ትራምፕ በኢራኑ ድርድር ደስተኛ አለመሆናቸውን ሲገልጹ፣ አገራት ዜጎቻቸውን እያስወጡ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ፕሬዝዳንት ትራምፕ በኢራን የኒውክሌር ፕሮግራም ላይ በተደረጉት የቅርብ ጊዜ ውይይቶች ደስተኛ ባይሆኑም ጥቃት ለመፈጸም ግን እስካሁን ድረስ ከውሳኔ ላይ አለመድረሳቸውን ተናገሩ።
"የሚያስፈልገንን ሊሰጡን ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ደስተኛ አይደለሁም" ሲሉ ትራምፕ ሐሙስ ዕለት በጄኔቫ ሲካሄድ የነበረው እና ያለ ስምምነት የተጠናቀቀው ድርድር ላይ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት በኢራን ላይ ወታደራዊ ኃይል መጠቀም እንደማይፈልጉ አፅንዖት ሰጥተው የተናገሩ ቢሆንም፣ አንዳንድ ጊዜ ግን "ማድረግ አለብህ" ብለዋል።
አሜሪካ በኢራን ላይ ጥቃት ልትሰነዝር እንደምትችል ስጋት የገባቸው በርካታ አገራት አርብ ዕለት በአካባቢው ላሉ ዜጎቻቸው ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል።
ዩናይትድ ኪንግደም በቴህራን ከሚገኘው ኤምባሲዋ ሠራተኞቿን ለጊዜው አስወጥታለች። ወደ እስራኤልም "አስፈላጊ ካልሆነ በስተቀር ሁሉም ጉዞዎች" እንዳይደረጉ በሚል የጉዞ መመሪያዋን አሻሽላለች።
ቻይና፣ ሕንድ እና ካናዳን ጨምሮ ሌሎች አገራት ዜጎቻቸው ጦርነቱ ሊከሰት ስለሚችል በተቻለ ፍጥነት ከኢራን ለቅቀው እንዲወጡ አሳስበዋል።
ጀርመን ዜጎቿ ወደ እስራኤል እንዳይጓዙ ስትመክር ፈረንሳይ ደግሞ ባይጓዙ መልካም መሆኑን ለዜጎቿ ገልጻለች።
ይህ በእንዲህ እንዳለ አሜሪካ በኢራን የሚገኙ ዜጎቿን "በፍጥነት" ለቅቀው እንዲወጡ አሳስባለች።
በእስራኤል የሚገኘው ኤምባሲዋ ወሳኝ ያልሆኑ ሠራተኞች እና ቤተሰቦቻቸው አገሪቱን ለቅቀው መውጣት እንደሚችሉ በመግለጽ ይህንንም "የንግድ በረራዎች ሳይቋረጡ" እንዲያደርጉት መክሯል።
ትራምፕ በቴህራን ላይ የኒውክሌር ፍላጎቷን በተመለከተ ስምምነት ላይ ካልተደረሰ ወታደራዊ እርምጃ እንደሚወስዱ አስጠንቅቀዋል።
አሜሪካ በአውሮፓውያኑ 2003 ኢራቅን ከወረረች ወዲህ በመካከለኛው ምሥራቅ ግዙፍ ነው የተባለ ወታደራዊ ኃይል አሰማርታለች።
ኢራን ደግሞ ጥቃት የሚፈጸምባት ከሆነ ምላሽ ለመስጠት ዝታለች።
ዋሽንግተን እና አጋሮቿ ኢራን የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ለማምረት እየተንቀሳቀሰች እንደሆነ ይጠረጠራሉ። ቴህራን ግን ይህንን በተደጋጋሚ አስተባብላለች።
ምንም እንኳን ያላትን ዩራኒየም ጦር መሣሪያ ለማምረት በሚያስችላት ደረጃ ብታበለጽግም ፕሮግራሟ ለሰላማዊ ዓላማ መሆኑን ትገልጻለች።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ አርብ ዕለት ለጋዜጠኞች "ማበልጸግ አያስፈልግም ብያለሁ... ያ ጨዋነት የጎደለው ነው ብዬ አስባለሁ።"
ትራምፕ ይህንን ያሉት የኦማን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባድር አልቡሳይዲ ቴህራን የበለፀገ ዩራኒየም ላለማከማቸት መስማማቷን በመግለጻቸው ነው። ይህም "ዩራኒየም ማበልጸግ ላይ የሚደረገውን ክርክር እርባና የሌለው ያደርገዋል" ብለዋል።
አልቡሳይዲ "የበለፀገ ዩራኒየም ማከማቸት ካልቻሉ ቦምብ መሥራት የሚችሉበት ምንም መንገድ የለም" ሲሉ ለሲቢኤስ ኒውስ ተናግረዋል።
ሐሙስ ዕለት የአሜሪካ እና የኢራን ባለሥልጣናት በጄኔቫ በተካሄደው ከፍተኛ የኒውክሌር ድርድር "ተጨባጭ ለውጥ" እንዳሳየ ተናግረው ነበር። ነገር ግን ጦርነትን የሚያስቀር ስምምነት የመደረሱ ዕድል አሁንም ግልጽ አይደለም።
አልቡሳይዲ እንዳሉት ሁለቱ ወገኖች ድርድሩን ከፕሬዚዳንቶቻቸው ጋር ከተመካከሩ በኋላ "በቅርቡ" ለመቀጠል ዕቅድ ያላቸው ሲሆን፣ በሚቀጥለው ሳምንት በቪየና ቴክኒካዊ ውይይቶች እንደሚካሄዱ ተናግረዋል።
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ በበኩላቸው "ጥሩ ለውጥ" መታየቱን ቢናገሩም፣ በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ከስምምነት ቢደረስም በሌሎች ጉዳዮች ላይ ግን አሁንም ልዩነቶች አሉ ብለዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከአንድ ሳምንት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ተጨማሪ ድርድሮች እንደሚደረጉ ተናግረዋል።
ፕሬዚዳንት ትራምፕ አርብ ዕለት የሰጡት አስተያየት ከአሜሪካ የተሰማ የመጀመሪያው ይፋዊ ምላሽ ነው።















