በቱርክ የተገናኙት ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ አለመግባባቶችን በሰላም እንደሚፈቱ ገለጹ

የፎቶው ባለመብት, MFA OF TURKEY
በቱርክ አሸማጋይነት በአንካራ ሰኔ 24/ 2016 ዓ.ም የተገናኙት ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በመካከላቸው ያሉ አለመግባባቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ቁርጠኛ መሆናቸውን ገለጹ።
በቱርክ ጋባዥነት ወደ አንካራ ያቀኑት የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታየ አጽቀስላሴ እና የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር አህመድ ሞሊም ከውይይታቸው በኋላ በጋራ ባወጡት መግለጫ ነው ይህንን ያስታወቁት።
ሚኒስትሮቹ ያላቸውን ልዩነቶች ለሁለቱም ተቀባይነት ባለው ማዕቀፍ ውስጥ ለመፍታት ያሉ ሁኔታዎችን እንደዳሱም የሶስቱ አገራት የጋራ መግለጫ አትቷል።
በቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሃካን ፊዳን አመቻችነት የተገናኙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በተናጥል በግልጽነት፣ወዳጅነት ባለው እና የወደፊቱን ያለመ ውይይት እንደነበራቸው ይኸው መግለጫ ጠቅሷል።
ራሷን በነጻ አገርነት ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር ከስድስት ወራት በፊት በተፈረመ የባህር በር መግባቢያ ምክንያት ውዝግብ ውስጥ የገቡት ሁለቱ አገራት የተፈጠረውን ውጥረት ለማርገብ ሲገናኙ ይህ የመጀመሪያቸው ነው።
ሁለቱ አገራት መልካም ጉርብትናን እና ቀጠናዊ መረጋጋትን ከግምት በማስገባት መፍትሄዎችን ለማመላከት ያለሙ ምክክሮችን ለመቀጠል መስማማታቸውን ገልጸዋል።
በዚህም መሰረት ሚኒስትሮቹ ለሁለተኛ ዙር ውይይት በአንካራ ነሐሴ 27/ 2016 ዓ.ም እንደሚገናኙ ተገልጿል።
የሶስቱ አገራት የጋራ መግለጫ ሁለቱ አገራት ልዩነታቸውን ለሁለቱም ተቀባይነት ባለው ማዕቀፍ ለመፍታት ያሉ ሁኔታዎችን እንደዳሰሰ ቢገልጽም እነዚህ ተቀባይነት አላቸው ስለተባሉ ጉዳዮች የተጠቀሰ ጉዳይ የለም።
ይህ በአንዲህ እንዳለ የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼይክ ሞሐሙድ ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የደረሰችውን የወደብ ስምምነት የመተው ምንም አይነት ምልክት አላሰየችም ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ ሰኞ ሰኔ 24/2016 ዓ.ም. የኢትዮጵያ፣ ሶማሊያ እና የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በጋራ ያወጡትን መግለጫ ተከትሎ በሰጡት አስያየት በኢትዮጵያ ጥያቄ አንካራ ላይ በተደረገው ውይይት የሶማሊያ እና የኢትዮጵያ ተወካዮች ፊት ለፊት ተገናኝተው አልተነጋገሩም።
የቀድሞው ሚኒስትር ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ይልቅ ከሶማሊያ ወደቦች ልትጠቀም የምትችልበት ስምምነት ሊኖር ይችላል ብለዋል።
የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም እንዲሁ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ወደ አንካራ ማቅናታቸውን በገለጸበት ጽሑፉ ስለ ንግግሩ አጀንዳ በዝርዝር ያለው ነገር ባይኖርም “የሶማሊያ ፌደራል መንግሥት የግዛት አንድነትን መጠበቅ መርሁ ላይ ቁርጠኛ ነው” ብሏል።
ከሶማሊላንድ ጋር ስለገባችው የባህር በር የመግባቢያ ስምምነት በይፋ መግለጫዎችን የማትሰጠው ኢትዮጵያ ከውይይቱ በፊት ምንም ባትልም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአገራቱን የጋራ መግለጫ ይፋዊ በሆነው ገጹ አውጥቷል።
ኢትዮጵያ የባሕር ኃይል ሰፈር በኪራይ የምታገኝበት እና በምትኩም ለሶማሊላንድ ዕውቅና የምትሰጥበት ስምምነት በሁለት ወራት ገደማ እንደሚፈረም የሶማሊላንድ የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ኢሳ ካይድ ለቢቢሲ ሶማሊኛ ከሳምንታት በፊት መናገራቸው ይታወሳል።
ኢትዮጵያ ራሷን እንደ ነጻ አገር ካወጀችው እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ካላገኘችው ሶማሊላንድ ጋር 20 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የባሕር ጠረፍ ለማግኘት የፈረመችው የመግባቢያ ሰነድ ሶማሊያን በእጅጉ አስቆጥቶ በቀጠናው ከፍተኛ ውጥረትን ያስከተለ ሆኗል።
ከሶማሊያ በኩል ተደጋጋሚ ክሶች እና መግለጫዎች ከመቅረባቸው በተጨማሪም ጉዳዩን ወደ መንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ወስዳዋለች።
በቅርቡም ከአፍሪካ ኅብረት ተልዕኮ ውጪ የሆኑ የኢትዮጵያ ወታደሮች በሕገወጥ መልኩ ድንበር ተሻግረው ወደ ሶማሊያ ገብተዋል ስትል ለተመድ የጸጥታ ምክር ቤት ከሳለች። ኢትዮጵያ በበኩሏ ሶማሊያ ያቀረበችው ክስ መሠረተ ቢስ ነው ስትል አጣጥላለች።
በተጨማሪም ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር ያላትን ስምምነት አዲሱ ተልዕኮ ከሚወሰንበት፣ ከሰኔ መጨረሻ በፊት ካልሰረዘች በአትሚስ ስር እንዲሁም በሁለትዮሽ ስምምነት የሰፈሩት ሁሉም የኢትዮጵያ ሠራዊት አባላት ከአገሪቱ እንደሚወጡ እንደሚደረግ የአገሪቱ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ሑሴን አሊ አስጠንቅቀዋል።
ለአስራ ሰባት ዓመታት ያህል ወታደሮቿን በሶማሊያ አሰማርታ የምትገኘው ኢትዮጵያ በበኩሏ ወታደሯቿን እንድታስወጣ ከተፈለገ በይፋ ጥያቄው ሲቀርብ ተግባራዊ እንደሚሆን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነቢዩ ተድላ ጠቁመው “ከሶማሊያ መንግሥት፣ ከአፍሪካ ኅብረትም ይሁን ከተባበሩት የመንግሥታቱ ድርጅት ኢትዮጵያ በሶማሊያ ያለውን ኃይሏን ታስወጣ የሚል በይፋ የቀረበ ነገር የለም” ብለዋል።












