ኢትዮጵያ በተመድ የሶማሊያ ተወካይ በፀጥታው ምክር ቤት ያደረጉት ንግግር እንዳሳዘናት አስታወቀች

የፎቶው ባለመብት, UN
ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር ያደረገችው የባሕር በር የመግባቢያ ስምምነትን ጦርነት ከማወጅ ጋር የሚስተካከል ነው በማለት ያነጻጸሩት በተባበሩት መንግሥታት የሶማሊያ ተወካይ ንግግር እጅጉን እንዳሳዘናት አስታወቀች።
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ ሰኞ የካቲት 11/2016 ዓ.ም. ሶማሊያን በተመለከተ በፀጥታው ምክር ቤት በተካሄደው ስብሰባ ላይ የሶማሊያው ተወካይ የሰጡት ማብራሪያ ከማሳዘን በተጨማሪ በሐሰት የተሞላ መሆኑን ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
አምባሳደር አቡካር ኡስማን የባሕር በር የመግባቢያ ስምምነቱ ኢትዮጵያ ወታደራዊ ሰፈር ለማቋቋም ስትል የሶማሊያን ግዛት የመጠቅለል ዕቅድ አላት ሲሉ ክሳቸውን ለፀጥታው ምክር ቤት አቅርበው ነበር።
የተመድ የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕከተኛ በበኩሉ የአምባሳደሩን ንግግር በሶማሊያ መንግሥት ባለሥልጣናት በኩል እየቀረበ ያለው ምክንያታዊነት የሌለው የማያባራ ውንጀላ አካል ነው ሲልም ወቅሷል።
ሆኖም በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ ሕዝቦች መካከል ያለውን የወንድማማችነት ትስስር በማክበር የሶማሊያ ተወካይ የተከተሉትን መንገድ እንደማይከተልም መግለጫው የአገሪቱን አቋም አንስቶ አጽንኦት ሰጥቷል።
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ትብብር፣ ወንድማማችነት እና የጋራ ተጠቃሚነት በቀጠናው እንዲሰፍን የሚያልም እንደሆነ አስፍሯል።
ኢትዮጵያ ሌሎች አገራት እውቅና ካልሰጧት ሶማሊላንድ ጋር የፈረመችው የመግባቢያ ስምምነት ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ ወይም ከዓለም አቀፍ አሰራር ጋር የሚቃረን እንዳልሆነም በመንግሥታቱ ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አስረድቷል።
ሌሎች አገራት በሊዝ የባሕር በር መዳረሻን ለማግኘት ከተፈራረሙት ጋር ተመሳሳይ ነው ሲልም አውስቷል።
የመግባቢያ ስምምነቱ ኢትዮጵያ የባሕር በር መዳረሻ እንዲኖራት በማድረግ ሁሉን ተጠቃሚ የሚያደርግ አጋርነት ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚገባው ያስታወሰው መልዕክተኛው “ኢትዮጵያ የማንንም ጥቅም የመጉዳት ሃሳብ የላትም” ብሏል።
በተባበሩት መንግሥታት የሶማሊያ አምባሳደር አቡካር ኦስማን ግን ለፀጥታው ምክር ቤት እንደተናገሩት የኢትዮጵያ ድርጊት ጽንፈኛው አልሻባብ እንዲያንሰራራ እና በአፍሪካ ቀንድ የጎሳ ተገንጣይ ቡድኖችን ሊያበረታታ እንደሚችል ተናግረው ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አገራቸው ከሶማሊያ ጋር ጦርነት ውስጥ የመግባት ፍላጎት እንደሌላት የመንግሥታቸውን አቋም ከዚህ ቀደም ማስታወቃቸው ይታወሳል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት ከሶማሊላንድ ፕሬዚዳንት ሙሴ ቤሂ ጋር ከሁለት ወር ገደማ በፊት የተፈራረሙት የባሕር በር የመግባቢያ ስምምነት ላይ የሚነሱ ጥያቄዎችን በተመለከተ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግሥታቸው ለሶማሊያ ሰላም እና አንድነት በመሥራት የሚወዳደረው አካልም እንደሌለም በዚሁ ወቅት ጠቅሰዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩን መልዕክት ያስተጋባው የቋሚ መልዕክተኛው መግለጫ “ኢትዮጵያ ለሶማሊያ ሰላም እና ደኅንነት ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍላለች” ብሏል።
ሶማሊያ በአሁኑ ወቅት ላለችበትም አንጻራዊ የሰላም መሻሻል ኢትዮጵያ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎቿን እንደገበረችም አስታውሷል።
ኢትዮጵያ በሶማሊያ ውስጥ ሊፈጠሩ የሚችሉ ማንኛውንም የፀጥታ ክፍተቶች ለመሙላትም መሬት ላይ ኃይሏን አሰማርታ አልሻባብን ስትፋለም መቆየቷንም ጠቅሶ ኢትዮጵያ አሁንም ከሶማሊያ ጋር ለመነጋገገር ዝግጁ መሆኑንም ገልጿል።
ኢትዮጵያ ራሷን እንደ ነጻ አገር ካወጀችው እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ካላገኘችው ሶማሊላንድ ጋር 20 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የባሕር ጠረፍ ለማግኘት የፈረመችው የመግባቢያ ሰነድ ሶማሊያን በእጅጉ አስቆጥቶ በቀጠናው ከፍተኛ ውጥረትን ያስከተለ ሆኗል።
ሁለቱ አገራት የገቡበት ውጥረትም የሶማሊያው ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼኽ መሐመድ የአፍሪካ ኅብረት መሪዎች ጉባኤ ላይ እንዳልሳተፍ በኢትዮጵያ የፀጥታ ኃይሎች ተከልክያለሁ ማለታቸውን ተከትሎም ነገሮች ተካረዋል።
ኢትዮጵያ በበኩሏ ክሱን ውድቅ ያደረገች ሲሆን፣ የሶማሊያ ልዑካን በመንግሥት የተመደቡላቸውን የፀጥታ ሠራተኞችን አንቀበልም በማለት ጠባቂዎቻቸው የጦር መሳሪያ ታጥቀው ጉባኤው ወደሚካሄድበት ስፍራ ለመግባት ሲሞክሩ በኅብረቱ የፀጥታ አካላት ተከልክለዋል ብላለች።
ከሶማሊያ በኩል ተደጋጋሚ ክሶች እና መግለጫዎች ከመቅረባቸው በተጨማሪም ጉዳዩን ወደ ተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ወስዳዋለች።
ኢትዮጵያም ጉዳዩ በአፍሪካ ኅብረት ማዕቀፍ የታየ በመሆኑ ምክር ቤቱ ሊመክርበት አይገባም በሚል ተቃውማ ነበር።
የመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ሁለት ጊዜ ባደረገው ስብሰባ በሁለቱ አገራት ውጥረት ዙሪያ ተወያይቶበታል።
ምክር ቤቱ ሶማሊያን አጀንዳ ካደረገበት ከሰኞው ስብሰባው በተጨማሪ ጥር 20/ 2016 ዓ.ም. “ሰላም እና ፀጥታ በአፍሪካ” በሚል ርዕስ የሁለቱን አገራት ውዝግብ በዝግ ሰብሰባ መክሮበታል።
በዚህም ስብሰባ ላይ የምክር ቤቱ አባላት የሶማሊያን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ማክበር እንደሚያስፈልግ ገልጸው፤ የአፍሪካ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ የሆኑትን ኦሉሴጎን ኦቦሳንጆን ልዑክ በማድረግ ሁለቱን አገራት ለማሸማገል የጀመረውን ጥረት ይደግፋል ብለዋል።












