የናይጄሪያ ፕሬዝዳንታዊ ውጤት መታወቅ ጀመረ

የፎቶው ባለመብት, EPA
በናይጄሪያ ወታደራዊ አገዛዝ እአአ 1999 ካበቃ በኋላ ከፍተኛ ፉክክር ታይቶበታል የተበላው የምርጫ ውጤት መታወቅ ጀምሯል።
በበርካታ ምርጫ ጣቢያዎች የምርጫ ውጤቶች እየተለጠፉ ሲሆን፤ ከደቡብ-ምዕራብ ኤኪቲ ግዛት የወጡ ይፋዊ ውጤቶች የገዢው ፓርቲ እጩ ቦላ ቲኑቡ አሸናፊ መሆናቸውን አሳይተዋል።
በዚህ ምርጫ ሦስት እጩዎች ጠንካራ ተፎካካሪ እንደሚሆኑ ይጠበቃል። ፒተር ኦቢ ከሌበር ፓርቲ፣ ቦላ ቲኑቡ ከገዢው ኦል ፕሮግረሲቭ ኮንግረስ እና አቲኩ አቡበከር ከፒፕልስ ዴሞክራቲክ ኮንግረስ ናይጄሪያን ሊመሩ የሚችሉ ናቸው።
ከሦስቱ ፖለቲከኞች በተጨማሪ ሌሎች 15 ፕሬዝዳንታዊ እጩዎች በዚህ ምርጫ ተሳታፊ ሆነዋል።
አንድ እጩ አሸናፊ ለመሆን አብዛኛውን ድምጽ ማግኘት ወይም ደግሞ በናይጄሪያ 36 ግዛቶች ከተሰጡት ድምጾች በሁለት ሦስተኛ ግዛት ከተሰጠው ድምጽ 25 በመቶ ማግኘት ይኖርበታል።
ይህን ማግኘት የማይችል እጩ ካለ በ21 ቀናት ውስጥ ዳግም ምርጫ ይካሄዳል።
በአፍሪካ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ድምጽ ሰጪ ተሳትፎ በሚያደርግበት በዚህ ምርጫ በተለይ ናይጄሪያውያን ወጣት ድምጽ ሰጪዎች በከፍተኛ ቁጥር ወጥተው መምረጣቸው ተገልጿል።
በአንዳንድ የአገሪቱ ክፍሎች ቅዳሜ ዕለት ባጋጠሙ መዘግየቶች እና ጥቃቶች የድምጽ አሰጣጥ ስነ-ስርዓት እስከ ትናንት እሁድ ድረስ እንዲራዘም ተደርጓል።
በሌሎች ስፍራዎች ደግሞ የድምጽ አሰጣጥ ሊጠናቀቅ ሰዓታት እስከ ቀሩበት ድረስ መራጮች ድምጽ አልሰጡም ነበር።
በመዲናዋ አቡጃ ደግሞ መራጮች ድምጽ ለመስጠት ሰዓታት ለመጠበቅ ተገደዋል። ለመጀመሪያ ግዜ የምትመርጠው ሱዛን ኤክፖህ ለቢቢሲ ስትናገር ድምጽ ለመስጠት በምርጫ ጣቢያ ለ13 ሰዓታት መጠበቋን ተናግራለች።
ሪቨርስ እና ሌጎስ በተሰኙ ግዛቶች ደግሞ ውጥረት ሰፍኗል። የውጥረቱ ምክንያት ደግሞ ፖለቲከኞች ድምጽ ቆጠራ ላይ መጭበርበር እንዳያጋጥም ደጋፊዎቻቸው ወደ ምርጫ ጣቢያዎች ሄደው ቆጠራውን እንዲከታተሉ መልዕክት ማስተላለፋቸው ነው።
በአስር ሺዎች ከሚቆጠሩ ምርጫ ጣቢያዎች የተሰባሰቡ ውጤቶች እየተደምሩ ነው። የምርጫ ኃላፊዎች የምርጫ ውጤቶችን ይዘው ወደ አቡጃ ካመሩ በኋላ ከመዲናዋ የየግዛቱ አሸናፊዎች ይፋ ይደረጋሉ።
አጠቃላይ የምርጫ ውጤቱ ከጥቂት ቀናት በኋላ ይፋ ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል።
ምርጫውን የሚያሸንፍ እጩ፤ ናይጄሪያ ላይ ለተጋረጡት የኢኮኖሚ ችግር፣ ለወጣቶች ሥራ አጥነት እና ሰፊ የደኅንነት እጦች ምላሽ መስጠት ይኖርበታል።












