“ከሃጥያት እና ከወንጀል በስተቀር ሁሉንም ዓይነት ሥራ ለመስራት ዝግጁ ነኝ”

ደንሳ ጫማ ስትጠርግ

የፎቶው ባለመብት, Densa

ደንሳ ታዲ በቦረና ዞን ያቤሎ ወረዳ፣ የያቤሎ ከተማ ነዋሪ ነች።

በማታው ትምህርት ክፍል የ12ኛ ክፍል ተማሪ የሆነችው ደንሳ ራሷን ለማስተማር ያገኘችውን ትሰራለች።

“የቦረና ወጣቶች ጫማ አይጠርጉም” ትላለች ስለ አካባቢዋ ወጣቶች የሥራ ባህል ስትናገር።

በአካባቢው ሴት ሆና ጫማ የምትጠርግ እርሷ ብቻ መሆኗን ለቢቢሲ ገልጻለች።

ደንሳ ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ክፍል ድረስ የተማረችው በዱቡሉቅ ሲሆን፣ ከሰባተኛ እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ ደግሞ ያቤሎ ነው።

ቦረና ተወልደው ያደጉ ወጣቶች “ጫማ አይጠርጉም፣ ጋሪ አይነዱም፣ ፀጉርም አይቆርጡም” የምትለው ደንሳ፣ እርሷ ግን የቤተሰቦቿ አቅም ደከም ሲል፣ ከትምህርቷ እንዳትስተጓጎል ገንዘብ ይገኝበታል ያለችውን ሥራ ጀመረች።

ከአርብቶ አደር ወላጆች የተገኘችው ደንሳ፣ ድርቅ ደጋግሞ የቤተሰቦቿን ጥሪት ሲበትን መፍትሔ በፍጥነት አበጀች።

ቤተሶቿ የነበሯቸው ከብቶች በድርቁ ምክንያት ቁጥራቸው ሲመናመን፣ የዘሩት ከመሬት ብቅ ሳይል ሲቀር ራሷን እየሰራች ለማስተማር እና ቤተሰቦቿን ለመደገፍ ወሰነች።

በአቅራቢያዋ ያገኘችው እና ብዙ ተፎካካሪ የሌለው ሥራ ደግሞ ጫማ መጥረግ ብቻ ነበር።

 “ከሃጥያት እና ከወንጀል በስተቀር ሁሉንም ዓይነት ሥራ ለመስራት ዝግጁ ነኝ” የምትለው ደንሳ ጫማ መጥረግን ለመማር በአቅራቢያዋ በዚህ ሥራ የሚተዳደሩ ታዳጊዎች ጋር ጎራ ብላ መመልከት ነበረባት።

ደንሳ ዛሬ ብቻ አይደለም። የመጀመርያ ደረጃ ተማሪ ሳለችም ቤተሰቦቿን ለመደጎም ወደ ጎዳና ወጥታ ጥቃቅን ሥራዎችን ትሰራ ነበር።

ከአንደኛ ክፍል እስከ ስድስተኛ ክፍል በዱቡሉቅ ከተማ በምትማርበት ወቅትም ሸንኮራ፣ እሸት፣ ቡና እና ሻይ እየሸጠች እራሷን ስትረዳ ነበር።

ስለዚህም ዛሬ ጎዳና የሊስትሮ እቃ ይዞ ወጥቶ ጫማ መጥረግ አልከበዳትም።

እርግጥ ነው የአካባቢው ማኅበረሰብ፣ ከእነርሱ ቀዬ የተገኘችው ደንሳ ጫማ መጥረግ መጀመሯ አስደንቋቸው የተወሰኑ ቃላት ሰንዝረውባት ያውቃሉ።

ያ ግን ለደንሳ ሞራሏን ከመስበር ይልቅ ስለ ሥራ ክቡርነት ደጋግማ የምትናገርበት አጋጣሚ ነው የፈጠረላት።

ይህች ተማሪ እንደምትለው በቦረና ውስጥ ወንድ ሆኖ የሰውን ጫማ የሚያጸዱ እምብዛም የሉም።

“ይህ ነገር ሥራ መሆኑንም የሚያውቅ ሰው የለም። ሊሰራው ወስኖ የሚገባበትም የለም። ይንቁታል። እኔንም የተለየ ሥራ ትሰርያለሽ ብለው ያደነቃሉ።”

የሚያበረታታት ብዙ ቢሆንም፣ በምትሰራው ሥራ የማይደሰቱ የቤተሰብ አባላት እንዳሉ ትናገራለች።

“ምን ሆነሽ ነው ይህን ዓይነት ሥራ ወደ መስራት የገባሽው? ከቸገረሽ ለምን አትነግሪንም ነበር ይሉኛል። ብዙ ሰዎች ደግሞ ያበረታቱኛል” ትለላች።

ምክንያት የሆናት የዘጠነኛ ክፍል ገጠመኝ

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ወጣት ደንሳ ታዲ፣ ዘጠነኛ ክፍል ሳለች መምህሯ የጠየቋት ጥያቄ እና የተናገሩት ንግግር በዓላማዋ እንድትበረታ እንዳደረጋት ትናገራለች።

“አስተማሪዬ ‘ለኢትዮጵያ እድገት እንቅፋት ምንድን ነው?’ ብሎ ጠየቀኝ። ኢትዮጵያ ውስጥ ሰዎች ሥራ ይንቃሉ ብዬ መለስኩለት” ትላለች የነበራቸውን ምልልስ ስታስታውስ።

መምህሯ ነገሯን በምሳሌ እንድታስረዳ ተጨማሪ ዕድል ሰጣት። እርሷም በአካባቢዋ የታዘበችውን እየዘረዘረች አስቀመጠች።

የአካባቢዋ ወጣቶች ዝቅ ብለው ጫማ መትረግ አይፈልጉም። ጋሪ አይነዱም፣ ጥቃቅን ንግድ ውስጥ መሰማራት አይፈልጉም።

ይህንን ታዝባለች፤ መምህሯም ታድያ “አንቺ ጫማ ትጠርጊያለሽ?” ሲል አንደጠየቃት ታስታውሳለች።

ጥያቄው ቀልድም፣ ቁም ነገርም ይዟል።

“አዎን አፀዳለሁ ብዬ ስመልስ ተማሪዎች በጣም ሳቁብኝ። ይሁን እንጂ እኔ በእነርሱ ሳቅ ከዓላማዬ ወደኋላ አልተመለስኩም። ከዚያን ቀን ጀምሮም የሚያስፍለጉኝን እቃዎች ማሟላት ጀመርኩኝ” ትላለች።

ይህ ግን ለዳንሳ ቀላል ውሳኔ አይደለም። የሚያውቋት ተዘባበቱባት። ነገዋን እያሳዩ ዛሬ ላይ የወሰነቸው ውሳኔ ምን ያህል ጎዶሎ አንደሆኑ በመጥቀስ ተሳለቁባት።

“አንዳንድ ሰዎች አንቺ ትልቅ ቦታ ለመድረስ የምትጠበቂ ነሽ። እንዴት ወደ ታች ተመለስሰሽ እንዲህ ዓይነት ሥራ ትሰርያለሽ በማለት ወደ ኋላ ሊመልሱኝ ሞክረዋል” ትላለች።

“እኔ ጠንካራ አቋም አለኝ ብዬ አምናለሁ። የምሰራውም ሥራ የማኅበረሰቡ ወግ እና ልማድን የሚተላላፍ እስካልሆነ ድረስ ያንን ከመስራት ወደኋላ አልመለስም።”

“ሰዎች በሁሉም ሁኔታ ውስጥ አስተያየት ከመስጠት ወደ ኋላ አይሉም” የምትለው ደንሳ ለዚህም “ዕቅዴን የሚገነባልኝን አስተያየት በመውሰድ ሞራል የሚያወርደውን ደግሞ በመገንዘብ ትቼው ማለፍ ነበረብኝ” ትላለች።

ደንሳ ጫማ መጥረግ ከጀመረች በኋላ ግን በርካታ ደንበኞችን አፈራች።

የ12ኛ ክፍል ማጠቃለያ ፈተና ተፈትና ውጤቷን እየተጠባበቀች የምትገኘው ደንሳ ከሥራዋ በሚተርፋት ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት እየተማረች መሆኑን ለቢቢሲ ገልጻለች።

ሥራ ለመፈለግ ሳይሆን ሥራዬን ማጠናከር እፈልጋለሁ

ደንሳ ወደፊትም ቢሆን ተቀጥሮ መስራት የሚል ነገርን ማሰብ አትፈልግም።

ሁሌም አዳዲስ ሥራ ፈጥሮ ከራስ አልፎ ለሌሎች ድጋፍ መሆን እቅዷ ነው።

“ትምህርት ለሁሉም ነገር አስፈላጊ ነው። እኔ ግን አንድም ቀን የመንግሥት መሥርያ ቤት ተቀጥሬ እሰራለሁ ብዬ አስቤ አላውቅም። ተቸግሬ መቅረት አልፈልግም። ትልቅ ራዕይ አለኝ” ትላለች።

ከልጅነቷ ጀምሮ ያለፈችበት የሥራ ባሕል በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ የራሷን ሥራ መጀመር እንደምትችል ልምድ እና በራስ መተማማን እንደፈጠረላት ትናገራለች።

ይህች ተማሪ ጫማ መጥረግ ከጀመረች በኋላ የመንግሥት ባለሥልጣናት እንዲሁም ደንበኞቿ ጨምሮ እየደገፏት እንደሆነ ትናገራለች።

“የከተማዋ ከንቲባ እንኳ እኔ ጋር መጥቶ ነበር። የሚያስፈልግሽን ነገር ሁሉ እናሟላልሻለን ብለውኛል። 10ሺህ ብር እና የመሥርያ ቦታ እንደሚሰጡኝ ቃል ገብተውልኝ ነው የሄዱት። ሌሎች ብዙ ሰዎችም አብረንሽ ነው ያለነው በማለት ብዙ አበረታተውኛል” ትላለች።

ተማሪ ደንሳ ታዲ ውጤት ከመጣላት ዩኒቨርስቲ በመግባት ‘ሊደርሺፕ’ መማር እንደምትፈልግ ትናገራለች።