የወረቀት ገንዘብ መጠቀም እናቆም ይሆን?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በኬንያ ማስቲካ ገዝቶ ለማላመጥ የወረቀት ገንዘብ አልያም ሳንቲም መያዝ ግድ አይደለም።
በአገሪቱ ሕዝብ ዘንድ በስፋት ተገልጋይ ያለው የሳፋሪኮሙ ‘ኤምፔሳ’ [የሞባይል ገንዘብ ዝውውር ዘዴ] ተጠቃሚ ከሆኑ ነገሩ ቀላል ነው።
በኬንያ ገንዘብ በሞባይል መላክ እና መቀበል የተጀመረው እኤአ በ2007 ነው።
በሞባይል የክፍያ ሥርዓት ሳፋሪኮም ኤምፔሳን መጀመሩን ተከትሎ ኬንያ ከአፍሪካ ቀዳሚ ናት።
በቻይናም ቢሆን አሊፔይ የተሰኘ የሞባይል ገንዘብ ክፍያ መተግበሪያ ተጠቃሚዎች ቁጥር 1 ቢሊዮን ያለፈው እኤአ በ2020 ነበር።
ከጊዜ ወደ ጊዜ ሲታይ፣ ዓለማችን የወረቀት ገንዘብን የሚተኩ አማራጮችን እያስተዋወቀች ነው።
ምንም እንኳ ኢትዮጵያ ዘግይታም ቢሆን ‘ቴሌብር’ን በኢትዮቴሌኮም ብታስተዋውቅም በአጭር ጊዜ 27.2 ሚሊዮን ደንበኞችን ማፍራቱን በቅርቡ ድርጅቱ ይፋ ያደረገው መረጃ ያሳያል።
እነዚህ 27 ሚሊዮን ተጠቃሚዎች ደግሞ በተንቀሳቃሽ ስልካቸው 166.1 ቢሊዮን ብሮችን አዘዋውረዋል።
ከድርጅቱ የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው ከሆነ ከባንክ ወደ ቴሌ ብር፣ ከቴሌ ብር ወደ ባንክ የሚደረገውን የገንዘብ ዝውውር ለማቀላጠፍ 15 ባንኮች ይሳተፋሉ።
ይህ ቁጥር በየጊዜው የሚያድግ ነው።
የተለያዩ የመንግሥት ተቋማትም የቴሌብር ተጠቃሚ በመሆን የክፍያ ሥርዓታቸውን አዘምነዋል።
ለማንኛውም ገንዘብ ነክ አገልግሎት ወደ ባንክ ከመሮጥ ይልቅ በኪስ ወዳለው ሞባይል መመልከት መፍትሄ እየሆነ ነው።
ይህንን ኢትዮጵያም ሆነች የቀሪው ዓለም አገራት እየሄዱበት ያለውን ለሚታዘብ በቅርቡ የወረቀት ገንዘብ መጠቀም እናቆም ይሆን? ብሎ መጠየቁ አይቀርም።
ባንኮችን ለመተካት የሚፍጭረጨሩት የቴሌኮም ኩባንያዎች
ባንኮች ቅርንጫፎቻቸውን የሚከፍቱት አዋጪነቱን አስልተው ነው።
ተቀማጭ ገንዘብ ላገኝ እችላለሁ? ተበዳሪስ? ወደ ውጭ እቃ የሚልክስ ይኖር ይሆን? የሚለው ባንኮች ቅርንጫፎቻቸውን ከመክፈታቸው በፊት የሚያነሷቸው ጥያቄዎች ናቸው።
ለዚህ ነው በአብዛኛው በከተሞች አካባቢ ባንኮች ተከማችተው የሚስተዋሉት።
የቴሌኮም ኩባንያዎች ደግሞ ሲምካርድ ያለው ደንበኛቸውን ሁሉ መያዝ እንደሚችሉ ታሳቢ በማድረግ የሞባይል ገንዘብ ዝውውር አገልግሎትን በስፋት እያስተዋወቁ ነው።
የኬንያው ሳፋሪኮም ‘ኤምፔሳ’ እንዲሁም የኢትዮጵያው ‘ቴሌብር’ ለዚህ ጥሩ ማሳያ ናቸው።
ለእነዚህ የቴሌኮም ኩባንያዎች አነስተኛ ሱቆች እንደ ባንክ ቅርንጫፍ ያገለግላሉ።
ገንዘብዎን ማስቀመጥ ይችላሉ። ወይም በተንቀሳቃሽ ስልክዎ አማካኝነት ገንዘብ መቀበል ይችላሉ። ለወዳጅ ዘመድዎ ገንዘብ ማስተላለፍም በጣም ቀላል ነው።
ይሄን ሁሉ ተግባር ለመፈጸም የሚያስፈልገው ደግሞ ተንቀሳቃሽ ስልክ ብቻ ነው። የበይነመረብ ወይም ኢንተርኔት አገልግሎት መኖርን አይጠይቅም።
የወረቀት ገንዘብ ይዞ መገኘት የግድ አይደለም። ከባንክዎ ወደ ተንቀሳቃሽ ስልክዎ፣ ከተንቀሳቃሽ ስልክዎ ወደ ባንክዎ ገንዘብ ማዘዋወር ዐይን ገልጦ የመክደን ያህል ቀሏል።
እነዚህ የቴሌኮም ኩባንያዎች ገንዘብ መክፈል እና መቀበል ከማስቻል አልፈው አነስተኛ ብድርም ያቀርባሉ።
የተመሰከረላቸው የሒሳብ አዋቂ የሆኑት አቶ ጥላሁን ግርማ ለረዥም ዓመታት በኢትዮጵያ ባንኮች ውስጥ በተለያየ ደረጃ አገልግለዋል።
አቶ ጥላሁን ይህን አነስተኛ ብድር የዕለት ተዕለት ሥራን ለማቀላጠፍ የሚበቃ እንጂ ትልቅ ኢንቨስትመንትን ለማስጀመር የሚውል አይደለም ይላሉ።
እነዚህ የቴሌኮም ኩባንያዎች የባንክ ሥራ ውስጥ የገቡት በርካታ ገንዘብ እጃቸው ላይ ስለሚገኝ መሆኑንም አክለው ያነሳሉ።
“በተለምዶ እነዚህ የቴሌኮም ካምፓኒዎች በጣም ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ አላቸው። . . . ይህንን ገንዘብ ባንክ ከማስቀመጥ ይልቅ መልሰው ለደንበኞቻቸው ቢያበድሩ የተሻለ የወለድ ምጣኔ እንደሚያገኙ ስለሚያውቁ ነው ይህንን ፕሮዳክት እያስተዋወቁ ያሉት።”
ይህ ግን ከባንክ አንጻር ሲታይ የተወሰነ የስጋት ደረጃ አለው ይላሉ አቶ ጥላሁን።
ባንኮች ከፍተኛ ዋጋ ያላቸውን ብድሮች ሲያበድሩ በዋስትና የሚይዙት ነገር ይጠይቃሉ።
በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ባንኮች የሚያበድሩት ማሽን፣ ቤት፣ መኪና፣ ሕንጻን የመሳሰሉ ቋሚ ንብረቶችን ይዘው ነው።
እነ ቴሌብር ይህንን ለማድረግ ስለማይችሉ ሊሰጡ የሚችሉት ብድር አነስተኛ መሆኑን አቶ ጥላሁን ያነሳሉ።
እነዚህ የቴሌ ኩባንያዎች የሚሰጡት ብድር የተጠቃሚዎችን የዕለት ፍጆታን ለማሟላት ወይንም አነስተኛ ንግድ ያላቸው ከሆነም ንግዳቸውን እንዲችሉ ለማድረግ መሆኑንም ያብራራሉ።
ስለዚህ እነዚህ የቴሌ ኩባንያዎች የጀመሯቸው የሞባይል ክፍያ አገልግሎቶች የባንክን ሚና ተክተው ይጫወታሉ ማለት እንደማይቻል ይገልጻሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሞባይል ገንዘብ ዝውውር ሙስናን ለመከላከል?
የኤሌክትሮኒክ የክፍያ ሥርዓቶች ማለትም የሞባይል ገንዘብ መክፈያ ሥርዓቶች፣ በካርድ ክፍያ መፈፀም ለተጠቃሚው ጥሬ ገንዘብ መሸከም ሳያስፈልገው ግብይትን በቀላሉ መፈፀም ያስችላሉ።
በተለይ ዓለም ወደ የበይነ መረብ (ኦንላየን) ግብይት ሥርዓት ሲሄድ፣ ተቋማት ምርታቸውን በድረገጾች ላይ ያቀርባሉ።
ተጠቃሚዎች የሚፈልጉትን ምርት መርጠው ሲገዙ ደንበኛውም ክፍያውን በኤሌክትሮኒክስ የክፍያ ሥርዓቶች በኩል መፈጸም ይችላል።
የፈለጉት ሱቅ ገብተው በኪስዎ ምንም ዓይነት ጥሬ ገንዘብ መያዝ ሳያስፈልግዎት የሚፈልጉትን እቃ ሸምተው በካርድዎ አልያም በሞባይል መክፈል መቻል የዘመናዊው ዓለም አንዱ ትሩፋት ነው።
በዚህም በዋናነት ጥሬ ገንዘብ ተሸክሞ የመንታፊዎች ሲሳይ ከመሆን መዳን ይቻላል።
በመቀጠል ደግሞ ሻጮችም ቢሆኑ ገቢያቸውን በሚገባ ማስተዳደር እንዲችሉ ዕድሉን ያመቻችላቸዋል።
የኤሌክትሮኒክስ የክፍያ ሥርዓት ሻጭንም ሆነ ገዢን ከስርቆት ታድጎ፣ የግብይት ምቹ ሁኔታን የመፍጠር ዕድል ይዟል።
የተመሰከረላቸው የሒሳብ አዋቂ የሆኑት አቶ ጥላሁን ግርማ፣ ደንበኞች ወደ ኢ-ባንኪንግ (ኤሌክትሮኒክ)፣ ወደ ካርድ ክፍያ በሚያደሉበት ወቅት መንግሥት የሕገወጥ ገንዘብ ዝውውርን፣ ሙስናን እና ሽብርተኛን የሚደግፉ ሰዎችን በቀላሉ ለመለየት ይረዳዋል ይላሉ።
“አብዛኛው ሰው ወደዚህ ሥርዓት ከገባ የሰዎች ገቢም ወጪም ተለይቶ ስለሚታወቅ የገንዘብ ምንጭን ለመከታተል ለመንግሥት ይጠቅመዋል።”
ኤምፔሳ በኬንያ ካስገኛቸው ጥቅሞች ሁሉ ሁለቱ ጎልተው ይነሳሉ።
ሙስና እና ዝርፊያ ማስወገድ።
ቴክኖሎጂው ሙስና እና ዝርፊያን ከመከላከሉም በላይ መንግሥት የታክስ ሄደቱን በሥርዓት እንዲቆጣጠርም ያደርገዋል።
ይሄም የኤምፔሳ አገልግሎት ቀጣዩ ትልቅ ጥቅም ሊሆን እንደሚችል ይታሰባል።
አቶ ጥላሁን በበኩላቸው የኤሌክትሮኒክስ ግብይት በአንድ አገር መለመድ በየዓመቱ መንግሥት ሚሊዮን ብሮችን ለማሳተም የሚያወጣውን “የገንዘብ ማሳተሚያ ወጪ” እንዲቀንስ ማስቻሉ መሆኑን ይጠቅሳሉ።
የጥሬ ገንዘብ ዝውውር በከፍተኛ ሁኔታ ሲቀንስ የወረቀት የገንዘብ ኖቶች ቶሎ አያረጁም የሚሉት ባለሙያው፣ “ቶሎ ቶሎ ያረጁ ብሮችን ለመተካት የሚወጣው ወጪ ስለሚቀንስ መንግሥት ከፍተኛ ተጠቃሚ ይሆናል” ይላሉ።
ትልልቅ ግብይቶች የሚፈፀሙት ከፍተኛ መጠን ባላቸው የወረቀት ገንዘብ አማካይነት መሆኑን የሚያነሱት አቶ ጥላሁን፣ እነዚህ ብሮች ሙስና ለሚፈጽሙም ሆነ ሐሰተኛ ብሮችን ለሚያትሙ ቀዳሚ ታላሚ ናቸው።
“የኤሌክትሮኒክስ ግብይት ሲኖር እነዚህን ኖቶች ከገበያ እየቀነሱ በመውጣት የፎርጀሪ እና የሙስና ወንጀሎችን መቀነስ የሚቻልበት ሁኔታ አለ።”
ሰዎች ወደ ኤሌክትሮኒክስ ግብይት ቢያመሩ፣ እነዚህን ከፍተኛ መጠን ያላቸውን ገንዘቦች ከገበያ በማውጣት ሙስናን እንዲሁም የሐሰተኛ ብሮችን ዝውውር በመቀነስ ረገድ ከፍ ያለ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው የሕንድን ምሳሌ በመጥቀስ ያስረዳሉ።
ሕንድ በአንድ ወቅት ገበያዋ ላይ በስፋት የሚዘዋወሩትን ባለ 500 እና ባለ 1000 ሩፒዎች [የሕንድ ገንዘብ] ሽብርተኝነትን ለመከላከል እንዲሁም፣ ሐሰተኛ ኖቶችን ለመቆጣጠር በሚል ከገበያው በማስወጣት ሰዎች ወደ ሞባይል ባንኪንግ እና የካርድ ክፍያ እንዲያተኩሩ ለማድረግ ሞክራ ነበር።
በዚህም አነስተኛ የገንዘብ ኖቶችን ተሸክሞ ትልልቅ ግብይቶችን ማድረግ አስቸጋሪ በመሆኑ፣ ሰዎች ወደ ባንክ እንዲመጡ እና የባንክ ሥርዓቱ ተጠቃሚዎች እንዲሆኑ ማድረግ መቻሉን ያወሳሉ።
ነገር ግን በሕንድ እነዚህ ትልልቅ የብር ኖቶች ተመልሰው ወደ ገበያው ሲገቡ ሰዎች ዳግም የወረቀት ገንዘብን ወደ መጠቀም ተመልሷ።
በኢትዮጵያም ቢሆን የሐሰተኛ ብር ኖቶችን የሚያትሙ ሰዎች ትኩረት ከፍተኛ መጠን ያላቸው ብሮች መሆኑን ያስታወሱት አቶ ጥላሁን፣ መንግሥት ይህንን ለመግታት የካርድ ክፍያ እና የሞባይል ባንኪንግ ላይ ቢሰራ ውጤታማ ሊሆን የሚችልበት ዕድል መኖሩን ይገልጻሉ።
ይህ የሕንድ ተሞክሮ ኢትዮጵያ ላይ ይሰራል ወይ የሚለው ግን ተጨባጭ ጥናት እንደሚፈልግ አቶ ጥላሁን ይጠቅሳሉ።
የኤሌክትሮኒክ የክፍያ ሥርዓቶችን ለመጠቀም ግን ማኅበረሰቡ ስለ ባንክ እና ኤሌክትሮኒክስ የክፍያ ዘዴዎች ያለው እውቀት የማይታለፍ ነጥብ መሆኑንም ያነሳሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ጥሬ ገንዘብን ከገበያ ለማስወገድ ይቻል ይሆን?
ኢትዮጵያ ውስጥ ዛሬም በሬ ለመግዛት ወደ ቁም ከብት ገበያ የሚሄድ ሸማች የወረቀት ገንዘብ ተሸክሞ ነው የሚሄደው።
የመርካቶ ተገበያዮችም ሆኑ የቦሌ የገበያ አዳራሽ ሸማቾች ጥሬ ገንዘብን እኩል ለግብይት ይጠቀማሉ።
በኢትዮጵያ የግብይት ሥርዓቱ ገና አልዘመነም። አቅርቦትም ቢሆን ዘመናዊነት የደረሰበት ላይ አልደረሰም።
ዛሬም መሃል አዲስ አበባ በጎች እና በሬዎች እየተነዱ ወደ ገበያ ይሄዳሉ።
ስለዚህ በኢትዮጵያ ጥሬ ገንዘብን ትቶ የሞባይል ክፍያ ሥርዓትን የሚጠቀም ማኅበረሰብ ለመገንባት በርካታ ጉዳዮች ከግምት አንደሚገቡ አቶ ጥላሁን ያነሳሉ።
ኢትዮጵያ ውስጥ ዛሬም ድረስ ወደ ባንክ የሚሄደቀው ሕዝብ ቁጥር አገሪቱ ካላት አጠቃላይ የሕዝብ ብዛት አንጻር ሲታይ አነስተኛ ነው።
ባንኮች በስፋት የሚገኙት እንዲሁም የአገሪቱ ምጣኔ ሀብትም በስፋት የሚዘወረው በከተሞች ነው።
የኢትዮጵያ ባንኮች ከብሔራዊ ባንክ በወጣ መመርያ መመሰረት ተገድደው ወደ ክልል ትንንሽ ከተሞች ቅርንጫፎቻቸውን በማስፋታቸው የባንክ ተደራሽነት እየጨመረ ቢመጣም፣ አሁንም ከባንክ ውጪ የሆነው ማኅበረሰብ ብዙ መሆኑን አቶ ጥላሁን ያነሳሉ።
እነዚህን ጉዳዮች በቅርበት ለሚከታተል የኢትዮጵያ ሸማች ከገንዘብ ንክኪ ነጻ የሆነ ግብይት ውስጥ በቅርቡ ጠቅልሎ ይገባል ብሎ መናገር አስቸጋሪ ነው።
አቶ ጥላሁን እድሜያቸው እስከ 25 የሆናቸው ወጣቶች ኢኮኖሚው እነርሱን ታሳቢ አድርጎ ስለሚሄድ ወደፊት ጥሬ ገንዘብን ትተው በሞባይል እና በካርድ የክፍያ ሥርዓቶች መጠቀም ይጀምራሉ የሚል ተስፋ እንዳላቸው በማንሳት “አሁን ግን ያ ሩቅ” እነደሆነ ይናገራሉ።
“የካሽ ዝውውር በጣም በከፍተኛ ሁኔታ እየቀነሰ ይመጣል? አዎ፤ ነገር ግን ‘ካሽለስ’ ኢኮኖሚ በአጭር ዓመታት ውስጥ ይፈጠራል የሚል እምነት የለኝም።”
በከተሞች የጥሬ ገንዘብ አስፈላጊነት ከጊዜ ወደጊዜ እየቀነሰ እንደሚመጣ ግን መናገር ይቻላል የሚሉት አቶ ጥላሁን፣ በሞባይሉ ገንዘብ ክፍያ መፈፀም መቻሉ፣ ወደ ባንክ የመሄድ ፍላጎቱ ከዕለት ዕለት መቀነሱ መልካም ጅማሮ መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል።
ከፍተኛ የሆነ የምጣኔ ሃብት ዝውውር ባለበት ከተማ የገንዘብ የዝውውር መጠን እየቀነሰ ከመጣ አንድምታው ከፍተኛ መሆኑንም ይናገራሉ።
ይህ ደግሞ የውጭ ባንኮች ወደ አገር ውስጥ ሲገቡ ይዘዋቸው የሚመጡት አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ጥሬ ገንዘብ የመጠቀምን ሂደት ለማስቀረት በማገዝ ረገድ የድርሻቸውን ሊወጡ ይችላሉ ሲሉ ተስፋቸውን ይናገራሉ።












