ኢትዮጵያ ውስጥ ምን ዓይነት ንብረት ቢኖርዎት ነው ግብር እንዲከፍሉ የሚገደዱት?

አዲስ አበባ

የፎቶው ባለመብት, addis ababa city admin.

የንብረት ግብር ኢትዮጵያ ውስጥ የተጀመረው በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመን መንግሥት እንደሆነ መዛግብት ያሳያሉ።

አብዮቱን ተከትሎ የመጣው ደርግ ባወጣው አዲስ ሕግ መሠረት የመሬት እና የጣሪያ ግብር ዜጎች እንዲከፍሉ ማድረግ ጀመረ።

በዚህ ወቅት መሬት ግብር የሚጣልበት ንብረት ሳይሆን ዜጎች ከመንግሥት የሚከራዩት ነበር። ቢሆንም ዓመታዊ ግብር መክፈል ግድ ይላል።

ኢሕአዴግ ወደ ሥልጣን ሲመጣ ‘ያረጀ ያፈጀ’ ያለውን የንብረት ግብር እንደ አዲስ ከልሶት ተግባራዊ ቢያደርገውም ሊዘልቅ አልቻለም።

ኢትዮጵያ ውስጥ የንብረት ግብር አለ ወይስ የለም የሚለው ሐሳብ አሁንም አከራካሪ ነው።

በቅርቡ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደራሴዎች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች በንብረት ግብር ጉዳይ አዲስ የሕግ ማዕቀፍ እንደሚያዘጋጅ አስታውቀዋል።

ምክር ቤቶቹ በጋራ ባሳለፉት ውሳኔ መሠረት በሁሉም ክልሎች የሚጣለው የንብረት ግብር “ተመጣጣኝ” ይሆናል ብለዋል።

የጋራ ምክር ቤቱ አባላት “በንብረት ላይ የሚጣለውን ግብር ክልሎች ያስተዳድሩት” ሲሉ በአብላጫ ድምፅ ወስነዋል።

ነገር ግን ይህ ግብር መጣል የለበትም ብለው የተቃወሙም የምክር ቤት አባላት ነበሩ።

በሌላ በኩል ይህ ግብር ተግባራዊ መሆን አለበት ብለው የሚከራከሩ አባላት “ለከተሞች የገቢ ምንጭ ይሆናል” ይላሉ።

ለመሆኑ የንብረት ግብር ምንድነው? ኢትዮጵያ ውስጥ ተግባራዊ የሚሆነውስ እንዴት ነው?

የንብረት ግብር

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የንብረት ግብር (ፕሮፐርቲ ታክስ) አንድ ግለሰብ አሊያም ሕጋዊ አካል ለሚጠቀምበት ንብረት ለመንግሥት የሚከፍለው ገንዘብ ማለት ነው።

በአብዛኛዎቹ የዓለም አገራት የንብረት ግብር የሚለካው ንብረቱ በየዓመቱ ተተምኖ የሚኖረውን ዋጋ መሠረት በማድረግ ነው።

በርካታ የዓለማችን ከተሞች የንብረት ግብር ጥለው በሚሰበስቡት ገንዘብ ራሳቸውን ይደጉማሉ።

አብዛኛውን ጊዜ የንብረት ግብር የሚጣልበት መሬት እና ሕንፃ ቢሆንም ተሽከርካሪዎች ላይም ግብር የሚጥሉ አገራት አሉ።

የንብረት ግብር “በቀጥታ ክፍያውን ከሚከፍለው ግለሰብ የሚሰበሰብ የግብር ዓይነት ነው” የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰር ጥላሁን ድረስ ናቸው።

የንብረት ግብር ሁለት ዓይነት ገፅታዎች እንዳሉት የሚያስረዱት በደብረ ማርቆስ ዩነቨርሲቲ መምህር እና ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ምሑሩ ሁለተኛው ድግሪያቸውን በመሬት አስተዳደር እና ንብረት ታክስ ሠርተዋል።

አንደኛው ‘ፕሮፐርቲ ትራንዛክሽን ታክስ’ ሲሆን፣ ይህ ማለት ንብረት ሲሸጥ እና ሲለወጥ ገቢ የሚደረግ ግብር ነው። ሁለተኛው እና ዐቢይ የሚባለው ግን ዓመታዊ የዋጋ ጭማሪን መሠረት አድርጎ ንብረት ላይ የሚጣለው ግብር ነው።

የንብረት ግብር የሚንቀሳቀስ እና የማይንቀሳቀስ ንብረትን ቢያካትትም ውጤታማ የሚባለው ግን በማይንቀሳቀሱት [በመሬት እና በሕንፃዎች] ላይ የሚጣለው የንብረት ግብር እንደሆነ ረዳት ፕሮፌሰሩ ይናገራሉ።

“የንብረት ግብር ከሌሎቹ የግብር ዓይነቶች የሚለየው በቀላሉ የሚደበቅ አለመሆኑ ነው። መንግሥት በሚሠራው የዋጋ ግምት (ቫሉዌሽን) መሠረት የአንድ ንብረት ዓመታዊ ዋጋ ተሰልቶ የሚጣል ነው። ስለዚህ ግለሰቦች ይህንን ግብር የሚደብቁበት መንገድ የላቸውም።”

በበርካታ አገራት የንብረት ግብርን ተግባራዊ የሚያደርጉት የከተማ አስተዳደሮች ናቸው። ነገር ግን በቀላል ወጪ እና ቴክኖሎጂ የሚሠራ አይደለም።

ቢሆንም ‘ፕሮፐርቲ ታክስ’ በጣም ትልቅ ቴክኖሎጂ እና የሰው ኃይል አቅም እንደሚጠይቅ ረዳት ፕሮፌሰሩ ጥላሁን ይገልጻሉ።

አክለውም የንብረት ግብር ገቢ ከመሰብሰብ ባለፈ ዜጎች ወጪን እንዲቀንሱ አሊያም ቁጠባ እንዲለምዱ ምክንያት ይሆናል።

የንብረት ግብር አሜሪካ ውስጥ የማዕከላዊው መንግሥት እና ክልላዊ አስተዳደሮች ከሚሰበስቡት ገቢ 30 በመቶውን ይይዛል።

ነገር ግን አሜሪካ ዝቅተኛ የንብረት ግብር ከሚያስከፍሉ አገራት መካከል ስትሆን፣ ቤልጂዬም እና ስፔንን የመሳሰሉ አገራት ደግሞ ከፍተኛው የንብረት ግብር በማስከፈል ይታወቃሉ።

አዲስ አበባ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የንብረት ግብር በኢትዮጵያ

“ኢትዮጵያ ውስጥ የንብረት ግብር አለ ወይስ የለም የሚለው በራሱ አከራካሪ ነው” ነው የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰር ጥላሁን፣ ቢሆንም ኢትዮጵያ ውስጥ የመጀመሪያው ግብር የሚባለው የንብረት ግብር እንደሆነ ይናገራሉ።

“እኔ ኢትዮጵያ ውስጥ የንብረት ግብር የለም ከሚሉት ጎራ አይደለሁም። ነገር ግን ቢያንስ ሁለተኛው የንብረት ግብር አለ። አንድ ንብረት ሲሸጥ ወይም ሲለወጥ የሚከናወነው (ትራንሳክሽናል) የግብር ዓይነት አለ።”

በደርግ ጊዜ የተጣለውን የጣሪያ ግብር እና የመሬት ኪራይ ፖሊሲ የሚያወሱት ምሑሩ ይህ ሕግ አሁንም እንዳለ ነገር ግን ብዙ ሰው እንደማያውቀው፣ ይህ የሆነበት ምክንያት የሚሰበሰበው የንብረት ግብር እጅግ አነስተኛ ስለሆነ እንደሆነም ያስረዳሉ።

አክለው አሁን ባለው ሁኔታ ሰዎች የንብረት ግብር የሚከፍሉት በፈቃዳቸው ለሌላ አግልግሎት ወደ ማዘጋጃ ቤት ሲሄዱ ነው።

“ስለዚህ የንብረት ግብር የለም ማለት አይቻልም። ነገር ግን በጣም የቆየ ስለሆነ ለዘመናዊው የግብር ሂደትን የሚመጥን አይደለም።”

ረዳት ፕሮፌሰር ጥላሁን መለስ ብለው ‘ትራንሳክሽናል’ ስላሉት የግብር ዓይነት ሲያስረዱ፣ ይህ የንብረት ግብር ዓይነት አንድ ግለሰብ ንብረት ሲሸጥ እና ሲለውጥ ለመንግሥት የሚከፍለው ግብር ነው። ይህ የሚከፈለው ግብር በእንግሊዝኛው ‘ስታምፕ ዱቲ’ (ቴምብር) ይባላል።

የንብረት ግብር የማያስከፍሉ አገራት ‘ስታምፕ ታክስ’ የተሰኘ አንድ ግለሰብ ንብረት ሲገዛ አሊያም ሲሸጥ ለመንግሥት የሚከፍለው ግብር አላቸው።

ኢትዮጵያ ውስጥ ለምሳሌ አንድ ሰው ቤት ሲሸጥ ሁለት በመቶ ግብር የመክፈል ግዴታ አለበት። “አንዳንድ ከተሞች ደግሞ ‘ሰርቪስ ቻርጅ’ ብለው ይቆርጣሉ። ለምሳሌ አዲስ አበባ 4 በመቶ ሌሎች ከተሞች ደግሞ 3 በመቶ ይቆርጣሉ።”

ነገር ግን ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ግለሰብ ምን ዓይነት ንብረት ሲኖረው፤ የትኛው ግብር ይጣልበታል የሚለው አከራካሪ እንደሆነ ምሑሩ ያነሳሉ።

ለዚህ ዋነኛው ምክንያት ይላሉ ጥላሁን “የቤት ባለቤት የሆነ፣ ሕንፃ ያለው፣ የሰርቪስ ሕንፃ ያለው. . . ይህንን ለይቶ ያስቀመጠ የግብር ሕግ አለመኖሩ” ነው።

መምህሩ በ2010/11 ዓ.ም. ድሬዳዋ፣ ባሕር ዳር እና መቀለ ላይ አተኩረው ስለንብረት ግብር ጥናት ሠርተዋል። በጥናታቸው ካስተዋሉት አንደኛው ጉዳይ የኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት ስለ ንብረት ግብር ግልፅ የሆነ አንቀፅ እንደሌለው ነው።

በጥናታቸው ማጠቃለያ “ለፌዴራል አሊያም ለክልሎች ተለይቶ የተሰጠ ግብር ስለሌለ የፌዴሬሽን እና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶች በጋራ መወሰን አለባቸው” የሚል ምክረ-ሐሳብ አቅርበዋል።

‘በአዲስ መልክ’ የመጣው የንብረት ግብር

ባለፈው ግንቦት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከአዲስ አበባ ከተማ ካቢኔ አባላት ጋር በነበራቸው ውይይት “ከተወሰነ የገንዘብ መጠን በላይ” የሚያወጡ ሕንፃዎች የንብረት ግብር እንዲከፍሉ የሚል ሐሳብ አንስተው ነበር።

ረዳት ፕሮፌሰር ጥላሁን እንደሚሉት የንብረት ግብር ጉዳይ ውይይት ሲደረግበት ከስምንት ዓመታት በላይ ፈጅቷል።

አሁን የፌዴሬሽን እና የሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት አባላት በጋራ ተወያይተው የንብረት ግብር ‘በአዲስ መልክ’ የሕግ ማዕቀፍ እንዲዘጋጅለት ውይይት ማድረጋቸው “ትልቅ እርምጃ” ነው ይላሉ።

ቢሆንም የንብረት ግብር በውስጡ በጣም የተወሳሰቡ ሐሳቦችን ስለያዘ በጥንቃቄ እንዲታይ የሚል ምክር አላቸው።

“ለምሳሌ መሬቱ ነው፣ ሕንፃው ነው ግብር የሚከፈልበት? መሬቱን ብቻ ነው ዋጋ የምናወጣለት ወይስ ከቤቱ ጋር? ምን ያህል ዋጋ ሲኖረው ነው ግብር የሚጣልበት? ይህ መመለስ አለበት።”

አክለው ሌላኛው ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ የሊዝ ሥርዓት እና የንብረት ግብር እንዴት አብረው ሊሄዱ ይችላሉ? የሚለው እንደሆነ ያነሳሉ።

የምክር ቤቶቹ አባላት ስለንብረት ግብር ውይይት ባደረጉበት ወቅት ከተነሱ ጥያቄዎች መካከል አንደኛው ዜጎች ሁለት ጊዜ ግብር ይከፍላሉ (ደብል ታክሴሽን) የሚል ነው።

“ዜጎች ግብር ከፍለው ከሚወስዱት ደመወዝ ቆጥበው በሠሩት ቤት ግብር ሊከፍሉ አይገባም” የሚል ሐሳብ ከምክር ቤት አባላት ተነስቷል።

ረዳት ፕሮፌሰር ጥላሁን “ደብል ታክሴሽን” ምን እንደሆነ አስረድተው ከላይ የተጠቀሰው ሐሳብ “የተሳሳተ እንደሆነ” ይናገራሉ።

እንደ ምሑሩ አንድ ሰው በተመሳሳይ ልውውጥ (ትራንሳክሽን) ሁለቴ እና ከዚያ በላይ ግብር ሲከፍል “ደብል ታክሴሽን” ይባላል።

“ለምሳሌ አንድ ሰው ደመወዝ ሲከፈለው የፌዴራል መንግሥት ታክስ አድርጎት ለመሥሪያ ቤት ሰጥቶ እንደገ እና ታክስ ቢደረግ ደብል ታክሴሽን እንለዋለን።”

እሳቸው እንደሚሉት ንብረት “ብቻውን የቆመ የገቢ ምንጭ” ነው። “ገቢው ወደ ብር ተቀየረ አልተቀየረ ሌላ ጉዳይ ነው።”

ኢትዮጵያ ከየትኛው አገር ይህን ፖሊሲ መቅዳት አለባት? በሚል ርዕስ በቅርቡ አንድ ጥናት እንደሠሩ የሚናገሩት ረዳት ፕሮፌሰሩ በዚህ ጥናታቸው አራት አገራት መካተታቸውን ይጠቅሳሉ።

ታንዛኒያን፣ ደቡብ አፍሪካን፣ ጋናን እና ታይላንድን በቃኘው ጥናታቸው ረዳት ፕሮፌሰሩ እና የጥናት አጋሮቻቸው ኢትዮጵያ ከእነዚህ አገራት ልምድ ልትወሰድ ትችላለች የሚል ምክረ-ሐሳብ አቅርበዋል።

“ነገር ግን ከሁሉም ለኢትዮጵያ የተሻለ ቀረብ ያለ ነው ብለን ያልነው የታንዛኒያ ነው።”

አዲሱ ማዕቀፍ ሲወጣ ማኅበረሰባዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊ እና ፖለቲካዊ ዳራው መታየት እንዳለበትም ይመክራሉ። ለምሳሌ በርካታ አገራት ፖለቲካዊ ዳራውን አይተው ኤምባሲዎች እና ዓለም አቀፍ ተቋማትን ከንብረት ግብር ነፃ እንደሚያደርጉ ይጠቅሳሉ።

የንብረት ግብር በአግባቡ ከተተገበረ “ለከተሞች ትልቅ የገቢ ምንጭ ሊሆን ይችላል” የሚለው ሐሳብ እንዲዘነጋ ግን አይፈልጉም።