አዲሱ መርሃ ግብር ከ1ሺህ በላይ አፍሪካውያን ወጣቶች 1 ቢሊዮን ዶላር ፈንድ ያሰባስባል፡ እሌኒ ገብረ መድህን (ዶ/ር)

ዶ/ር እሌኒ

የፎቶው ባለመብት, AIDA MULUNEH

የተባበሩት መንግሥታት የልማት ድርጅት (ዩኤንዲፒ) በቅርቡ ያስተዋወቀው አፍሪካውያን ጀማሪ የስራ ፈጣሪዎችን የሚደግፈው መርሃ ግብር 1 ቢሊዮን ዶላር በማሰባሰብ ከ1 ሺህ በላይ ወጣቶችን ለመደገፍ እንደሚሰራ ከቀናት በፊት ዘርፉን እንዲመሩ የተመረጡት እሌኒ ገብረ መድህን (ዶ/ር) ለቢቢሲ ገለጹ።

መርሃ ግብሩ ከመንግሥታዊና ከግል ተቋማት በሚገኝ ገንዘብ አፍሪካውያን ወጣት የስራ ፈጣሪዎችን በእውቀት፣ ገንዘብና ምቹ የስራ ሁኔታ በመፍጠር የሚደግፍ ሲሆን ለቀጣዮቹ 10 ዓመታት የሚተገበር ነው።

ድጋፉ የስራ ፈጣሪዎችን ከትምህርትና ከቢዝነስ ተቋማት ጋር የሚገናኙበትን ዕድልም የሚፈጥር ነው።

እሌኒ ገብረ መድህን (ዶ/ር) ጨምረው እንደተናገሩት ይህ አፍሪካዊ ወጣትና ጀማሪ ስራ ፈጣሪዎችን የሚደግፈው መርሃ ግብር እስከ 10 በሚደርሱ የአፍሪካ ሀገራት ማዕከላት (hub) ይኖሩታል።

በ10 ዓመታት ውስጥ ከ1 ሺህ በላይ ስራ ፈጣሪዎችን መደገፍና "ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ" የሚሰራው መርሃግብሩ "አንዳንዶቹ [ጀማሪ የስራ ፈጣራ ድርጅቶች] አንዳንዶቹ ደግሞ በጣም ትልልቅ ኩባንያ ይሆናሉ። አንዳንዶቹ ባሉበት ሆነው ሊቀጥሉ ይችላሉ። ግን ሃሳቡ ምንድን ነው ቢያንስ እነዚህን አንድ ሺህ ድርጅቶች ትልቅ ቦታ ለማድረስና ለመደገፍ ነው ዓላማው" ሲሉ ያስረዳሉ።

በመርሃ ግብሩ አማካኝነት የሚሰበሰበው ገንዘብ ተከፋፍሎ ወጣት የስራ ፈጣሪ አፍሪካውያንን በሁለት መልኩ እንደሚደግፍ እሌኒ (ዶ/ር) ተናግረዋል። መርሃ ግብሩ "የፈጠራ ስራ ድርጅቶችን የሚያለማ በአንድ በኩል ተቋም ይኖረዋል። በሌላ በኩል ደግሞ ለሚለሙት[የፈጠራ ስራዎች] ገንዘብ የሚያበረክት" አካል ይኖረዋል።

እንደ አውሮፓውያኑ በ2022 መጀመሪያ ላይ ወደ ስራ የሚገባውን ይህንን መርሃ ግብር፣ የመግሥትና የግል ተቋማት በጥምር በገንዘብ የሚደግፉበት (blended finance) ስርዓትን ይከተላል።

"ያ ማለት መንግሥታዊ የልማት ድርጅቶችም የሚሳተፉበት እንደገና ደግሞ የግል ፋይናንስ ድርጅቶችም የሚሳተፉበት ነው።... የፈጠራ ስራ አደጋ (Risk) ያለው ስለሆነ ፈጠራ የምንለው ነገር ሃሳቡ ላይሰራ ይችላል...blended finance ሞዴሉ ምንድን ነው? ጥቅሙ የመንግሥታዊ ወይም ልማታዊ ድርጅቶች አደጋውን ለመሸከም የሚችሉበት አሰራር ሆኖ፣ የግል ድርጅቶቹ ደግሞ እውቀትም ብዙ ነገር ይዘው ይመጣሉ" የሚሉት ኃላፊዋ ይህንን መሰል አሰራር በአፍሪካ ደረጃ እስካሁን ተተግብሮ እንደማያውቅ ተናግረዋል።

መርሃ ግብሩ ጀማሪ ስራ ፈጣሪዎችን እንዴት ይደግፋል?

በተባበሩት መንግሥታት የልማት ድርጅት አማካኝነት በቀጣዩ የፈረንጆቹ ዓመት የሚተገበረው አፍሪካዊ ወጣትና ጀማሪ ስራ ፈጣሪዎችን (entrepreneur) የሚደግፈው መርሃ ግብር ከ8 እስከ 10 በሚደርሱ የአፍሪካ ሀገራት ማዕከላት (hub) ይኖረዋል።

ማዕከላቱ የሚቋቋምባቸው ሀገራት ገና ባይመረጡም አንድ ማዕከል አንድ የፈጠራ ስራ መስክ ላይ ብቻ በማተኮር ከገንዘብ ጀምሮ የተለያዩ ድጋፎችን ያደርጋል።

"አንዱ ጋ ለምሳሌ በግብርና ላይ ሲያተኩር የፈጠራ ድርጅቶች እዛ ሙሉ ለሙሉ ድጋፍ የሚያገኙበት፣ ፈንድ የሚገኙበት፣ ከሌሎች ፓርትነሮች [አጋሮች]፣ ከውጪ ኩባንያዎች ጋ የሚገናኙበት የተመቻቸ ሁኔታ የሚፈጠርላቸው [እንዲሆንላቸው ያደርጋል] የተመረጡ ቦታዎች ላይ ይህንን አይነት አሰራር ለመፍጠር ነው። እስካሁን እንደዚህ አይነት አሰራር አልታየም በአፍሪካ" ሲሉ ገልጸዋል።

በየወቅቱ የተለያዩ ዓለም አቀፍና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት የወጣቶች የስራ ፈጠራዎች በማወዳደር የገንዘብ ሽልማት እንደሚያበረክቱ ያስታወሱት እሌኒ (ዶ/ር) "ወጣቶቹ ለ 5 ሺህ ዶላር [በምሳሌነት የጠቀሱት የሽልማት ገንዘብ መጠን ነው] ሲሯሯጡ ነው የምናየው፤ ቢዝነስ እያለሙ እየሰሩ እንዳልሆኑ ነው የምናየው። ይሄ ይጎዳል እንጂ እየጠቀመ አይደለም ማለት እንችላለን። ስለዚህ በተሻለና በተስተካከለ መልኩ ጠቅላላ ተዋናዮችንም ይዘን የምንሄድበትን አሰራር መፍጠር አለብን የሚል ነው።"

እሌኒ (ዶ/ር) የሚመሩት አዲሱ የተመድ የልማት ድርጅት መርሃ ግብር ለጀማሪ የስራ ፈጣሪዎች ከገንዘብ ባሻገር የተለያዩ ድጋፍ ያደርጋል። ይህም ወጣቶቹን በስራ ፈጠራ የተሰማሩበት የቢዝነስ ዘርፍ ውስጥ ካሉ አካላት ጋር ማስተሳሰርን ይጨምራል። የወጣቶቹ የፈጠራ ሃሳብ በእውቀትና ምርምር የሚደገፍበትን ስርዓትንም ያመቻቻል።

ባለፉት አራት ዓመታት በአፍሪካ አንድ ቢሊዮን ዶላር ማንቀሳቀስ የቻሉ ስድስት የስራ ፈጣራ ተቋማት መፈጠራቸውን የጠቀሱት እሌኒ (ዶ/ር)፣ ይህ የስራ ፈጠራዎች ምን ያህል አቅም እንዳላቸው አመላካች ነው ይላሉ።

"እና የሚገርመው እነዚህን ኩባንያዎች የፈጠሩት እድሜያቸው በ20 ቤት ግፋ ቢል 30 የሆኑ ወጣቶች ናቸው።...እንደነዚህ አይነት ሌሎች ድርጅቶች እንዲፈጠሩ እድል መፈጠር ነው አሁን የጀመርኩት ስራ ዓላማ" ሲሉ ያስረዳሉ።

በሌላ በኩል ለወጣቶች የስራ ፈጠራ የሚውለውን ገንዘብ በፍትሃዊነት በአገራት መካከል እንዲከፋፈል ማድረግ ነው። በአሁን ሰዓት ለጀማሪ የስራ ፈጣሪዎች ከተለያዩ ተቋማት አፍሪካን ታሳቢ በማድረግ ፈሰስ የሚደረገው ገንዘብ፣ 80 በመቶ ወደ ወደ ናይጄሪያ እንደሚሄድና የተቀረውም ለጥቂት ሀገራት እንደሚከፋፈል የሚናገሩት ኃላፊዋ አዲሱ የተመድ የልማት ድርጅት መርሃ ግብር ይህንን እንደሚቀይርና የፋይናንስ ምንጮችንም እንደሚያሰፋ አብራርተዋል።

ይህ ሃሳብ እንዴት ተፈጠረ?

ከሁለት ዓመት በፊት በጋና አክራ በተመድ የልማት ድርጅት አማካኝነት የአፍሪካ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ለአፍሪካ ልማት በሚል መሪ ሃሳብ ምክክር ተካሂዶ ነበር።

በምክክሩ ከተሳፉት ተጽዕኖ ፈጣሪ አፍሪካውያን መካከል አንዷ የነበሩት እሌኒ (ዶ/ር) ለልማት ድርጅቱ ምክር ሃሳብ እንዲሰጥ የተዋቀረው ቡድን አባል ነበሩ። ቡድኑ ለአፍሪካ ልማት የሚጠቅሙ ዘላቂ ሃሳቦችን እንዲያፈልቅ ይጠበቅ ነበር።

እናም በምክክሩ፣ በአዲስ አበባ የወጣቶችን የስራ ፈጠራ የሚደግፈውን 'ብሉ ሙን' የተሰኘ ተቋም የሚመሩት እሌኒ (ዶ/ር) አፍሪካውያን ጀማሪ ወጣት የስራ ፈጣሪዎችን በገንዘብና በተለያዩ መንገድ የሚደገፍ አሰራር እንዲኖር መጠየቃቸውን ያስረዳሉ።

ለዚህም መነሻ ያደርጉት እርሳቸው በሚመሩት ተቋም አማካኝነት የገንዘብ ድጋፍ የሚያገኙ ወጣቶች የተለያዩ ችግሮች እንደሚገጥማቸው መመልከታቸውን ነው። በመንግሥታዊ ተቋማት አሰራሮች ወይም በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ምክንያት "ስራቸው ብዙም ርቆ አይሄድም።"

እናም ይህንን እንቅፋት የሚያቃልልና የፈጠራ ስራዎችን ለመድጋፍ ያለውን ዘላቂ የፋይናስ ምንጭ ችግር ሊቀርፍ የሚችል አሰራር በተመድ የልማት ድርጅት አማካኝነት እንዲዘረጋ ሀሳብ አቅርበዋል።

የአህጉሪቱ ተጽዕኖ ፈጣሪዎችና የቁልፍ ተቋማት መሪዎች በተሳተፉት መድረክ የተነሳውን ይህን ሀሳብ "ሁሉም እንደወደዱት" ጠቅሰዋል። ታዲያ መርሃ ግብሩ ከዛ በኋላ ባሉት ሁለት ዓመታት ምክክር ሲደረግበት ቆይቶ ከቀናት በፊት ይፍ ሆኗል። እናም እርሳቸው ያመነጩትን ሃሳብ እንዲመሩት ሹመት የተሰጣቸው ሲሆን በፈረንጆች አዲስ አመትም ስራቸውን ይጀምራሉ።

እሌኒ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ የምርት ገበያን ወይም ECXን በመመስረትና በመምራት በሶስት ዓመታት ውስጥ 1.2 ቢሊዮን ዶላር ያንቀሳቀሰ ተቋም እንዲሆን አድርገውታል።

ከ25 ዓመታት ለሚልቅ ጊዜ በግብርና የንግድ ስርዓትና በወጣቶች የስራ ፈጠራና ላይ የሰሩ ሲሆን ኢትዮጵያውያን የስራ ፈጣሪዎች የሚደግፍ 'ብሉ ሙን' የተሰኘ ተቋም አቋቁመዋል።

በሌላ በኩል ምቹ የስራ ከባቢን ለመፍጠር በማቀድ ለአጭርና ለረጅም ጊዜ የስራ ቦታን የሚቀርብ 'ብሉ ስፔስ' የተሰኘ ተቋምም መስርተዋል።

እርሳቸው ወደ አዲሱ ኃላፊነት ሲዘዋወሩ የመሰረቷቸው ሁለት ተቋማት የቦርድ ሊቀመንበር ሆነው 'ብሉ ሙን' እና 'ብሉ ስፔስ' ስራቸው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።