“ቦረና ውስጥ ያለው ሁኔታ ለማየት እንኳን የሚከብድ ነው” አብነት ከበደ

የፎቶው ባለመብት, Master Abinet Kebede
በሚያከናውነው በጎ ሥራ የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎችን ቀልብ ስቧል። የደካማ እናቶች ጎጆ ገብቶ የጎደለውን አይቶ ሞልቷል።
ጠያቂ የሌላቸውን ህሙማን ሆስፒታል ተገኝቶ ጠይቋል።
ያለ እናት ልጆች የሚያሳድጉ አባቶችን፣ ያለ ጧሪ የቀሩ አረጋውያንን፣ ጎዳና ላይ ከልጆቻቸው ጋር የወደቁ እናቶችን ለመደገፍ የቻለውን ሁሉ አድርጓል።
ሱቅ ወስዶ፣ ልብስ ገዝቶ፣ እግራቸውን ዝቅ ብሎ አጥቦ፣ ጫማ አጫምቷል። የታረዙትን አልብሷል።
ትርፍራፊ የናፈቃቸውን፣ ምግብ ቤት ወስዶ በክብር አብሯቸው ማዕድ ቆርሷል። ይህንን ሲያደርግ የሚያሳዩ አጫጭር ቪዲዎቹን በማኅበራዊ ሚዲያ በርካቶች ተቀባብለውታል።
በእነዚህ ቪዲዮዎች የሚታዩ ሕጻናት፣እናቶችና አባቶች ደስታ የሚጋባ ነው።
አሁን ደግሞ በድርቅ ክፉኛ ለተጎዳው የቦረና ሕዝብ የድጋፍ እጁን እየዘረጋ ይገኛል።
ይህ ወጣት ማስተር አብነት ከበደ ይባላል። ትውልድ እና እድገቱ በደቡብ ክልል፣ ከምባታ ጠንባሮ ዞን፣ ዱራሜ ከተማ ነው።
የሚተዳደረው በሞተር ሳይክል ስፖርት ነው።
በሞተር ሳይክል ላይ የሚከወኑ ትርዒቶችን እያሳየ የሚያገኘውን ገቢም ለበጎ አላማ ያውላል።
“በጎ ሥራ ለሁላችንም የተፈቀደ ነው” የሚለው አብነት፣ የበጎ ፈቃድ ሥራን የጀመረው ከልጅነቱ እንደሆነ ይናገራል። እርሱ እንደሚለው በጎ ማድረግን ከቤተሰቡ ተምሮት ነው ያደገው።
አብነት በጎ ሥራው ሌሎችን ያነሳሳል ብሎ በማኅበራዊ ሚዲያ ማጋራት ከጀመረ የተቆጠረው ስድስት ወራት ገደማ ቢሆንም ከዚህ በፊት በርካታ ሥራዎችን እንደሠራ ይናገራል።
“ቤት ለሌላቸው ለ17 ቤተሰብ ቤት ሰርተናል።ሥራ መሥራት ያልቻሉ፤ ነገር ግን አቅም ላላቸው ከ200 በላይ ሰዎች የሥራ ዕድል ፈጥረናል” ይላል።
ይህንን ሁሉ የሚያደርገው ግን ብቻውን አይደለም።
በውጭ እና በአገር ውስጥ ያሉ ሰዎችም እንደሚደግፉት ይናገራል።አደራ ለሚሰጡት አደራውን ይወጣል።
አብነት እንደሚለው በየሳምንቱ ተቸግረው ጎዳና ላይ ያሉ ሰባት ሰዎችን አቅሙ በሚፈቅደው መጠን ይረዳል።
ለዚህ ተግባሩ በአንድ ወር ውስጥ ከ1 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ እንደሚያደርግም ይናገራል።
“ይህ ሥራ መልካም እና ሃብታም ልብ ሲኖር ብቻ የሚደረግ ነው።ሰውን ለመርዳት የሚያነሳሳው መልካም ልብ ብቻ ነው። በጎ ለማድረግ ምንም ስሌት የለውም” ይላል።

የፎቶው ባለመብት, Master Abinet Kebede
“በቦረና ያለው ሁኔታ ለማየትም ጭምር የሚከብድ ነው”
ከአምስት ቀናት ገደማ በፊት ነበር።
አብነት አንድ ልብ የሚሰብር ምሥል በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ሲጋራ ተመለከተ።
በድርቅ በተጎዳው የቦረና አካባቢ አንዲት ሥጋቸው አጥንታቸው ላይ የተጣበቀ እና ኩርምት ብለው የተቀመጡ እናትን የሚያሳይ ምሥል።
ከቀኑ 9፡00 ሰዓት ገደማ ነበር።ያየው ምሥል እረፍት ነስቶት ዋለ። ሌሊቱን አልተኛም ነበር።
“የሚነጋ አልመሰለኝም ነበር” ይላል ያሳለፈውን ሌሊት ሲያስታውስ።ኮንትራት መኪና ይዞ ከሚኖርበት ዱራሜ ወደ ሻሸመኔ ጉዞ ጀመረ።
ከሌሊቱ 7፡00 ሻሸመኔ ገባ። እዚያ በቂ እረፍት እንኳን ሳይወስድ ከሌሊቱ 10፡00 ወደ ያቤሎ የሚያደርገውን ጉዞ ጀመረ።
“እያቆራረጥኩ ያቤሎ ከተማ ደረስኩ” ይላል።
እዚያ በማኅበራዊ ሚዲያ የሚያውቁት “ሰዎችን ለመርዳት ነው ወይ የመጣኸው?” ሲሉ በተስፋ ጠየቁት።
“አዎ! ትክክለኛ የሚረዱ ሰዎች ያሉበትን ቦታ አመላክቱኝ አልኳቸው” ይላል። ከዚያም ከከተማው ወጣ ብሎ በሚገኝ ሥፍራ አመራ።የአካባቢው ነዋሪዎች ከጠበቀው በላይ በባሰ ሁኔታ ውስጥ ሆነው እንዳገኛቸው አብነት ይናገራል።
“መሬቱ ደረቅ ነው።የሚበላም ሆነ የሚጠጣ የለም።ከብቶቻቸው አልቀዋል። ሰዎቹም አጥንታቸው ብቻ ነው የቀረው።ለማየት ጭምር ነው የሚከብደው” ብሏል በሥፍራው የታዘበውን ሲናገር።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በፎቶ ያያቸውን እናት ፍለጋ . . .
አብነት እንቅልፍ ነስተውት በሌሊት ጉዞ ያስጀመሩትን እና በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በምሥል ያያቸውን እናት ሊያገኛቸው ብዙ ጥረት አድርጎ እንደነበር ይናገራል።ነገር ግን “የጠየቅኳቸው ሁሉ በሕይወት እንደሌሉ ነው የነገሩኝ።” ብሏል።
ይህንን ሲሰማ ልቡ ክፉኛ ተሰበረ። ደርሶ አንዳች ነገር በማድረግ ቀና ሊያደርጋቸው ባለመቻሉ ከማዘን ውጪ ምርጫ አልነበረውም።
“ሌሎቹም ወደ ዚያው እየሄዱ ነው” ሲልም ቀሪዎቹን ለመርዳት የሸቀጦች ማከፋፋያ ሱቆች ወዳሉበት ወደ ያቤሎ ከተማ ተመልሶ አቅሙ የፈቀደውን በመግዛት እየረዳ እንደሚገኝ ለቢቢሲ አማርኛ ገልጿል።
“ከብቶች አሉ ማለት አይቻልም።የተወሰኑ አካባቢዎች ብቻ አንድ ሁለት ይታያሉ።ልጆቻቸው የሚበሉት አጥተው፣ ታመው፣ ተኝተው ይታያሉ። ሰውም ያለበት ሁኔታ ጥሩ ነው የሚባል አይደለም።
የሚቀርብላቸው እርዳታው በቂ አይደለም።ሁሉም ሊረባረብ ይገባል። በመንግሥት ብቻ የሚቻል አይደለም። አቅማችን የሚፈቅደውን ሁሉ ማድረግ አለብን” ሲልም አብነት ጥሪ አቅርቧል።
በቦረና ዞን፣ ተልተሌ ወረዳ ዲቤ ጋያ ቀበሌ አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ ኤንጌ ዋሪዮ፣ በአካባቢው ከተከሰተ የምግብ እጥረት ጋር ተያይዞ የሰዎች ሕይወት ማለፉን ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ለቢቢሲ አፋን ኦሮሞ ገልጸው ነበር።
ይሁን እንጂ የወረዳ የአደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ኃላፊ ገልመ ሞሉ፣ በረሃብ ምክንያት ሰዎች እየሞቱ ነው ለሚለው የደረሳቸው መረጃ እንደሌለ ገልጸው፣ ሆኖም ሕጻናትና አረጋውያን በምግብ እጥረት ምክንያት ከቀላል በሽታዎች ማገገም እየቻሉ አይደለም ብለዋል።
የኦሮሚያ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ቢሮም በድርቁ ሳቢያ በቦረና ዞን ውስጥ ያለፈ የሰው ሕይወት የለም ሲል በማኅበራዊ የትስስር ገጹ አስፍሯል።
የተልተሌ ወረዳ ነዋሪ የሆኑ ጉዮ ቱሩ የተባሉ አባት ግን፣ ከአንድ ሳምንት በፊት የ16 ዓመት ልጃቸው በረሃብ ለህመም ተዳርጎ ሕይወቱ ማለፉን ተናግረዋል።

የፎቶው ባለመብት, Master Abinet Kebede
“የምውለውም ሆነ የማድረው ከቦረና እናቶችና አባቶች ጋር ነው”
አብነት ወደ ቦረና ከተጓዘ ጀምሮ የሚያድረውም ሆነ የሚውለው እዚያው ካሉ እናቶች እና አባቶች ጋር እንደሆነ ይናገራል። እርሱ እንደሚለው በሥፍራው የተዘጋጁ ጊዜያዊ መጠለያዎች አሉ።
“ከእነርሱ ጋር አብሮ ሆኖ መጫወት በራሱ ለእነርሱም ለእኛም ተስፋ ነው።አሁን ያለኝ የአዕምሮ እረፍት የተለየ ነው። ፈጣሪ ዝናብ እስከሚያዘንብላቸው ድረስም እዚያው ለመቆየት ነው ያሰብኩት” ሲልም ዕቅዱን ተናግሯል።
በቻለው አቅምም የሚችለው በማድረግ ችግር ላይ ያሉትን ሰዎች መደገፉን እንደሚቀጥል ተናግሯል።
“በእኔ በኩል መርዳት የሚፈልጉ ሰዎች በስልክ እያገኙኝ ነው። በእኔ በኩል ብቻ በአንድ ቀን ከሁለት ሚሊየን ብር በላይ ገንዘብ ተስብስቧል።” የሚለው አብነት በሌሎች ቀና ሰዎች ትብብር እርዳታ እያደረገላቸው እንደሚገኝ ገልጿል።
ይህንን በጎ ሥራውን ቤተሰቦቹ እንደሚደግፉለት የሚናገረው አብነት፣አቅሙ በሚችለው ሁሉ ለተቸገሩት እንዲደርስ እንሚያበረታቱት ይናገራል።
“ቦረና ስላለው ሁኔታ የሚያሳይ ቪዲዮ ልኬላቸው ነበር። ‘ወደ እዚህ እንዳትመጣ!’ ነው ያሉኝ” ብሏል።
እንዲያውም ታናሽ ወንድሙ እና ጓደኛው ሊቀላቀሉት እንዳሰቡም ገልጿል።
ከዚህ በፊት በተንቀሳቀሰበት የኢትዮጵያ ክፍል ሁሉ አቅሙ በሚችለው ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን እንደረዳ የሚናገረው አብነት፣ “መልካም ነገር ለመሥራት አካባቢ አይገድብም ብዬ ነው የማስበው” ይላል።
አብነት ባለው አቅም የተቸገሩ ሰዎችን መርዳት ሊያሳካ የሚፈልገው ህልሙ ነው።
በተለይም ተቸግረው በጎዳና ላይ የሚኖሩ እናቶችን እና አባቶችን አንስቶ በተለያዩ ክልሎች እንዲሁም በፌደራል ደረጃ በአንድ ተቋም የሚኖሩበትን መንገድ ማመቻቸት ይፈልጋል።
ሥራ ላጡት የሥራ ዕድሎችን መፍጠርም ምኞቱ ነው።












