ግብርና፡ አርሶ አደሮችን በሳተላይት የምታግዘው ኡጋንዳዊቷ የናሳ ሳይንቲስት

ዶ/ር ካትሪን

ለባድሚንተን ስፖርት ፍቅር ያላት ኡጋንዳዊቷ ካትሪን ናካሌምቤ ፍላጎቷ ዩኒቨርሲቲ ገብቶ የስፖርት ሳይንስ ማጥናት ነበር።

ነገር ግን የሚያስፈልገውን የመመዘኛ ነጥብ ባለማሟላቷ ምክንያት ይህን ማድረግ አልቻለችም።

ቢሆንም የትምህርት ጉዞዋ በዚህ አልተቋጨም። አሁን በምድራችን ቀዳሚ ከሚባሉት የህዋ ምርምር ተቋማት አንዱ በሆነው የአሜሪካው ናሳ ውስጥ ሳይንቲስት ናት።

ዶክተር ካትሪን በሰሜን ምሥራቅ ኡጋንዳ ውስጥ በምትገኘው ካራሞጆንግ በሚባለው አካባቢ ለሚኖሩ አርሶ አደሮች "የሳተላይት ምስል ተጠቅሜ የናንተን ግብርና ማሳደግ እችላለሁ" ስትላቸው ሳቅ ቀድሟቸው ነበር።

ሳይንቲስቷ ከሳተላይት የተገኙ ጥራታቸው ከፍ ያሉ ምስሎችን ተጠቅማ አርሶ አደሮችንና መንግሥትን ማገዝ ነው ሕልሟ።

ነገር ግን ይህን ለማድረግ አርሶ አደሮቹ ወደሚኖሩበት የገጠሩ ክፍል በመሄድ ማሳቸው ውስጥ መገኘት ግድ ይላታል።

በሌላ አነጋገር ከህዋ ላይ በሚገኘው መረጃ ብቻ ሳርን፣ ከገብስ ወይም ከበቆሎ መለየት አይቻልምና።

"አንዱን ገበሬ ያለኝን ምስል ሳየው አረንጓዴ ነገር እንጂ በውል ምን እንደሆነ መለየት አልቻልኩም ብዬ በአስተርጓሚ ነገርኩት" ትላለች።

"አትሜ ያመጣሁትን ምስል ሳሳየው ገባውና 'ነይ ማሳየን ላሳይሽ' አለኝ" ስትል ለቢቢሲ ትናገራለች።

አብዛኛዎቹ ገብሬዎች በአነስተኛ ማሳዎች ላይ ብቻ ወቅት ጠብቀው ነው የሚፈልጉት ሰብል የሚያመርቱት።

በአሜሪካው ሜሪላንድ ዩኒቨርሲቲ የጂኦግራፊ ሳይንስ ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር የሆነችው ካትሪን (ዶ/ር) የሳተላይት ምስል ተጠቅማ ግብርና እና የአየር ንብረት ለውጥን ታጠናለች።

ከሳተላይት የሚገኘው ምስል መሬት ካለው መረጃ ጋር ተዳምሮ የሰብሎችን ቀመር የሚያጠና ቴክኖሊጂ ለመሥራት ይውላል።

ካትሪን (ዶ/ር) በዚህ ሥራዋ ነው እየተጠናቀቀ ባለው የ2020 'የአፍሪካ ፉድ ፕራይዝ' ሽልማትን ከቡርኪናፋሶው አንድሬ ባቲዮኖ (ዶ/ር) ጋር የተጋራችው።

ካትሪን (ዶ/ር) በአሁኑ ጊዜ ናሳ ውስጥ የአፍሪካ ምግብና ግብርና ፕሮግራም ኃላፊ ናት።

"ከሰማይ ላይ የትኛው አካባቢ የተገነባ እንደሆነ፣ የትኛው ደረቅ፣ ወይም ውሃ ያለው እንደሆነ መለየት ይቻላል" ትላለች ሳይንቲስቷ።

"አልፎም የትኛው ቦታ ለሰብል የሚሆን መሬት ነው፤ ጫካ የሆነውስ የቱ ነው የሚለውን መለየት ችለናል። የ30 ዓመት ሰብል የማምረት ልምድ ስላለን የትኛው ጤናማ መሬት እንደሆነ የትኛው ደግሞ ሊሻሻል እንደሚገባው አውቀናል።"

ካትሪን (ዶ/ር) አርሶ አደሮች ስለሰብላቸው መረጃን በሞባይል እንዲት መላክ እንደሚችሉ ስታሰለጥን

የፎቶው ባለመብት, CATHERINE NAKALEMBE

የምስሉ መግለጫ, ካትሪን (ዶ/ር) አርሶ አደሮች ስለሰብላቸው መረጃን በሞባይል እንዲት መላክ እንደሚችሉ ስታሰለጥን

መፍትሄ ለአርሶ አደሮች

አጥኚዎች ከመሬት የሚያገኙትን ወይም አርሶ አደሮች የሚልኳቸውን መረጃዎች በመጠቀም ሳይንቲስቷ ካርታ ታዘጋጃለች።

ካርታው የገበሬዎቹ ሰበል ከሌሎች አካባቢዎች ጋር ሲነፃፀር እያደገ ነው ወይስ አይደለም የሚለውን ለመለየት ያስችላል።

ይህ መንገድ አሜሪካ ውስጥ ለትላልቅ በዘመናዊ የግብርና መሳሪያዎች ለሚካሄዱ እርሻ ሥራዎች ጥቅም ላይ ይውላል። መረጃው መቼ ሰብል መመረት እንዳለበትና መሬቱ ምን ያህል ዝግጁ እንደሆነ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል።

ይህ መረጃ አነስተኛ ማሳ ላላቸው ኡጋንዳ ውስጥ ላሉ ወይም ለሌሎች የአህጉሪቱ አርሶ አደሮች እጅግ ጠቃሚ ነው።

"ለምሳሌ በሚቀጥሉ ቀናት ዝናብ እንደሚዘንብ እርግጠኛ ከሆንን አርሶ አደሮች ማሳቸውን እንዲያዘጋጁ እንነግራቸዋለን። ዝናብ ከሌለም ጊዜያቸውን እንዲሁ እንዳያባክኑ እናስረዳቸዋለን።"

በአፍሪካ አብዛኛዎቹ የእርሻ ማሳዎች ቁራሽ መሬት ናቸው። ሰብል ማምረትን በተመለከተም ይህን ያህል መረጃ የለም።

ነገር ግን ከሳተላይት የሚገኘው መረጃ ወደ አካባቢው ቋንቋ ተተርጉሞ በስልክ የፅሁፍ መልዕክት፣ ወይም በሬዲዮ፣ አሊያም በግብርና ሠራተኞች አማካይነት ሊተላለፍ ይችላል።

አልፎም መንግሥታት ይህንን መረጃ ተጠቅመው ተፈጥሯዊ አደጋ በሚመጣ ጊዜ ማኅበረሰቡ ከድርቅ እንዲጠበቅ አስፈላጊውን ሊያደርጉ ይችላሉ።

አስካሁንም የካትሪን (ዶ/ር) ጥናት በካራሞጃ የሚኖሩ 84 ሺህ ገበሬዎች በአየር ለውጥ ሳቢያ በሚመጣ የዝናብ እጥረት እንዳይጎዱ መታደግ ችሏል።

በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ሰብል ለሚያመርቱ ኡጋንዳውያን አርሶ አደሮች የሳይንቲስቷ ጥናት መፍትሄ ይዞ መጥቷል።

ዝናብ በማይኖርበት ወቅት አርሶ አደሮች ትኩረታቸውን ወደ ሌላ ሥራ እንዲያደርጉና ቤተሰቦቻቸውን እንዲያግዙ ይደረጋል።

ካትሪን (ዶ/ር) ለሥራዋ የተበረከተላት ያልጠበቀችው ሽልማት

የፎቶው ባለመብት, AFRICA FOOD PRIZE

የምስሉ መግለጫ, ካትሪን (ዶ/ር) ለሥራዋ የተበረከተላት ያልጠበቀችው ሽልማት

በድንገ የመጣ ሳይንቲስትነት

ካትሪን (ዶ/ር) ከሜካኒክ አባቷና ምግብ ቤት ከምታስዳድረው እናቷ የተወለደችው በኡጋንዳዋ ዋና ከተማ ካምፓላ ነው።

"ሥራዬ ከሳተላይት ጋር የተገናኘ ይሆናል ብዬ አንድም ቀን አስቤ አላውቅም" ትላለች።

ከእህቶቿ ጋር ባድሚንተን መጫወት ታዘወትር ነበር። ሕልሟም በስፖርት ሳይንስ ዲግሪ መጫን ነበር።

ነገር ግን ያለሽ ውጤት በታዋቂው የማኬሬሬ ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ሳይንስ ክፍል ለመግባትና ለመማር አይበቃም ስትባል ወደ ኢንቫይሮንሜንታል [የአካባቢ] ሳይንስ ክፍል አቀናች።

ትምህርቷን ለመማር ያግዛት ዘንድ ለኡጋንዳ ዱር እንስሳት ባለሥልጣን ለመሥራት አመለከተች።

ካርታ ማጥናት እወድ ነበር የምትለው ካትሪን ለመጀመሪያ ጊዜ ካርታ ለማጥናት ተራራ ላይ ወጥታ የተሰማትን ሐሴት አትዘነጋውም።

አሁን በአፍሪካ የተለያዩ አገራት ውስጥ እየተዘዋወረች ለመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ስለ ምግብ ዋስትና ምክር የምትለግሰው ካትሪን በወቅቱ የማስተርስ ድግሪዋን ለመማር ለጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ ማመልከቻ አስገባችና እድሉን አገኘች።

ሁለተኛ ዲግሪዋን እንደጨረሰች ደግሞ የዶክትሬት ድግሪዋን ለመከታተል እዚያው አሜሪካ ሜሪላንድ ዩኒቨርሲቲ ገባች።

ሳይንቲስቷ ካትሪን (ዶ/ር) የእራሷን ተሞክሮ መሰረት አድርጋ ወጣት ጥቁር ሴቶች ወደ አካባቢ ሳይንስ ጥናት እንዲገቡ ምክር ትለግሳለች።

የ2020 የአፍሪካ 'ፉድ ፕራይዝ' ሽልማት አሸናፊ ስትሆን የተሰማትን ደስታ መደበቅ አትችልም። ስልክ ተደውሎላት "የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዝደንት ኦሌሴጉን ኦባሳንጆ ይፈልጉሻል፤ መሥመር ላይ ጠብቂ" ስትባል የአጭበርባሪዎች ስልት ይሆን ብላ ጠርጥራም ነበር።

"አስቡት እስቲ፤ አሁን እኔ የዊኪፔዲያ ገፅ አለኝ።"

አሁን አሁን ራሴን ለሰዎች ሳስተዋውቅ 'የ2020 የአፍሪካ ፉድ ፕራይዝ አሸናፊ ነኝ' ማለት ማስታወስ አለብኝ" ትላለች በፈገግታ።

"አምስት ኪሎ ግራም የሚመዝን ሽልማት ተሰጥቶኛል። በሕልሜ እንዳልሆነ ማረጋገጫው ይሄ ነው።"