የመንግሥት ኃይሎች በአማራ ክልል የጤና ተቋማት እና ባለሙያዎች ላይ ጥቃት ፈጽመዋል፡ሂዩማን ራይትስ ዋች

ታማሚ እና አስታማሚ

የፎቶው ባለመብት, Amhara Health Bureau

የኢትዮጵያ መንግሥት ኃይሎች በአማራ ክልል ከጦር ወንጀል ጋር የሚስተካከሉ መጠነ ሰፊ ጥቃቶችን በጤና ባለሙያዎች፣ በህሙማን እና በጤና ተቋማት ላይ ፈጽመዋል ሲል የመብት ተሟጋቹ ሂማን ራይትስ ዋች ከሰሰ።

አንድ ዓመት ሊሞላው በተቃረበው በአማራ ክልል በፌደራሉ መንግሥት ሠራዊት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል እየተካሄደ ባለው ግጭት፣ የመንግሥቱ ኃይሎች እና ተባባሪ ሚሊሻዎች በክልሉ የጤና ተቋማት ላይ ፈጽመዋቸዋል ያላቸውን ጥቃቶች በተመለከተ ሂዩማን ራይትስ ዋች ዝርዝር ሪፖርት አውጥቷል።

ሪፖርቱ በክልሉ ግጭቱ ከተቀሰቀሰበት ካለፈው ዓመት ማብቂያ አንስቶ የመንግሥት ኃይሎች ቢያንስ 13 በሚደርሱ ከተሞች በጤና ተቋማት እና በሠራተኞች እንዲሁም በትራንስፖርት አገልግሎቶች ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን የሚያመለክቱ መረጃዎችን ማሰባሰቡን አመልክቷል።

የሂማን ራይትስ ዋች የአፍሪካ ምክትል ዳይሬክተር ላቲሺያ ባድር “የኢትዮጵያ ፌደራል ኃይሎች ለሰላማዊ ሰዎች ሕይወት ግድ ሳይሰጣቸው ካለተጠያቂነት በጣም አስፈላጊ የሆነውን የጤና አገልግሎት በሚሰጡት ተቋማት ላይ ጥቃት ፈጽመዋል” ብለዋል።

ምክትል ዳይሬክተሯ ጨምረውም የኢትዮጵያ መንግሥት ጥቃት ፈጻሚዎቹን ለድርጊታቸው ተጠያቂ የማያደርግ ከሆነ ተመሳሳይ ድርጊቶች ሊቀጥሉ ይችላሉ የሚል ስጋት እንዳላቸው ገልጸዋል።

በአማራ ክልል ያለው ጦርነት በህክምና ግብዓት እጥረት እና በእንቅስቃሴ ገደብ ምክንያት ህሙማን ተገቢውን ህክምና እንዳያገኙ ከማገዱ ባለፈ፤የህክምና ባለሙያዎች በተለይም በመንግሥት ኃይሎች እንግልት፣ ወከባ እና ዛቻ እንደሚደርስባቸው ስማቸው እና የሚሠሩባቸው ተቋማት እንዳይገለጽ የጠየቁ ባለሙያዎች ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

የመንግሥት ኃይሎች የቡድን መሳሪያዎች የተጠመዱባቸውን ተሽከርካሪዎች የጤና ተቋማት ቅጥር ጊቢ ውስጥ ይዘው እንደሚገቡ እና ወታደሮችም እስከ ትጥቃቸው ወደ ታካሚዎች እና የቀዶ ጥገና (ኦፕሬሽን) ክፍል እንደሚገቡ ባለሙያዎች ለቢቢቢ ገልጸዋል።

ሂዩማን ራይትስ ዋች ካለፈው ዓመት ነሐሴ አስካለፈው ግንቦት ድረስ ከርቀት ካናገራቸው 58 የጥቃቱ ሰለባዎች፣ የዐይን እማኞች፣ የህክምና ባለሙያዎች እና የእርዳታ ሠራተኞች መረጃ መሰብሰቡን ጠቅሶ፣ ለሪፖርቱ የሳተላይት ምሥሎችን እንዲሁም የተረጋገጡ ቪዲዎችን እና ፎቶግራፎችን ተጠቅሟል።

የመንግሥት ኃይሎች የሚፈጽሟቸው በደሎች በክልሉ በሥራ ላይ ያሉ ሆስፒታሎችን እንቅስቃሴ “አደጋ ላይ ጥሏል ወይም አስተጓጉሏል” የሚለው የመብት ተከራካሪው፣ ይህ ሁኔታ የህክምና ተቋማቱን እና ባለሙያዎቹ በሚጠበቅባቸው ሁኔታ አገልግሎት እንዳይሰጡ እንቅፋት ሆኗል ብሏል።

“ወታደሮች የፋኖ አባላት ናቸው የተባሉ ሰዎችን ጨምሮ ለቆሰሉ እና ለታመሙ ሰዎች አገልግሎት የሚሰጡ የህክምና ባለሙያዎችን ይደበድባሉ፣ በዘፈቀደ ያስራሉ፣ ያስፈራራሉ። በተጨማሪም በአምቡላንሶች እና በሕክምና ተሽከርካሪዎች ላይ ጥቃት ይፈጽማሉ፣ በሰብአዊ እርዳታ መካከል ጣልቃ ይገባሉ። ይህም የአማራ ሕዝብን የጤና አገልግሎት እንዳያገኝ አድርጎታል” ብሏል።

ቢቢሲ ያናገራቸው ባለሙያዎችም በመሳሪያ ታጅቦ ህክምና ለመስጠት “ውስጣችን ይረበሻል” የሚሉት ባለሙያዎች፤ “የፋኖን ታጣቂዎችን ታክማላችሁ” በሚልም እንግልት እና ዛቻ እንደሚደርስባቸው ይናገራሉ።

ህክምናቸውን ሳይጨርሱ በመንግሥት ኃይሎች ተይዘው የሚወሰዱ ታካሚዎች እንዳሉ የሚናገሩት ባለሙያዎች፤ በሚደርስባቸው ጫና ምክንያት በሥራ ገበታቸው ላይ ወጣ ገባ እያሉ ለመሥራት መገደዳቸውን ይገልጻሉ።

ወታደሮች “በህክምና ሥራው ውስጥ ሲገቡ የባለሙያው ሥነ ልቦና ይጎዳል፣ እንዲሁም የታካሚዎችን ግላዊ መብት ሲነኩ ብዙ ጫና አለው” ያሉ በአንድ የዞን ከተማ የመንግሥት ሆስፒታል የሚያገለግሉ ባለሙያ፤ ጫናው ተዘርዝሮ የሚያልቅ አይደለም ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የሂዩማን ራይትስ ዋች ሪፖርት ከጠቀሳቻው ማሳያዎች ውስጥም ባለፈው ጥር የመንግሥት ኃይሎች አንድ የህክምና ባለሙያን ለበርካታ ቀናት በጦር ካምፕ ውስጥ አስረው ማቆየታቸውን ገልጿል።

ባለሙያው በሰጠው ቃልም “ምርመራ ያደረገብኝ ኮሎኔል ‘ዶክተር ፋኖ’ እያለ ነበር የሚጠራኝ” በማለት፣ “ለምን ለፋኖ ህክምና ትሰጣለህ በማለት ነበር ጥያቄውን የጀመረው። ጨምሮም ፋኖ ሰዎች አይደሉም...እነሱ ጭራቆች ናቸው” እንዳለው ተናግሯል።

የሰብአዊ መብቶች ድርጅቱ የፌደራል መንግሥቱ ኃይሎች ነዋሪዎችን ከፋኖ ጋር ግንኙነት አላቸው በሚል ጥርጣሬ ማሰርን ጨምሮ በሚወስዷቸው እርምጃዎች ህክምና በሚያስፈልጋቸው ሰዎች ዘንድ ስጋት በመፈጠሩ ሰዎች የህክምና ተቋማትን አገልግሎት እንዳያገኙ አደናቅፈዋል ብሏል።

በዓለም አቀፍ የሰብአዊነት ሕግ በጦርነት ውስጥ ቢሆን እንኳን የህክምና ተቋማት፣ ባለሙያዎች፣ ህሙማን እና አምቡላንሶች ልዩ ጥበቃ እንዲያገኙ የሚያዝ መሆኑን በመጥቀስ፤ አገራት እነዚህ ደንቦች በማክበር የሰዎችን የጤና እንክብካቤ የማግኘት መብት ማክበር ይጠበቅባቸዋል ብሏል።

አንድ ዓመት ሊሞላው በተቃረበው የአማራ ክልል ግጭት ምክንያት በበርካታ የክልሉ አካባቢዎች እንቅስቃሴዎች መስተጓጎላቸው መሠረታዊ አገልግሎቶች መደናቀፋቸው ይታወቃል። ከእነዚህም መካከል የህክምና ተቋማት ዋነኞቹ ተጎጂዎች መሆናቸው ይነገራል።

በዚህም ሳቢያ የህክምና መገልገያ አቅርቦቶች በመቆረጣቸው፣ በክልሉ ሆስፒታሎች እና የጤና ማዕከላት ውስጥ በጣም አስፈላጊ የሆኑ መሠረታዊ መድኃኒቶች ለረዥም ጊዜ የቆየ እና ከባድ እጥረት በመፍጠር ተገቢውን አገልግሎት እንዳይሰጡ ምክንያት ሆኗል።

በኦክስጂን እና በመድኃኒት እጥረት እንዲሁም በኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጥ ዶክተሮች እና የጤና ሠራተኞች በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሥራቸውን እንደሚያከናውኑ ያመለከተው ሪፖርቱ፤ “የደም ባንክ ሥራ አቁሟል።... አንዲት በምጥ ላይ የነበረች እናትን ከጄኔሬተር የሚመነጭ ኤሌክትሪክ በመጠቀም ለማዋለድ ቤተሰቦቿ ነዳጅ እንዲያመጡ ጠይቀናል” ሲል አንድ ዶክተር መናገሩን ሪፖርቱ ገልጿል።

ቢቢሲ ያናገራቸው ባለሙያም በጥይት ቆስለው ለሚመጡ ታካሚዎች የደም እጥረት በማጋጠሙ፤ ቤተሰብ እና ተፈላጊው የደም ዓይነት ካልተገኘ ባለሙያው ደም ለመስጠትም የሚገደድበት ሁኔታ እንዳለም ተናግረዋል።

ህክምና በጦርነቱ አውድ ያለበትን ሁኔታ “አስከፊ ነው” ሲሉ የገለጹት ባለሞያው፤ እንደ ኤችአይቪ፣ ቲቢ፣ ስኳር እና ደም ግፊት ያለባቸው ታማሚዎች መድኃኒት በአግባቡ እያገኙ አይደለም ይላሉ።

በክልሉ ያለው ሁኔታ አስቸጋሪ የሆነው ለጤና ባለሙያዎች ብቻ ሳይሆን ለሰብአዊ እርዳታ ድርጅቶችም መሆኑን ሪፖርቱ ጠቅሷል። እየተካሄዱ ባሉ ውጊያዎች፣ በሚፈጸሙ ጥቃቶች፣ በእንቅስቃሴ ገደቦች ምክንያት ተገቢውን ድጋፍ ማድረግ እንዳልቻሉ ተገልጿል።

በተጨማሪም የእርዳታ ሠራተኞች ዒላማ ስለሚደረጉ ጉዳት እየደረሰባቸው በመሆኑ፣ ግጭቱ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ አስካሁን በአማራ ክልል ውስጥ ዘጠኝ የእርዳታ ሠራተኞች ሲገደሉ፣ ከእነዚህም ውስጥ አራቱ የተገደሉት ካለፈው ጥር ወር ወዲህ ነው።

ሂማን ራይትስ ዋች የመንግሥት ኃይሎች በጤና ተቋማት ላይ የሚፈጽሟቸውን ጥቃቶች በተመለከተ የደረሰበትን ግኝት ለመንግሥት አሳውቋ አስተያየት ቢጠይቅም ምላሽ አለማግኘቱን ገልጿል።

የመብት ድርጅቱ መንግሥት በጤና ባለሙያዎች፣ በጤና ተቋማት፣ በህሙማን እና በተያያዥ አገልግሎቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን በአስቸኳይ እንዲያስቆም፤ አገራት እና ዓለም አቀፍ ተቋማት መንግሥት ጥቃት ፈጻሚዎቹን ተጠያቂ እንዲያደርግ ግፊት እንዲያደርጉ እና ጉዳት የደረሰባቸው ተቋማት ወደ ሥራቸው እንዲመለሱ ድጋፍ እንዲሰጡ ጥሪ አቅርቧል።

የአማራ ክልል መንግሥት ከሦስት ወራት በፊት በሰጠው መግለጫ ጦርነቱ የጤናውን ዘርፍ አደጋ ላይ እንደጣለው መግለጹ ይታወሳል።

በክልሉ ባለው ጦርነት 967 የሚሆኑ የጤና ተቋማት ጉዳት እንደደረሰባቸው የየክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱልከሪም መንግሥቱ አስታውቀው ነበር።

ኃላፊው በጤና ተቋማቱ ላይ የደረሰውን ውድመት በመዘርዘር በተለይም መድኃኒቶች እና አምቡላንሶች መዘረፋቸውን ገልጸዋል።

በጤና ተቋማቱ ላይ የደሰው ጉዳት ሦስት ቢሊዮን ብር እንደሆነ የጠቀሱት ኃላፊው፣ 124 የሚሆኑ አምቡላንሶች “ተዘርፈው” ለጦርነቱ አገልግሎት እየዋሉ ነው ብለዋል።

ኃላፊው ለዝርፊያው የመንግሥት ኃይሎችን እተዋጉ ያሉትን የፋኖ ኃይሎች ተጠያቂ አድርገዋል።