በአንድ ጀንበር ሚሊየነር የሆነው ታንዛኒያዊ ሌላ 2 ሚሊዮን ዶላር አገኘ

የፎቶው ባለመብት, Tanzania Ministry of Minerals
በጥቃቅንና አነስተኛ ደረጃ ተደራጅቶ ማዕድን ቆፋሪ ሆኖ ሲሰራ በለስ ቀንቶት በዓለም እጅግ ውድ ማዕድን አግኝቶ የነበረው ታንዛኒያዊ ሌላ ሚሊዮኖችን ወደ ኪሱ አስገብቷል፡፡
ሳኒኒዩ ላይዘር ባለፈው ሰኔ ነበር በድንገት ታንዛናይት የሚባልና ምናልባትም በሰሜን ታንዛኒያ ብቻ የሚገኝ እጅግ የከበረ ድንጋይ አግኝቶ በአንዲት ጀንበር የናጠጠ ሀብታም የሆነው፡፡
በሰኔ ወር ያገኛቸውን ሁለት የከበሩ ድንጋዮች በሦስት ሚሊዮን ተኩል ዶላር ሽጧቸው ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ሌላ የከበረ ድንጋይ በሁለት ሚሊዮን ዶላር ሽጦታል፡፡
የዚህ ሰው ሀብትም በአንድ ጊዜ አምስት ሚሊዮን ዶላር ተኩል ደርሷል፡፡
አሁን ያገኘው ማዕድን 6.3 ኪሎ ግራም የሚመዝን ነው፡፡ ላለው ይጨመርለታል ነው ነገሩ፡፡
ታንዛናይት ማዕድን ውድ ጌጣ ጌጦችን ለመሥራት የሚያገለግል የከበረ ድንጋይ ነው፡፡
በዓለም ላይ በሚቀጥሉት 20 ዓመታት ከምድር ይጠፋሉ ከሚባሉ ማዕድኖች አንዱ ሲሆን በምድር ላይ የቀረው ታንዛናይት መጠን እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡
ማዕድኑ በተለያዩ ቀለማት ሊገኝ ይችላል፡፡ አረንጓዴ፣ ቀይ፣ ሐምራዊና ሰማያዊ ቀለማት አሉት፡፡ የዋጋው ውድነት የሚወሰነው በቀለሙ ድምቀትና ጥራት ነው፡፡ ደማቅ ቀለም ያለው ታንዛናይት ውድ ዋጋ ያወጣል፡፡
አቶ ላዚየር ጥቃቅንና አነስተኛ ማዕድን አውጪዎችን' እኔን አርአያ በማድረግ ተስፋ ሳትቆርጡ ቆፍሩ' ብሏቸዋል፡፡
ማዕድን አውጪዎቹ የከበረ ድንጋዩን ሲያገኙ በውድ ዋጋ የሚሸጡት ለመንግሥት በሕጋዊ መንገድ ነው፡፡
የቢቢሲው አቡባካር ፋማኡ ከታንዛንያ ዋና ከተማ ዶዶማ እንደዘገበው በርካታ ጥቃቅንና አነስተኛ ማዕድን ቆፋሪዎች መንግሥት ክፍያ ያዘገይብናል ብለው ቅሬታ ያቀርባሉ፡፡
ባለፈው ሰኔ 9.2 ኪሎ ግራምና 5.8 ኪ.ግራም የሚመዝኑ ሁለት የገበሩ ድንጋዮችን ካገኘ በኋላ አቶ ላይዘር ቅልጥ ያለ ድግስ አዘጋጃለሁ፣ የደስ ደስም አበላለሁ ብሎ ነበር ለቢቢሲ፡፡
ሰኞ ለታ ግን ሐሳቡን እንደቀየረ ተናግሯል፡፡ ከድግስ ይልቅ በአገሬ በማንያራ ገጠር ሲማንጂሮ ቀበሌ ገበሬ ማኅበር አንድ ትምህርት ቤትና አንድ የጤና ማዕከል እገነባለሁ ብሏል፡፡
በሰኔ ወር ለቢቢሲ ‹ሚሊየነር መሆኔ አኗኗሬን አይለውጠውም፣ ሁለት ሺ የሚሆኑ ከብቶቼን እየተንከባከብኩ ሕይወቴን እቀጥላለሁ ብሎ ነበር፡፡
ሚሊየነር በመሆኔ አደጋ ይደርስብኛል ብዬም አልሰጋም፣ ጥበቃም አያስፈልገኝም ሲል ለቢቢሲ አረጋግጧል፡፡
በጥቃቅንና አነስተኛ የተደራጁ ታንዛንያዊያን ከመንግሥት ፍቃድ አግኝተው በማዕድን ማውጣት ቢሰማሩም ሕገ ወጥ ማዕድን አውጪዎችም የዛኑ ያህል በርካታ ናቸው፡፡ በተለይም ትልልቅ የማዕድን አውጪ የውጭ ኩባንያዎች በሚሰሩባቸው አካባቢዎች በርካታ ሕገ ወጥ ማዕድን ቆፋሪዎች ይሰማራሉ፡፡
በጎርጎሳውያኑ 2017 አወዛጋቢው የታንዛንያ ፕሬዝዳንት ጆን ማጉፉሊ ወታደሮቻቸው 24 ኪሎ ሜትር አጥር በማንያራ ሜሬላኒ የማዕድን አካባቢ እንዲያጥሩ አዘዋቸው ነበር፡፡ ይህ አካባቢ በአለም በብቸኝነት ታንዛናይት የከበረ ድንጋይ ይገኝበታል ተብሎ የሚታሰብ ቦታ ነው፡፡
አጥሩ ከታጠረ ከዓመት በኋላ መንግሥት በታንዛናይት ማዕድን የማገኘው ገቢ ጨምሯል፣ አጥር ማጠሬ በጄ ሲል አስታውቋል፡፡












