በወልድያ በፖሊስ ጣቢያ ላይ በተፈጸመ ጥቃት የፀጥታ ኃይሎች መገደላቸውን እና መወሰዳቸውን ነዋሪዎች ተናገሩ

ወልዲያ

የፎቶው ባለመብት, arts tv

በአማራ ክልል ወልድያ ከተማ በፖሊስ ጣቢያ ላይ ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት ቢያንስ ሁለት የፀጥታ ኃይል አባላት ሲገደሉ ሌሎች መቁሰላቸውን ሦስት የከተማዋ ነዋሪዎች እና የሆስፒታል ምንጭ ለቢቢሲ ተናገሩ። ቢያንስ ሁለት የፖሊስ ኃይል አባላት ደግሞ በታጣቂዎቹ መወሰዳቸውን ቢቢሲ ያነጋገራቸው ምንጮች ገልጸዋል።

የሰሜን ወሎ ዞን ዋና ከተማ በሆነችው ወልድያ ከተማ “ጎንደር በር” በተባለው አካባቢ በሚገኘው ሁለተኛ ፖሊስ ጣቢያ ላይ ጥቃት የተፈጸመው፤ እሁድ ሐምሌ 7/2016 ዓ.ም. እንደሆነ በጣቢያው አቅራቢያ ነዋሪ የሆኑ ሦስት የከተማዋ ነዋሪዎች ተናግረዋል። ሌሊት ሰባት ሰዓት ገደማ አንስቶ መሰማት የጀመረው የተኩስ ልውውጥ ለአንድ ሰዓት ገደማ የቆየ እንደነበር ነዋሪዎቹ ጠቅሰዋል።

የተኩስ ልውውጥ የተጀመረው በአማራ ክልል ከመንግሥት ኃይሎች ጋር ውጊያ ውስጥ ያለው የፋኖ ታጣቂዎች “ወደ ፖሊስ ጣቢያው በመሄድ ጥቃት በመክፈታቸው” እንደሆነ ሁለት ነዋሪዎች አስረድተዋል።

አንድ ነዋሪ፤ “ከሁለት ቀን በፊት መርጦ በተባለ አካባቢ [በታጣቂዎች እና ፀጥታ ኃይሎች መካከል] ግጭት ነበር። ፋኖዎች [በፖሊስ ጣቢያው ላይ] ጥቃት የከፈቱት በግጭቱ ጥቆማ ያደረጉት ‘የፖሊስ ኃይሎች ናቸው’ በሚል ነው። እነዚያን የፖሊስ አባላት ለማጥቃት ነው የመጡት” ሲሉ ለጥቃቱ መነሻ ነው ያሉትን ጉዳይ አስረድተዋል።

ከሌሊቱ ሰባት ተኩል በኋላ የነበረው የተኩስ ድምጽ ከፍተኛ እንደነበር የሚናገሩ በፖሊስ ጣቢያው በቅርብ ርቀት ላይ ነዋሪ የሆኑ ሌላ ምንጭ በበኩላቸው “አብዛኛው የተኩስ ድምጽ ይሰማ የነበረው ከአንድ ወገን” እንደነበር ጠቅሰዋል።

በፖሊስ ጣቢያው ላይ የተከፈተው ተኩስ ድምጽ መሰማቱን ተከትሎ በቅርብ በሚገኝ ኬላ ላይ ተሰማርተው የነበሩ የክልሉ አድማ ብተና አባላት ወደ አካባቢው ደርሰው እንደበረ በማግስቱ ከፀጥታ ኃይሎች መስማታቸውን ምንጩ ጠቅሰዋል።

በእሁድ ሌሊቱ ጥቃት “አንድ የአድማ ብተና አባልን ጨምሮ ሦስት የፖሊስ አባላት” ሕይወታቸው እንዳለፈ የገለጹት እኚህ የአካባቢው ነዋሪ፤ ሦስት የፖሊስ አባላት ደግሞ መቆሰላቸውን ተናግረዋል። ምንጩ፤ ከቆሰሉት የፀጥታ ኃይሎች መካከል የሚያውቁት አንድ የፖሊስ አባል ለህክምና ወደ ደሴ ከተማ መወሰዱን ተናግረዋል።

ሌላ የአካባቢው ነዋሪም በተመሳሳይ ሦስት ፖሊሶች ሕይወታቸው እንዳለፈ እና ሌሎች ሦስት አባላት እንደቆሰሉ ገልጸዋል። በጥቃቱ ሦስት የፖሊስ አባላት መገደላቸውን የሚናገሩ ሌላ ነዋሪ ደግሞ የተጎዱ የፀጥታ ኃይሎች ቁጥርን ወደ አምስት ከፍ አድርገዋል። ከእነዚህ ውስጥም ለተጨማሪ ህክምና ወደ ደሴ ከተማ የተላኩ እንዳሉ ጠቅሰዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሌሊት ላይ የተኩስ ልውውጡን መስማታቸውን የገለጹ አንድ ወልድያ አጠቃላይ ሆስፒታል ምንጭ፤ ጠዋት ላይ ወደ ሥራ ሲገቡ የሁለት የፖሊስ አባላትን አስከሬን መመልከታቸውን ለቢቢሲ ገልጸዋል። የፖሊስ አባላቱ የተገደሉት ሌሊት ላይ በነበረው ጥቃት እንደሆነ ከባልደረቦቻቸውን መስማታቸውንም አክለዋል።

ከተገደሉት እና ከቆሰሉት የፀጥታ ኃይሎች በተጨማሪ በታጣቂዎች የተወሰዱ የፖሊስ አባላትም እንዳሉ ቢቢሲ ያነጋገራቸው አራት ነዋሪዎች ገልጸዋል። ይሁንና ነዋሪዎቹ የተወሰዱት የፖሊስ አባላት ቁጥርን በተመለከተ ለቢቢሲ የሰጡት መረጃ ልዩነት ያለው ነው።

ሁለት ነዋሪዎች ሁለት የፖሊስ አባላት እንደተወሰዱ ሲናገሩ፤ አንድ ምንጭ ቁጥራቸው አራት እንደሆነ ጠቅሰዋል። ሌላ ምንጭ ደግሞ የፖሊስ አባላቱን ብዛት ሰባት አድርሰውታል።

በታጣቂዎች ተወስደዋል ከተባሉት የፖሊስ አባላት መካከል በዕለቱ ተረኛ የነበረች የትራፊክ ፖሊስ እንደምትገኝበት ቢቢሲ ካነጋገራቸው ነዋሪዎች ውስጥ ሦስቱ ገልጸዋል። በፖሊስ ጣቢያው ላይ ጥቃት የተከፈተው “የትራፊክ ፖሊስ አባሏ በስምሪት ላይ ቆይታ ለእረፍት” ወደ ጣቢያ በተመለሰችበት ወቅት እንደሆነ አንድ ነዋሪ ተናግረዋል።

የትራፊክ አባሏ አስረስ እንደምትባል አንድ የአካባቢው ነዋሪ ተናግረዋል። ሌላ ነዋሪ በበኩላቸው የትራፊክ አባሏን በታጣቂዎች መወሰድ የሰሙት ከቤተሰብ መሆኑን አስረድተዋል።

ቢቢሲ በፖሊስ ጣቢያው ላይ ደርሷል ስለተባለው ጥቃት ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ወደ ሰሜን ወሎ ዞን እና ወልድያ ከተማ አስተዳደር ኃላፊዎች ያደረጋቸው ተደጋጋሚ የስልክ ጥሪዎች ምላሽ አላገኙም።

በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱት የፋኖ ታታቂዎች እና የመንግሥት ኃይሎች ውጊያ ግጭት ውስጥ ከገቡበት ባለፈው ዓመት አንስቶ፤ ይህ ዓይነቱ ጥቃት ሲፈጸም የመጀመሪያ ጊዜ አይደለም።

እሁድ ዕለት ጥቃት ባስተናገደው ሁለተኛ ፖሊስ ጣቢያ ላይ ከዚህ ቀደምም ተኩስ ተከፍቶ እንደነበር ሁለት ነዋሪዎች አስታውሰዋል።

በኅዳር ላይ ደግሞ በከተማዋ በሚገኝ የዞኑ ማረሚያ ቤት ላይ በተመሳሳይ መልኩ ታጣቂዎች ሌሊት ላይ ተኩስ ከፍተው በመቶዎች የሚቆጠሩ እስረኞችን ማስለቀቃቸውን በወቅቱ ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።

______

*ቢቢሲ ለዚህ ዘገባ ያነጋገራቸው የወልድያ ከተማ ነዋሪዎች ለደኅንነታቸው ሲሉ ስማቸው እንዲጠቀስ ፈቃደኛ አይደሉም።