ኮሮናቫይረስ፡ ፈተና ውስጥ የገባው የግብርና ዘርፍ

የአይቮሪኮስት አርሶአደሮች

የፎቶው ባለመብት, ISSOUF SANOGO

ከኮሮረናቫይረስ ወረርሽኝ በኋላ በርካታ ነገሮች ተቀያይረዋል። ሰው የማይንቀሳቀስባቸው ዋና ጎዳናዎች ታይተዋል፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የሚታደሟቸው የእግር ኳስ ውድድሮች ያለ ድጋፍ ተካሂደዋል፣ የዓለም መሪዎች ሳይቀር የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ አድርገው ታይተዋል።

ምናልባት ለብዙዎችም ኮሮረናቫይረስ ሲባል በጭንቅላታቸው የሚመጡት ምስሎች እነዚህ ሊሆኑ ይችላሉ። ነገር ግን ወረርሽኙ በአይናችን ከምናያቸውና በቅርቡ ከምናስተውላቸው ነገሮች በተጨማሪ የበርካቶችን ሕይወት ከስረ መሰረቱ ቀይሯል፤ እንዳልነበር አድርጎ አበላሽቷል።

ነገር ግን ወረርሽኙ ያስከተለው ጉዳት በሁሉም አገራትና አህጉራት ተመሳሳይ አይደለም። እንዳውም ንጽጽሩ በበርካቶች ዘንድ ግርምትን የፈጠረ ነው።

አፍሪካ ውስጥ ብቻ በ36 አገራት የሚገኙ 73 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ ከባድ የምግብ እጥረት የጋጠማቸው ሲሆን በአውሮፓ ግን ግማሽ ሚሊየን የሚሆኑት ብቻ የምግብ እጥረት እንዳጋጠማቸው የዓለም ምግብ ፕሮግራም ገልጿል።

ከዚህ በፊት በኢቦላ ወረርሽኝ ስትሰቃይ የነበረችው ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና በእርስ በርስ ጦርነት የምትታመሰው ደቡብ ሱዳን ደግሞ በወረርሽኙ ምክንያት ከፍተኛ የምግብ እጥረት ያጋጠማቸው አገራት ናቸው።

በአፍሪካ የሚገኙ ገበሬዎች በክረምት ወር የሚዘሩትን ዘር ማግኘት ያልቻሉ ሲሆን በአሜሪካ ደግሞ የእርድ አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶች በመዘጋታቸው ከብቶቻቸውን ሳይፈልጉ ለማቆየት ተገድደዋል፣ ወተት ገዢ አጥተው ምርታቸውን ለመድፋት ተገድደዋል።

የኮሮረናቫይረስ ወረርሽኝም በዓለማችን ላይ ያለውን የምግብ ስርጭት ስርአት ቁልጭ አድርጎ አሳይቷል።

ባደጉት አገራት ከግብርና ስራ ጋር የተከሰቱት ችግሮች ቀላል የሚባሉ ባይሆኑም ድሀ በሚባሉትና በማደግ ላሉት አገራት ግን ጉዳቱ ከፍተኛ ነው።

በድሆቹ አገራት ግብርና በብዛት የጉልበት ስራ ላይ የተንጠለጠለ ሲሆን ዘር ከመዝራት አንስቶ እስከ መሰብሰብ ድረስ ባህላዊ በሆነና በርካታ ሰዎች በሚያሳትፍ መልኩ ነው የሚካሄደው።

በአውሮፓ ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከሰት ጋር ተያይዞ ተግባራዊ በተደረጉት የእንቅስቃሴ ገደብና ሌሎች እርምጃዎች ምክንያት በግብርናው ዘርፍ ላይ በጊዜያዊነት ተቀጥረው ይሰሩ የነበሩ በርካታ ሰዎች ሕይወት የተመሰቃቀለ ሲሆን ምርቱን የሚሸጡትም ሰዎች ቢሆኑ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

ይህንን ተከትሎም የምግብ ስርጭቱ ላይ ከፍተኛ አለመረጋጋትና እጥረት ተከስቷል።

ለምሳሌ ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ 75 ሺ ሰዎች በጊዜያዊነት በግብርና ስራ ላይ ተቀጥረው ይሰሩ ነበር። አብዛኛዎቹ ደግሞ ከሌሎች የአውሮፓ ሕብረት አባል አገራት የመጡ ናቸው።

ወረርሽኙን ተከትሎ በተጣሉ የእንቅስቃሴ ገደቦችና ሌሎች የጥንቃቄ እርምጃዎች ምክንያት ታዲያ እነዚህ ሰራተኞች በስራ ቦታቸው ላይ መገኘት ባለመቻላቸው አብዛኛዎቹ ወደመጡባቸው አገራት ተመልሰዋል።

ገበሬዎችን የጉልበት ስራውን የሚሰራላቸው ሰው በማጣታቸው ተቸግረዋል።

በአጠቃላይ በአውሮፓ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ጊዜያዊ ሰራተኞች ከስራ ውጪ መሆናቸውን ተከትሎ የግብርናው ዘርፍ ከፍተኛውን ጉዳት አስተናግዷል።

በተመሳሳይ በአውስትራሊያም ቢሆን በአትክልት ምርት ላይ ተሰማርተው ከሚገኙ ሰዎች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በጊዜያዊነት ተቀጥረው የሚሰሩ ሲሆኑ በአሜሪካ ደግሞ 10 በመቶ የሚሆነውን ቁጥር ይይዛሉ።

በካናዳ ያሉ ትልልቅ ማሳዎች ደግሞ ከ60 ሺ በላይ የሚሆኑ ከሌሎች አገራት የመጡ ሰራተኞችን ቀጥረው ያሰራሉ። በብራዚል ደግሞ ቡና አምራች ገበሬዎች በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን በጊዜያዊነት ቀጥረው ያሰሩ ነበር።

ነገር ግን በእንቅስቃሴ ገደቡ ምክንያት እነዚህ ሰዎች በስራ ገበታቸው ላይ መገኘት አለመቻላቸው ዘርፉ ላይ ከሚያስከትለው ጉዳት በተጨማሪ ሕይወታቸውን በዚሁ ስራ ላይ ላደረጉ ሰዎች ትልቅ ፈተና ሆኖባቸዋል።

ከግብርናው ዘርፍ ሳንወጣ የከብት አርቢዎች ሕይወትም ቢሆን በዚሁ ወረርሽኝ ምክንያት ተጎድቷል። ምንም እንኳን ይሄ ዘርፍ በተለይም እርድ ላይ ያለው ሂደት ከኮሮረናቫይረስ ወረርሽኝ በፊትም ከፍተኛ ንጽህና የሚፈልግ ቢሆንም ከኮቪድ-19 በኋላ ግን ነገሮች ከባድ ሆነዋል።

በአውሮፓ 90 በመቶ የሚሆነው የስጋ ምርት እዛው የተመረተበት አገር ውስጥ አልያም አውሮፓ ውስጥ ነው ጥቅም ላይ የሚውለው። ነገር ግን ይህ ማለት ከእንቅስቃሴ ገደቡ ጋር በተያያዘ ችግር አያጋጥመውም ማለት አይደለም።

ምርቱ ተቀናባብሮ ወደ ተጠቃሚዎች እስከሚደርስበት ባሉት የሂደት ስርአቶች ውስጥ የሚሰሩ በርካታ ሰዎች ከስራ ውጪ ሆነዋል አልያም ስራቸውን በአግባቡ እንዳይሰሩ ሆነዋል። እዚህም ጋር ተጠያቂው ኮሮረናቫይረስ ነው።

በአፍሪካ ደግሞ በግብርና፣ ማዕድን እና ግንባታ ዘርፎች ላይ የኮሮናቫይረስ ጉዳትን ለመቀነስ አገራት ቀጣይነት ያለውና ውጤታማ እርምጃ በፍጥነት መውሰድ ግድ ይላቸዋል።

ግብርና የአህጉሪቱን ኢኮኖሚ በእጅጉ የሚደግፍ ዘርፍ እንደመሆኑ ደግሞ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ባለሙያዎች ከወዲሁ እያሳሰቡ ነው። በዚህም ምክንያት አብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገራት የዝናብ ወቅት ሲቃረብ የገበሬዎች ማሳ በተቻለ መጠን በሰብል እንዲሞላ ማድረግ አለባቸው።

የአብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገራት ኢኮኖሚ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ መር ሽሽግር በሚያደርጉበት በዚህ ወቅት የኮሮረናቫይረስ ወረርሽኝ መከሰት ትልቅ ስጋት ነው።

ከዚህ በተጨማሪ መንግሥታት የከተማ ግብርና ላይ ያላቸውን መቀየር ግድ ይላቸዋል። ምክንያቱም ለብዙ ዓመታት ሲሰራበት የነበረውን የግብርና ስርአት ይዞ መቀጠል ስለማይቻል ዜጎች በቀላሉ አትክልትና ፍራፍሬዎችን በከተሞች አካባቢ እንዲ|ያመርቱ ማድረግ ከኮሮረናቫይረስ በኋላም አዋጭ አካሄድ ይሆናል።