አዲሱ የብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲ ማዕቀፍ ምን ማለት ነው?

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዢ ማሞ ምህረቱ

የፎቶው ባለመብት, nbe

የምስሉ መግለጫ, የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዢ ማሞ ምህረቱ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አዲስ የገንዘብ ፖሊሲ ማዕቀፍ ይፋ ማድረጉን ማክሰኞ ምሽት ሐምሌ 2/2016 ዓ.ም. ባወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል።

ይህ የገንዘብ ፖሊሲ ማዕቀፍ በኢኮኖሚ እና ፋይናንስ ባለሙያዎች ዘንድ አዎንታዊ አስተያየት እያስተናገደ ሲሆን ጥያቄም የሚያነሱ አሉ።

ለመሆኑ በጦርነት፣ በወረርሽኝ እና በዓለም አቀፍ ፖለቲካል ኢኮኖሚ ጫና ስር ለወደቀው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ምን ማለት ነው?

የብሔራዊ ባንክ ገዢ ማሞ ምህረቱ ይፋ ያደረጉትን አዲስ የገንዘብ ፖሊሲ ማዕቀፍ በተመለከተ ቢቢሲ ሁለት የኢኮኖሚ እና የፋይናንስ ባለሙያዎችን አነጋግሯል።

እነዚህ ባለሙያዎች በዩናይትድ ኪንግደም የሚገኙት ዶ/ር አብዱልመናን መሐመድ እና አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ባለሙያ ናቸው።

ጉዳዩን ከሥሩ ለመረዳት ከሁሉም በፊት የገንዘብ ፖሊሲን ምንነት ማወቅ የብሔራዊ ባንኩን አዲስ የፖሊሲ ማዕቀፍ ለመረዳት ያግዛል።

ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁት የኢኮኖሚ ባለሙያ፤ “አንድ ኢኮኖሚ የሚመራባቸው ሁለት መሠረታዊ ፖሊሲዎች ናቸው አሉ” ይላሉ።

እነዚህ ፖሊሲዎች የገንዘብ ፖሊሲ (monetary policy) እና የበጀት ፖሊሲ (fiscal policy) ናቸው።

የገንዘብ ፖሊሲ ምንድን ነው?

የምጣኔ ሀብት ባለሙያ የገንዘብ ፖሊሲን ዘመናዊ ኢኮኖሚዎች ከተደራጁ በኋላ የገበያ እንቅስቃሴዎችን በመዳኘት በኢኮኖሚ ውስጥ የሚፈጠሩ ሀብቶችን ለማጠራቀም ወይም ለማከማቸት ጥቅም ላይ የሚውል ገንዘብ ነው ሲሉ ያብራሩታል።

እዚች ጋር እኛ ምሳሌ እናቅርብ እርስዎ ለአሠሪዎ በሚሰጡት አገልግሎት የሚከፈልዎትን ገንዘብ ተጠቅመው በአቅራቢያዎ ካለ ነጋዴ አስቤዛ ሊሸምቱ ይችላሉ እንበል። ለኪስ ሞላ ያለ ደመወዝ ካለዎት ደግሞ ሊቆጥቡት ይችላሉ።

እርስዎ የጉልበት አሊያም አዕምሯዊ ሀብትዎን ተጠቅመው ከአሠሪዎ ገንዘብ ያገኛሉ፤ ነጋዴው ደግሞ በእጁ ያለውን ምርት [ሀብት] ተጠቅሞ ከእርስዎ ገንዘብ ያገኛል።

በቀላሉ ይህ እነዚህ ኢኮኖሚ ውስጥ ያሉ ገንዘብ ተኮር የሆኑ ከገንዘብ እንቅስቃሴ ጋር የሚያያዙ ሁኔታዎች የሚመሩበት የፖሊሲ ማዕቀፍ ነው የገንዘብ ፖሊሲ ይባላል።

ይህ ፖሊሲ በአንድ ኢኮኖሚ ውስጥ ያለውን የገንዘብ ሥርጭት፣ እንቅስቃሴ፣ አስተዳደር እና ገንዘቡ ሊሰጥ የሚገባውን ጥቅም ያስተዳድራል።

በተጨማሪም ገንዘብ በሰዎች የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ ሊያመጣ የሚችለውን ወይም የሚገባውን ውጤት እና በኢኮኖሚው ውስጥ ልንፈጥራቸው የምንፈልጋቸውን እውነታዎች ለማምጣት የምጠቀምበት የፖሊሲ ማዕቀፍ ነው።

እንደ ምጣኔ ሃብት ባለሙያው ገለጻ ይህ የገንዘብ ፖሊሲ “በቅርበት ከአጠቃላይ የበጀት ፖሊሲው ጋር ይተሳሰራል።”

የበጀት ፖሊሲ በቀላሉ ሲተረጎም የመንግሥት የገቢ እና የወጪ ሁኔታን የሚያስተዳድር የፖሊሲ ማዕቀፍ ልንለው እንችላለን። የኢኮኖሚ ባለሙያው “የመንግሥት የወጪ እና የገቢ ሁኔታ ገንዘብ ከሚተዳደርበት የገንዘብ ፖሊሲ ጋር በጣም ጥብቅ ቁርኝት ያለው” ይላሉ።

የኢትዮጵያ የገንዘብ ፖሊሲ ምን ይመስላል?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ማሞ ምህረቱ ይፋ ተደረገ ካሉት አዲስ የገንዘብ ፖሊሲ ማዕቀፍ በፊት ኢትዮጵያ የምትከተለው ፖሊሲ ምን ዓይነት ነበር?

ዶ/ር አብዱልመናን ብሔራዊ ባንክ ይጠቀምበት የነበረው የገንዘብ ፖሊሲ “በዋጋ ግሸበት ምክንያት ኢኮኖሚው ውስጥ ያለው የገንዘብ መጠን ከኢኮኖሚው እድገት ሲበልጥ ነው የሚል መነሻ ሃሳብ አለው” ይላሉ።

ይህ ምን ማለት ነው?

ለምሳሌ ኢኮኖሚው ውስጥ ያለው የገንዘብ መጠን በ10 በመቶ እያደገ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት በአንጻሩ አምስት በመቶ ከሆነ የዋጋ ግሽበት ያስከትላል። ይህ እንደ ዶ/ር አብዱልመናን ገለጻ ከብሔራዊ ባንክ የቀድሞ የገንዘብ ፖሊሲ ጀርባ ያለ አመክንዮ ነው።

ባለፉት ጊዜያት የገንዘብ [ጥሬ ገንዘብ እና በባንክ አካውንት ውስጥ ያለን ተቀማጭ] ዕድገትን ከአገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ጋር ማጣጣም ነበር ብሔራዊ ባንክ ሲሞክር የነበረው።

ነገር ግን ብሔራዊ ባንክ ኢኮኖሚው ውስጥ የሚኖረውን የገንዘብ መጠን መቆጣጠር አለመቻሉን ዶ/ር አብዱልመናን ያነሳሉ።

ይህን ሲያብራሩ ዶ/ር አብዱልመናን “የኢትዮጵያ መንግሥት ከብሔራዊ ባንክ ገንዘብ በሚበደርበት ጊዜ ጥሬ ገንዘብ ይፈጠራል። የኢትዮጵያ መንግሥት ይበደርና አውጥቶ በጥሬ ገንዘብ ክፍያ ሲፈጽም ሕብረተሰቡ ውስጥ ይገባል ማለት ነው” ይላሉ።

ከዚህ በተጨማሪም ብሔራዊ ባንክ የአገሪቱን የኢኮኖሚ ዕድገት መገመት ላይ የሚኖረው ትክክለኝነት ሌላው ዶ/ር አብዱልመናን የሚያነሱት ጉዳይ ነው።

ስማቸው እዳይጠቀስ የጠየቁት የምጣኔ ሃብት ባለሙያ ከዚህ በፊት ስራ ላይ የነበረው የገንዘብ ፖሊሲ፤ “በራሱ የማይቆም ነጻ ሆኖ የማይተዳደር የበጀት ፖሊሲውን በዋነኛነት የበጀት ጉድለቱን መሰረት ያደረገ” መሆኑን ያስረዳሉ።

የዋጋ ግሽበትን ማረጋጋትን እንደ ዋነኛ ዓላማ የሚወስደው የቀድሞው የፖሊሲ ማዕቀፍ በአፈጻጸም ረገድ የተለያዩ መሳሪያዎችን እንደሚጠቀም ባለሙያው ይገልጻሉ።

ባለሙያው “በዋነኛነት አስገዳጅ ሕግጋትን በማስቀመጥ ማምጣት የሚፈለግውን ለውጥ ለመፍጠር ሙከራ የሚያደርግ የገንዘብ ፖሊሲ ነበር” ሲሉ ፖሊሲውን ይገልጹታል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ህንጻ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ህንጻ

አዲሱ የፖሊሲ ማዕቀፍ ምንድን ነው?

ስለ ቀድሞው የብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲ ማዕቀፍ ይህን ካልን አዲሱ ማዕቀፍ ምን አይነት ለውጦችን ያመጣል የሚለውን ደግሞ እንመልከት።

ባንኩ በመግለጫው ካለፈው ዓመት ጀምሮ፤ “ዝቅተኛ እና የተረጋጋ የዋጋ ሁኔታ መኖሩን ለማረጋገጥ የሚያስችል ዘመናዊ የገንዘብ ፖሊሲ ማዕቀፍ ለመዘርጋት ሲሠራ” መቆየቱን ጠቁሟል።

ይህን ተክትሎም አዲሱን የፖሊሲ ማዕቀፍ ተግባራዊ ለማድረግ የሚረዱ ያላቸውን እርምጃዎች በዚሁ ቀን ባንኩ ይፋ አድርጓል።

ከእነዚህ እርምጃዎች መካከል ቀዳሚው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክን የገንዘብ ፖሊሲ በወለድ ተመን ላይ ወደተመሠረተ የገንዘብ ፖሊሲ ማሸጋጋር ነው።

በአዲሱ የፖሊሲ ማዕቀፍ መሠረት ባንኩ የፖሊሲ አቋሙን ለማሳየት እና የገንዘብ እና የብድር ሁኔታዎችን ለመወሰን የሚረዳ የወለድ ምጣኔ የፖሊሲ ተመን እንደሚጠቀም ተገልጿል።

ይህ ምን ማለት ነው?

ዶ/ር አብዱልመናን የፖሊሲ ማዕቀፉ መነሻ ሃሳብ “የዋጋ ግሽበት ምክንያት አጠቃላይ የአገሪቱ ፍላጎት ከአጠቃላይ አቅርቦት መብለጥ ነው” የሚል መሆኑን ያነሳሉ።

ስለዚህ የባንኩ እርምጃ ፍላጎት ከአቅርቦት ከበለጠ የዋጋ ግሽበት ይፈጥራል፤ ሁለቱን ለማጣጣም የወለድ መጠን ሚና አለው የሚል ነው።

የወለድ መጠን ብድር ላይ ያለው ተጽዕኖ ግልጽ ነው። የወለድ መጠኑ ከፍተኛ ከሆነ ተበዳሪ ማቅማማት ይጀምራል። ስለዚህ ብሔራዊ ባንክ ብዙ የገንዘብ ፍሰት በኢኮኖሚው ላይ አለ ብሎ ካሰብ ዋጋ ግሽበትን ለማረጋጋት የወለድ ምጣኔውን ከፍ ሊያደርገው ይችላል። ይህ በበኩሉ ባንኮችን እንዲሁም ከባንኮች የሚበደሩ ግለሰቦችን የመበደር ፍላጎት ይቀንሰዋል።

ዶ/ር አብዱልመናን ይህን ሲያብራሩ “ተበዳሪ ከሌለ ኢኮኖሚው ውስጥ ፍላጎት ይቀዛቀዛል፣ ኢንቨስትመንት ይቀዛቀዛል የወለድ መጠኑ በጣም ከፍ ካለ ሰዎች ከመሸመት ይልቅ ገንዘባቸውን ያስቀምጡታል [ይህ] አጠቃላይ ኢኮኖሚውን ያቀዛቅዘዋል የዋጋ ግሽበትንም ያረጋጋል” ይላሉ።

ዶ/ር አብዱልመናን “ብሔራዊ ባንክ ባንኮቹ ብዙ ገንዘብ እጃቸው ላይ አለ ሊያበድሩ ይችላሉ ብሎ ካሰበ ያንን ከባንኮቹ እሱ ተበዳሪ ሆኖ ይሰበስበዋል። ባንኮቹ እጅ ላይ ያለውን ገንዘብ ከኢኮኖሚው ያስወጣዋል” ሲሉ ያክላሉ።

በሌላ በኩል ኢኮኖሚው ውስጥ ያለው የገንዘብ ዝውውር አንሷል ኢኮኖሚውም ተቀዛቅዟል ብሎ ሲያስብ ብሔራዊ ባንክ ወለድ ምጣኔውን ዝቅ ያደርገዋል።

ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁት ባለሙያ ይህን “ዝቅ ሲል ደግሞ ገንዘብ መውሰድ ቀላል ስለሚሆን ብዙ ገንዘብ ይወስዱ እና ብዙ ብድር ይሰጣሉ ብዙ ብድር ከሰጡ ብዙ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ይኖራል” ሲሉ ያብራሩታል።

የአንድ ብር ኖት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የብሔራዊ ባንክ የወለድ ምጣኔ 15 በመቶ ነው

የወለድ ምጣኔ ተመን ምን ማለት ነው?

ብሔራዊ ባንክ እንደ ኢኮኖሚው ሁኔታ የወለድ ምጣኔ ተመኑ ላይ ማሻሻያዎችን እንደሚያደርግ በባንኩ መግለጫ ላይ ተመላክቷል።

የብሔራዊ ባንክ ፖሊሲ ነክ የወለድ ምጣኔ 15 በመቶ እንደሚሆንም በዚሁ መግለጫ ላይ ሰፍሯል። በመግለጫው መሠረት “ይህ የማዕከላዊ ባንክ የወለድ ምጣኔ እንደ የዋጋ ንረት እና የገንዘብ ሁኔታ እየታየ ከፍ ወይም ዝቅ ይሆናል።”

ይህ 15 በመቶ ወለድ ምጣኔ ባንኮች ከብሔራዊ ባንክ ገንዘብ ሊበደሩ ቢፈልጉ የሚከፍሉት የወለድ ምጣኔ ነው። ይህ ማለት ግን ቁርጥ ያለ የ15 በመቶ ወለድ ይከፍላሉ ማለት አይደለም።

ባንኩ እንደገለጸው ኢኮኖሚውን መሠረት በማድረግ ከፍ ወይም ዝቅ ሊል ይችላል። ከዚህ በተጨማሪ ይህን የወለድ ምጣኔ ተመን ባንኮች እርስ በእርስ በሚወዳደሩበት ወቅት እንደ አመላካች ይጠቀሙበታል።

የባንክ ለባንክ የወለድ ተመን ከማዕከላዊ ባንኩ የ15 በመቶ የፖሊሲ ነክ የወለድ ምጣኔ ጋር የማይጣጣም ከሆነ፤ “ብሔራዊ ባንኩ ሁኔታውን ለማስተካከል ከባንኮች ጋር የግብይት ጨረታን ይጠቀማል” ሲል መግለጫው ያትታል።

ብሔራዊ ባንክ ከገንዘብ ፖሊሲ ጋር የተያያዙ ጨረታዎችን በየሁለት ሳምንቱ እንደሚያወጣ በመግለጫ ላይ ሰፍሯል።

በመግለጫው መሠረት እነዚህ ጨረታዎች የሚደረጉት፤ “ብሔራዊ ባንክ ከወቅታዊ ሁኔታዎች በመነሳት ከባንክ ስርዓት ውስጥ ትርፍ ገንዘብ ለመሰብሰብ ወይም ለጨማሪ ገንዘብ ለመልቀቅ እንዲያስችለው ነው”።

ግራፍ

የፎቶው ባለመብት, National Bank of Ethiopia

የምስሉ መግለጫ, የዋጋ ግሽበት ባለፈው ዓመት ከነበረበት ቅናሽ ማሳየቱን ብሔራዊ ባንክ አሳታውቋል

አዲሱ የገንዘብ ፖሊሲ ለዋጋ ግሽበት ይዞ ይመጣል?

የዋጋ ግሽበት ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት እንደሚፈልግ የሚገልጹት ዶ/ር አብዱልመናን፤ “በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት የዋጋ ግሽበትን ለመዋጋት ቁርጠኛ መሆን አለበት” ይላሉ።

ከዚህ በተጨማሪም ነጻ እና ተዓማኒ ማዕካላዊ ባንክ እንዲሁም የተሻለ የፋይናንስ ሥርዓት መኖር አለባቸው ሲሉ ያክላሉ።

የብሔራዊ ባንክ አዲሱ ፖሊሲ “ተስፋ ሰጪ ይመስላል” የሚሉት ዶ/ር አብዱልመናን “ብሔራዊ ባንክም መንግሥትም ቁርጠኛ ለመሆን የፈለገ ይመስላል” ይላሉ።

ለዚህም አዲሱ የፖሊሲ ማዕቀፍ በተጨማሪ በቅርቡ ለፓርላማ የቀረበውን የብሔራዊ ባንክ አዋጅ በማሳያነት ይጠቅሳሉ። ከሳምንታት በፊት ለፓርላማ የቀረበው አዋጁ የፌደራል መንግሥት ከአገር ውስጥ ገቢ ከ15 በመቶ የበለጠ የገንዘብ ብድር ማግኘት እንዳይችል የሚገድብ ነው።

ዶ/ር አብዱልመናን አዲሱ የፖሊሲ ማዕቀፍ “በዘላቂነት የዋጋ ግሽበትን ለመከላከል የሚረዳ ነው ብዬ አስባለሁ” ሲሉ ተናግረዋል።

“ሽግግሩ አስፈላጊ ነው” የሚሉት ሌላኛው የኢኮኖሚ ባለሙያ በበኩላቸው “ገበያውን ራሱን መሠረት አድርጎ የዋጋ ግሽበቱን ወደ ማረጋጋት እየተሄደ ነው” ይላሉ። ባለሙያው አክለውም “ይሄ በየትኛውም ዘመናዊ ኢኮኖሚ ውስጥ ጥቅም ላይ የሚውል ነው” ብለዋል።

ሆኖም ግን ሁለት ስጋቶች እንዳሉባቸው አልሸሸጉም።

የመጀመሪያው የባለሙያው ስጋት፤ “በጣም ሰፊ የሆነ የኢመደበኛ ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ባለበት አገር ይኼኛውን የፖሊሲ ተመን በመወሰን የሚመጣው ለውጥ በቂ ይሆናል ወይ?” የሚል ነው።

ከባንክ ውጪ የሚንቀሳቀስ ብዙ ጥሬ ገንዘብ መኖሩን የሚያነሱት ባለሙያው፤ “ከባንክ ውጪ የሚንቀሳቀሰው ጥሬ ገንዘብ በጣም ብዙ ሆኖ የገንዘብ ፖሊሲው ውጤታማ ይሆናል ወይ የሚለው ሌላ ነገር ነው” ሲሉ ሌላኛውን ስጋታቸውን ይገልጻሉ።