የዛምቢያው ፕሬዝዳንት ጥንዶች የአጋሮቻቸውን ስልክ መበርበራቸው ለፍቺ ምክንያት ሊሆን ይችላል አሉ

ስልኩን የሚመለከት ግለሰብ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ጥንዶች በትዳራቸው ውስጥ ሰላም እንዲኖር የአጋሮቻቸውን ስልክ ከመበርበር እንዲቆጠቡ የዛምቢያው ፕሬዝዳንት ሃካይንዳ ሂቺሌማ መከሩ።

ፕሬዝዳንቱ ይህንን ያልተለመደ አይነት ምክር ለአገራቸው ጥንዶች የሰነዘሩት በአገራቸው ውስጥ ያለውን ከፍተኛ ነው የተባለ የፍቺ ችግርን በሚመለከት በተናገሩበት ወቅት ነው።

መረጃዎች እንዳመለከቱት በዛምቢያ ውስጥ ባለፈው የፈረንጆች ዓመት ብቻ ከ22,000 በላይ ፍቺዎች ተፈጽመዋል፤ የአገሪቱ ፕሬዝዳንትም ይህንን ክስተት “መጥፎ ዕድል” ሲሉ ገልጸውታል።

በጋብቻ ውስጥ የዕኩልነት መብት አለመኖር፣ አመንዝራነት፣ ጾታዊ ጥቃት፣ ስድብ እና የጭካኔ ድርጊቶች በዛምቢያ ለፍቺ ሰበብ ተደርገው በፍርድ ቤት የቀረቡ ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው ተብለዋል።

“የምንጋባው ለፍቅር ስንል እንጂ አንዳችን አንዳችንን ለመቆጣጠር ወይም ጣት በመጠቋቆም ለመካሰስ አይደለም” በማለት አንድ ባሕላዊ ንጉሥን ባስተናገዱበት ጊዜ ፕሬዝዳንት ሂቺሌማ መናገራቸውን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

ጨምረውም “ነጻነት ማለት የራሳችንን ነጻነት የመገደብ ኃላፊነት እንጂ በሌሎች ነጻነት ውስጥ ጣልቃ መግባት አይደለም። አንዳችሁ ሌላኛችሁን ታገሱ፣ ተረዱ” በማለት በትዳር ውስጥም ነጻነት እንዳለ እና ከልክ ያለፈ ቁጥጥር አደጋ እንዳለው አመልክተዋል።

በዛምቢያ ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ፍቺ መመዝገቡ ፕሬዝዳንቱ ያሳሰባቸው ሲሆን፣ ጥንዶች የአጋሮቻቸው ሞባይልን መፈተሽ ከፍቺ ጋር ስላለው ግንኙነት ፕሬዝዳንቱ ማብራሪያ ስለመስጠታቸው ዘገባዎቹ ያሉት ነገር የለም።