አማራ እና ትግራይ ክልሎች በሚወዛገቡባቸው የጠለምት አካባቢዎች ሰሞኑን የተፈጠረው ምንድን ነው?

የፎቶው ባለመብት, TELEMT WEREDE/FB
አማራ እና ትግራይ ክልሎች በይገባኛል በሚወዛገቡባቸው የጠለምት/ጸለምት አካባቢዎች ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ውጥረት መንገሡን ነዋሪዎች እና የአካባቢዎቹ አስተዳደሮች ተናገሩ።
ከግንቦት 26/2016 ዓ.ም. ጀምሮ ‘የትግራይ ኃይሎች’ ወደ ጠለምት/ጸለምት ወረዳዎች ለመግባት እንቅስቃሴ ማድረጋቸውን ነዋሪዎች እና አስተዳዳሪዎች ለቢቢሲ ገልጸዋል።
የምሥራቅ ጠለምት ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ሞላልኝ በበኩላቸው መከላከያን ጨምሮ የፀጥታ ኃይሎች “ባደረጉት ጥረት” የትግራይ ኃይሎች አካባቢውን ለቅቀው እንዲወጡ ሆኗል ብለዋል።
“መከላከያ [እንቅስቃሴው] ትክክል እንዳልሆነ፤ መመለስ እንዳለበት ለመሪዎች [በማሳወቅ] እንዲመለስ ጥረት አድርጓል። የእኛም ሰላም አስከባሪ [የአካባቢው የፀጥታ ኃይል] ነበረን። እንዳንጋጭ፤ እነሱ ወደ መጡበት እንዲመለሱ አድርጓል” ሲሉ ግጭት እንዳልተፈጠረ ተናግረዋል።
አስተዳዳሪው የትግራይ ኃይሎች ሰሞነኛ እንቅስቃሴ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር በአወዛጋቢው አካባቢዎች በአማራ ክልል የተዘረጉ አስተዳደሮችን ለማፍረስ እና ተፈናቃዮችን ለመመለስ የያዘውን ዕቅድ ለመፈጸም ነውም ብለዋል።
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑት ጄኔራል ታደሰ ወረደ በሚያዝያ ወር መጨረሻ በሰጡት መግለጫ እስከ ግንቦት 30/2016 ዓ.ም. ድረስ የወረዳዎቹ አስተዳደሮች እንደሚፈርሱ እና ተፈናቃዮች እንደሚመለሱ ገልጸው ነበር።
ቢቢሲ ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዝዳንት እና ከሰላም ፀጥታ ቢሮ ጉዳዩን በተመለከተ ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ተደጋጋሚ ጥረት ስልኮቻቸው ስለማይነሱ አልተሳኩም።
“ውዥንብር ተፈጥሮ ነበር”
የሰሜኑ ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን አስተዳደር ውስጥ የተጠቃለሉት የጠለምት ወረዳዎች በትግራይ ክልል ‘ምዕራብ ትግራይ’ ተብለው ከሚጠሩ አካባቢዎች መካከል ነበሩ።
ሁለት ወረዳዎች እና አንድ የከተማ አስተዳደር ያለው ጠለምት፣ በአካባቢው በተለይም ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በተከዜ ወንዝ ተፋሰስ አካባቢ ወደሚገኙ የተለያዩ ቀበሌዎች “ለመግባት” የትግራይ ኃይሎች እንቅስቃሴ አድርገዋል ተብሏል።
እንቅስቃሴውን ተከትሎ 200 ሺህ የሚሆኑ ሰዎች ይኖሩበታል ተብሎ በሚገመተው የጠለምት አካባቢ ዳግም ግጭት ሊቀሰቀስ ይችላል የሚል ስጋት ተደቅኖበታል።
አንድ የማይጸብሪ ከተማ ነዋሪ ሰሬንታ መዳብር፣ ዲማና ፍየል ውሃ በተባሉ አካባቢዎች ከግንቦት 28 ጀምሮ የትግራይ ኃይሎች “ሠራዊት ጭነው መጥተው ነበር” ሲሉ እማኝነታቸውን ገልጸው፤ አካባቢዎቹን ለመቆጣጠር እንቅስቃሴ እንደነበር ተናግረዋል።
“ተኩስ አልነበረም። ነገር ግን የእነርሱ [የትግራይ ኃይሎች] በአካባቢው የመታየታቸው መረጃ በከተማ ውስጥ ውዥንብር ፈጥሮ ነበር” በማለት ገበያ እስከመበተን የደረሰ ፍርሃት ተፈጥሮ እንደነበር ጠቁመዋል።
አቶ አብርሃ የተባሉ የምዕራብ ጠለምት ወረዳ ነዋሪም ማኅበረሰቡ መደበኛ ሕይወቱን እንዳይመራ “የትግራይ ኃይሎች ወደ አካባቢው ወጣ ገባ እያሉ ትንኮሳ እየፈጸሙ ነው" ብለዋል።
የምዕራብ ጠለምት ወረዳ የፀጥታ እና ደኅንነት ኃላፊ አቶ አለቤ አለሙ “ከዳር እስከ ዳር በየአቅጣጫው ተዘጋጅተው ነበር” ሲሉ የትግራይ ኃይሎችን እንቅስቃሴ ገልጸው፤ እንቅስቃሴው “በተከዜ ወንዝ ዳር ዳር ነው” ብለዋል።
“. . . መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴ ጀምረው ነበር። ታጣቂዎችን ተልዕኮ ሰጥተው አስርገው በማስገባት የአካባቢ አመራር የተገደሉ አሉ። እንደዚህ ዓይነት ሥራ እየሰሩ ነው የሰነበቱት” ብለዋል።
የትግራይ ኃይሎች ማኅበረ፣ ዋልድባ፣ ጭሬ የሚባሉ አካባቢዎች ላይ ገብተው ነበር ያሉት ኃላፊው፤ ከትግራይ የተላኩ ናቸው ያሏቸው ‘ሰርጎ ገቦች’ አቶ ጌታቸው የተባሉ የምዕራብ ጠለምት ወረዳ አመራርን ገድለዋል ሲሉም ከሰዋል።
የግጭት መቀስቀስ ስጋት
በምሥራቅ ጠለምት ወረዳ ደግሞ “በርካታ ኃይል አሰልፈዋል” የተባሉት የትግራይ ኃይሎች ከግንቦት 30 ጀምሮ “በሦስት አቅጣጫ” ለመግባት እንቅስቃሴ ማድረጋቸውን አስተዳዳሪው አቶ ሞላልኝ በላይነህ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ድል አንባ፣ ጨር እና ጥርሰጌ በሚባሉ ቦታዎች ላይ “ገብተው ነበር” ያሉት አስተዳዳሪው፤ በነዋሪዎች ላይ ድብደባን ጨምሮ ከመኖሪያቸው እንዲሸሹ አድርገዋል ብለዋል።
በጠለምት አካባቢ ከሳምንት በላይ ዘልቋል የተባለው የታጣቂዎች እንቅስቃሴ በሰሜኑ ጦርነት ጉዳት በደረሰበት አካባቢ ግጭት ዳግም ሊቀሰቀስ ይችላል የሚል ስጋትን አሳድሯል።
“ሕዝቡ እንዲፈራ፣ ድንጋጤ እንዲያድርበት እና ከመኖሪያ አካባቢው እንዲሸሽ ጫና እየተደረገበት ነው” ያሉት አቶ አብርሃ፤ መረጃዎች በስፋት መሰራጨታቸውን ጠቅሰው በሁኔታው ነዋሪው ተሸብሯል ሲሉ ሁኔታውን ገልጸውታል።
ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንድ ነዋሪው በማኅበረሰቡ ዘንድ ግጭት ዳግም ሊቀሰቀስ ይችላል የሚል ስጋት ማደሩን ጠቁመው፤ ራያ አካባቢ የነበረውን ሁኔታ ለአብነት አንስተዋል።
አቶ ሙለይ የተባሉ ሌላ ነዋሪም በተከዜ ወንዝ አካባቢ የትግራይ ኃይሎች እንቅስቃሴ እንደነበር ጠቅሰው፤ ማኅበረሰቡ “ጦርነት መልሶ እንዳይቀሰቀስ፤ [አካባቢው] የውጊያ ቦታ እንዳይሆን” ስጋት እንደፈጠረ ተናግረዋል።
ባለፉት ቀናት በአዋሳኝ አካባቢዎች በነበረው እንቅስቃሴ የተኩስ ልውውጦች እንዳልነበሩ የተናገሩት አቶ አብርሃ፣ ነገር ግን “ጦርነት ይከፈታል በሚል” በማኅበረሰቡ ውስጥ ፍርሃት መንገሡን አመልክተዋል።
“ጦርነት ሕይወት ያጠፋል፤ ንብረት ይወድማል። ኑሮን እንዳንኖር ስለሚያደርግ [ማኅበረሰቡ ስጋቱ] እኛ ይበቃናል [የሚል ነው]። . . . በ2013/2014 ላይ ገንዘባችንን፤ ንብረታችንን ጨርሰናል፤ ልጆቻንን ጭምር ነው ያጣነው፤ ይሄ ነገር [ግጭት] እንዲመጣብን አንፈልግም” ብለዋል።
“ወጣ ገባ” በማለት በአካባቢው እየተንቀሳቀሱ ነው የተባሉትን የትግራይ ኃይሎችን በተመለከተ በክልሉ መንግሥት በኩል መረጃ ያለ መሆኑን የሰሜን ጎንደር አስተዳዳሪ ዲያቆን ሸጋው ውቤ ተናግረዋል።
ከግንቦት ወር መጨረሻ ቀናት ጀምሯል የተባለው እንቅስቃሴ እስከ ሰኔ 4/2016 ዓ.ም ድረስ መዝለቁን ነዋሪዎች እና አስተዳዳሪዎች ተናግረዋል።
መቋጫ ያላገኘው ጉዳይ
የጠለምት አካባቢ አሁን ላይ “በተጠንቀቅ ላይ ነው” ያሉት የሰሜን ጎንደር ዞን አስተዳዳሪ፤ እንቅስቃሴውንም “ወረራ” ሲሉ ባለፈው ሳምንት በአድርቃይ ወረዳ የተፈጸመን ጥቃት በአስረጂነት አንስተዋል።
“. . . እስካሁን ባለንበት ነባራዊ ሁኔታ ይፋዊ ግጭት አልተፈጠረም። ነገር ግን በሌላኛው በኩል ግጭቱን አይቀሬ የሚያደርጉ እንቅስቃሴዎች አሉ” ሲሉ ከፍተኛ ውጥረት እንዳለ ተናግረዋል።
የዞኑ አስተዳዳሪ የትግራይ ኃይሎች ዲማ ማኅበረ፣ ማይገመሬ፣ ጨር ሚካኤል እና ጨጨሬ ታዲዮስ ገዳም የተባሉ አካባቢዎች ላይ “አሁንም አሉ” ያሉ ሲሆን፤ ከጠለምት አካባቢዎች ጠቅልለው አልወጡም ብለዋል።
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዝዳንት ጄኔራል ታደሰ ወረደ በሚያዝያ ወር መጨረሻ በሰጡት መግለጫ እስከ ግንቦት 30/2016 ዓ.ም. ድረስ የወረዳዎቹ አስተዳደሮች እንደሚፈርሱ እና ተፈናቃዮች እንደሚመለሱ ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ስምምነት መደረሱን መግለጻቸው ይታወሳል።
ይህንን በተመለከተ በቢቢሲ የተጠየቁት የሰሜን ጎንደር አስተዳዳሪ “እኛ የሌለንበት ስምምነት የለም” በማለት ምክትል ፕሬዝዳንቱ የጠቀሱትን ‘ስምምነት’ እንደማያውቁ እና “እኛ የምናውቀው የፕሪቶሪያውን ስምምነት ነው” በማለት መልሰዋል።
የአማራ ክልል እና የትግራይ ክልሎች በይገባናል የሚወዛገቡባቸው አካባቢዎች የትግራይ ጦርነት ከመቀስቀሱ በፊት በትግራይ ክልል ስር የነበሩ ሲሆን፣ በአማራ ክልል በኩል ያለ አግባብ ተካልለዋል በማለት ጥያቄ ሲቀርብ ቆይቷል።
የጦርነቱን መቀስቀስ ተከትሎ የአማራ ክልል ኃይሎች ጥያቄ የሚነሳባቸውን አካባቢዎች በመቆጣጠር ክልሉ እያስተዳደራቸው ቢገኝም፣ የትግራይ ክልል ግን አካባቢዎቹ ወደ አስተዳደሩ እንዲመለሱ በተደጋጋሚ እየጠየቀ ነው።
የሁለት ዓመቱ ደም አፋሳሽ ጦርነት ከተጠናቀቀ በኋላ የፌደራል መንግሥቱ፣ የአማራ እና የትግራይ ክልሎች ለአወዛጋቢዎቹ ቦታዎች ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት እየሠሩ መሆናቸውን እየገለጹ ቢሆንም፣ በሁሉም አካባቢዎች ዳግም ግጭት ሊቀሰቀስ ይችላል የሚል ስጋት ተፈጥሯል።
በአወዛጋቢዎቹ ወረዳዎች ባለፈው ሰሞን እየተየ ያለውን ውጥረት በተመለከተ የፌደራል መንግሥቱ፣ የአማራም ሆነ የትግራይ ክልሎች እስካሁን ያሉት ነገር የለም።












