ጦርነቱ በሩሲያ፣ በዩክሬን እና በምዕራባውያን ላይ ምን አይነት ጉልህ ለውጥ አስከተለ?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሩሲያ ዩክሬን ላይ ወረራ ከከፈተች እነሆ ዛሬ የካቲት 17/2015 ዓ.ም. አንድ ዓመት ሞላው።
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በዩክሬን ዶምባስ ክልል ሠራዊታቸው “ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ” መጀመሩን በአገሪቱ ቴሌቪዥን ቀርበው ነበር ጦርነቱ መጀመሩን ያወጁት።
ይህንንም ተከትሎ የመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ፑቲን የከፈቱትን ወረራ እንዲያቆሙ ጥሪ አቅርቦ ነበር።
የአየር ጥቃት ማስጠንቀቂያ ደወል ነዋሪውን ባሸበራት ዋና ከተማ ኪዬቭ የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ደግሞ “መሬታችንን፣ ነጻነታችንን፣ ሕይወታችንን ለመንጠቅ የሚደረግን ሙከራ እንከላከላለን” ብለው ክተት አቀጁ።
ባለፈው አንድ ዓመት የተካሄደው ጦርነት ከሁለቱ አገራት ባሻገር በመላው ዓለም ከፍተኛ ምጣኔ ሀብታዊ እና ፖለቲካዊ ተጽእኖን አስከትሏል።
በተለይ በሁለቱ አገራት አጠቃላይ ሁኔታ ላይ ያመጣው ለውጥም እጅግ የጎላ ነው። በተለይ በሕዝቡ የዕለት ከዕለት ሕይወት፣ መፈናቀል፣ ምጣኔ ሀብት፣ ግዛት፣ ወታደራዊ አቅም እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ላይ ያስከተለው ለውጥ ከፍ ያለ ነው።
ከእነዚህም መካከል ጦርነቱ በአንድ ዓመት ውስጥ ጉልህ ተጽእኖ ያስከተለባቸውን አንዳንድ ለውጦች በምስሎች አስደግፈን መለስ ብለን እንቃኝ።
የይዞታ ለውጥ

የሩሲያ መስፋፋት
ሩሲያ በይፋ ጦርነቱን ከመጀመሯ በፊት የምትደግፋቸው ተገንጣይ ኃይሎች በምሥራቃዊ ዩክሬን ከሚገኘው የዶምባስ ክልል ውስጥ ሰፊ መጠን የለውን ይዞታ ተቆጣጥረው ነበር።
ለዚህም ከወረራው ጥቂት ቀናት ቀደም ብለው ፕሬዝዳንት ፑቲን እራሳቸውን የዶኔትስክ ሕዝብ ሪፐብሊክ እና የሉሃንስክ ሕዝብ ሪፐብሊክ ያሉትን ተገንጣይ የዩክሬን ግዛቶችን እንደ ነጻ አገር እውቅና ሰጥተዋል።
ይህንንም ዩክሬን፣ ኔቶ እና የምዕራባውያን አገራት መጀመሪያ ላይ የወገዙት ቢሆንም ኋላ ላይ ግን የሩሲያ ወታደሮች ወደ ግዛቶቹ እንዲገቡ ተስማምተው ነበር።
ሩሲያ ጦርነቱ ከመቀስቀሱ ከስድስት ዓመታት ቀደም ብላ የዩክሬን ግዛት የነበረችውን ክራይሚያን በቁጥጥሯ ስር አስገብታ ከግዛቷ ጋር ቀላቅላታለች።
ነገር ግን በርካታ አገራት ክራይሚያን የሚያውቋት አሁንም የዩክሬን ግዛት እንደሆነች ነው።

የሩሲያ ዕቅድ እና አሁን ያለችበት
ጦርነቱ ከጀመረ አንድ ዓመት ቢሆነውም በአሁኑ ወቅት ሩሲያ በጦርነቱ ጅማሬ ወቅት ከተቆጣጠረችው ያነሰ የዩክሬን ግዛት በእጇ ይገኛል። ነገር ግን አሁንም በምሥራቅ እና በደቡብ በኩል ሰፊ ቦታዎችን ይዛ ትገኛለች።
የሩሲያ ሠራዊት ዋና ከተማዋን ኪዬቭን ለመቆጣጠር ያደረገው ሙከራ ከከሸፈበት በኋላ ትኩረቱን በቁጥጥሩ ስር ያሉ አካባቢዎችን ይዞታ ማጠናከር እና ወደ ክራይሚያ የሚያገናኙ መስመሮችን ማስፋት ላይ አድርጓል።
ባለፈው ዓመት ግንቦት ላይ ማሪዩፖል ውስጥ የሚገኘውን አካባቢ በመቆጣጠር በደቡብ እና በምሥራቅ ያሉ ይዞታዎቿን የሚያገናኝ መስመር ለመክፈት ከመቻሏ በላይ የዩክሬን የባሕር ዳርቻዎችን ለመያዝ ችላለች።
ነገር ግን ከዚያ በኋላ በተደረጉ ውጊያዎች የዩክሬን ኃይሎች በርካታ ድሎችን ለመቀዳጀት ችለዋል።
ዩክሬናውያን ባለፈው መስከረም በጀመሩት መልሶ ማጥቃት፣ በሩሲያ ተይዘውባቸው የነበሩ ቦታዎችን ማስለቀቅ ችለዋል። ነገር ግን አሁንም በርካታ ቦታዎች በሩሲያ ጦር ቁጥጥር ስር ይገኛሉ።
በዚህ ጦርነት ፊት ለፊት ከመደረገው ውጊያ ባሻገር የሩሲያ ሠራዊት በዩክሬን ከተሞች እና የኃይል ማከፋፈያዎች ላይ ከፍተኛ የሚሳኤል ጥቃቶችን መፈጸሙ ተዘግቧል።
ይህም የሆነው የዩክሬን ኃይሎች ክራይሚያን ከሩሲያ ጋር በሚያገናኘው ድልድይ ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን ተከትሎ ነው።

ለስደት የተዳረጉ ዩክሬናውያን
በአንድ ዓመቱ ጦርነት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እንደሞቱ ቢታመንም፣ ሁለቱም አገራት የደረሰባቸውን ወታደራዊ ጉዳት ይፋ አላደረጉም።
የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን እንዳለው አስከ የካቲት 06/2015 ዓ.ም. ድረስ በዩክሬን በኩል 7,199 የሰላማዊ ሰዎች ሞት የተመዘገበ ሲሆን፣ 11,756 የሚሆኑት ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል።
ነገር ግን ከባድ ጦርነት ከሚካሄድባቸው ስፍራዎች መረጃ ለማግኘት አስቸጋሪ በመሆኑ አሃዙ ከዚህም ከፍ ያለ እንደሚሆን አመልክቷል።
ሩሲያ ወረራውን ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ 44 ሚሊዮን ሕዝብ ካላት ዩክሬን 7.7 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ሩሲያን ጨምሮ ወደ ተለያዩ የአውሮፓ አገራት ለመሰደድ ተገደዋል።
በተጨማሪም ሌሎች ሰባት ሚሊዮን የሚሆኑት ደግሞ እዚያው ዩክሬን ውስጥ ተፈናቅለው እንደሚገኙ የመንግሥታቱ ድርጅት የስደተኞች ተቋም ገልጿል።
ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ስደተኞች የሚገኙት ሩሲያ ውስጥ ሲሆን፣ በተከታይነት ደግሞ አብዛኞቹ በፖላንድ፣ በጀርመን እና በቼክ ሪፐብሊክ ውስጥ ተጠልለዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም የዩክሬናውያን ስደተኞችን ሁኔታ “ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ በኃይል በፈጣን ሁኔታ የተሰደደበት ክስተት ነው” ብሎታል።
በአብዛኛው ሴቶች እና ህጻናት በርካታ የዩክሬን ዜጋ የሆኑ ስደተኞች በመላው አውሮፓ ባሉ ከተሞች ውስጥ የሞቀ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።
ነገር ግን ጦርነቱ በዓለም ዙሪያ ባስከተለው ምጣኔ ሃብታዊ ጫና እና የኑሮ ውድነት ምክንያት የጀርመን እና የሌሎች አገራት ባለሥልጣናት እስከመቼ ስደተኞቹን እያስተናገዱ እንደሚቆዩ እየጠየቁ ነው።
በጦርነቱ ምክንያት በተለይ ሴቶች፣ ሕጻናት፣ በእድሜ የገፉ ሰዎች እና አካል ጉዳተኞች በጣም በአስቸጋሪ ሆኔታ ውስጥ እንደሚገኙ የተባበሩት መንግሥታቱ እና የድርጅቱ ሰብአዊ እርዳታ እንዲሁም የስደተኞች ጉዳይ ተቋማት ሁኔታው በአሁኑ ጊዜ አሳሳቢ መሆኑን ገልጸዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የጦር መሳሪያ አቅርቦት
ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ ትልቅ ለውጥ የታየው የዩክሬን ጦር ጥቅም ላይ ባዋላቸው እጅግ ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎች እና በሚያስታጥቋት አገራት ላይ ነው።
ሩሲያ በዓለም ላይ የጦር መሳሪያዎችን አምርቶ ለሌሎች አገራት በመሸጥ በሁለተኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ ስትሆን፣ ጦርነቱ በተጀመረበት ጊዜ ያላት ኃይል ከዩክሬን ጋር ሲነጻጸር ሰፊ ልዩነት ነበረው።
ባላት ዘርፈ ብዙ ወታራዊ አቅም የበላይነት የተነሳም በዩክሬን ላይ በከፈተችው ወረራ በአጭር ጊዜ ውስጥ የምትፈልገውን ታሳካለች የሚል ግምት ነበረ።
ነገር ግን የሩሲያን ወረራ በይፋ በመቃወም የኔቶ አባል አገራት እና አብዛኞቹ ምዕራባውያን ከሩሲያ በተቃራኒ በመቆም ለዩክሬን ድጋፍ ሰጥተዋል። በአንድ ዓመት ውስጥም ከ30 በላይ አገራት ለዩክሬን ሠራዊት የተለያዩ አይነት ወታደራዊ ትጥቆችን ሰጥተዋል።
በለንደን ኪንግስ ኮሌጅ የጦርነት ጥናቶች ክፍል ባልደረባ የሆኑት ዶ/ር ባርባራ ዛንቼታ “ቭላድሚር ፑቲን ጦርነቱን ሲጀምሩ ዩክሬን አሜን ብላ እንደምትቀበለው፣ ሌሎች አገራትም ትርጉም ያለው ጣልቃ ገብነት እንደማይኖራቸው ገምተው ነበር” ብለዋል።
ጨምረውም ይህ የፑቲን የተሳሳተ ስሌት የተራዘመ ጦርነትን በማስከተል መቼ ሊያበቃ እንደሚችል ለመገመት አስቸጋሪ ሁኔታን እንደፈጠረ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ከባድ መሳሪያዎች
የጦርነቱ ፍጥጫ በተባባሰበት ጊዜ በሺዎች የሚቆጠሩ ‘ኤንላው’ የተባሉ ከትከሻ ላይ የሚወነጨፉ ፀረ ታንክ መሳሪያዎች በምዕራባውያን ለዩክሬን ተሰጠዋል።
ይህም ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ በነበሩት ቀናት የሩሲያ ጦር ወደ ዋና ከተማዋ ኪዬቭ ያደርግ የነበረው ግስጋሴ የተገታው በእነዚህ የጦር መሳሪያዎች ድጋፍ እንደሆነ ይታመናል።
ከዚያ በኋላም አብዛኞቹ ውጊያዎች ሲካሄዱ የቆዩት በምሥራቃዊ የአገሪቱ ክፍል ውስጥ ሲሆን፣ በዚህም ረጅም ርቀት የሚሸፍኑ የጦር መሳሪያዎችን የዩክሬን ኃይሎች በመጠቀማቸው ውጤት ለማግኘት ችለዋል።
አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ካናዳ እና አውስትራሊያ ኤም777 ሆዊትዘር መድፎችን እና ከፍተኛ ኃይል እንዳላቸው የሚነገርላቸውን ኤም142 ሂማራስ የተባሉትን የመሳሰሉ የሮኬት ማስወንጨፊያዎችን ለዩክሬን ሠራዊት አስታጥቀዋል።
ጦርነቱ በተጀመረበት ጊዜ አሮጌ የሶቪየት ዘመን ከመሬት ወደ አየር የሚወንጨፉ ሚሳኤሎች ብቻ የነበራት ዩክሬን፣ በአንድ ዓመት ውስጥ ከምዕራባውያኑ አገራት የተለያዩ አይነት እጅግ ዘመናዊ ተወንጫፊ ሚሳኤሎችን ከአሜሪካ፣ ከጀመርመን እና ከዩናይትድ ኪንግደም አግኝታለች።
በተጨማሪም እጅግ ዘመናዊ የሆነውን የፀረ ሚሳኤል መከላከያ ሥርዓት የሆነውን ፓትሪዮት ሚሳኤልን ከአሜሪካ፣ ከጀርመን እና ከኔዘርላንድስ እንደሚሰጠት አገራቱ ገልጸዋል።

የትጥቅ አቅርቦት
በሩሲያ በኩል ደግሞ ምንም እንኳን ሞስኮ እና ፒዮንግያንግ ቢያስተባብሉትም የአሜሪካ ባለሥልጣናት እንደሚሉት በምዕራባውያን የተጣለባት ማዕቀብ ሩሲያ ፊቷን ወደ ሰሜን ኮሪያ እድታዞር አድርጓታል።
በዚህም በጦርነቱ ውስጥ የሩሲያ ሠራዊት ጥቅም ላይ ያዋላቸውን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሮኬቶች እና የመድፍ ተተኳሾችን ለማግኘት ሰሜን ኮሪያ እየቀረበላት ነው ይላሉ።
ከዚህ አንጻር ዩክሬን ከምዕራባውያኑ አጋሮቿ ለረጅም ርቀት የጦር መሳሪያዎቿ አስተማማይ የተተኳሽ አቅርቦትን በማግኘት በኩል ከሩሲያ የተሻለች እንደሆነ ይነገራል።
ይህም ዩክሬን በምሥራቅ እና በደቡብ ላገኘችው ስኬት እንዲሁም በማዕከላዊው ግንባር ደግሞ የሩሲያ ኃይሎችን ጥቃት ለመከላከል አስችሏታል።
ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ ዩክሬን ከምዕራባውያን አጋሮቿ ከቀረቡላት በተጨማሪ ያስፈለጉኛል የምትላቸው እና ቃል የተገቡላት የጦር መሳሪያዎች በቶሎ ለወታደሮቿ ባለመቅረባቸው ቅሬታዋን ስታሰማ ቆይታለች።
በጦርነቱ ጅማሬ ላይ ብረት ለበስ ተሽከርካሪዎች ያቀረቡላት ምዕራባውያን ታንኮችን ለመስጠት ፈቃደኛ ለመሆን ግን አንድ ዓመት ወስዶባቸዋል።
ብሪታኒያ፣ አሜሪካ እና ጀርመን በዓለማችን ዘመናዊ የተባሉ ታንኮች ባለቤቶች ቢሆኑም፣ የሩሲያን አጸፋ በመፍራት ታንኮቹን ለዩክሬን ለማስታጠቅ ሲያመነቱ ቆይተዋል።

ከብዙ ጊዜ ውትወታ በኋላ ባለፈው ጥር ወር ላይ ምዕራባውያኑ አገራት ዘመናዊዎቹን ታንኮች ለዩክሬን እንደሚሰጡ አስታውቀዋል።
በዚህም ዩናይትድ ኪንግደም ቻሌንጀር 2፣ አሜሪካ ኤም1 ኤብራምስ እና ጀርመን ደግሞ ሊዮፓርድ የተባሉትን እንዲሁም ሌሎችም አገራት እጅግ ዘመናዊ ታንኮቻቸውን ለዩክሬን ለመስጠት በይፋ ቃል ገብተዋል።
በብሪታኒያ ጦር ውስጥ የቀድሞ አዛዥ የነበሩት እና በዓለም አቀፉ ስትራተጂክ ጥናት ኢንስቲቲዩት ውስጥ አጥኚ የሆኑት ቤን ባሪ፣ የምዕራባውያን ታንኮች በጦርነቱ ውስጥ ልዩነትን የሚፈጥሩ መሆናቸውን አመልክተዋል።
ነገር ግን አስካሁን የተገባው ቃል ብቻውን ግን ወሳኝ አለመሆኑን ለቢቢሲ ተናገረው “ነገር ግን በታንኮች ብቻ ጦርነትን ማሸነፍ እንደማይቻል ታሪክ አሳይቶናል” ብለዋል።
ምዕራባውያን ዩክሬንን ታንክ ማስታጠቃቸው ሩሲያን አስቆጥቷል፤ የፕሬዝዳንት ፑቲን ቃል አቀባይ ዲሜትሪ ፔስኮቭ ተጨማሪ የጦር መሳሪያ አቅርቦት “ጦርነቱን የበለጠ እንደሚያባብሰው” በማስጠንቀቅ “ሌሎች አገራትም በቀጥታ በግጭቱ ውስጥ እየሳተፉ መሆናቸውን” እንደሚያሳይ ተናግረዋል።
ይህ ስጋት ነው አስካሁን የዩክሬን ወዳጆች ታንኮችን ከመስጠት እንዲዘገዩ ያደረጋቸው። እንዲሁም ዩክሬን በተደጋጋሚ ተዋጊ ጄቶች ወዳጆቿ እንዲያስታጥቋት ብትጠይቅም አስካሁን አውንታዊ ምላሽ የሰጣት የለም።
ቢሆንም ግን ቱርክ ሰራሽ የሆነው ባይራክታት ቲቢ2 የተባለው ሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) ከጦርነቱ ጅማሬ አንስቶ ለቅኝት እና ኢላማን ለመለየት በዩክሬን ሠራዊት ጥቅም ላይ እየዋለ ነው። የድሮኖቹ አምራች የሆነው የቱርክ ተቋም በሽያጭ እና በስጦታ ለዩክሬን ሲያቀርብ ቆይቷል።
በሌላ በኩል ደግሞ ሩሲያ የዩክሬን ከተሞችን እና የኃይል ማመንጫዎችን ለማጥቃት “ካሚካዚ” የተባሉትን አጥፍቶ ጠፊ ድሮኖች እና ተወንጫፊ ሚሳኤሎችን ተጠቅማለች።
እነዚህን ድሮኖች ኢራን ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት ለሩሲያ ማቅረቧን ብታረጋግጥም፣ ነገር ግን በጦርነቱ ወቅት ኢራን በመቶዎች የሚቆጠሩ ድሮኖችን ለሩሲያ በምስጢር ማስታጠቋ ይነገራል።












