በስደተኞች የተነሳ የካናዳ የሕዝብ ቁጥር በአንድ ሚሊዮን ጨመረ

የአሁኑ የሕዝብ ብዛት ዕድገት ካናዳ ከአውሮፓውያኑ 1957 ወዲህ ያየችው ከፍተኛው ነው ተብሏል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የአሁኑ የሕዝብ ብዛት ዕድገት ካናዳ ከአውሮፓውያኑ 1957 ወዲህ ያየችው ከፍተኛው ነው ተብሏል

ከረዥም ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የካናዳ ሕዝብ ቁጥር በአንድ ሚሊዮን ጨመረ።

መንግሥት እንዳለው ከሆነ ባለፈው አንድ ዓመት ብቻ የካናዳ ሕዝብ ቁጥር ከ38 ሚሊዮን 516 ሺህ 138 ወደ 39 ሚሊዮን 566 ሺህ 248 ከፍ ብሏል።

ካናዳ እንደ ጎርጎሮሲያውያኑ አቆጣጠር ከ1957 ወዲህ እንዲህ ዓይነት የሕዝብ ዕድገት አጋጥሟት አያውቅም ተብሏል።

የሥነ ሕዝብ ዕድገቷ ለመጀመሪያ ጊዜ 2.7 በመቶ የሆነውም ከረዥም ዓመታት በኋላ ነው።

ይህ ድንገተኛ የሕዝብ ቁጥር ጭማሪ የመጣው ደግሞ በዋናነት የካናዳ መንግሥት ሠራተኛ ኃይል ፍለጋ በርካታ ስደተኞችን ለመቀበል በመወሰኑ ነው።

ካናዳ በዕድሜ የገፉ ሚሊዮን ዜጎችን ለመደገፍ በስደተኞች ላይ ጥገኛ ሆናለች።

የካናዳ ስታትስቲክስ ባለሥልጣን እንደሚለው ስደተኞችን የመቀበሉ ነገር በጎ ጎን ቢኖረውም በቤት አቅርቦት፣ በመሠረተ ልማት እና በትራንስፖርት ረገድ ጫና የተፈጠረባቸው የካናዳ አካባቢዎች አሉ ብሏል።

ለካናዳ ሕዝብ በአንድ ሚሊዮን መጨመር 96 እጁን የሚይዘው የስደተኞች ወደ አገር ውስጥ በስፋት መግባታቸው ሲሆን፣ ቀሪው ግን የአገሬው ሕዝብ የወሊድ ምጣኔ ማደግ ያመጣው ነው።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ መንግሥታቸው ስደተኞችን በብዛት እንደሚቀበል ወደ ሥልጣን በመጡ ማግስት ነበር ያስታወቁት። ይህም በፈረንጆቹ 2015 መሆኑ ነው።

ባለፈው ዓመት ደግሞ መንግሥታቸው በ2025 ግማሽ ሚሊዮን ስደተኞችን እንደሚቀበል አስታውቆ ነበር።

የካናዳ መንግሥት ከዚህ ሌላ በዩክሬን ጦርነት የተፈናቀሉ በርካታ ዜጎችን የተቀበለ ሲሆን፣ በተመሳሳይ ከአፍጋኒስታን እንዲሁም ከመሬት መንቀጥቀጡ በኋላ በቱርክ እና በሶሪያ ችግር ላይ የወደቁ ዜጎችንም ተቀብሏል።

እስከ አሁን የካናዳ መንግሥት ከደረሱት አንድ ሚሊዮን ማመለከቻዎች ወደ 600 ሺህ የሚሆኑትን ተቀብሎ አጽድቋል።

ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ 130 ሺህ የሚሆኑት ካናዳ ደርሰዋል።

የስደተኞችን ወደ ካናዳ በብዛት የመግባት ጉዳይ በካናዳ የፖለቲካ ፓርቲዎች መነጋገሪያ እየሆነ መጥቷል።

በቶሮንቶ ዩኒቨርስቲ የሚያስተምሩት ፕሮፌሰር ሃንሰን ለቢቢሲ እንዳሉት ካናዳ ብሔራዊ ማንነቷ “በብዝሃ ባሕል ማዕከልነት” ነው የተገነባው።

ይህ በተለይ ከአሜሪካ እና ከአውሮፓ አገራት ጋር ስትነጻጸር ልዩ ያደርጋታል ይላሉ።

በዚህ የተነሳ በአገሬው ዘንድ ስደተኞችን በተመለከተ በአመዛኙ አዎንታዊ አመለካከት አለ።

ካናዳ እንዲህ እንደ ዘንድሮ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር መመንደግ ያየችው ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ እና የሃንጋሪ አብዮትን ተከትሎ በተፈጠሩ ሁኔታዎች ነበር።

ይህን ተከትሎ በርካታ ሕዝብ ወደ ካናዳ ተሰዶ ነበር።

ካናዳ በ2022 ብቻ 437,000 ስደተኞችን ተቀብላለች።

ይህን የካናዳ የሕዝብ ቁጥር ጭማሪ ተከትሎ ቡድን ሰባት (ጂ7) ተብለው ከሚጠሩ ብልጹግ አገራት በሕዝብ ዕድገት ግስጋሴ ቁጥር አንድ አገር ሆናለች።

የካናዳ የሕዝብ ዕድገት በዚሁ ከቀጠለ በ26 ዓመት ውስጥ አሁን ያለውን እጥፍ እንደሚደርስ ይጠበቃል።