ለመጀመሪያ ጊዜ ጨረቃን ከረገጡት አንዱ በ93 ዓመታቸው ለአራተኛ ጊዜ ተሞሸሩ

የፎቶው ባለመብት, @TheRealBuzz
በታሪክ ጨረቃን ከረገጡ የመጀመሪያዎቹ ሰዎች መካከል አንዱ የሆኑት ታዋቂው የአሜሪካ የቀድሞ ጠፈረተኛ በዝ አልድሪን በ93 ዓመት የልደት በዓላቸው ዕለት ለአራተኛ ጊዜ ተሞሸሩ።
አልድሪን ወደ ህዋ ከተደረጉ ጉዞዎች መካከል በታሪካዊነቷ በቀዳሚነት በምተጠቀሰው አፖሎ 11 መንኩራኩር ወደ ጨረቃ ካቀኑት ጠፈረተኞች መካከል አንዱ ነበሩ።
በወቅቱ የተልዕኮው አዛዥ ከነበሩት ከኒል አርምስትሮንግ ጋር ወደ ጨረቃ ያመሩት በዝ አልድሪን የጨረቃን ገጽ በመርገጥ የመጀመሪያዎቹ ለመሆን በቅተዋል።
የ93 ዓመቱ የቀድሞው ፓይለት አልድሪን አንካ ፋውር ከተባሉት አዲሷ ሚስታቸው ጋር ጋብቻ ስለመፈጸማቸው ይፋ ባደረገበት ጊዜ “በአፍላ ጉርምስና ተያይዞ እንደመኮብለል ያህል ደስታ ተሰምቶኛል” ብለዋል።
አልድሪን በታሪክ በጨረቃ ላይ ከተራመዱ ሦስት ሰዎች መካከል በአሁኑ ጊዜ በሕይወት የሚገኙ ብቸኛው ግለሰብ ናቸው።
ሎስ አንጀለስ ውስጥ የፈጸሙትን የጋብቻ ሥነ ሥርዓታቸውን የሚያሳዩ ፎቶግራፎችን በትዊተር ገጻቸው ላይም አጋርተዋል።

የፎቶው ባለመብት, @THEREALBUZZ
“በሕይወት እንዳለ በአየር በረራ ታሪክ ስመጥር እንደሆነ ግለሰብ በ93ኛ ዓመት የልደት በዓሌ ዕለት ከረጅም ጊዜ ፍቅረኛዬ ከዶ/ር አንካ ፋውር ጋር የጋብቻ ቀለበት ማድረጌን ሳሳውቅ ክብር ይሰማኛል” ሲሉ ትዊተር ላይ አስፍረዋል።
የአልድሪን አጋር በመሆን ጋብቻቸውን የፈጸሙት የ63 ዓመቷ አዛውንት ዶ/ር ፋውር፣ የኬሚካል ምህንድስና ባለሙያ ናቸው። እንዲሁም ሚስት የባለቤታቸው ንብረት የሆነው ‘በዝ አልድሪን ቬንቸርስ’ የተባለው ተቋም ምክትል ሥራ አስፈጻሚ ናቸው።
ከዛሬ 50 ዓመታት በፊት ኒል አርምስትሮንግ እና በዝ አልድሪን በአፖሎ 11 ወደ ጨረቃ በመጓዝ ከሰው ልጅ ሁሉ ጨረቃን በመርገጥ የመጀመሪያዎቹ ሲሆኑ 600 ሚሊዮን የሚሆን ሕዝብ በቴሌቪዥን ተመልክቷቸዋል። ይህም በወቅቱ በታሪክ ከፍተኛ ቁጥር ባለው ሕዝብ የታየ ክስትት ሆኗል።
በዚህም ሳቢያ አልድሪን በወቅቱ በአንድ ጊዜ በምድር ላይ ዝነኛ ከሆኑት ሰዎች መካከል አንዱ ሆኑ። በተከታይ ወራትም በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ላይ በመቅረብ፣ በርካቶች ጋርም አብረው ፎቶ በመናሳት እና በተለያዩ መድረኮች ላይ ተናጋሪ በመሆን ዝናቸው ናኝቷል።
“ከዚያ በኋላ ያን ያህል ዝነኛ እሆናለሁ ብዬ አላሰብኩም ነበር” ሲሉ ከ20 ዓመታት በፊት ለሎስ አንጀለስ ታይምስ በሰጠው ቃለ ምልልስ ላይ ተናግረው፣ “በዚያ መጠን በሕዝብ ዐይን ውስጥ ለመግባት ዝግጁ ያልነበርኩ ከመሆኑ በተጨማሪ ምቾትም አልነበረኝም” ብለው ነበር።
አልድሪን ዝናን ካተረፈላቸው የጨረቃ ጉዞ ቀደም ሲል፣ በኮሪያ ጦርነት ወቅት ለአሜሪካ አየር ኃይል የተዋጊ ጀት አብራሪ ነበሩ።
በዝ አልድሪን ከአራት ዓመታት በፊት በ2018 (እአአ) ለትርፍ ያልተቋቋመ ምክር እና እውቀትን የሚያጋራ የባለሙያዎች ስብስብ የሆነ የህዋ ጉዳዮችን የሚመለከተውን ‘ስፔስፍላይት ኢኒስቲቲዩት’ መስርተዋል።












