የኢትዮጵያን የክፍያ ስርዓት ለማዘመን የሚጥሩት ወጣቶች

የፎቶው ባለመብት, Chapa Technologies
የኮቪድ ወረርሽኝ በዓለም ላይ ተከስቶ በርካታ ሁነቶችን ከስር መሰረቱ በቀየረበት ወቅት የአገሪቱን የፋይናንስ ዘርፍ የሚመራው እና የሚቆጣጠረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክም አዲስ መመሪያ ይፋ አደረገ።
ይህም መመሪያ ከባንክ ውጪ ያሉ ድርጅቶች ዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት መስጠት የሚችሉበት ነው።
በዚህም መሰረት ለባንኮች ብቻ ይፈቀድ የነበረውን የዲጂታል ባንክ አገልግሎት፣ ባንክ ላልሆኑ ለአገር ውስጥ የክፍያ መፈጸሚያ ሰነድ እና ለክፍያ ሥርዓት ኦፕሬተሮች ፍቃድ መስጠት አስችሏል።
ይህ ለባንኮች ብቻ ይፈቀድ የነበረው የዲጂታል ባንክ አገልግሎትን ባንክ ያልሆኑ ኦፕሬተሮችም በዘርፉ ላይ መሰማራት እንደሚችሉ የተረዱት ናኤል ኃይለማርያም እና እስራኤል ጎይቶም ይህንን እድል ለመጠቀም በማሰብ መንቀሳቀስ ጀመሩ።
ቻፓ ፋይናንሻል ቴክኖሎጂስ አክሲዮን ማህበር፣ ቻፓ፣ በአገር ውስጥ የፋይናንስ ስርዓቱን ለማቀላጠፍ አልመው ፈቃድ ካገኙ ባንክ ነክ ካልሆኑ ተቋማት መካከል አንዱ ነው።
ቻፓ ፊንቴክ (Fintech) ከሚባለው እና በፍጥነት እያደገ ካለ የፋይናንስ ዘርፍ የሚመደብ ነው።
በአጭሩ ፊንቴክ ማለት፣ የገንዘብ ቴክኖሎጂዎችን፣ሰው ሠራሽ ልኅቀትን (አርተፊሻል ኢንተለጀንስ)፣ ብሎክ ቼይን፣ ክላውድ ኮምፒውቲንግን እና ዳታን በመጠቀም የፋይናንስ ስርዓቱን ለማዘመን የሚሰራ ነው።
የቻፓ መስራች የሆኑት ናኤል ኃይለማርያም እና እስራኤል ጎይቶም የተገናኙት በቻይና ዩኒቨርስቲ ውስጥ በሚማሩበት ወቅት ነው።
ናኤል በዳታ ሳይንስ እና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሁለተኛ ዲግሪውን ሲሰራ፣ እስራኤል ደግሞ ፊዚክስ፣ ማይክሮ ኤሌክትሪክ ሳይንስ እና ኢንጂነሪንግ በማጥናት ሰው ሠራሽ ልኅቀት (አርቴፍሻል ኢንተለጀንስ)ላይ የምርምር ስራ እያካሄደ ነበር።
ናኤል ስለ ድርጅታቸው ዓላማ ሲገልጽ “በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ስራ ፈጣሪዎችን እና ቢዝነሶችን ማበረታታት እንዲሁም ከዓለም አቀፉ ኢኮኖሚ ጋር ማስተሳሰር ነው” ይላል
ቻፓ የኦንላይን (በበይነ መረብ የሚደረግ) ክፍያን በቀላል መንገድ፣ ለቢዝነሶች እንዲከፈል የሚያስችል ስርዓት ነው።
ቻፓን የሚጠቀሙ ሰዎች በኦንላይን ከየትኛውም ባንክ ክፍያ መቀበል እንዲችሉ ተደርጎ መሰራቱን መስራቾቹ ይናገራሉ።
ከአገር ውስጥ ባንኮች ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ካሉ የየትኛውም የገንዘብ አስተላላፊዎች እና ባንኮች በኦንላይን ክፍያ መቀበል ያስችላል።
ዲጂታል ፋይናንስ በኢትዮጵያ በጅምር ደረጃ ላይ ቢሆንም የክፍያ አገልግሎትን ለሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል በቀላሉ፣ በአነስተኛ ወጪ እና በጊዜ እንዲሁም አስተማማኝ በሆነ መልኩ በማድረስ፣ የፋይናንስ አገልግሎት ተጠቃሚዎችን ፍላጎት በመጨመር የፋይናንስ ዘርፉን ዓለም አቀፍ ውድድር ውስጥ ለማስገባት መታቀዱን ብሔራዊ ባንክ በአንድ ወቅት ተናግሮ ነበር።
ብሔራዊ ባንክ የአገሪቱን የክፍያ ስርዓት በተመለከተ በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር 2011 የብሔራዊ ሲስተም አዋጅ በማውጣትና በተግባር በማዋል በሁሉም ባንኮች ደንበኞች አማካኝነት ከአንዱ ባንክ ወደ ሌላ ባንክ የሚደረጉትን የክፍያ ትዕዛዞች ወድያውኑ ክፍያው እንዲፈጸም የሚስችል ሥርዓት ዘርግቶ እያስተዳደረ ይገኛል።
ቻፓ እንዴት ተመሰረተ?
ናኤል እና እስራኤል በተለያዩ የአውሮፓ አገራት ለትምህርት እና ለስራ ተጉዘዋል።
“ሁሌም ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣ ዲጂታል ሴክተሩ ደካማ መሆኑን እናስተውላለን። ይህ ደግሞ ሰዎች የፈጠራ እውቀታቸው በማነሱ ወይንም ደግሞ ዲጂታል ፕላትፎርሞች [መድረኮች] ስለሌሉ አይደለም። ነገር ግን በኦንላይን ክፍያ ለመፈፀም የሚያስችል ስርዓት አለመዘርጋቱ ነበር ችግሩ።” ይላል።
በአውሮፓ አገራት ክፍያ ለመፈፀም ሰዎች ስልካቸውን አልያም የባንክ ካርዳቸውን መጠቀም ሲመርጡ በኢትዮጵያ ግን አሁንም ወረቀት ገንዘብን ወይም ሳንቲም ተሸክሞ መንቀሳቀስ አልቀረም።
እስራኤል ብሔራዊ ባንክ ይህንን መመርያ ከማውጣቱ በፊት ራሱ እንዴት አድርጎ ክፍያዎችን በኦንላይን መክፈል እንደሚቻል ያስብ ነበር።
የዲጂታል ክፍያ አገልግሎት በአጠቃላይ ከግለሰብ ጀምሮ እስከ መንግሥት በተለይም በፋይናንስ ዘርፍ ውስጥ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው።
“ብሔራዊ ባንክ መመርያውን ይፋ ባደረገበት ወቅት ሁለታችንም ኢትዮጵያ ነበርን። ስለዚህም የረዥም ግዜ እቅዳችንን ለማሳካት ይህንን እድል ተጠቀምንበት” በማለት የአመሰራረቱን ሂደት ያስረዳል።

የፎቶው ባለመብት, Chapa Technologies
ስርዓቱ የሚሰራው እንዴት ነው?
በኢትዮጵያ ውስጥ መንግሥታዊም ሆኑ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ምርትና አገልግሎታቸውን ለአገር ውስጥ ወይንም ባህር ማዶ ለሚገኙ ደንበኞቻቸው ሸጠው ክፍያ መቀበል በቀላሉ የሚታሰብ ነገር አይደለም።
በይበልጥ ደግሞ አገልግሎቱን በኦንላይን ማግኘት አስቸጋሪ ነው። ይህ ቻፓ ፋይናንሻል ቴክኖሎጂስ የዘረጋው ስርዓት ይህንን ለማቃለል የተሰራ ነው ነው።
ናኤል በበኩሉ በአገር ውስጥ ከአንድ ወገን በኦንላይን የተፈፀመን ክፍያ ገንዘብ ማውጣት ራሱ ውስብሰብ መሆኑን ይናገራል።
“በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኝ ቢዝነስ በኦንላየን ክፍያ መቀበል ከፈለገ ኢንሳን ጨምሮ በርካታ ስፍራዎች መርገጥ ይጠበቅበታል።”
አክሎም “እኛ ይህንን ስርዓት በአንድ ነው ያቀናጀነው” ብሏል።
የኦንላይን ክፍያዎች ከአገር ውጪ የሚፈፀሙትን ክፍያዎች ብቻ ሳይሆን የአገር ውስጥ ክፍያዎችንም ያካትታል።
“በአነስተኛ ንግድ ላይ የተሰማሩ በአገር ውስጥ አንዲሁም ከአገር ውጪ የሚገኙ ደንበኞቻቸውን በኦንላይን እንድያገኙ ማድረግ ችለናል” ይላል ናኤል።
“ኩባንያችን ሞባይል መኒ ወይንም ፔይፓል እንዲሁም ቴሌ ብር አይደለም። ያሉትን የክፍያ ስርቶች በአንድ ላይ ነው ያስተሳሰርነው’” ሲል ያክላል እስራኤል።
ነጋዴዎችም አገልግሎታቸውን ከራሳቸው ድረገጽ እንዲሁም በኦንላይን ያገኛሉ። በኦንላይን ክፍያቸውን ለማግኘት ግን ቻፓ መመዝገብ ይኖርባቸዋል።
የገጠማቸው ተግዳሮቶች
እነ ናኤል ብሔራዊ ባንክ ይህንን መመርያ ይፋ ከማድረጉ በፊት ስለ ዲጂታል ክፍያ አስፈላጊነት እና ሁሉን አሳላጭነት ለማስረዳት በርካታ መንግሥታዊ ተቋማትን በር አንኳኩተዋል።
ለብሔራዊ ባንክ ባለ 80 ገጽ ማብራርያ አቅርበው ቢያስረዱም ልፋታቸው ውሃ አለመቋጠሩን ያስታውሳሉ።
ከዚህ በፊት ግን በረገጧቸው የመንግሥት ተቋማት ሁሉ አይቻልም ቀዳሚ ምላሽም ነበር።
የኮሮና ወረርሽኝ መምጣት አለምን ከስር መሰረቱ እንደቀየረው በአገሪቱም ያለው የዲጂታል ፋይናንስ ዘርፍ ሁኔታ በፍጥነት ተለወጠ።
“በርካታ ነገር ተለውጧል። የመንግሥት ባለስልጣናት ቴክኖሎጂ አፍቃሪ እየሆኑ ነው። ከዚህ በፊት ግን በተለይ በፖሊሲ ረገድ ችግር ነበር።”
ሁለቱ ወጣቶች የገጠሟቸውን ተግዳሮቶች አልፈው አሁን 18 ሰራተኞችን ቀጥረው ማሰረት ችለዋል።
አገልግሎታቸውንም ወደ ምስራቅ አፍሪካ ከዚያም በመላው አፍሪካ የማስፋፋት ህልም አላቸው።
“እቅዳችን ኢትዮጵያን በ2025 ከዓለም ኢኮኖሚ ጋር ማስተሳሰር እንዲሁም 100 ሺህ ስራ ፈጣሪዎች እና ቢዝነሶችን ማገዝ ነው” በማለት እንደማጠቃለያ ኃሳብ ናኤል ተናግሯል።












