የወሊድ መጠን በመቀነሱ ጃፓን አሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ መሆኗን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስጠነቀቁ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በጃፓን ያለው የወሊድ መጠን መቀነስ አገሪቱን አሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ እንደጣለው ጠቅላይ ሚኒስትር ፉሚዮ ኪሺዳ ተናገሩ።
በዚህም ሳቢያ አገሪቱ እንቅስቃሴ የምታቆምበት አፋፍ ላይ እንደሆነች አስጠንቅቀዋል።
ከ125 ሚሊየን የጃፓን ዜጎች መካከል በዓመት ከ800,000 በላይ የወሊድ መጠን እንዳለ ተገልጿል። እአአ በ1970ዎቹ ቁጥሩ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ነበር።
የጃፓንን ጎረቤቶች ጨምሮ በብዙ አገራት የወሊድ መጠን እየቀነሰ መጥቷል።
በጃፓን በሕይወት የመቆየት መጠን እየጨመረ ሲመጣ የወሊድ መጠን ቀንሷል። በዚህ ምክንያትም የአረጋውያን ቁጥር እየጨመረ የወጣቶች ቁጥር እየቀነሰ መጥቷል።
ጃፓን በዓለም ከ65 ዓመት በላይ በሆኑ ሰዎች ብዛት ሁለተኛ ደረጃ ላይ ናት።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ “እንደ ማኅበረሰብ እንቀጥላለን ወይ የሚለው አጠያያቂ ደረጃ ደርሷል። ልጆች ተኮር ፖሊሲዎች ትኩረት ይሻሉ። በዚህ ዘርፍ የሚሠራው ሥራ አሁን ካለው እጥፍ ወጪ ያስፈልገዋል። ግንቦት ላይ ይህን ጉዳይ የተመለከተ ዘርፍ ይቋቋማል” ሲሉ ለአገሪቱ ሕግ አውጭዎች ተናግረዋል።
መንግሥት ከዚህ ቀደምም ተመሳሳይ ፕሮጀክቶች ጀምሮ አልተሳካለትም።
የጃፓን የሕዝብ ቁጥር በአውሮፓውያኑ 2017 ከነበረበት 128 ሚሊዮን በምዕተ ዓመቱ መጨረሻ ወደ 53 ሚሊዮን እንደሚወርድ በ2020 የወጣ ጥናት ይጠቁማል።
ጃፓን ስደተኞች የምትቀበልበት ሕግ ጥብቅ ቢሆንም በቅርቡ በመጠኑ ላልቷል። ተንታኞች እንደሚሉት ግን አረጋውያን የበዙበት ማኅበረሰብ የተሻለ ወደፊት የሚኖረው ሕጉ በአግባቡ ከላላ ነው።
የኑሮ ውድነት፣ በሥራ እና በኑሮ የሚጠመዱ ሴቶች ቁጥር መጨመር፣ የወሊድ መቆጣጠሪያ ተደራሽነት መስፋት እና ሴቶች ውስን ልጆች ብቻ ለመውለድ መወሰናቸው ለወሊድ መጠን መቀነስ አስተዋጽኦ አድርገዋል።
ባለፈው ሳምንት ቻይና በ60 ዓመታት የመጀመሪያውን የወሊድ መጠን መቀነስ ሪፖርት አድርጋለች።
በ2050 ከጃፓን ሕዝብ አንድ ሦስተኛው እንደማይኖር ይገመታል።
በአገሪቱ ከውጭ ዜጎች የተወለዱ 3 በመቶ ብቻ ናቸው።
በጃፓን ከሌሎች አገር ዜጎች እና ከጃፓናውያን የሚወለዱ ሰዎች የሚሰጣቸው ቦታ አከራካሪ ሆኖ ዘልቋል።
የኑሮ ውድነት መባባስ ለወሊድ መጠን መቀነስ አንዱ ምክንያት ሲሆን፣ ጃፓን የሠራተኞች ክፍያን ባለፉት 30 ዓመታት አላሻሻለችም።
ተንታኞች እንደሚሉት፣ ስደተኞችን መግፋት ዋጋ የሚያስከፍላቸው አገራት ምሳሌ መሆን የምትችለው ጃፓን ናት።












