በታይም መጽሔት የ2021 ተጽዕኖ ፈጣሪ በመሆን የተመረጠችው ሳራ መንክር ማን ናት?

ሳራ መንክር የግሮ ኢንተለጀንስ መስራች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ግሮ ኢንተለጀንስ አርሶ አደሮች እና መንግሥታት የተሻለ ውሳኔ እንዲወስኑ ለማገዝ ይሰራል

ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ሳራ መንክር በታይም መጽሔት ከዓመቱ ተጽዕኖ ፈጣሪ የዓለማችን 100 ሰዎች መካከል አንዷ በመሆን ተመርጣለች።

ኢትዮጵያዊቷ ሥራ ፈጣሪ እና የምግብ ፖሊሲ ስፔሻሊስቷ ሳራ ከተጽዕኖ ፈጣሪ ሰዎች ዝርዝር ውስጥ ተካትታለች።

የግሮ ኢንተለጀንስ መስራችና የበላይ ኃላፊ የሆነችው ሳራ፣ የዓመቱ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰዎች ዝርዝር ውስጥ የተካተተችው በምግብ ዋስትና እና በአየር ንብረት ላይ በሰራችው ስራ ነው።

ታይም መጽሔት በ2021 ተጽዕኖ ፈጣሪ ብሎ የመረጣቸው በአካዳሚ፣ በሳይንስ፣ በአክቲቪዝም እና ምጣኔ ሀብት ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ሰዎችን ነው።

በዚህም ሳራ መንክር በዓለም ዙሪያ ካሉ የዓመቱ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰዎች መካከል አንዷ ሆና ለመመረጥ በቅታለች።

ሳራ አዲስ አበባ ውስጥ ተወልዳ ያደገች ሲሆን ወደ አሜሪካ ያመራችው በ1970ዎቹ ነበር።

በኋላም ሴቶች በሚማሩበት ማውንት ሆዮኬ ኮሌጅ እንዲሁም በለንደን ስኩል ኦፍ ኢኮኖሚክስ የመጀመሪያ ዲግሪዋን በኢኮኖሚክስ እና በአፍሪካ ጥናቶች እንዲሁም ከኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ ደግሞ ኤም ቢኤ ማግኘቷን ትናገራለች።

በወቅቱ በጣም አነስተኛ ቁጥር ያላቸውን የዓለም አቀፍ ተማሪዎች ከሚቀጥሩ ተቋማት መካከል አንዱ በሆነው ዎል ስትሪት የሥራ ላይ ልምምድ አገኘች።

በዚያ ወቅትም በነዳጅ እና ጋዝ ሽያጭ ላይ ለተሰማራ ኩባንያ ነበር ትሰራ የምትሰራው።

በ29 ዓመቷ በዎል ስትሪት ያላትን ሥራ በመተው 'ግሮ ኢንተለጀንስ' የተሰኘ ኩባንያ መሰረተች።

በወቅቱ የምግብ ዋስትና ላይ ለመስራት በመወሰን ሥራዋን ስታቆም "ከኢትዮጵያ ጋር የሚያስተሳስራት ሥራ" እንደሚሆን ተናግራ ነበር።

በአፍሪካ የምግብ ዋስትና አለመረጋገጥ አንገብጋቢ ጉዳይ መሆኑን የተረዳችው ሳራ፣ በዋናነት ከገበሬው ጋር በመስራት ችግሮችን ከስር መሠረታቸው ለመቅረፍ ማለሟን ታስረዳለች።

ሳራ ከዎል ስትሪት ለቃ 'ግሎ ኢንተለጀንስን' እስክትመሰርት ድረስ ሁለት ዓመት ያህል የማሰላሰያ እና የማሰቢያ ጊዜ ወስዳለች።

እኤአ በ2014 'ግሎ ኢንተለጀንስ' ስትመሰርት በዓለም የተለያዩ አካባቢዎች በመጓዝ እና ከገበሬዎች ጋር በመገናኘት እንዲሁም የእርሻ ስፍራዎችን በመጎብኘት የሚያስፈልጋትን መረጃዎች ሰበሰበች።

በዚህ ወቅት በግብርናው ዘርፍ የሚያስፈልገው አዲስ እውቀት ነው ወይስ ያለውን እውቀት ማደራጀት የሚለውን ካጠናች በኋላ ችግሩ ተቋማዊ መሆኑን መረዳቷን ትናገራለች።

ከዚህ በፊት በኢነርጂ ገበያ ውስጥ በምትሰራበት ወቅት ያላትን ልምድ እንደ ግብዓት በመጠቀም ግብርናውን እንዴት ማሸጋገር እንደሚቻል ትናገራለች።

ግሮ ኢንተለጀንስ ከዓለም ላይ ከሳተላይት፣ ከሚቲዎሮሎጂ፣ ከመንግሥት ተቋማት፣ ከሸቀጦች ዝውውር፣ ከአነስተኛ ንግድ ተቋማት፣ መረጃዎችን በመሰብሰብ የማደራጀት እና የመቀመር ሥራ እንደያከናውን ትናገራለች።

ሳራ መንክር የግሮ ኢንተለጀንስ መስራች

የፎቶው ባለመብት, Pacific Press

ግብርና አራት ወይንም የአምስት ሰብሎች ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የአስር ሺዎች ነው የምትለው ሳራ፣ ሰብሎች እና እንስሳት የሚያስተሳስር፣ ልፋት የሚጠይቅና ውስብስብ መሆኑን ታስረዳለች።

ግሎ ኢንተለጀንስ በአሁን ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ የግብርናውን አቅርቦት እና ፍላጎት መተንበይ የሚያስችለው ደረጃ ላይ ይገኛል።

"በሕይወታችን የምንሰራው ነገረ ሁሉ ከግብርና ጋር በአንድም፤ በሌላም መንገድ የተሳሰረ ነው" የምትለው ሳራ፣ ባለፉት ዓመታት የኮሮናቫይረስ ወረርሽን እና የአየር ጠባይ ለውጥ የሰው ልጅ ምን ያህል ለአደጋ እና ለወረርሽኞች ተጋላጭ መሆኑን እንዳሳያት በመግለጽ፣ "የሰው ልጅን በእውቀት በማስታጠቅ የሚገጥሙ ተግዳሮቶች ማሸነፍ ይቻላል" ስትል ታምናለች።

እንደ ሳራ እምነት ከሆነ ግን ይህንን እወቀት ለማስተላላፍ እና የዓለም ማኅበረሰብን ለማብቃት "የጋራ መግባቢያ ቋንቋ" ያስፈልጋል።

ስለዚህ ማንም ረሃብን፣ ከአየር ጠባይ ለውጥ የሚፈጠር ውድመትን ለመከላከል እንዲሁም ቀውስን ለመቀልበስ የሚያስችል ቋንቋ በመፈለግ እና ለዓለም በማሳወቅ ረገድ ሳራ ጠንክራ እየሰራች መሆኑን ትናገራለች።

ግሮ ኢንተለጀንስ በግብርናው ዘረፍ የሚገጥሙ ትልልቅ ተግዳሮቶችን በቴክኖሎጂ በመታገዝ መቅረፍ እንደሚቻልም ጠንካራ እምነት አለው።

እንደ ሳራ ከሆነ ረሃብንም ሆነ የአየር ንብረት ለውጥን በቴክኖሎጂ በመታገዝ ድል መምታት ይቻላል።

ከዚህ በተጨማሪ አስፈላጊውን ቴክኖሎጂ ተጠቅሞ አርሶ አደሩን በማገዝ የተሻለ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚቻል ትናገራለች።

ሳራ በበላይነት በምታስተዳድረው ግሎ ኢንተለጀንስ በዓለም አቀፉ ግብርና ኤኮ ሲስተም ውስጥ ዳታን ወደ ተጨባች እውቀት መቀየር የሚችል አርተፊሻል ኢንተለጀንስ ትጠቀማለች።

ሳራ የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ ከፍተኛ አማካሪ ቡድንን እንድትቀላቀል ጥያቄ ቀርቦላታል።

በዚህ ቡድን ውስጥ ሳራ በምግብ ሥርዓት፣ ንግድ እና የአቅርቦት ሰንሰለት ላይ ያላትን ልምድ እና ሙያ እንድታበረክት ይጠበቃል።

ታይም መጽሔት ባለንበት የፈረንጆች ዓመት 100 ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰዎች ብሎ ከዘረዘራቸው መካከል የዓለም ንግድ ድርጅት የበላይ ኃላፊ ይገኙበታል።

የዓለም ንግድ ድርጅትን ለመምራት የመጀመሪያዋ ሴት እና አፍሪካዊ የሆኑት ናይጄሪያዊቷ ዶ/ር ንጎዚ ኦኮንጆ-ኢዊላ "ሥራን ጥንቅቅ አድርጎ" በማከናወን ምስጋና ተችሯቸዋል።

የታይም 100 ሰዎች ዝርዝር ውስጥ ደቡብ አፍሪካዊው የቴስላ የበላይ ኃላፊ ኤለን መስክ፣ የቤኒን ድምጻዊ አንጀሊክ ኪጆ፣ የአፍሪካ ሕብረት የኮቪድ ምላሽን የሚያስተባብሩት ካሜሮናዊው ዶ/ር ጆን ንኬንጋሶንግ እንዲሁም ኬንያዊቷ አካባቢ ጥበቃ አክቲቪስት ፊልስ ኦሚዶ ይገኙበታል።

በተጨማሪም ሴኔጋላዊቷ ደራሲ እና ሙዚቀኛ ፍሌዊን ሳር ከተጽዕኖ ፈጣሪ ሰዎች ዝርዝር ውስጥ ተካትቷል።