውን አቋም ለምክር ቤቱ አስረድተዋል። ዐቢይ በዚህ ገለጻቸው “ከሁለቱም ተፋላሚ ኃይሎች 100 ፐርሰንት ገለልተኛ አቋም ይዘን ሁለቱም ወደ ሰላም እንዲመጡ ስንሠራ ቆይተናል አሁንም የምንሠራው በዚያው መንገድ ነው” ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, pm office
“ኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት እና ወታደር በጅምላ አይገድልም”
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ የመንግሥት ኃይሎች የጅምላ ግድያዎችን ፈጽመዋል በሚል በመንግሥታቸው ላይ የቀረበውን ክስ አስተባብለዋል።
ዐቢይ ይህን ማስተባበያ የሰጡት የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ተወካይ አቶ አበባው ደሳለው፤ “መንግሥት ጅምላ ግድያ እና ሌሎች የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለማቆም ምን የወሰነው ጉዳይ አለ?” በሚል ላቀረቡት ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ ነው።
አቶ አበባው ደሳለው “ባለፉት አስር ወራት አስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ሰበብ በማድረግ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጽመዋል። ባልታጠቁ ሰዎች ላይ ጅምላ ግድያዎች በመንግስት ኃይሎች ተፈጽሟል” ሲሉ ከስሰዋል። አቶ አበባው ይህን ክሳቸውን አካባቢዎችን በመጥቀስ ጭምር በማስረጃ ለማስደገፍ ሞክረዋል።
የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካዩ “የጅምላ ግድያ” ተፈጸመባቸው በሚል የጠቀሷቸው የአማራ ክልል አካባቢዎች መርዓዊ፣ ጅጋ፣ ደብረ ኤሊያስ፣ ፍኖተ ሰላም፣ ደብረ ሲና፣ ጎንደር እና ወሎ ናቸው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን የፓርላማ አባሉን ውንጀላ፤ “በጅምላ ኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት እና ወታደር አይገድልም። በጅምላ ለማሸነፍ ይነሳ እና ሲሞት ነው በጅምላ ሞትኩ የሚለው” ሲሉ አስተባብለዋል።
የፕሪቶሪያው ስምምነት አፈጻጸም እና የተፈናቃዮች መመለስ
ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ከቀረቡ ጥያቄዎች መካከል የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) እና የፌደራል መንግሥት መካከል የተፈረመው የፕሪቶሪያው ሰላም ስምምነት አፈጻጸም አንደኛው ነው።
ጥያቄውን ያቀረቡት ራህመት አወል ተባሉት የምክር ቤት አባል “በፕሪቶሪያው ስምምነት አፈጻጸም ዙሪያ የተለያዩ ውዥምብሮች እየተዘሩ” መሆኑን በመጥቀስ “የስምምነቱ አፈጻጸም ምን ደረጃ ላይ ይገኛል?” ሲሉ ጠይቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ ሰላም ስምምነቱ “ዋና አንኳር” ጉዳዮች የቀድሞ ተዋጊዎችን መልሶ ማቋቋም እና ተፈናቃዮችን መመልስ መሆኑን ጠቁመዋል።
ከራያ እና ከጠለምት የተፈናቀሉ ሰዎች የወደ ቀያቸው መመለስ እንደተጀመረ ያስታወሱት ዐቢይ “በራያ የነበረው አመላለስ ችግር አለበት፤ ከአስቀመጥነው አቅጣጫ፣ ካስቀመትነው መንገድ ወጣ ያለ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም “እናንት ስላጠፋችሁ ሕዝብ ተመልሶ ከሚወጣ ባስቀመጥነው አቅጣጫ የሚቆይበት መንገድ ይፈጠር ብለን ለማስተካከል ሙከራ እያደረግን ነው። በጸለምት ደግሞ ከራያ ተምረን ተሻለ ጅማሮዎች አሉ” ብለዋል።
ተፈናቃዮችን የመመለሱ ሥራ “አልጋ በአልጋ ነው ማለት አይደለም” ያሉት ዐቢይ፤ “አንዴ ከዚህ አንዴ ከዚያ ሰዎች እንቅፋት ይፈጥራሉ” ሲሉ ተደምጠዋል።
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር እና የህወሓት ዋና ዋና ኃላፊዎች “በሰላማዊ መንገድ ጉዳዩ እንዲፈታ ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው” ብለው እንደሚያምኑ የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “ከመንግሥቱ እና ከህወሃት ዋነኛ ኃላፈዎች ውጪ ግን ነገር ቢበላሽ የሚፈልጉ ሰዎች አሉ። አሁንም እልኸኝነታቸው ያልቀነሰ አሁንም የበዛ ቁጣ ያላቸው ግለሰቦች አሉ” ሲሉ ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ምን አሉ?
ዐቢይ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ሰፋ ያለ ጊዜ ወስደው ምላሽ እና ማብራሪያዎችን ሰጥተዋል። በዚህ ማብራሪያቸው ላይ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ካለፈው ዓመት፣ አለፍ ሲልም ከለውጡ በፊት ከነበረው ጋር እያነጻጸሩ ለፓርላማ አባላቱ ገልጻ አድርገዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ገለጻቸውን የጀመሩት በኢኮኖሚው ዘርፍ “ስኬታማ ዓመት ነው ያሳለፍነው” በማለት ነው።
ሊጠናቀቅ ሦስት ቀናት በቀሩት የ2016 ዓ.ም. በጀት ዓመት መንግሥት 529 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ 466 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን፣ እንዲሁም 716 ቢሊዮን ብር ወጪ ማድረጉን ተናግረዋል።
ከገቢ አንጻር ሦስት “አንኳር ችግሮች” መኖራቸውን የጠቀሱት ጠ/ሚ ዐቢይ፤ ቀዳሚው ኮንትሮባንድ መሆኑን ገልጸዋል። “ኮንትሮባንድ አሁንም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ጋሬጣ ሆኖ ያለ ጉዳይ ነው። በርካታ ሸቀጦች ወርቅን ጨምሮ ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ ወደ ተለያየ አገር ይሄዳሉ” ብለዋል።
የገቢ ስወራ እና የንግድ ማጭበርበር በተመሳሳይ አገሪቱ ገቢ እንዳታገኝ እያደረጉ ያሉ “ችግሮች” መሆናቸውንም ጠቁመዋል።
“ዘንድሮ ኤክስፖርት አቅማችን ከአምናው ያንሳል፣ አምናውን ልናሳክ አንችልም የሚል ግምገማ” እንደነበር ዐቢይ አህመድ ለፓርላማ አባላት ገልጸዋል። ከዚህ ግምገማ ላይ የተደረሰው “ቀይ ባሕር ላይ በገጠመው ሁኔታ” ምክንያት መሆኑን አክለዋል።
በእስራኤል እና በሐማስ መካከል ጦርነት መቀስቀሱን ተከትሎ የየመን ታጣቂ ቡድን ሁቲ በቀይ ባሕር በኩል ሸቀጦችን በሚያጓጉዙ መርከቦች ላይ ጥቃት እየፈጸሙ መሆኑ በአካባቢው የንግድ እንቅስቃሴን አስተጓጉሏል።
“ያንንም ገምግመን ባጠረ ጊዜ አይሻሻልም፣ ኤክስፖርታችን ይጎዳል የሚል ግምገማ ነበር። ነገር ግን ዘንድሮ ከአምናው ከአራት ፐርሰንት በላይ እድገት ያለው ኤክስፖርት ማሳካት ተችሏል። ይህ በጣም ትልቅ ድል ነው ከነበር ችግር አንጻር” ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አጠቃላይ የኢኮኖሚውን አፈጻጸም በተመለከተ “ከውጊያው፣ ከእርዳታ ማነስ፣ ከብድር መጥፋት፣ በቀይ ባሕር ካገጠመን ችግር አንጻር ሲታይ ዘንድሮ ተሳካ ነው ብለን ነው የምገመግመው” ሲሉ ተናግዋል።












