የባህር ዳር ጫት ከገበያ ሊጠፋ ነው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከባህር ዳር 25 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው ዘጌ ነዋሪ የሆነው ሙላት ኢብራሂም ለ12 ዓመታት የመከላከያ ሠራዊት አባል ሆኖ አገሩን ሲያገለግል ቆይቷል። ከ1991 እስከ 2003 ዓ.ም ድረስ።
ከዚያ በኋላም ማረሻ እና ሞፈር ይዞ እርሻ ላይ በመሠማራት ሌላኛውን የህይወቱን ምዕራፍ ጀመረ። ጫት ማምረት ደግሞ ቀዳሚ ሥራው ሆነ።
ካለው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እና ሌሎች ሲሠሩት መመልከቱ ከሌሎች የግብርና ዘርፎች ይልቅ ወደ ጫት እንዲያዘነብል አድርጎታል። "ከውትድርና ስመጣ ህብረተሰቡ ጫት ነበር የሚተክለው። እኔም ከዚህ በኋላ ነበር ወደ ጫት ማምረት የገባሁት" ሲል ያስታውሳል።
ባለፉት ዓመታት ጫት እያመረተ ቢቆይም ያሰበውን ያህል ውጤታማ መሆን ግን አልቻለም።
የሥራው አድካሚነት፣ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መሄድ እንዲሁም በኅብረተሰቡ ዘንድ የጫት ሱስ መስፋፋቱ ሌሎች አማራጮችን እንዲያይ ግድ አለው።
"ጓሮውን ጨምሮ ሁሉም አካባቢ በጫት የተሸፈነ ነው። ሌላ የተተከለ ነገር የለም። ጫት ተሽጦም ለኅብረተሰቡ የሚሰጠው አገልግሎት የለም- ከሱስ ባለፈ ማለት ነው። ከጫት የሚገኘው ገንዘብ ጎጂ ባይሆን አዋጭም አይደለም። ሆኖም ጫት ማምረት ላይ ከተሠማራህ ሌላ ለመስራት ያስቸግራል። ሁሌም ተከታተሉኝ ይላል" ሲል ሙላቱ ያስረዳል።
በአካባቢው በግብርና ሥራ ከተሠማሩት አንዱ የሆነው ኡመር አልቃድርም በዚህ ሃሳብ ይስማማል። ከቤተሶቼ ባገኘሁት ማሳ ላይ ጫት በማምረት ወደ ግብርና እንደገባ በመጥቀስ፤ ለስምንት ወይም ለአስር ዓመታት አካባቢ ጫት ለማምረት ደክሟል።
ጫት "ብዙም ዋጋ የለውም። ታገኛለህ፤ ሠራተኛ ላይ ታወጣለህ። ብዙ ልፋት እና ወጪ አለው። ትል የሚበላው አለ። ሌላ ሥራ መሥራት አይቻልም። ልፋት ብቻ ነው። ወጣቱም ወደዚህ ሱስ ገብቷል" ይላል።

ጫትን በሙዝ
አሁን አሁን ግን ሙላትና ኡመርን የመሳሳሉ ጫትን የሚያመርቱ ሰዎች ፊታቸውን ወደሌሎች ምርቶች እያዞሩ ነው።
በባህር ዳር ከተማ አስተዳደር የግብርና መምሪያ የዘጌ 01 ቀበሌ የግብርና ጽህፈት ቤት አስተባባሪ የሆኑት አቶ አድማሱ ተካ እንደሚሉት ጫቱን በሌላ ተክል የመቀየር ሃሳብ በአብዛኛው ከአካባቢው ፍላጎት የመነጨ ነው።
"ጫት ሥራ በማስፈታት ያቦዝናል፣ ህይወትንና ጤናን ያቃውሳል። የአካባቢው ነዋሪዎች ጫት ለወጣቶች ጠንቅ በመሆኑ መጥፋት አለበት እያሉ ነው። ጫት አይጠቅምም ለዚህ መጥፋት አለበት" ማለታቸውን ያስታውሳሉ።
ለዚህ ደግሞ የተመራጭ ተደርጎ የታሰበው አካባቢው ላይ የተሻለ ምርታማ ሆነው ኅብረተሰቡን የሚጠቅሙ እንደሙዝ፣ አቮካዶ፣ ቡና እና የመሳሰሉትን ማምረት ሆነ።
ይህንን ለማድረግ ደግሞ የግብርና ባለሙያዎች እና አርሶ አደሮች አርባ ምንጭ ድረስ በመሄድ በአካባቢው ውጤታማ ስለሆነው የሙዝ እርሻ የልምድ ልውውጥ አድርገዋል።
"አርባ ምንጭ ድረስ አርሶ አደሮችን ጭምር ይዘን ሄድን ነበር። የሙዝ ምርቱ በጣም የተለየ ነው። መኪና እየገባ ምርቱን ለገበያ ያቀርባል" የሚሉት አቶ አድማሱ ተካ ይህንን በአርዓያነት በመከተል በአካባቢያቸው ተግባራዊ ለማድረግ እንደወሰኑ ይናገራሉ።
በዘጌ 01 ቀበሌ በርካታ አርሶ አደሮች በጫት ተሸፍነው የነበሩ ማሳዎቻቸውን ሱስ ከሚያስዝ ወደ ሚጠቅም ተክል በመቀየር ላይ ናቸው። አሁን ሙዙ አድጎ ለፍሬ ሲያፈራ ጫቱን በማስወገድ ከሙዙ በመጠቀም ላይ ናቸው።
አርባ ምንጭ ሄደው እንደተመለከቱት ማሳቸው ድረስ መኪና ገብቶ ምርታቸውን ለገበያ የሚቀርብበት መንገድን እየፈለጉ ነው። "እኛም ማሳው አፍርቶ ሁለት ጎጥ ሙሉ ሙዝ ሆኖ በመኪና በመጫን አርሶ አደሩ ተጠቃሚ እንዲሆን ነው የምንፈልገው። ጫት ለልጅ ማታለያ አይሆንም። ሙዝ ግን ለሰውነትም ገንቢ ነው" ይላሉ አቶ አድማሱ።
ጫትን ቀስ በቀስ ማስወጣት
አቶ ሙላት ኢብራሒም በባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ግብርና መምሪያ የአትክልት እና ፍራፍሬ ባለሙያ ናቸው። የጫት ማሳን በአትክልትና ፍራፍሬ የመቀየር ሥራ በሁለት መንገድ እየተሠራ ነው ይላሉ።
"አንደናው የጫት ማሳ የሌላቸው ሙሉ ለሙሉ ወደዚያ ሳይገቡ ወደ ሌሎች አትክልት እና ፍራፍሬዎች እንዲያመሩ ማድረግ ነው። ሁለተኛው፤ የተከሉት ደግሞ ከጫቱ ወጥተው አትክልት እና ፍራፍሬ እንዲያመርቱ ለማድረግ ነው። ለዚህ ደግሞ ስልጠና ይሰጣል" ይላሉ።
አቶ አድማሱ እንደሚሉት ጫትን በጊዜ ሂደት ወደ ሙዝ መቀየር ጥረት እየተደረገ ነው። ለዚህም መጀመሪያ ጫቱን ሙሉ ለሙሉ ሳያጠፉ አልፎ አልፎ ሙዝ እንዲተክሉ በማድረግ ቀስ በቀስ ለውጥ እየተደረገ ነው።

በዚህ ዘዴ ወደ ሥራው የሚገቡ አርሶ አደሮች ቁጥርም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ይገኛል።
"ይሄንን ከሞከርን አንድ አመት ሊሆነን ነው" የሚሉት አቶ አቶ አድማሱ "ሰባት አርሶ አደሮች ሙሉ ለሙሉ ጫት አጥፍተው በሙዝ ተክተዋል። በርካቶች ደግሞ ጫት መሃል ሙዝ የተከሉ አሉ። ወደፊት ጫት ይጠፋ እና ሙዝ ቦታውን ይይዛል።"
ሌሎች ደግሞ ሙዝን በጫት ተክል መሃል የተከሉ ሲሆኑ ከሁለት ዓመት በኋላ አየር ንብረቱም ስለሚመች ሙሉ ለሙሉ በሙዝ የሚተካ ይሆናል። በዚህ ሂደትም ጫት ለሙዝ ቦታ እየለቀቀ ይሄዳል ይላሉ።
ጫቱ ሙሉ ለሙሉ ባይጠፋም ከፍተኛ ለውጥ በአካባቢው እየታየ መሆኑን በመጥቀስ "በቀበሌው ከአምስት እስከ ስድስት ሔክታር የሚሆን የጫት ማሳ ነበር። ከሁለት እስከ ሦስት ሔክታር የሚሆነው አሁን ከጫት ነጻ ሆኖ ሙዝ ብቻ ለምቶበታል" ሲሉ አቶ አድማሱ ያስረዳሉ።
የሙዝ ገቢ ከጫት ይበልጣል?
ጫቱን በሙዝ ተክል በመቀየራቸው ሙላትና እሱን የመሰሉ አርሶ አደሮች የተለያየ ጥቅም በማግኘት ላይ እንደሆኑ ይጠቅሳሉ።"አሁን ምርት እያገኘን ለገበያ እያቀረብን ነው። ምርቱም ጥሩ ነው" ይላል ሙላት።
ኡመርም በበኩሉ "ወደ ሥራ ከገባን ሁለት ዓመት ሆነን። ለማልማት አንድ ዓመት ፈጀብን። በሁለተኛው ዓመት አፍርቷል። አሁን ጥሩ ነው። ለህብረተሰቡ እዚሁ እናቀርባለን። ሙዝ ከቀጸደቀ እና ካደገ በኋላ አልፎ አልፎ መንከባከብ እንጂ አድካሚ አይደለም" ይላል።
ብዙዎች ከጫት የሚገኘው ገቢ ከፍተኛ መሆኑን በመጥቀስ ወደ ሥራው እንደሚገቡ ቢጠቅሱም እነሙላት ግን ከሙዝም ጥሩ ገቢ ማግኘት እንደሚቻል ይናገራሉ።

"ከጫት አንጻር በየሳምንቱ ወይም ሁለት ሳምንት የተወሰነ የምታገኘው ነገር አለ። ወጪውም በዚያው ልክ ነው። ሆኖም ግን ሙዙ ሁሉም አፍርቷል። ተረካቢ ስናገኝ ቆንጆ ገቢ አለው። እስካሁን እዚሁ እየሸጠን ነው። የበለጠ ገበያ ቢኖር ደግሞ አዋጪ ነው" በማለት የሙዝ ምርት ሥራው ስለማይበዛ ሌላ ነገርም ለመስራት እድል እንደሚሰጥ ሙላት ይገልጻል ።
ኡመር አልቃድር በበኩሉ "እዚህ አካባቢ የገበያ ትስስር አልተፈጠረም። [ሙዝ በኪሎ] ባህር ዳር ላይ 30 እና 40 ብር ሆኖ እዚህ ከ20-25 ብር እንሸጣለን። ትስስር ከተፈጠረ እኛም እንጠቀማለን። ሰዉም ከእኛ ልምድ ይወስዳል" ሲል የገበያ ዕድሉ ከተሻሻለ የሚገኘው ገቢም እንደሚጨምር ያምናል።
ከሙዝ ምርቱ ባሻገር የሙዝ ችግኝ ማዘጋጀቱም ሌላ የገቢ እድልን እንደሚፈጥር አቶ አድማሱ ይናገራሉ፤ "አርሶ አደሮቹ ባለፈው ሁለት መኪና ችግኝ ሸጠዋል። በአግባቡ ከተሠራ በኢኮኖሚ ረገድ ሙዝ አዋጪ ተክል ነው። የጫት እና የሙዝን ማሳ ብናይ ከአንድ የሙዝ ተክል እንኳን ከ200 እስከ 250 ፍሬ ሙዝ ይገኛል። ይኼንን ወደ ሂሳብ ስንቀይረው ሰፊ ልዩነት አለው።"
ከውትድርና ወደ ግብርና የገባው ሙላት፤ ጥሩ ገቢ አገኝበታለሁ ያለው የጫት ተክል ከአድካሚነቱ ባሻገር የጠበቀውን ያህል ገንዘብ ካለማስገኘቱ ባሻገር ወታቶችን በሱስ እንዲጠመዱ ምክንያት መሆኑ ስላሳሰበው ፊቱን ወደ ሙዝ ምርት በማዞር በአካባቢው ላሉ አርሶ አደሮች አርዓያ ለመሆን እየተጋ ነው።
"ከዚህ በኋላ ጫት ካለው ጎጂነት አንጻር በሌላ አትክልት ሙሉ ለሙሉ መቀየር አለበት። ጥቅሙም ለራስ ብቻ ሳይሆን ለአካባቢው ኅብረተሰብ ና ለአገርም ነው" በማለት ሙዝ ማንም ለጉዳት ሳይዳርግ አምራቹንም የሚጠቅም ምርት እንደሆነ ካገኘው ጥቅም ተነስቶ ሙላት ይናገራል።
"የጫት ማሳዬን ወደ ሙዝ ሙዝ መቀየሬ የተሻለ ነገር ለማግኘት አስችሎኛል። ጫት በብዙ ሥራን የሚጠይቅና አድካሚ ነው። ሙዝ ግን ሥራው ቀለል ያለ ስለሆነ ሌላ ሥራን ለመስራት እድልን ይሰጣል" ሲል ያገኘውን ጠቀሜታ በመጥቀስ ያጠቃልላል።















