ውጤታማ የአፍሪካ ገበሬ በመባል የተሸለመችው ሃረጉ ጎበዛይ

ሃረጉ በእርሻ ቦታዋ ላይ ከእንግዶች ጋር

የፎቶው ባለመብት, Dawit/twitter

ወይዘሮ ሃረጉ ጎበዛይ፤ በአንድ ወቅት በገጠራማ የትግራይ ወረዳዎች ትዳር መስርተው፣ ልጆች ወልደው፣ የባለቤታቸውን የወር ገቢ እየተጠባበቁ በዝቅተኛ የህይወት ደረጃ ከሚኖሩት ሴት ገበሬዎች መካከል አንዷ ነበረች።

በወቅቱ፤ የራሴ የምትለው መውደቂያ ያልነበራትና በእናቷ ስር ተጠግታ የምትኖር ባለ ትዳር ሴትም ነበረች።

ይሁን እንጂ፤ ባለቤቷ በሚያገኘው አነስተኛ ገቢ ከእጅ ወደ አፍ የሆነን ኑሮ ሳይቀይሩ እንቅልፍ ለወይዘሮ ሃረጉ የሚታለም አልነበረም።

"ግብርና እሞክር ነበር፤ ግን ደግሞ የሚያጠግብ ምርት አላገኝበትም። አካባቢያችን ቆላ ስለሆነ ከአንድ ሄክታር ከሁለት እስከ ሦስት ኩንታል ምርት ብቻ ነው የሚገኘው። በጦርነት የተጠቃ ድንበርም ስለሆነ ምድረ በዳ ሆኖ ነበር" ትላለች።

አርሶ አደር ሃረጉ፤ በትግራይ ክልል ማእከላይ ዞን ወረዳ መረብለኸ ከተማ ራማ ዓዲ አርባዕተ ኗሪ ናት።

በትምህርት ብዙም አልገፋችም፤ አራተኛ ክፍል ግን ደርሳለች። ስለዚህ ከዚህ የድህነት ኑሮዋ የሚቀይራት ትምህርት ሳይሆን ድንጋይ የበዛበት መሬትዋን ማልማት ብቻ ነው።

የነበራት መሬትም ብዙም የምትመካበት አይደለም፤ 1.5 ሄክታር ብቻ ናት።

በ1997 ዓ. ም፤ ያቺን መሬትዋ ይዛ ወደ እርሻ ልማት መግባት ወሰነች። ይሁን እንጂ በቀላሉ ታርሶ የሚለሰልስ መሬት አይደለም የያዘችው።

ከላይ እሰከ ታች ድንጋይ ብቻ የወረረው መሬት ነው።

"በእስራኤል አፈር ከሌላ አካባቢ መጥቶ ነው መሬት የሚለማው ሲባል በቴሌቪዥን ስሰማ፣ እኔም መሬቱን ለመለወጥ በድፍረት ጀመርኩት። አፈር የሚባል አልነበረውም፤ ስለዚህ አንድ ሜትር ከግማሽ ቆፍሬ፣ ከሌላ ቦታ አፈር አምጥቼ ሞላሁት። ከዛ በኋላ ቋሚ አትልክቶች ተከልኩ" ትላለች።

በአካባቢው የመስኖ ልማት የተለመደ እንዳልነበረ የምትናገረው አርሶ አደር ሃረጉ፤ እንደ ማሽላ፣ ዳጉሳና ሽምብራ የመሳሰሉት አዝዕርቶች ይዘወተሩ እንደነበር ታወሳለች።

"ትግራይ ድንጋይ እንጂ ፍራፍሬ የሚገኝ የማይመስለው ብዙ ነው፤ ከተሰራ ግን የማይቀየር የለም። ለዚህም ነው ከኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት በፊት ከኤርትራ መጥተው በአካባቢያችን መሬት ተከራይተው በመስኖ ልማት ቋሚ አትክልቶች ሲያለሙ ከነበሩት ኤርትራውያን ልምድ ወስጄ የእኔን ድንጋያማ መሬት መቀየር የቻልኩት" በማለት ትገልጻለች።

"እያበደች ነው ይሉኝ ነበር"

ይህ አፈር ያልነበረው መሬት ለም አፈር በማልበስ በመጀመሪያዎቹ አምስት አመታት ቲማቲም፣ ሽንኩርት፣ ቃርያና ሌሎች ገቢ ሊያስገኙላት የሚችሉ አትክልቶች በመትከል ስራ ጀመረች።

እንዲህ እያለች፤ መሬቱንም ወደ 12 ሄክታር በማሳደግ አፕል፣ ኬንት፣ ቶሚ፣ ኪት፣ ዳዶ የሚባሉ የማንጎ አይነቶች የሚገኙባቸው ሰባት የማንጎ ዝርያዎች ተከለችበት።

ሃረጉ ማሳ ላይ ካፈሩ የማንጎ ዛፎች መካከል

የፎቶው ባለመብት, Merebleke communication

"የእኔ መሬት ልዩ የሚያደርገው ዐለት እንጂ የሚታረስ መሬት አይደለም የነበረው። በ1982 ዓ. ም ለገበሬዎች ታድሎ ማንም ሰው ሳይጠቀምበት የቆየ ነው። በኋላ በ1997 ዓ. ም ትንሽም ቢሆን ልሞክረው ብዬ ድንጋይና እሾህ እያጸዳሁ ማልማት ጀመርኩ። ያኔ ይህች ሴት በየበረሃው የምትሄደው እያበደች ነው፣ ሌላ ስራ አትሰራም የሚሉኝ ነበሩ። አሁን ህይወቴ ተቀይሮ ሲያዩ ደግሞ ያኔ ከእሷ ጋር ብንሮጥ ኖሮ ይላሉ" ስትል ትውስታዋን ታጋራለች።

ዓለትም ፈንቅላ ይሁን እሾህ ለቅማ አፈር የሌለው መሬት አለማለሁ ብላ ስትነሳ የሳቁባትና 'የሴቶች ስራ አትሰራም' ሲሉ ያንቋሸሽዋት ጥቂቶች እንዳልነበሩ የምትናገረው ሃረጉ፤ የልማት አርበኛ ሆና ለሌሎች አርአያ የሆነችበት ደረጃ በመድረሷ ደስተኛ ናት።

በአንድ ቀን የመቀለ ዩኒቨርሲቲ የግብርና ተማሪዎችን ይዞ በመሄድ ይሄንን ስራዋን የተመለከተ የተፈጥሮአዊ ሃብትና የደረቅ መሬት ልማት ኮሌጅ አስተማሪ ዶክተር ዳዊት ገብረእግዚኣብሄር፣ "ድንጋይ ወደ ፍራፍሬ የቀየረች ሴት" የሚል ስያሜ ሰጥቷታል።

እሷም "ስንስቅባት የነበረው ለዚህ ለውጥ ነበር ለካ ያላሉ የሉም። ባለቤቴም ፖሊስ ስለነበረ በተለያዩ አካባቢዎች ስለሚንቀሳቀስ ለብቻዬ ነበር የምኖረው። እሱም ስራዬን ከሚቃወሙት አንዱ ነበር። 'በረሃ ለበረሃ ከምትሮጪ ሌላ ስራ አትሰሪም . . . መቼ ያልፍልኛል ብለሽ ነው?' ይለኝ ነበር" በማለት ያለፈችውን ታስታውሳለች።

"በራሴ ትግል ብቻ ነው እዚህ የደረስኩት" ትላለች።

ከጊዜ በኋላ ደጋፊዋ የሆነው ባለቤቷም ስራውን ትቶ ከእርሷ ጋር በግብርና ስራ ከተሰማራ አመታት አስቆጥሯል።

የእርሻ ማሳ ወደሚገኝበት ቦታ የሚያደርስ መንገድ የለም፣ ከፍተኛ የውሃ እጥረት ያለበት አካባቢ መሆኑም ሌላ ትልቁ ፈተና ነበር።

አርሶ አደሯ ግን በእነዚህና ሌሎች አዳጋች ችግሮች ተስፋ በመቁረጥ እጅና እግር አጣጥፎ መቀመጥን አልመረጠችም።

ይልቁንስ፤ 1.2 ሚሊየን ብር በማውጣት የመስኖ መስመር ስትዘረጋ የሚያጋጥማትን የውሃ ችግር ፈታች።

ቀጥላም 820 ሺ ብር ወጪ በማድረግ ምርቶችዋን በቀላሉ ወደ ገበያ የሚያደርስላትና ስራዋን ለመጎብኘት የሚመጡት ሰዎች በመኪና የሚሻገሩበት ድልድይ ሰራች።

ይህንን በማድረግ ራስዋን ጨምሮ በአካባቢዋ የሚገኙ 80 አባወራዎች ከበፊት ችግሮቻቸው እረፍት እንዲያገኙ በማድረግ፤ በህይወትዋም ትልቅ ስኬት የምትለውን ለማስመዝገብ የበቃች አርሶ አደር መሆን ችላለች።

"ከዚህ በፊት መንገድ ስላልነበረ የእርሻ ባለሞያዎች በእግራቸው ነበር የሚመጡት። እኔም በዚህ ሁሉ ችግር ተስፋ አልቆረጥኩም፤ አንድ ቀን ይህ ጨለማ ተገልጦ ይበራልኛል የሚል ተስፋ ነበረኝ። እነሆ በርቶልኛል" በማለት በጥረቷ ደስተኛ መሆንዋን ትገልጻለች።

ሃረጉ ማሳ ላይ ምን ይገኛል?

በአሁኑ ወቅት ሰባት የማንጎ ዝርያዎች ለገበያ ታቀርባለች። በዋናነት አፕል ማንጎን በብዛት ታመርታለች።

ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ፤ ዴስሞሲየም፣ የዝሆን ሳር፣ የግጦሽ ሳር፣ ተፈጥሮአዊ ጸረ ተባይ ሆኖ የሚያገለግለው የኒም ቅጠልና ሌሎች አትክልቶች ያሉት ሰፊ ማሳ ይገኛል።

መስኖ

የፎቶው ባለመብት, Merebleke communication

ለዚህ ሁሉ ዘመናዊ ማዳበሪያም ሆነ ጸረ ተባይ አትጠቀምም።

ከባለፈው አመት ጀምሮ አርሶ አደሯ ያላት 12 ሄክታር መሬት በሙሉ ምርት መስጠት ስለ ጀመረ ከ6700 ቋሚ ተክል በአመት ወደ 2500 ኩንታል የሚጠጋ ፍራፍሬ እንደምታገኝ ትናገራለች።

"አብዛኛዎቹን ደምበኞቼ በስልክ እንጂ በአካል አላውቃቸውም። በትግራይና አዲስ አበባ ግን ብዙ ደንበኛ እንዳለኝ አውቃለሁ አፕል ማንጎ ጥሩ ገበያ ያለው ሲሆን፤ በዚህ አመት አዲስ አበባ ያሉትን ናቸው በብዛት የወሰዱልኝ" ትላለች።

ራማ፤ ኢትዮጵያ ኤርትራ ከሚገናኙባቸው ድንበሮች አንዱ ሲሆን፤ ከሁለት አመት በፊት በሁለት አገራት የሰላም ስምምነት በኋላ ሲከፈት ጥሩ ገበያ እንደነበራትም ገልጻለች።

"በወቅቱ በኪሎ 80 ብር ስሸጥ ነበር፤ ጊዜው አጭር ቢሆንም ጥሩ ነበር። የድንበሩ መከፈት ለሁላችንም ጠቅሞን ነበረ፤ ሁሌም ሰላም ቢሆን እላለሁ። በዚህ የገበሬውም ህይወት ይቀየራል፤ ተጠቃሚውም በቀላሉ የሚፈልገውን ማግኘት ይችላል" የሚል እምነት አላት።

ይሄንን ስራ ከጀመረች በኋላ ባሉት አመታት የነበረው ጉዞ ቀላል እንዳልነበረ ግን አትዘነጋም። በየጊዜው የሚያጋጥም የሞተር መሰበር፣ መክሰርና ገበያ ማጣት በተደጋጋሚ የተጋፈጠቻቸው ችግሮች ናቸው።

"ሲከስር ያጣሁትን ቶሎ እተካለሁ በማለት የሚሰደድ አለ፤ እኔ ግን ያንን አልመረጥኩም። ሁሉንም ችዬ ስላለፍኩትም በኑሮዬ ምንም ያልነበረኝ ሰው አሁን ሦስትና አራት ቦታ ላይ ቤት ሰርቼ ጥሩ ህይወት እየመራሁ ነው" ስትል ልፋት የሚጠይቅ ስራ እንደሆነ ትገልጻለች።

ወይዘሮ ሃረጉ የስድስት ልጆች እናት ናት። ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ገብተው የሚማሩ መኖራቸውንም ትናገራለች።

የሃረጉ ማሳ በርቀት ሲታይ

የፎቶው ባለመብት, dawit

ታዲያ ሁሉም የቤተሰብ አባል በዚህ ማሳ የራሱ የስራ ድርሻ ይዞ ለተጨማሪ እድገት ይተጋል።

በተጨማሪም ለ16 ሴቶችና ለ16 ወንዶች ቋሚ የስራ እድል ፈጥራለች። በገንዘብ እጥረት ትምህርታቸውን ማቋረጥ የለባቸውም ብላ ለምታምንባቸው ከ50 እስከ 60 ለሚሆኑ ወጣት ተማሪዎችም በሰአት ሰርተው ገቢ በማግኘት ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ ታደርጋለች።

ይሄንን ጥረትና ትጋት ሲከታተል የቆየው ዶክተር ዳዊት፤ ጥቅምት ወር ላይ ውጤታማ የአፍሪካ ገበሬ ተብላ እንድትሸለም በ 'አፍሪካን ፋርመርስ ስቶሪስ' ላይ አመለከተላት። መሸለምዋንም የነገራትም እሱ ነው።

"በዚህ ሁኔታ አንዲት ሴት ራስዋን ቀይራ ፍራፍሬዎች በማምረት ሌሎችን ለመለወጥ ስትጥርና ስትሸለም ከማየት በላይ የሚያስደስት የለም" ይላል።

ወይዘሮ ሃረጉ በበኩሏ፤ "በየጊዜው ስሸለም ብርታት ነው የሚሆነኝ። አሁን ግን ትግራይን በመወከል ይሄንን ሽልማት ማግኘቴ ኩራት ይሰማኛል። በዚህ ልጆቼም ደስተኞች ናቸው። እኛም እንዲህ ሌላ እንሰራልን፣ ወደ ፋብሪካና ኢንዳስትሪ እናሳድገዋለን ይሉኛል" በማለት የወደፊት ምኞትዋን ታጋራለች።

"እኔ ስጀምር አካባቢዬ ላይ ብድርና ባንክ ስላልነበረ በ1700 ብር ብቻ ነው የጀመርኩት። አሁን ግን በተለያየ መልኩ ብድር ስለሚገኝ የምትቀየርበት ነገር ሩቅ አይደለም" በማለት ሁሉም በስራ እንዲተጋ ታበረታታለች።