ካናዳ በመንግሥት ንብረት ቲክቶክ መጠቀም ክልክል ነው አለች

የቲክ ቶክ አርማ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ካናዳ ከማክሰኞ የካቲት 22፣ 2015 ዓ.ም ጀምሮ መንግሥት በገዛው ‘ኤሌክትሮኒክስ’ ቲክቶክ መጠቀም ክልል ነው አለች።

ይህ ውሳኔ የተላለፈው የካናዳው ዋና የመረጃ መኮንን መተግበሪያው “ለግላዊ መረጃ ደኅንነት አደጋ ነው” የሚል ጥናት ምክረ-ሐሳብ ከሰጡ በኋላ መሆኑ ተሰምቷል።

የቲክቶክ ቃለ አቀባይ በካናዳ መንግሥት ውሳኔ ኩባንያው እንደተከፋ ገልጠዋል።

የአውሮፓ ኮሚሽን ተመሳሳይ ውሳኔ ካሳለፈ ከቀናት በኋላ ነው የካናዳ መንግሥት ይህን ይፋ ያደረገው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ እንዳሉት መተግበሪያው ለመረጃ ደኅንነት አስጊ እንደሆነ ጠቋሚ ፍንጮች ስላሉ ነው ውሳኔው የተላለፈው።

“ይህ የመጀመሪያው እርምጃ ሊሆን ይችላል። ምናልባትም የመጨረሻውም ሊሆን ይችላል”ሲሉ ሰኞ ዕለት በሰጡ ጋዜጣዊ መግለጫ ተናግረዋል።

ቲክቶክ ግላዊ መረጃን በመበዝበዝ ከፍተኛ ወቀሳ የሚደርስበት ሲሆን ከቻይና መንግሥት ጋር ያለው ቁርኝትም ያስተቸዋል።

አጫጭር ተንቀሳቃሽ ምስሎች ማጋሪያው መድረክ ባይትዳንስ የተሰኘው ኩባንያ ንብረት ነው።

የዩናይትድ ስቴትስ የፌዴራሉ መንግሥት ሠራተኞች ቲክቶክን እንዳይጠቀሙ የተከለከሉት ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት ነበር።

ሰኞ ዕለት ዋይት ሐውስ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በሚቀጥሉት 30 ቀናት ከኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎቻቸው ቲክቶክን እንዲያስወግዱ ትዕዛዝ ሰጥቷል።

በርካታ የአሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎች መተግበሪያውን ከኔትዎርኮቻቸው ላይ ያስወገዱት ሲሆን በሕንድና በሌሎች የእስያ ሃገራትም የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ተመሳሳይ እርምጃ እየወሰዱ ነው።

ኩባንያው፤ የቻይና መንግሥት መረጃውን እንደማያገኝበትና ቻይና ያለው ቲክቶክ ከሌላው ዓለም ፈፅሞ የተለየ መሆኑን ደጋግሞ ይናገራል።

ነገር ግን ባለፈው ዓመት ኩባንያው አንዳንድ የቻይና ቲክቶክ ሠራተኞች የአውሮፓውን መረጃ ሊያገኙ እንደሚችሉ አምኗል።

የአውሮፓ ሕብረት ኮሚሽን ሠራተኞች ከመጋቢት 15 ጀምሮ ቲክቶክን በኮሚሽኑ ንብረት መጠቀም አይችሉም።

የካናዳ የመረጃ ደኅንነት ተቆጣጣሪዎች መተግበሪያው “አስፈላጊ የሚባሉ” መረጃዎችን ያለተጠቃሚዎች ፈቃድ እየሰበሰበ መሆን አለመሆኑን ለማጣራት ምርመራ ጀምረዋል።

ቶሮንቶ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ባስጠናው ጥናት መሠረት ከካናዳ ሕዝብ ሩብ ያህሉ ቲክቶከ ይጠቀማል።

የካናዳ ግምዣ ቤት ቦርድ ፕሬዝደንት የሆኑት ሞና ፎርቲዬ መንግሥታቸው “የመንግሥትን መረጃዎች ለመጠበቅ ቁርጠኛ” መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህ ሳምንት መንግሥት ገዝቶ ለሠራተኞች ካደላቸው ተንቀሳቃሽ ስልኮች ውስጥ ቲክቶክ ይጠፋል።

ምንም እንኳ መተግበሪያው መረጃን ሊያገኝ እንደሚችል መረጃዎች ቢኖሩም እስካሁን ድረስ የመንግሥት መረጃዎችን ማግኘት ችሏል ወይ የሚል አልተጣራም ብለዋል ባለሥልጣኗ።

የግምዣ ቤት ቦርድ ፕሬዝደንትና ዋና የመረጃ ኃለቃ የሆኑት ሞና “ቲክቶክን በተንቀሳቃሽ ስልክ መጠቀም ስልኩ ላሉት መረጃዎች አጋልጦ ሊሰጥ ይችላል” ብለዋል።

ቲክቶክ ይህን ውሳኔ ተከትሎ ባወጣው መግለጫ የካናዳ መንግሥት ኩባንያውን ሳያማክር አሊያም በቂ ማስረጃ ሳይኖረው ይህን ማድረጉ አሳዛኝ መሆኑን ገልጧል።