በአማራ ክልል ሥር የነበሩት የጠለምት አስተዳደሮች መፍረሳቸው ተገለጸ

ምዕራብ ጠለምት እና ማይጠብሪ አካባቢዎች በአማራ ክልል ስር መሆናቸውን የሚያሳይ "የእንኳን ደህና መጣችሁ" ባነር

የፎቶው ባለመብት, North Gonder Comm.

በአማራ ክልል መስተዳደር ሥር የተቋቋሙት ሦስት የጠለምት እና ማይጸብሪ አካባቢ አስተዳደሮች ፈርሰው፤ ቢሮዎቻቸው መታሸጋቸውን የአካባቢው ምንጮች ለቢቢሲ ተናገሩ። በጦርነት ምክንያት ከአካባቢዎቹ ተፈናቅለው የነበሩ ነዋሪዎችም ወደ ቀያቸው እየተመለሱ መሆኑ ተገልጿል።

የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት መነሳትን ተከትሎ በአማራ ክልል ሥር ሲተዳደሩ ከቆዩ አካባቢዎች ውስጥ የጸለምቲ (በአማራ ክልል ስር ጠለምት በሚል የሚጠሩት) ሁለት ወረዳዎች እና አንድ የከተማ አስተዳደር ተጠቃሽ ናቸው።

ምሥራቅ እና ምዕራብ ጠለምት ወረዳ እንዲሁም የማይጸብሪ ከተማ አስተዳደር የሚል አስተዳደራዊ መጠሪያ የተሰጣቸው እነዚህ አካባቢዎች በአማራ ክልል ውስጥ የነበሩት ለሰሜን ጎንደር ዞን ተጠሪ ሆነው ነው።

ላለፉት ዓመታት የቆው የሦስቱ መዋቅሮች አስተዳደር የፈረሰው ካለፈው ሳምንት አርብ ሰኔ 21/2016 ዓ.ም. አንስቶ እንደሆነ የሰሜን ጎንደር ዞን እና የአካባቢው አስተዳደሮች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በአማራ ክልል የተሾሙ አንድ የአካባቢው ባለሥልጣን፣ ሦስቱ የጠለምት አካባቢዎች አስተዳደር የነበራቸው “መንግሥታዊ መዋቅር” አገልግሎት መስጠት እንዲያቆም የተደረገው “ከፌደራል እና ከአማራ ክልል” ከተወከሉ የመንግሥት እና የብልጽግና ፓርቲ ኃላፊዎች ጋር ስብሰባ ከተደረገ በኋላ እንደሆነ ገልጸዋል።

አርብ ዕለት በነበረው በዚህ ስብሰባ ላይ አካባቢውን ሲመሩ የነበሩት በአማራ ክልል የተሾሙ አመራሮች “ሥራ እንዲያቆሙ ትዕዛዝ እንደተሰጣቸው” አስረድተዋል። ከዚሁ ዕለት አንስቶም የአስተዳደሮቹ ቢሮዎች መታሸጋቸውን ምንጩ ተናግረዋል።

ይህንኑ የሚያረጋግጥ ሪፖርት እንደደረሳቸው የሚገልጹ አንድ የሰሜን ጎንደር ዞን አስተዳደር ምንጭ በበኩላቸው፤ “[የአካባቢዎቹ መዋቅሮች] እስከ አርብ ሥራ ላይ ነበሩ። ከአርብ በኋላ መከላከያ ቢሮዎችን የማሸግ ሥራ ሰርቷል” ብለዋል።

ከመዋቅሮቹ መፍረስ በተጨማሪ፤ በአካባቢዎቹ ላይ ሲንቀሳቀሱ የነበሩት “ፖሊስ፣ ሚኒሻ እና ሰላማ አስከባሪ ኃይል” ከቅዳሜ ዕለት አንስቶ አጎራባች ወደ ሆነው የሰሜን ጎንደር ዞን አዲ አርቃይ ወረዳ “እንዲወጡ” መደረጉን የአካባቢው አስተዳደር ምንጭ ገልጸዋል።

ይህ ከተከናወነበት ቅዳሜ ዕለት አንስቶም በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ምክንያት ከአካባቢው የተፈናቀሉ ነዋሪዎች መመለስ እንደጀመሩ ሁለቱ ምንጮች ገልጸዋል።

ተፈናቃዮችን የሚመልሱ ተሽከርካሪዎች
የምስሉ መግለጫ, በጦርነቱ ምክንያት የተፈናቀሉትን ነዋሪዎች የመመለስ ሥራ ከቀናት በፊት ተጀምሯል
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በዕለቱ ወደ አካባቢው የተመለሱ አንድ ተፈናቃይ ማይጸብሪ ከተማ ሲደርሱ “የታጠቁ [ሰዎች] ከነጦር መሳሪያዎቻቸው ሲንቀሳቀሱ” እንደተመለከቱ ለቢቢሲ ተናግረዋል። የመንግሥት ቢሮዎች ግን ዝግ መሆናቸውን የገለጹት ተመላሹ፤ ወደ ከተማው ያደረሳቸው ተሽከርካሪ ተሳፋሪዎቹን ያወረደው “በትምህርት ቤት ውስጥ” መሆኑንም አስረድተዋል።

የአካበቢው አስተዳደር እና የሰሜን ጎንደር ዞን ምንጮች በበኩላቸው ተመላሾች ወደ ቅያቸው ከደረሱ በኋላ ወደ “ቀድሞ መኖሪያ ቤቶቻቸው” እየተመለሱ መሆኑን ተናግረዋል።

ተመላሾች ወደ የቤታቸው የመመለሳቸውን ጉዳይ ክትትል የሚያደርጉት በማይጸብሪ ከተማ የሚገኙ ከአማራ ክልል መንግሥት እና ትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የተወጣጡ ታዛቢዎች እንደሆኑ የጠለምት አካባቢዎች አስተዳደር ምንጭ ገልጸዋል።

ተወካዮቹ የታዛቢነት ሚናቸውን የሚወጡት “የአካባቢው አስተዳደሮች ፈርሰዋል? የታጠቁ ኃይሎች ወጥተዋል? ተፈናቃዮች በምን ዓይነት ሁኔታ እየገቡ ነው?” በሚሉት ጉዳዮች ላይ እንደሆነም ገልጸዋል።

ከሁለቱ ክልሎች የተወጣጡ ተወካዮች ተፈናቃዮች ጉዞ ከሚጀምሩበት እንዳባጉና ከተባለ የትግራይ ክልል አካባቢ ጀምሮ በታዛቢነት እንደተሰማሩ የሰሜን ጎንደር ዞን ምንጭ ጠቅሰዋል። ጨምረውም ተፈናቃዮች በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር አማካኝነት እንዳባጉና ከደረሰቡ በኋላ ያለውን ሂደት የሚመራው የመከላከያ ሠራዊት መሆኑን አስረድተዋል።

የመከላከያ ሠራዊት ይህንን ሥራ የሚያከናውነው ተፈናቃዎቹ ከሚመለሱባቸው አካባቢዎች ተመርጠው ወደ እንዳባጉና በተወሰዱ ነዋሪዎች እገዛ እንደሆነም ተናግረዋል።

ነዋሪዎቹ የተመረጡት “ቀበሌዎቹን በደንብ ያውቃሉ” በሚል መነሻነት እንደሆነ የሚገልጹት ምንጩ፤ ተፈናቃዎቹ “በእርግጥም የአካባቢው ነዋሪ መሆናቸውን የማረጋገጥ” ሚና እንዳላቸው አስረድተዋል።

ለዚህ ሚና የተለዩ ሰዎች ከአካባቢዎቹ ተመርጠው ወደ እንዳባጉና መሄዳቸውን የጠለምት አካባቢዎች አስተዳደር ምንጭ አረጋግጠዋል። ይሁንና ምንጩ የተመረጡት ነዋሪዎች “በተባለው ልክ እየሠሩ አይደለም” ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል።

እንዳባጉና ላይ የሚናወነውን “የተፈናቃዎችን ነዋሪነት የማረጋገጥ” ሥራን የሚታዘቡት ከአማራ እና ከትግራይ ክልሎች የተወጣጡ አመራሮች እንደሆኑ ሁለቱ ምንጮች ተናግረዋል።

ከአማራ ክልል በኩል ከተወከሉት አመራሮች መካከል እንደሆኑ የተጠቀሱት ሰሜን ጎንደር ዞን አስተዳዳሪ ዲያቆን ሸጋው ውቤ፤ የተፈናቃዎች መመለስን በመለከተ ከቢቢሲ ለቀረበላቸው ጥያቄ “ሥራ ላይ ነን። አሁን ማውራት አንችልም” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

የትግራይ ክልል የማኅበራዊ ጉዳይ እና መልሶ ማቋቋም ቢሮ ኃላፊ ሜጀር ጄኔራል ዘውዱ ኪሮስም በተመሳሳይ ስለ ተፈናቃዎች የመመለስ ሂደት መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

ሜጀር ጄኔራል ዘውዱ ለቀረበላቸው ጥያቄ መልስ ሲሰጡ፤ “የመጀመሪያውን ዙር ከጨረስን በኋላ ብንሰጥ ይሻላል” ብለዋል።

ለረጅም ጊዜ በአማራ እና በትግራይ ክልሎች መካከል በይገባኛል ሲያወዛግቡ ከቆዩት አካባቢዎች የጦርነቱን መቀስቀስ ተከትሎ የተፈናቀሉ ሰዎችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ በፌደራል መንግሥቱ እና በሁለቱ ክልሎች አማካይነት የተለያዩ ተግባራት ሲከናወኑ የቆዩ ሲሆን፣ አሁን እየተካሄደ ያለው የመጀመሪያው እርምጃ እንደሆነ ይነገራል።