ሶማሊያ የኢትዮጵያ ወታደሮች ወደ ግዛቴ ጥሰው ገብተዋል ስትል ለፀጥታው ምክር ቤት ከሰሰች

የፎቶው ባለመብት, un
ሶማሊያ የኢትዮጵያ ወታደሮች “በሕገወጥ መንገድ ድንበር ጥሰው” ወደ ግዛቴ ገብተዋል ስትል ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ከሰሰች።
ተመድ እና የአፍሪካ ኅብረት በሶማሊያ ፀጥታ ላይ ባላቸው ሚና ዙሪያ በመከረው የሰኞው ሰኔ 17/2016 ዓ.ም. ስብሰባ ላይ ነው በመንግሥታቱ ድርጅት የሶማሊያ አምባሳደር አቡባከር ኡስማን የኢትዮጵያ ወታደሮችን ድንበር ጥሰው በመግባት የከሰሱት።
ከአፍሪካ ኅብረት ተልዕኮ ውጪ የሆኑት የኢትዮጵያ ወታደሮች ድንበር ከተሻገሩ በኋላም ከሶማሊያ የፀጥታ ኃይሎች ጋር የተኩስ ልውውጥ አድርገዋል ብለዋል።
“የኢትዮጵያ ወታደሮች በሕገወጥ መልኩ ድንበር መጣስን ጨምሮ በሚፈጽሟቸው እርምጃዎች ምክንያት አገሪቷ መስከረም ወር ላይ ያቀደችውን ሽግግር ለማራዘም ተገዳለች” ብለዋል።
አምባሳደሩን በመጪው መስከረም ሊደረግ ስለታሰበው እና በዚህ ምክንያት ተራዝሟል ስላሉት ሽግግር ተጨማሪ መረጃ አልሰጡም።
“እነዚህ የማተራመስ እርምጃዎች በሶማሊያ እንዲሁም በቀጠናው ላይ ሊኖራቸው የሚችለውን አንድምታ ምክር ቤቱ እንዲያስብበት የሶማሊያ መንግሥት ያሳስባል” ሲሉም አምባሳደሩ ለምክር ቤቱ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ መከላከያም ሆነ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በጉዳዩ ላይ አስካሁን ምንም አስተያየት አልሰጡም።
ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ከኢትዮጵያ ጋር ከሚዋሰኑ የሶማሊያ ግዛቶች መካከል አንዷ የሆነችው የሂራን ግዛት ከተማ ማታባ ነዋሪዎች በከፍተኛ ሁኔታ የታጠቁ በሺዎች የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ሠራዊት አባላትን መመልከታቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የማታባን ከተማ አስተዳዳሪ ወታደሮቹ የአል-ሸባብ ታጣቂዎችን እየተከተሉ ከመንግሥት ፍቃድ ውጪ የሶማሊያን ድንበር ማቋረጣቸውን ከገለጹ በኋላ የሠራዊቱ አባላት ወደመጡበት መመለሳቸውን ለቢቢሲ ሶማልኛ ተናግረዋል።
በደቡባዊ ሶማሊያ የምትገኘው ሂራን ግዛት አስተዳዳሪ በሽር አብዲራሃማን ሼኬዬ ለቢቢሲ ሶማልኛ ወደ ሶማሊያ ግዛት ገብተው የነበሩት ወታደሮች ቁጥር ወደ 3ሺህ እንደሚጠጋ ገልጸዋል።
አንዳንዶች በቁጥር ከ3 ሺህ እስከ 4 ሺህ የሚያደርሷቸው የኢትዮጵያ ሠራዊት አባላት ከኢትዮጵያዋ ፈርፈር ከተባለች የድንበር ከተማ ተነስተው ሶማሊያ የገቡት አርብ ሰኔ 14/2016 ዓ.ም. መሆኑ ተነግሯል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኢትዮጵያ ወታደሮች ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ የአልሻባብን ስጋት ለመከታተል ድንበር አቋርጠው ወደ ሂራን ክልል ከገቡ በኋላ በማግስቱ መውጣታቸውን ሮይተርስ የአካባቢውን ሽማግሌዎች አናግሮ ዘግቧል።
ኢትዮጵያ የሶማሊያ የሽግግር መንግሥት ወታደሮቿን እንድታስገባ ከጠየቀበት ጊዜ ጀምሮ ለአስራ ሰባት ዓመታት ያህል በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ስር በሚገኘው የሰላም አስከባሪ ልዑክ አሰማርታ ትገኛለች።
የአፍሪካ ኅብረት የሰላም አስከባሪ ልዑክ (አሚሶም) በአውሮፓውያኑ 2022 በአፍሪካ ኅብረት የሽግግር ተልዕኮ (አትሚስ) ሲተካም ከብሩንዲ፣ ከኬንያ እና ከኡጋንዳ ጋር በመሆን ወታደሮቿ በሰላም ማስከበሩ ተግባር ቀጥለዋል።
ባለፈው ዓመት የኢትዮጵያ ወታደሮችን ጨምሮ በሶማሊያ ተሰማርተው ከሚገኙት 18 ሺህ 500 ያህሉ 5 ሺዎቹ ከአገሪቱ እንዲወጡ ተደርገዋል።
በሚቀጥሉት ሳምንታትም በርካታ ወታደሮች የሚቀነሱ ሲሆን የአፍሪካ ኅብረት የሽግግር የሰላም ተልዕኮ በመጪው ዓመት ጥር ተልዕኮውን አጠናቆ የፀጥታውን ሁኔታም የሶማሊያ መንግሥት እንዲረከብ ይደረጋል።
ሆኖም የፀጥታ ክፍተቶች እንዳይፈጠሩ ከአስር ሺህ የማይበልጡ ወታደሮች ያሉበት የሰላም አስከባሪዎች ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ባለበት እንደሚሰማራ ተጠቅሷል።
ራሷን በነጻ አገርነት ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር በተፈረመ የባሕር በር መግባቢያ አወዛጋቢ ስምምነት ምክንያት የአፍሪካ ኅብረት የሰላም ተልዕኮ ከመጠናቀቁ በፊት ሶማሊያ በሺዎች የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ወታደሮችን እንዲወጡ እንደምትፈልግ አስታውቃለች።
ኢትዮጵያ በአትሚስ ስር 3 ሺህ ያህል ወታደሮችን እንዲሁም ከሶማሊያ ጋር ባላት የሁለትዮሽ ስምምነት እስከ 7 ሺህ የሚሆኑ ወታደሮችን አሰማርታለች።
ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር ያላትን ስምምነት አዲሱ ተልዕኮ ከሚወሰንበት፣ ከሰኔ መጨረሻ በፊት ካልሰረዘች በአትሚስ ስር እንዲሁም በሁለትዮሽ ስምምነት የሰፈሩት ሁሉም የኢትዮጵያ ሠራዊት አባላት ከአገሪቱ እንደሚወጡ እንደሚደረግ የአገሪቱ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ሑሴን አሊ አስጠንቅቀዋል።
በቅርቡ የኢትዮጵያ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ለብሔራዊ ቴሌቪዥን ሲናገሩ ከግማሽ በላይ የሚሆነው የሶማሊያ ግዛት በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሚጠበቅ መሆኑን ተናግረዋል።
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ “የሶማሊያ መንግሥት ሞቃዲሾ እንዲቀመጥ ያደረገው የኢትዮጵያ መካለከያ ሠራዊት ነው” በማለት “የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ነገ ቢወጣ የሶማሊያ ፌደራል መንግሥት ሞቃዲሾ የሚቀመጥ አይመስለኝም” ብለዋል።
የተባበሩት መንግሥታት የሶማሊያ ተልዕኮ ሥልጣኑን በሶማሊያ ላለው ቡድን እንዲያሸጋግር እንዲሁም ከአፍሪካ ኅብረት ተልዕኮ በኋላ ምን ሊሆን ይችላል በሚል ርዕስ ላይ በመከረበት በዚህ ጉባኤ ከኢትዮጵያ ጋር ያለው ውጥረትም ተነስቷል።
ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቻርተር እንድታከብር ጥሪ ያቀረቡት አምባሳደር አቡባካር “የጥፋት ስምምነት” ብለው የጠሩትን ከሶማሊላንድ ጋር የተደረገውን የመግባቢያ ስምምነት በአስቸኳይ እንደገና በማጤን ጉርብትናዋን ታሳይ በማለት መልዕክት አስተላልፈዋል።
የአሜሪካ የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ተወካይም በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል ያለው የፖለቲካ ውጥረት ሊያመጣ የሚችለው “አሉታዊ ተጽዕኖ” እንዳሳሰባቸው ገልጸው ሁኔታውን ለማርገብ ዲፕሎማሲያዊ ውይይት እንዲደረግ አሳስበዋል።
ያሉት ቀጣናዊ ውጥረቶች የአፍሪካ ኅብረት የሰላም አስከባሪ የሽግግር ኃይል ከወጣ በኋላ ያለውን ተልዕኮ በማቀድ እና በማሰማራት ረገድ ጣልቃ እንዲፈጠርበት እንዲሁም የደኅንንት ክፍተቶችም ሊፈጠር አይገባም ብለዋል።
በሶማሊያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተልዕኮ (ዩኤንኤስኦኤም) ኃላፊ ጄምስ ስዋን ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ የተፈራረሙት የባሕር በር የመግባቢያ ስምምነት የአፍሪካ ቀንድ ቀጣናን ውጥረት ውስጥ ከትቶታል ብለዋል።
የሶማሊያን ሉዓላዊነት፣ የግዛት አንድነት ማክበር እንደሚያስፈልግ አጽንኦት በሰጡበት በዚህ ንግግር ሁለቱ አገራት ይህንን ጉዳይ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱት አበረታተዋል።
ኢትዮጵያ የባሕር ኃይል ሰፈር በኪራይ የምታገኝበት እና በምትኩም ለሶማሊላንድ ዕውቅና የምትሰጥበት ስምምነት በሁለት ወራት ገደማ እንደሚፈረም የሶማሊላንድ የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ኢሳ ካይድ ለቢቢሲ ሶማሊኛ ከሳምንታት በፊት መናገራቸው ይታወሳል።
ሚኒስትሩ በተጨማሪም ከዶቼቬለ አማርኛ ጋር ባደረጉት ቆይታ ኢትዮጵያ ለባሕር ኃይል የጦር ሠፈር ልትከራይ የምትችላቸው ሦስት አማራጭ ቦታዎች ተለይተዋል ብለው ነበር።
ኢትዮጵያ ራሷን እንደ ነጻ አገር ካወጀችው እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ካላገኘችው ሶማሊላንድ ጋር 20 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የባሕር ጠረፍ ለማግኘት የፈረመችው የመግባቢያ ሰነድ ሶማሊያን በእጅጉ አስቆጥቶ በቀጠናው ከፍተኛ ውጥረትን ያስከተለ ሆኗል።
ከሶማሊያ በኩል ተደጋጋሚ ክሶች እና መግለጫዎች ከመቅረባቸው በተጨማሪም ጉዳዩን ወደ መንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ወስዳዋለች።












