መድኃኒት መግዣ ለሌላቸው ሰዎች ለዓመታት ገንዘብ በምስጢር ሲለግሱ የነበሩ ግለሰብ ታወቁ

የፎቶው ባለመብት, TANIA NIX
በአሜሪካ አላባማ ግዛት በምትገኘው ግራልዲን ከተማ የሚኖሩ ሰዎች አንድ ሺህም አይሞሉም። ሁሉም ሰው ስለ ጎረቤቱ ያውቃል። ኳስ አብረው ያያሉ።
አንድ ምስጢር ግን እስካሁን ማንም ሳይሰማው ቆይቷል። የከተማው ነዋሪዎች ላለፉት አሥርታት ሲረዳቸው የነበረ ‘ጠባቂ መልዓክ’ አላቸው።
ሆዲ ቺልደርስ ይባላሉ ግለሰቡ። ሙሉ ሕይወታቸውን በዚያው ከተማ በግብርና ነው ያሳለፉት።
ቤተሰቡ ‘ቀና፣ ፈጣሪን የሚወድ’ ሲል ይገልጻቸዋል።
ሰው ሲታመም ከጓሯቸው አትክልት ይልካሉ ‘እግዜር ይማራችሁ’ ብለው ፖስት ካርድም ይልካሉ።
ይሄን ሁሉ በጎ ሥራ ብዙዎች ቢያውቁም ሆዲ ከዚህም በላይ ለከተማዋ ነዋሪዎች ያደረጉትን ልገሳ ግን በምስጢር ነበር የያዙት።
ከአሥር ዓመታት በላይ በየወሩ መድኃኒት መግዣ ለሌላቸው ሰዎች 100 ዶላር ሲለግሱ ቆይተዋል።
በከተማው ለሚገኝ ፋርማሲ ነው ገንዘቡን የሚሰጡት። ወደ ፋርማሲው ሄደው የታዘዘላቸውን መድኃኒት ለመግዛት ገንዘብ የሌላቸው ሰዎች መድኃኒት እንዲያገኙ አስችለዋል።
ባለፉት ዓመታት ወደ 12,000 ዶላር ለግሰዋል። ገንዘቡን ሲሰጡ ‘ለማንም ሳትነግሩ በምስጢር ያዙልኝ’ ብለው ነው።
የዓመታት ምስጢር
ብሮክ ዋከር በከተማው ፋርማሲስት ናት።
“አጠገቤ መጥቶ መድኃኒት መግዛት የማይችል ሰው ይገጥምሻል? ሲለኝ አዎ አልኩት” ስትል ታስታውሳለች።
ከዚያም ብር ጠቅልለው ሰጧትና “መድኃኒት መግዛት የማይችል ሰው ሲያጋጥምሽ በዚህ ገንዘብ ሸፍኚ። ገንዘቡን ማን እንደሰጠሽ እንዳትናገሪ። መድኃኒት ለማን እንደገዛሽም ለእኔ እንዳትነግሪኝ። የፈጣሪ ስጦታ ነው ብቻ በያቸው” አሏል።
የዚያኑ ቀን መድኃኒት መግዛት ላልቻለ ሰው በሆዲ ልገሳ መድኃኒት ሸጠች። ደውላም አመሰገነቻቸው። ልገሳው አንድ ጊዜ ብቻ የሚያደርጉት መስሏት ነበር። እሳቸው ግን በየወሩ ለአሥር ዓመታት ቀጠሉበት።
“ለአሥር ዓመታት በየወሩ ገንዘብ ሲሰጠኝ ለማንም እንዳትናገሪ ይለኝ ነበር” ትላለች።

የፎቶው ባለመብት, TANIA NIX
ሕይወት የታደገ ደግነት
ሆዲ የጤና እክል ሲገጥማቸው ከቤት መውጣት ተሳናቸው። ልጃቸው ታኒያ ኒክስ ምስጢራቸውን ያወቀችው በዚህ ወቅት ነበር።
አባቷ ከቤት መውጣት ስላልቻሉ በየወሩ ለፋርማሲው የሚሰጡትን ገንዘብ እንድታደርስላቸው ጠየቋት።
“በሕይወት እስካለሁ ድረስ በየወሩ ፋርማሲ እየሄድሽ 100 ዶላር ስጪልኝ አለኝ” ስትል ታስታውሳለች።
አባቷ የቀድሞ አየር ኃይል ባልደረባ የነበሩ እና ሃይማኖተኛም ስለሆኑ በጎ ድርጊት መፈጸማቸው አላስደነቃትም።
አባቷ ለማኅበረሰቡ እና ለአገራቸው እንደሚቆረቆሩ እንዲሁም ሰዎችን ከመርዳት ወደኋላ እንደማይሉ ትናገራለች።
ሆዲ በ80 ዓመታቸው ባለፈው ታኅሣሥ ወር ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።

የፎቶው ባለመብት, TANIA NIX
ልጃቸው ታኒያ የአባቷን ምስጢር ማጋራቷ ድብልቅ ስሜት ነው የፈጠረባት።
በቀብር ሥነ ሥርዓታቸው ላይ ነበር ይህንን ታሪክ የተናገረችው።
አንድ የከተማው ነዋሪ ልጇ ኤፒ-ፔን ታዞለት ቤተሰቡ 600 ዶላር አጥቶ አጣብቂኝ ውስጥ ሲገባ፣ የሆዲ ልገሳ የልጃቸውን ሕይወት እንዳዳነው ተናግራለች።
የታኒያ አባት ደግነት በከተማውና በመገናኛ ብዙኃን ለመሰማት ጊዜ አልወሰደበትም።
ዋሽንግተን ፖስት ላይ ዘገባው ከወጣ በኋላ ከመላው አሜሪካ ሰዎች ወደ ከተማው ፋርማሲ እየደወሉ እርዳታውን ለመቀጠል ጠይቀዋል።
ታኒያ እንደምትለው መከፋፈል በበዛበት ወቅት የአባቷ ደግነት በማኅበረሰቡ ዘንድ መቀራረብ የሚፈጥር ነው።
“ሰዎች ስለ ሌሎች ሰዎች ግድ እንደሚሰጣቸው ተስፋ የሰጠ ነው” ብላለች።












