የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር መጨመር አደጋ ወይስ ዕድል?

የፎቶው ባለመብት, AFP
*[ይህ ሪፖርት ከአንድ ዓመት በፊት የተዘጋጀ ሲሆን፣ አሁን የዓለም ሥነ ሕዝብ ቀንን ምክንያት በማድረግ በድጋሚ የቀረበ ነው]
የዓለማችን ቁጥር አንድ ሃብታም ኢላን መስክ በርካታ መድረኮች ላይ ሲቀርብ ከአፉ የማይጠፋ አንድ ሐሳብ አለ - የሕዝብ ቁጥር።
ኢላን የሰው ልጅ ወደፊት ከሚገጥሙት ከባድ ፈተናዎች መካከል አንዱ የሕዝብ ቁጥር ዕድገት መመናመን ነው ይላል።
ወደፊት ማርስን መቆጣጠር አለብን የሚል አቋም ያለው ይህ ቢሊየነር “ልንወልድ፣ ልንዋለድ ይገባል” ሲል ይሞግታል።
በሌላ በኩል የዓለም መንግሥታት የሕዝብ ቁጥር ጨምሯል፤ ልንገታው ይገባል በማለት ፖሊሲ ቀርጸው ተግባራዊ ማድረግ ከጀመሩ ሰነባብተዋል።
ይህ ግን ለኢላን የሚዋጥ ሐሳብ አይደለም።
“አንድ ቦታ ታጭቀን ስለምንኖር ነው እንጂ ምድራችን በርካታ ሰው መያዝ ትችላለች” ይላል።
ዋሺንግተን ፖስት የተሰኘው ጋዜጣ ከሰባት ዓመት በፊት ባተመው ፅሑፉ ጠቅላላው የዓለማችን ሕዝብ ኒው ዮርክ በተሰኘችው ከተማ ውስጥ ብቻ መኖር ይችላል ሲል አስነብቧል።
በወቅቱ የዓለም ሕዝብ ቁጥር 7 ቢሊዮን አካባቢ ነበር።
የዓለማችን ሕዝብ ቁጥር በ20ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ከነበረው ሦስት እጥፍ አድጓል። በሚቀጥለው ኅዳር ወር ደግሞ ቁጥራችን 8 ቢሊየን ይደርሳል።
በምድራችን በርካታ ሕዝብ ያላት አገር ቻይና ናት። ነገር ግን በቅርቡ ይህን ሥፍራ ለሕንድ እንደምትለቅ የመንግሥታቱ ድርጅት ገልጿል።
ነገር ግን የዓለም ሕዝብ ቁጥር እንደሚባለው በፍጥነት እያደገ አይመስልም።
በዚህም በስልሳ ዓመታት ውስጥ ዝቅተኛ የተባለውን የሕዝብ ቁጥር ዕድገት በ2020 አስመዝግባለች።
ይህ ከ1950ዎቹ በኋላ ዘገምተኛ የተባለው የሕዝብ ቁጥር እድገት ከ40 ዓመታት በኋላ ድጋሚ አሻቅቦ የሕዝብ ቁጥር 10.4 ቢሊየን ይደርሳል ይላል የተባበሩት መንግሥታት ትንበያ።
የመንግሥታቱ ድርጅት በቅርቡ ባወጣው ትንበያ ሕንድን ጨምሮ ስምንት አገራት የዓለማችንን ግማሽ ሕዝብ ይይዛሉ ብሏል።
ኢትዮጵያ ከእነዚህ ስምንት አገራት መካከል ተካታለች።
ግብፅ፣ ናይጄሪያ፣ ታንዛኒያ፣ ዲሞክራቲክ ኮንጎ፣ ሕንድ፣ ፓኪስታን እና ፊሊፒንስ ሌሎቹ አገራት ናቸው።
ለመሆኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር እንዲህ መመንደጉ አደጋ ነው ወይስ ተጨማሪ ጉልበት?
የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር ከየት ወደ የት?
የዓለም ባንክ ቁጥር እንደሚያሳየው የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር ከ60 ዓመታት በፊት ከነበረው በአምስት እጥፍ አድጓል።
ከአምስት ዓመት በታች ያሉ ሕፃናት ሞት ባለፉት 50 ዓመታት እየቀነሰ መጥቷል።
ለምሳሌ በ1970 ከአንድ ሺህ ሕፃናት 244 ጨቅላዎች ይሞቱ ነበር። ይህ ቁጥር በ2019 ወደ 50 ወርዷል።
ነገር ግን ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት የነበረው ዕድገት ፈጣን የሚባል አልነበረም።
የተባበሩት መንግሥት የሕፃናት መርጃ (ዩኒሴፍ) አንዲት ኢትዮጵያዊት እናት በአማካይ 4.6 ልጆች ትወልዳለች ሲል ከአራት ዓመት በፊት ገልጾ ነበር።
ኢትዮጵያ በምጣኔ ሃብት አላደጉም ከሚባሉ አገራት መካከል ትመደባለች።
ለዓለም ሕዝብ ዕድገት ብዙ ያበርክታሉ ተብለው የተገመቱ እንደ ኮንጎና ታንዛኒያ ያሉ አገራትም ምጣኔ ሃብታቸው እንጭጭ ነው።
የተባበሩት መንግሥታት ምጣኔ ሃብታቸው የሚንገዳገድ አገራት የሕዝብ ቁጥር ዕድገት አደጋ ሊሆንባቸው ይችላል ሲል ያስጠነቅቃል።
ይህን የሚሉት የተባበሩት መንግሥታት የምጣኔ ሃብትና ማኅበራዊ ጉዳዮች ዋና ፀሐፊ ሊዪ ዤንሚን ናቸው።
የሕዝብ ቁጥር መጨመሩ ድህነትን ለመግታት፤ የተመጣጠነ ምግብ ለማቅረብ እንዲሁም ትምህርትና ጤናን ለማዳረስ የሚደረገውን ጥረት ይፈትነዋል ይላሉ ሊዪ።
ምጣኔ ሃብት እና የሕዝብ ዕድገት
ለንደን የሚገኙት የምጣኔ ሃብት ባለሙያው አብዱልመናን መሐመድ የሕዝብ ዕድገት እና ምጣኔ ሃብት የሚነጣጠሉ አይደሉም ይላሉ።
የምጣኔ ሃብት ዕድገት የሦስት ማዕዘናት ውጤት ነው ይላሉ ባለሙያው።
“አንደኛው የሰው ጉልበት ነው፤ ሁለተኛው የካፒታል ክምችት ሲሆን ሦስተኛው ደግሞ የቴክኖሎጂ መሻሻል ነው።”
አብዱልመናን፤ እኒህ ሦስቱ ከተቀናጁ ለምጣኔ ሃብት ዕድገት ያላቸው ፋይዳ የትየለሌ ነው ባይ ናቸው።
“ለምሳሌ የሕዝብ ዕድገቱ ፍጥነቱ የተቀዛቀዘባቸው አገራት የካፒታል ክምችታቸውና ቴክኖሎጂ አግዟቸው ካልሆነ በቀር ምጣኔ ሃብቱን ማሳደግ አይችሉም።”
ወደ ኢትዮጵያ እንምጣ።
“እንደኛ ዓይነት አገራት የሰው ጉልበትን ተጠቅመው ካፒታል ሲያከማቹና ቴክኖሎጂያቸውን ሲያሳድጉ ነው ለውጥ ማምጣት የሚችሉት” ሲሉ ያስረዳሉ።
ታድያ ኢትዮጵያ አሁን ያላት የሕዝብ ቁጥር ያግዛታል ወይስ አደጋ ይደቅንባታል?
የቴክኖሎጂ “ኢኖቬሽን” ትልቅ ኢንቨስትመንት ስለሚጠይቅ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ አገራት ሊከብድ ይችላል እንበል ይላሉ አብዱልመናን።
“ግን ሌላው ዓለም የሚጠቀምባቸውን ቴክኖሎጂዎች በማስገባት ከሰው ኃይል ጋር አጣምረን የማንጠቀምበት ከሆነ አደጋ ነው።”
ሦስቱን ማዕዘናት አቀናጅቶ ጥቅም ላይ አለማዋል ፖለቲካዊ ችግር ሊያስከት እንደሚችል የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ያስረዳሉ።
“ይህ ካልሆነ የሕዝብ ቁጥር መጨመር ፖለቲካዊ፣ ኢኮሚያዊ እና ማኅበራዊ ችግር ሊሆንብን እንደሚችል ምንም ጥርጥር የለውም።”
አብዱልመናን አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ወጣት እንደሆነ በመጠቆም “ወጣቱ ሥራ ከሌለው ለማኅበራዊ፣ ለኢኮኖሚያዊና ለፖለቲካዊ ቀውስ” እንደሚዳርግ ይናገራሉ።

ለኢትዮጵያ የሚያዋጣት ፖሊስ የቱ ነው?
“ወደ ኋላ ዞር ብለን ያለውን 15 ዓመት ብንመለከት ይበልጥ ሲበረታታ የነበረው የመንግሥት ኢንቨስትመንት ነው።”
ይህ ፖሊሲ የምጣኔ ሃብት ዕድገት ቢያመጣም የሥራ ፈጠራ ላይ ደካማ የሚባል ፖሊሲ ነበረን ሲሉ ይሞግታሉ - አብዱልመናን።
“ብዙ ሕዝብ የሚቀጥርልን የኢንዱስትሪው መስክ አላደገም። አገልግሎት ሰጪው ዘርፍ ግን አድጓል። ይህ ደግሞ ሥራ የሌለው የተማረ ወጣት እንዲበዛ አድርጓል።
“አሁን ልንከተለው የሚገባው አምራች ኢንዱስትሪውን ሊያሳድግ የሚችለውን መንገድ ነው። የግል ዘርፉን የሚያበረታታ [አገልግሎትና ሸቀጥ ንግድ ሳይሆን] በዋናነት ምርት ላይ የሚያተኩር ፖሊሲ ሊሆን ይገባል” ይላሉ።
የአገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታ፣ የዋጋ ግሽበት፣ መንግሥት ያለበት ዕዳ ማነቆ ሊሆኑ እንደሚችሉ ባለሙያው ከግምት ያስገባሉ።
አብዱልመናን “ኢትዮጵያዊያን ሥራ ወዳድ አይደሉም” ከሚሉ ሰዎች ጋር በፍፁም አይስማሙም።
“እኛ እንደማንኛውም ሕብረተሰብ ነን። ኢትዮጵያዊያን ውጭ አገር ሲሄዱ ጠንክረው ይሠራሉ አይደል እንዴ? እንደማንኛውም ሰው ተምረው የፈለጉበት መድረስ ይችላሉ። ያለንበት ሁኔታ ነው መታየት ያለበት።”
አብደልመናን የሕዝብ ቁጥር ዕድገትን መግታት ከባድ እንደሆነ ጠቅሰው አማራጩ ዕድገቱን እንደ አጋጣሚ መጠቀም እንደሆነ ቻይናን በምሳሌነት አንስተው ያስረዳሉ።
ፈጣን የሕዝብ ቁጥር ዕድገት ያላቸው አገራት ድህነትን መቀነስ ቢችሉም ቀላል አይደለም ይላል የተባበሩት መንግሥታት ዘገባ።
ድርጅቱ ለምሳሌ አንጎላን ጠቅሶ ባለፉት 20 ዓመታት የእናቶችና ሕፃናትን ሞት ብትቀንስም ግማሽ ያህል ሕዝቧ አሁንም ድህነት ውስጥ ነው ይላል።
ማዳጋስካርም እንዲሁ ለበርካታ ዓመታት የሕዝብ ቁጥሯ ዕድገት ከ3 በመቶ በበለጠ ባያድግም አሁን ድህነት ውስጥ ካሉ አገራት መካከል ናት።
“አገራዊ ሰላም ያስፈልገናል”
ይህ ሪፖርት ሲዘጋጅ የገንዘብ ሚኒስቴር ከፍተኛ አማካሪ የነበሩት እና አሁን የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ዳይሬክተር የሆኑት ብሩክ ታዬ (ዶ/ር) የሰው ኃይልን በተመለከተ ከአብዱልመናን መሐመድ ጋር ይስማማሉ።
“ምሳሌ ለመስጠት ያህል አሥሩም የስኳር ፋብሪካዎች ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ቢገቡ 300 ሺህ ለሚደርሱ ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ።”
የመንግሥት ፖሊሲና የምጣኔ ሃብት እንቀስቃሴ በትክክለኛው መንገድ የተቀረፀ ከሆነ የሕዝብ ብዛት ዕድል እንጂ ፈተና አይሆንም ይላሉ አማካሪው።
ብሩክ (ዶ/ር) እንደሚሉት የኢትዮጵያ ጥቅል አገራዊ ምርት [ጂዲፒ] ከሌሎች ከ100 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ካላቸው አገራት ጋር ሲነፃፀር ዝቅ ያለ ነው።
“ያለን ተፈጥራዊ ሃብት ከሕዝብ ቁጥሩ ጋር ተደምሮ ጥቅም ላይ እንዲውል ብዙ መሥራት ይጠበቅብናል። በየዓመቱ ተመርቆ ሥራ ፍለጋ ላይ ያለውን ወጣትና የሚፈጠረውን የሥራ ዕድል ማመጣጠን አለብን።”
አማካሪው እንደሚያምኑት ኢትዮጵያ ያልተጠቀመችባቸው ብዙ ዘርፎች ስላሉ ሥራ ፈላጊውንና ሥራ ፈጠራውን ማመዛዘን ይቻላል። ነገር ግን ይህ እንዲሆን የተመቻቸ ፖሊሲ ያስፈልጋል።
“ለምሳሌ ሳፋሪኮምን እንመልከት። ይህ የዛሬ ዓመት ያልነበረ ድርጅት ነው። አሁን ግን ሥራ ጀምሮ ብዙ ሰዎችን መቀጠር ችሏል። እንደኔ እምነት ብዙ ያልተነኩ ብዙ ዘርፎች አሉ።”
ብሩክ (ዶ/ር) ኢንዶኔዢያን በምሳሌነት በማንሳት የሕዝብ ቁጥር ዕድገትን እንደ ዕድል መጠቀም እንደሚቻል ያብራራሉ።
“ባለፉት 15 ዓመታት በርካታ ፈተናዎችን ያለፈችው ኢነዶኔዢያ እንደኛ ብዙ ብሔሮች ያሏት፣ የሕዝብ ቁጥሯም ከእኛ ከሁለት እጥፍ በላይ የሚበልጥ አገር ናት። አሁን ጥቅል አገራዊ ምርት [ጂዲፒ] ከአንድ ትሪሊየን በላይ ነው [የኢትዮጵያ 117 ቢሊዮን አካባቢ ነው]። እኛም በደንብ ስላልተጠቀምንበት እንጂ ያለን አቅም የትየለሌ ነው።”
ነገር ግን ይላሉ አማካሪው ይህንን ለማሳካት ከሁሉም በላይ “አገራዊ ሰላም” ያስፈልገናል።
የአፍሪካ ዲቨሎፕመንት ፖሊሲ ተቋም ዋና ዳይሬክተር ኤሊያ ዙሉም (ዶ/ር) እንዲሁ ኢትዮጵያ በትምህርት፣ በአቅም ግንባታና በጤና ታግዛ ሕዝቧን ለኢኮኖሚ ሽግግር ልትጠቀምበት ትችላለች ሲሉ ለቢቢሲ ይናገራሉ።
ኢትዮጵያና ናይጄሪያ በአህጉረ አፍሪካ ከፍተኛ የሕዝብ ዕድገት እያስመዘገቡ ያሉ ቀዳሚ አገራት ናቸው።
በአሁኑ ወቅት በየዓመቱ የኢትዮጵያ ሕዝብ በሁለት ሚሊዮን ሲያድግ፣ የናይጄሪያ ሕዝብ ደግሞ በአምስት ሚሊየን ይመነደጋል።
ዳይሬክተሩ “የሕዝብ ቁጥር ዕድገት ለልማት ትልቅ ፀጋ ሊሆን ይችላል” ይላሉ።
“እነዚህ አገራት በአቅም ግንባታ፣ በሥራ ዕድል ፈጠራና የግል ዘርፉን በማሳደግ በኩል ብዙ ሥራ ይጠብቃቸዋል። ትልቅ ሕዝብ ካለ እና የተማረ እንዲሁም የሠለጠነ ከሆነ ለምጣኔ ሃብት ትልቅ ሚና አለው። ነገር ግን በተቃራኒው ሕዝቡ ሥራ አጥና ጤናው ያልተጠበቀ ከሆነ ግን ጥፋትን ያስከትላል።”
በአፍሪካ በርካታ አገራት ሴቶች በአማካይ ከ4 እስከ 5 ልጆች ይወልዳሉ። ይህ ሴቶች ትምህርት እያቋረጡ አሊያም ወደ ዩኒቨርሲቲ እየገቡ እንዳልሆነ ጠቋሚ እንደሆነ የሚጠቅሱት ኤሊያ (ዶ/ር) “ሴቶች በብዛት ትምህርት ገበታ ላይ እንዲገኙ ማድረግ አስፈላጊ ነው” ይላሉ።
በፈረንጆቹ 1994 ግብፅ በተካሄደ የሕዝብ ቁጥርና ልማት ስብሰባ መንግሥታት አንድ ስምምነት ላይ ደርሰው ነበር። ይህ ስምምነት ‘ጥንዶች ምን ያህል ልጅ መውለድ እንዳለባቸው መወሰን፣ እንዲሁም የሕዝብ ቁጥርን መቆጣጠር የመንግሥት ሥራ አይደለም’ የሚል ነው።
ነገር ግን ይላሉ ኤሊያ “የቤተሰብ ዕቅድ ትምህርትና መረጃ እንዲሁም መከላከያ አማራጮችን የማቅረብ ኃላፊነት የመንግሥት ነው።”
“እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ባላቸው አገራት ሴቶች የእርግዝና መከላከያ አማራጮችን ላያገኙ ይችላሉ።”
የሕዝብ ቁጥር ዕድገትን መግታት ይቻላል?
“የሕዝብ ቁጥር ሊቀንስ ይችላል እንጂ መግታት አይቻልም” ይላሉ ብሩክ (ዶ/ር)።
“ለምሳሌ የእኛ ሕዝብ ቁጥር ዕድገት 2.5 ነው። ሌሎች ከዚህ ያነሰ ዕድገት የሚያስመዘግቡ አገራት አሉ። ይህ እየቀነሰ ይሄዳል እንጂ መግታት አይቻልም።”
ከአንድ ልጅ በላይ መውልድን በፖሊሲ ከልክለው የነበሩ አገራት አሁን ወደ ጎልማሳነት ዕድሜ እየሄደ ያለው ሕዝባቸው እየበዛ መሆኑን አማካሪው ይናገራሉ።
የምጣኔ ሃብት ባለሙያው አብዱልመናንም “የማይሆን ነው” ይላሉ።
የዓለም የሕዝብ ቁጥር
- በሚቀጥለው ኅዳር 2022 የዓለም ሕዝብ ቁጥር 8 ቢልየን ይደርሳል
- ቁጥሩ በ2030 ወደ 8.5 ቢሊየን፣ በ2050 9.7 ቢሊየን፣ በ2100 ደግሞ 10.4 ቢሊየን ሊደርስ ይችላል
- በ2019 አንድ ሰው በሕይወት የሚቆይበት አማካይ ዕድሜ 72.8 ደርሷል
- ምጣኔ ሃብታቸው ዝቅተኛ የሆነ አገራት አማካይ ዕድሜ ከዓለም አቀፉ በ7 ዝቅ ያለ ነው
- ኢትዮጵያ፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ግብፅ፣ ሕንድ፣ ናይጄሪያ፣ ፓኪስታን፣ ፊሊፒንስን እና ታንዛኒያ በሚቀጥሉት 30 ዓመታት የዓለማችንን ግማሽ ሕዝብ ይይዛሉ
- ከሰሃራ በታች ያሉ አገራት እስከ 2100 ድረስ ሕዝባቸው ማደጉን ይቀጥላል ተብሎ ይጠበቃል












