በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል የተፈጠረው አለመግባባት በቱርክ ጥረት መፍትሄ ያገኛል?

ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ እና ጠቅላይ ሚኒስር ዐቢይ አሕመድ
የምስሉ መግለጫ, ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ እና ጠቅላይ ሚኒስር ዐቢይ አሕመድ

ነጻ አገርነቷን ያወጀችው ሶማሊላንድ ከወደብ አልባዋ ኢትዮጵያ ጋር የባሕር ጠረፍ በኪራይ ለመስጠት የሚያስችላትን ስምምነት ከተፈራረመች በኋላ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ባለፉት ወራት ውጥረት አይሎ ቆይቷል።

ዝርዝሩ አሁን ድረስ ይፋ ያልተደረገው የባሕር በር አገልግሎት ስምምነት ሕገወጥ እና “የወረራ ድርጊት” ነው ያለችው ሶማሊላንድን እንደተገንጣይ ግዛቷ የምትመለከታት ሶማሊያ ደስተኛ አለመሆኗን የገለጸችው ወዲያው ነበር።

በተጨማሪም በስምምነቱ ኢትዮጵያ ከሦስት አስርት ዓመታት በፊት በአገሪቱ የተካሄደውን የእስር በርስ ጦርነት ተከትሎ ነጻነቷን ላወጀችው ሶማሊላንድ እንደ አገር ዕውቅናን እንደምትሰጥ መገለጹ ሶማሊያን የበለጠ አስቆጥቷል።

የአፍሪካ ኅብረት እና አሜሪካ የሶማሊያን የግዛት አንድነት እንደሚደግፉ እና ሁለቱም አገራት ውጥረቱን እንዲያረግቡ ጠይቀዋል።

አሁን ደግሞ ቱርክ የኢትዮጵያን እና የሶማሊያን ልዑካን ወደ ዋና ከተማዋ አንካራ ለውይይት በመጋበዝ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት እያደረገች ነው።

ድርድሩ የተሳካ ነበር?

በቱርክ አማካይነት የተካሄደው ንግግር በከፊል የተሳካ ነበር ማለት ይቻላል።

የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ሰኞ ሰኔ 24/2016 ዓ.ም. በቱርክ ዋና ከተማ ቢገኙም፣ ፊት ለፊት ተቀምጠው ግን ለመነጋገር ፈቃደኛ አልሆኑም።

የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በሁለቱ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች መካከል የተካሄደውን ንግግር “ግልጽ፣ የወዳጅነት እና የወደፊቱን የሚመለከት” ሲሉ ነበር የገለጹት።

ሁለቱ ወገኖች በሚቀጥለው ነሐሴ ወር መጨረሻ ላይ ሌላ ዙር ንግግር ለማድረግ ቀጠሮ ይዘዋል። ምንጮች ለቢቢሲ እንደተናገሩት እስከዚያ ድረስ መሻሻሎች ካሉ የአገራቱ መሪዎች ሊገናኙ እና ሊነጋገሩ የሚችሉበት ተስፋ አለ።

ቱርክ ለምን ተሳተፈች?

ቱርክ ከሶማሊያ ጋር የቀረበ ግንኙነት ያላት ሲሆን፣ ሁለቱ መንግሥታት በቅርቡ ቱርክ የሶማሊያን የባሕር ጠረፍ ለመጠበቅ እና የባሕር ኃይሏን መልሳ ለመገንባት የሚያስችል የ10 ዓመት የመከላከያ ስምምነት ተፈራርመዋል።

የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ እንዳሉት፣ ቱርክ ንግግሩን እንድታመቻች ጥያቄው የቀረበው ከኢትዮጵያ በኩል ነው።

ይህም ሶማሊያ ከምዕራባውያን እና ከባሕረ ሰላጤው አገራት ድጋፍ ለማግኘት ዲፕሎማሲያዊ ዘመቻ እያደረገች ባለበት ጊዜ ኢትዮጵያ ውጥረቱን ለማርገብ ፍላጎት እንዳለት አመልክቷል።

ነገር ግን ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር ከፈረመችው ስምምነት ስለመውጣቷ “ምንም አመላከች ነገር የለም” ሲሉ የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ በምን ተስማሙ?

በኢትዮጵያ እና በሶማሊላንድ መሪዎች መካከል ከስምምነት የተደረሰበት ትክክለኛው ሰነድ አስካሁን ለሕዝብ ይፋ አልተደረገም። ይህንንም በተመለከተ ሁለቱ ወገኖች የተፈራረሙት የመግባባቢያ ሰነድ የተለያዩ ይዘቶች በመውጣታቸው መለየት አስቻጋሪ ሆኗል።

የመግባቢያ ስምምነቱ አሳሪ እና ሕጋዊ ሰነድ ከመሆኑ ይልቅ የፍላጎት መግለጫ ነው። ነገር ግን የትኛው ወደብ እንደሆነ ባይታወቅም ሶማሊላንድ ለኢትዮጵያ የንግድ እንቅስቃሴ የሚውል የባሕር መተላለፊያ በር ለመስጠት ዝግጁ መሆኗ ግልጽ ነው።

ስምምነቱ ወታደራዊ ገጽታም አለው። በዚህም ሶማሊላንድ እንዳሳወቀችው የተወሰነ የባሕር ዳርቻ ለኢትዮጵያ ባሕር ኃይል በኪራይ የምትስጥ ሲሆን፣ ይህንንም ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።

በምላሹም ሶማሊላንድ በአፍሪካ ስኬታማ ከሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የባለቤትነት ድርሻን ታገኛለች።

ነገር ግን አጠያያቂ የሆነው ጉዳይ የሚነሳው፣ ቀድሞ በብሪታኒያ የሞግዚት አስተዳደር ስር የነበረችው እና ባለፉት 30 ዓመታት ማንም እንደአገርነት ዕውቅና ሊሰጣት ላልደፈረው ለሶማሊላንድ ኢትዮጵያ የነጻ አገርነት ዕውቅናን ትሰጣለች ወይ? የሚለው ነው።

በኢትዮጵያ እና በሶማሊላንድ መካከል የመግባቢያ ስምምነቱ በተፈረመበት ጊዜ የሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ አብዲ እንዳሉት፣ ስምምነቱ ወደፊት ኢትዮጵያ ሶማሊላንድን የነጻ አገርነት እውቅናን እንደምትሰጥ ያካትታል።

ኢትዮጵያ ግን ይህንን አላረጋገጠችም። ይልቁንም መንግሥት ከስምምነቱ መፈረም ከቀናት በኋላ በሰጠው ማብራሪያ “...ሶማሊላንድ ዕውቅናን ለማግኘት ከምታደርገው ጥረት አንጻር አቋም ለመያዝ ጥልቅ ግምገማ እንደሚደረግ” የሚገልጽ ሀሳብ ተካቷል።

ካርታ

ስምምነቱ ለምን አወዛጋቢ ሆነ?

ለሶማሊያ ሶማሊላንድ የማትነጠል የግዛቷ አካል ናት። ስለዚህም ሶማሊላንድ ከሌላ አገር ጋር የምታደርገው ማንኛውም ዓይነት ስምምነት ከሶማሊያ ፈቃድ ውጪ ከሆነ ችግርን ሊያስከትል ይችላል።

የመግባቢያ ሰነዱ ከተፈመ በኋላ ሶማሊያ ስምምነቱ “የወረራ” ድርጊት ነው በማለት፣ “ለሰላም እና መረጋጋት...እንቅፋት ነው” ብላለች። በተጨማሪም በአዲስ አበባ ያሉትን አምባሳደሯን ስትጠራ፣ ይህንንም ተለትሎ በሞቃዲሾ የኢትዮጵያ አምባሳደርም አገሪቱን ለቀው ወጥተዋል።

የሶማሊያው ፕሬዝዳንትም “አገራችንን አስፈላጊ በሆነው አማራጭ ሁሉ እንከላከላለን፣ ሊረዳን ከሚፈልግ ከየትኛውም ወዳጃችን ድጋፍ እንፈልጋለን” ሲሉ ቁጣቸውን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያን የአገራቸው “ጠላት” ብለው የጠሩት ፕሬዝዳንቱ፣ ሶማሊያውያን ወጣቶች “አገራቸውን ለመከላከል” ዝግጁ እንዲሆኑም ጥሪ አቅርበው ነበር።

ስምምነቱን ተከትሎ ተቃውሞ ለማሰማት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተሳተፉበት የተቃውሞ ሰልፍ ሞቃዲሾ ውስጥ ተካሂዷል።

ታሪካዊ ባላንጣነት ያላቸው ሶማሊያ እና ኢትዮጵያ በአውሮፓውያኑ 1977 እና 1978 የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልልን ለመቆጣጠር አውዳሚ ጦርነትን አካሂደዋል።

ሶማሊላንድ በምን ሁኔታ ላይ ናት?

ቀድሞ በብሪታኒያ የሞግዚት አስተዳደር ስር የነበረችው ሶማሊላንድ በአውሮፓውያኑ 1991 ነጻነቷን ያወጀች ስትሆን፣ በአግባቡ የሚሠራ ፖለቲካዊ ሥርዓትን፣ መደበኛ ምርጫ ማካሄድን፣ የፖሊስ ኃይልን እና የራሷ የሆነ ገንዘብን ጨምሮ አንድ አገር የሚያስፈልገው ነገሮች ሁሉ አሏት።

በተጨማሪም ሶማሊላንድ ባለፉት ሦስት አስርት ዓመታት ሶማሊያን ከሚያምሰው ግጭት እና ቀውስ ገለል ብላ ተረጋግታ ቆይታለች።

ነገር ግን ከየትኛውም የዓለም አገር እንደ ነጻ አገር ዕውቅናን ማግኘት ግን ሳትችል ቀርታለች።

ሶማሊላንድ እንደምትለው ኢትዮጵያ በሆነ ጊዜ ለአገሪቱ ዕውቅና የምትሰጥ ከሆነ፣ እርምጃው በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ መሠረታዊ የሆነ ለውጥን ያስከትላል።

በኢትዮጵያ እና በሶማሊላንድ መካከል የተደረሰው ስምምነት ሶማሊያ ውስጥ ተቃውሞን ቀስቅሷል

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, በኢትዮጵያ እና በሶማሊላንድ መካከል የተደረሰው ስምምነት ሶማሊያ ውስጥ ተቃውሞን ቀስቅሷል

ኢትዮጵያ ለምን ስምምነቱን ፈለገችው?

ባለፈው ዓመት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የባሕር በር ጉዳይ ለኢትዮጵያ የኅልውና ጉዳይ ነው ብለው ተናግረው ነበር።

ኤርትራ ከኢትዮጵያ ስትገነጠል የባሕር በር ያጣችው ኢትዮጵያ ከ100 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት ስትሆን፣ ይህም በዓለም ላይ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ያላት ወደብ አልባ አገር ያደርጋታል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ኢትዮጵያ ፍላጎቷን በኃይል ለማሳካት ትሞክር ይሆናል የሚል ስጋት ፈጥሮ ነበር።

ከሶማሊላንድ ጋር የተፈረመው ስምምነትም ታሪካዊ ተብሎ ዓላማውም ሰላማዊ መሆኑ አጽንኦት ተሰጥቶታል።

“በመንግሥት ይፋ የተደረገው አቋም ከማንም ጋር በጦርነት ላለመፈላለግ ባለ ጽኑ አቋም ላይ የተመሠረተ ነው” ሲል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ከስምምነቱ በኋላ ገልጿል።

ነገር ግን ውዝግቡን በግልጽ ባጣቀሰ ሁኔታ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከስምምነቱ ከቀናት በኋላ በኤክስ ላይ ባሳፈሩት ጽሁፍ “ነገሮች በለመድናቸው ወይም በምናውቃቸው ወይም በምንገምታቸው መንገዶች ይሄዳሉ ብለን ከጠበቅን [ዕድሎች] ሊያመልጡን ይችላሉ።”

አክለውም አንዳንድ ጊዜ ግባችንን ለማሳካት “ከተለመደው መንገድ ውጪ” ማሰብ ያስፈልጋል ብለዋል።

ሌሎች ምን አሉ?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የአፍሪካ ኅብረቱ ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሐማት “እየተቀጣጠለ ያለውን ውጥረት ለማርገብ” መረጋጋት እና መከባበር እንዲፈጠር ጥሪ ካቀረቡት መካከል ቀዳሚው ናቸው።

የሊቀመንበሩ መግለጫም በአሜሪካ መንግሥት፣ በአረብ ሊግ እና በአውሮፓ ኅብረትም ድጋፍ አግኝቷል።

በቅርቡ በመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ስብሰባ ላይ የአሜሪካ ከፍተኛ ዲፕሎማት የሆኑት ሮበርት ዉድ አገራቸው “በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል ያለው ውጥረት እና በጋራ የፀጥታ ጉዳዮች ላይ እያደረሰ ያለው አሉታዊ ተፅእኖ እንዳሳሰባት” ገልጸው ነበር።

ከታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ምክንያት ከኢትዮጵያ ጋር ውዝግብ ውስጥ የምትገኘው ግብፅ ደግሞ ሶማሊያን እንደምትደግፍ በይፋ አስታውቃለች።

ከስምምነቱ መፈረም በኋላ የግብፁ ፕሬዝዳንት አብዱል ፋታህ ኤል-ሲሲ ለሶማሊያው አቻቸው የሶማሊያን “ደኅንነት እና መረጋጋት ለመጠበቅ” ግብፅ አብራቸው እንደምትቆም አረጋግጠዋል።

ሶማሊላንድ እና ኢትዮጵያ ስምምነት ከተፈራረሙ በኋላ የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ቀጣናዊ ድጋፍ ለማሰባሰብ ሁለት ጊዜ ወደ ኤርትራ ተጉዘዋል። የኤርትራው ፕሬዝዳንት በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ወቅት የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የቅርብ አጋር የነበሩ ሲሆን፣ አሁን ግን ግንኙነታቸው የተቀዛቀዘ ይመስላል።

በተጨማሪም ኤርትራ የኢትዮጵያ የባሕር መተላላፊያ የማግኘት ፍላጎት እንደሚያሳስባት ይነገራል።

ሌላኛው ከኢትዮጵያ እና ከሶማሊያ ጋር የቀረበ ግንኙነት ያላት ጎረቤት አገር ኬንያ ከጉዳዩ ገለል ብላ ምንም አይነት አስተያየት በይፋ ያልሰጠች ሲሆን፣ ኡጋንዳም በጉዳዩ ላይ ግልጽ ያለ አቋሟን ሳታንጸባርቅ ቆይታለች።

በቀጣናው ከፍተኛ ሚና ያላቸው ሳዑዲ አረቢያ እና ቻይና ለሞቃዲሾ እንደ ዲፕሎማሲያዊ ድል የሚታየውን የሶማሊያ የግዛት አንድነት እንደሚደግፉ ገልጸዋል።