ከፖሊስ ለማምለጥ በተደጋጋሚ የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና ያደረገው ዕፅ አዘዋዋሪ ተያዘ

ፊቱን በቀዶ ሕክምና ያስቀየረው ታይላንዳዊው ዕፅ አዘዋዋሪ

የፎቶው ባለመብት, THAILAND NATIONAL POLICE

የምስሉ መግለጫ, ፊቱን በቀዶ ሕክምና ያስቀየረው ታይላንዳዊው ዕፅ አዘዋዋሪ

ከሕግ ክትትል ለማምለጥ በርካታ ጊዜ በተደጋጋሚ የፊቱን ገጽታ ለመቀየር የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና ያደረገው ታይላንዳዊ ዕፅ አዘዋዋሪ በቁጥጥር ሥር ዋለ።

ታይላንዳዊው ዕፅ አዘዋዋሪ ‘መልከ መልካም ኮሪያዊ’ መስሎ ከፖሊስ ለማምለጥ ያደረገው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል።

ሳሃራት ሳዋንግጃንግ ፊቱን ብቻ ሳይሆን ስሙን ጭምር 'ጂሚን ቼዎንግ' በሚል መጠሪያጠሪያ ቀይሮ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል።

ፊቱን በፕላስቲ ቀዶ ሕክምና አስቀይሮ ዕፁን ሲያዘዋውር የነበረው ይህ ግለሰብ፣ ባለፈው ሳምንት ባንግኮክ ውስጥ በፖሊስ ቁጥጥር ውሏል።

የታይላንድ ፖሊስ የ25 ዓመቱን ተጠርጣሪ በቁጥጥር ሥር ለማዋል ለሦስት ወራት ያክል ሲያሳድደው ነበር።

ፖሊሰ እንደሚለው የግለሰቡ የቀድሞ ፊቱ በቀዶ ሕክምናው ምክንያት ሙሉ በሙሉ ተቀይሯል።

ኤክስታሲ የተሰኘውን ዕፅ ለሻጮች እና ገዢዎች ሲያከፋፍል በነበረበት ጊዜ ያገኘውን መረጃ ተከትሎ ነው ፖሊስ ግለሰቡን የያዘው።

የዐይን እማኞች ሰውዬውን ‘መልከ መልካሙ ኮሪያዊ’ እያሉ እንደሚጠሩት ፖሊስ ገልጿል።

መልኩን ብቻ ሳይሆን ስሙንም የቀየረው ዕፅ አዘዋዋሪው በቁጥጥር ሥር ከዋለ በኋላ ማንነቱን የቀየረው ደቡብ ኮሪያ ገብቶ ሕይወትን እንደ አዲስ መጀመር ፈልጎ እንደሆነ ለፖሊስ ተናግሯል።

ሳሃራት፤ ሕገ-ወጥ ዕፅ ወደ አገር ውስጥ በማስገባት ወንጀል ተከሷል።

ኤምዲኤምኤ አሊያም ኤክስታሲ የተሰኘውን ዕፅ ቁጥጥር በማይደረግበት የኢንተርኔት ገጽ [ዳርክ ዌብ] አማካይነት ማዘዙን እና በክሪፕቶከረንሲ መክፈሉን አምኗል።

ሰውዬው ከዚህ ቀደም ሦስት ጊዜ በሕግ ቁጥጥር ሥር ውሎ ነበር።

በአንድ ወቅት ኃይል በመጠቀም ወንጀል ተከሶ ሳለ ፖሊስ 2 ኪሎ ግራም የሚመዝን ፈሳሽ ዕፅና 290 የኤክስታሲ እንክብል አግኝቶበት ነበር።

ነገር ግን በቁጥጥር ሥር ከዋለበት አምልጦ ፊቱን በቀዶ ሕክምና ማስቀየሩን ፖሊስ ደርሶበታል።

የታይላንድ ፖሊስ ሜጀር ጄኔራል ታማሱቴ “ባንግኮክ ውስጥ ላለው የኤምዲኤምኤ ወረርሽኝ አንዱ ተጠያቂ ነው” ነው ሲሉ ግለሰቡን ገልፀውታል።

“ይህ የዕፅ አዘዋዋሪዎች አለቃ ነው። በ25 ዓመቱ ኤምዲኤምኤ ከአውሮፓ እያስገባ ነበር። በውጭ አገራት ሌሎች ተጠርጣሪዎች እንዳሉ እናምናለን። ምርመራችንን እንቀጥላለን” ብለዋው ሜጀር ጀነራሉ።