“የ16 ዓመት ልጄ በረሃብ ምክንያት ሞተ” በቦረና የሚኖሩ አባት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በደቡባዊ የኢትዮጵያ ክፍል የተከሰተው ድርቅ ባስከተለው ረሃብ ምክንያት የሰዎች ሕይወት ማለፉን ነዋሪዎች እና አንድ የአካባቢው ባለሥልጣን ተናገሩ።
የቦረና ዞን ተልተሌ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት አቶ ጉዮ ቱሩ በረሃብ ምክንያት ከአንድ ሳምንት በፊት የ16 ዓመት ልጃቸውን በሞት እንዳጡ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“ቆሪ ጉዮ የተባለው ልጄ 16 ዓመቱ ነበር። ጤናማ እና ጠንካራ ነበር። ነገር ግን በረሃብ ምክንያት ታመመ። ምንም አልነበረንም። የነበሩን ከብቶች በድርቁ አልቀዋል።
“ሆስፒታል ወስደነው ነበር። ችግሩ ከምግብ እጥረት ጋር የተያያዘ ነው አሉን። ከዚያ ከሆስፒታል እንደተመለሰ ሞተ” በማለት አባት የልጃቸውን አሟሟት ይናገራሉ።
የቦረና ዞን የተልተሌ ወረዳ ዲቤ ጋያ ቀበሌ አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ ኤንጌ ዋሪዮ፣ በአካባቢው ከተከሰተ የምግብ እጥረት ጋር ተያይዞ የሰባት ሰዎች ሕይወት ማለፉን ለቢቢሲ ገልጸዋል።
እንደ አስተዳዳሪው ከሆነ ከምግብ እጥረት ጋር በተያያዘ ሕይወታቸውን ካጡት መካከል የሁለት ወር ጨቅላ እንደሚገኝበት ተናግረዋል።
“በአካባቢው ከሁለት ወር ህጻን ጀምሮ እስከ አዛውንቶች ድረስ በረሃብ ምክንያት ሰባት የሚሆኑ ሰዎች ሞተዋል። ሰዎች ያለ ምግብ ብዙ ቀን እየቆዩ ነው። ያሏቸውም ከብቶች አልቀውባቸዋል።”
አስተዳዳሪው ይህን ቢሉም የተልተሌ ወረዳ የአደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ኃላፊ ገልመ ሞሉ፣ በረሃብ ምክንያት ሰዎች እየሞቱ ነው ለሚለው የደረሳቸው መረጃ የለም ብለዋል።
ይሁን እንጂ ሕጻናት አረጋውያን በምግብ እጥረት ምክንያት ከቀላል በሽታዎች ማገገም እየቻሉ አይደለም ብለዋል - ኃላፊው።
በቦረና ዞን የተከሰተው ድርቅ በቤት እንስሳት ላይ ያደረሰው ጉዳት ደግሞ እጅግ የከፋ ነው። በመቶዎች የሚቆጠሩ ከብቶቻቸውን በድርቁ ምክንያት አጥተው በርካታ አርብቶ አደሮች ባዶ እጃቸውን ቀርተዋል።
የተልተሌ ወረዳ ነዋሪ ቱራ ሮባ ከዚህ ቀደም 150 ከብቶች የነበራቸው ቢሆንም አሁን ሁሉም ከብቶች አልቀው አራት ብቻ እንደቀሯቸው ተናግረዋል።
“ድርቅ ክፉኛ ጎድቶናል። እኛ አርብቶ አደሮች ነን። በከብት ነው የምንተዳዳረው። አሁን እነዚያን ከብቶች ሁሉ አጥተናል። ብዙ ከብት አላቸው ተብለው የሚጠሩም ብዙ አጥተዋል። እኔ 150 ከሚደርሱ ከብቶቼ የቀሩልኝ አራት ብቻ ናቸው። እነርሱም ችለው ከመሬት የሚነሱ አይደሉም። በውሃ እና መኖ እጥረት ተጎድተዋል” ይላል።
የዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (አይኦኤም) ከፈረንጆቹ 2021 መጨረሻ ጀምሮ በኢትዮጵያ በድርቅ ምክንያት 4.5 የቤት እንስሳት መሞታቸውን ገልጿል።
አስቸኳይ እርዳታ ለ800 ሺህ ሰዎች
በኢትዮጵያ፣ በጎረቤት አገራት ሶማሊያ እና ኬንያ ለአምስት ተከታታይ ወቅቶች ዝናብ አለመጣሉን ተከትሎ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ለምግብ እጥረት በመጋለጣቸው አስቸኳይ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ዓለም አቀፍ እና አካባቢያዊ ተቋማት ሲያሳስቡ ቆይተዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት ከቀናት በፊት ባወጣው መግለጫ ለአምስት ተከታታይ የዝናብ ወቅቶ ዝናብ አለመዝነቡ 24 ሚሊዮን ሰዎችን ለአስከፊ የምግብ እጥረት አጋልጧል ብሏል።
በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞንም በድርቁ ምክንያት ከ800 ሺህ በላይ ሰዎች ለአስቸኳይ የምግብ እርዳታ መጋለጣቸው የዞኑ አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ጽ/ቤት ኃላፊ ለቢቢሲ ገልጿል።
“መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በጋራ ሆነን የሰራነው የዳሰሳ ጥናት 867 ሺህ 140 የሚሆኑ ሰዎች አስቸኳይ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው አሳይቷል” ያሉት ኃላፊው፤ በዞኑ የሚገኙ ሁሉም ወረዳዎች በተመሳሳይ መጠን በድርቁ መጎዳታቸውን ገልጸዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
“እየቀረበ ያለው ድጋፍ አነስተኛ ነው”
በድርቁ የተጎዱ ነዋሪዎች፣ የወረዳው አስተዳደሪም ሆኑ የአደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ጽ/ቤት ኃላፊው ከተጎጂዎች አንጻር እየተደረገ ያለው ድጋፍ አነስተኛ መሆኑን ይናገራሉ።
የተልተሌ ወረዳ የአደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ኃላፊ ገልመ ሞሉ በቂ የምግብ እርዳታ እየደረሰ ባለመሆኑ ሰዎች ከቀላል በሽታ እንኳ ለማገገም አልቻሉም ይላል።
የቦረና ዞን አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ኃላፊ አቶ ሊበን ሳራን በዞኑ አስቸኳይ የምግብ አርዳታ ከሚያስፈልጋቸው ስምንት መቶ ሺህ በላይ ሰዎች፣ ከሁለት መቶ ሺህ ለሚበልጡት እርዳታ እየደረሰ አይደለም ብለዋል።
“ይህኛው ወረዳ ይሻላል የሚባል ነገር የለም። የተጎጂዎች ቁጥር እየጨመረ ነው። የምግብ እርዳታ በመንግሥት፣ መንግሥታዊ ባልሆኑ እና በተለያዩ ተቋማት እየቀረበ ቢሆንም፤ እርዳታውና የችግሩ ስፋት አልተመጣጠነም።
“ከ867 ሺህ በላይ ተጎጂዎች፣ ከ200 ሺህ በላዩ እስካሁን ምንም እርዳታ አልደረሳቸውም። ይህ ደግሞ ርቀት ላይ በመሆናቸው መድረስ አቅቶን ሳይሆን በቂ የምግብ እረዳታ አቅርቦት ስለሌለ ነው።”
የቦረና ዞን የተልተሌ ወረዳ አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ ኤንጌ ዋሪዮ በበኩላቸው፤ “መንግሥት የሚደግፈው የተወሰነ ነው። እየቀረበ ያለው ድጋፍም በቂ አይደለም። ሕጻናት እና አዛውንቶች በረሃብ ምክንያት እየሞቱ ነው” ይላሉ።
የዞን እና ወረዳ ኃላፊዎቹ አስቸኳይ ተጨማሪ እርዳታ እንዲቀርብ ድርጅቶች እና ተቋማትን ጨምሮ ለተያዩ አካላት ጥሪ አቅርበዋል።
በድርቁ ምክንያት ከብቶቻቸውን አጥተው ባዶ እጃቸውን ለቀሩት ቱራ ሮባን ለመሳሰሉ አርብቶ አደሮች አሁን ረሃቡ ከሞት ጋር እንዲፋጠጡ አድርጓቸዋል።
አርብቶ አደሩ የተልተሌ ነዋሪ፤ “ድሮም ጀምሮ የምናውቀው የምንኖረው በወተት ነው። አሁን እሱ የለም። ሰው በምግብ እጥረት እየተጎዳ ነው። አሁን ቀላል ህመም እንኳን ሰው እየገደለ ነው። አሁን ከከብቶች አልፎ ሰዎችን እየጎዳ ነው ያለው።”












