ዩክሬን የምዕራባውያንን ታንኮች ለምን ፈለገች? እነሱስ ለመስጠት ለምን ፈሩ?

የዩክሬን ወታደር ከታንክ ፊት ቆሞ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በሩሲያ የተያዙባትን ግዛቶቿን ለማስመለስ በመቶዎች የሚቆጠሩ ታንኮችን ምዕራባውያን ወዳጆቿ እንዲሰጧት ዩክሬን እየወተወተች ነው።

አስካሁን ዩናይትድ ኪንግደም 14 ታንኮችን ለመስጠት የፈቀደች ሲሆን፣ ሌሎቹ አገራትም መሳሪያዎቹን ለመስጠት ቃላቸውን ይሰጣሉ ተብሎ እየተጠበቀ ነው።

ታንኮች ከከባድ መሳሪያነታቸው በተጨማሪ በእግርኞች በሚደረግ የማጥቃት ውጊያ ውስጥ ቁልፍ ሚና አላቸው። በቀላሉ በመንቀሳቀስ ለእግረኛ ወታደሮች ሽፋን እየሰጡ ምሽጎችን ለመስበርና ይዞታን ለማስፋት ጠቃሚ ናቸው።

ስለዚህም በጦር ግንባሮች የበለጠ ቁጥር ያላቸውን ታንኮች የሚያሰልፍ ኃይል የበላይነትን ለመያዝ ዕድል ይኖረዋል።

ለመሆኑ ዓመት ሊሞላው በተቃረበ ጦርነት ውስጥ የሚገኙት ሩሲያ እና ዩክሬን ስንት ታንኮች አሏቸው?

ዩክሬን በሩሲያ ወደ ተከፈተባት ጦርነት ውስጥ ስትገባ ከ30 ዓመታት በፊት የተመረቱ እና እርጅናቸው ጎልቶ የሚታይ ቲ-72ን የመሳሰሉ 900 ታንኮችን ታጥቃ ነው።

ወታደራዊ ድጋፍ የሚሰጡ አገራት

“አብዛኞቹ የዩክሬን ታንኮች ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት አስፈላጊው ጥገና ስላልተደረገላቸው፣ ምናልባት ምንም የማይጠቅሙ ሊሆኑ ይችላሉ” የሚሉት በለንደኑ ኪንግስ ኮሌጅ የመከላከያ ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር ማሪና ሚሮን ናቸው።

ሩሲያ ግን ወረራውን ስትጀምር ከ3,000 በላይ ታንኮችን ከማሰለፏ በተጨማሪ፣ በርካታ ታንኮችንም በተጠባባቂነት ይዛለች።

በዚህም ምክንያት የሩሲያን የታንክ ሠራዊት ለመቋቋም ዩክሬን ምዕራባውያን አገራት አስከ 300 የሚደርሱ ዘመናዊ ታንኮችን እንዲሰጧት ጠይቃለች።

ይህም ዩክሬን በሩሲያ የተያዙባትን ቦታዎች ለማስመለስ በቀጣይ ወራት ታካሂደዋለች ተብሎ ለሚታሰበው ዘመቻ ልትጠቀምባቸው ትችላለች ተብሎ ይታመናል።

“በከባድ ሁኔታ በመድፍ የሚጠበቀውን የሩሲያን የመከላከያ መስመርን በእግረኛ ወታደሮች ሰብሮ ለመግባት የታንኮች ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል” ይላሉ በሮያል ዩናይትድ ሰርቪስስ ኢኒስቲቲዩት በምድር ውጊያ ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር ጃክ ዋትሊንግ።

ቲ-72

የምዕራባውያኑ ታንኮች ምን አይነት ናቸው?

ምዕራባውያኑ ታንኮችን የመሳሰሉ ለማጥቃት የሚውሉ ከባድ መሳሪያዎችን ለዩክሬን ቢያስታጥቁ ሩሲያን ሊያስቆያጣ እና ጦርነቱን ሊያስፋፋው ይችላል የሚል ስጋት ነበራቸው።

ስለዚህም በጦርነቱ መጀመሪያ ላይ መንግሥታቱ ለዩክሬን ለመስጠት የፈቀዱት ፀረ ታንክ ሚሳኤሎችን የመሳሰሉ የመከላከያ መሳሪያዎችን ብቻ ነበር።

ባለፉት ወራት ውስጥ ዩክሬን ያገኘቻቸው የታንክ ድጋፎች ከቀድሞዎቹ ኮሚኒስት የምሥራቅ አውሮፓ አገራት ከፖላንድ፣ ከስሎቫኪያ እና ከቼክ ሪፐብሊክ የተሰጧት 200 ቲ-72 ታንኮች ብቻ ናቸው።

ከዚህ ውጪ ዩናይትድ ኪንግደም ኢላማቸውን በመምታት የተሳካላቸው ናቸው የሚባሉትን 14 ቻሌንጀር የተባሉ ዘመናዊ ታንኮችን ለመስጠት ቃል በመግባት የመጀመሪያዋ ናት።

ነገር ግን እነዚህ ታንኮች የሚጠቀሙት ተተኳስ ሌሎች የኔቶ አባል አገራት ከሚጠቀሙት የተለየ በመሆኑ፣ ቻሌንጀር 2 ታንኮችን በአስፈላጊው ሁኔታ ዩክሬን ችግር ለመጠቀም ፈታኝ ሊሆንባት ይችላል እየተባለ ነው።

ቻሌንጀር 2 ታንክ

ዩክሬን ከሁሉም በላይ የጀርመን ሰራሾቹን ሊዮፓርድ 2 የተባሉትን ታንኮች ለማግኘት በእጅጉ ጓግታለች።

እነዚህ ቀላል ክብደት ያላቸው እና ፈጣን ታንኮች የሚጠቀሙት መደበኛ ተተኳሾችን በመሆኑ በቀላሉ ወደ ጦር ግንባሮች ልታሰማራቸው ትችላለች። አጋሮቿም ካላቸው ክምችት ላይ ተተኳሾችን ሊያቀርቡላት ይችላሉ።

በአጠቃላይ 25 ሊዮፓርድ የተሰኙት ታንኮች ያሏቸው ፖላንድ እና ፊንላንድ ለዩክሬን ሊሰጡ ፍላጎት ቢኖራቸውም፣ ለዚህም የታንኮቹ አምራች የሆነችው ጀርመን መፍቀድ ይኖርባታል።

ነገር ግን ጀርመን እነዚህን ታንኮች አራሷም ሆነ ሌሎች አገራት ለዩክሬን አሳልፈው እንዲሰጡ እስካሁን ያልፈቀደች ሲሆን፣ ምዕራባውያን አጋሮቿ አውንታዊ ምላሽ እንድትሰጥ እና አራሷም ዩክሬንን እንድታስታጥቅ ግፊት እያደረጉባት ነው።

ዩክሬን በተጨማሪ አሜሪካ ካሏት እንዲሁም በዓለም ላይ እጅግ ዘመናዊ ናቸው ከሚባሉት ኤም1 ኤብራምስ ታንኮቿ መካከል የተወሰኑትን እንድታስታጥቃት ጠይቃለች። ነገር ግን እስካሁን አሜሪካ ለዚህ ጥያቄ ምላሽ አልሰጠችም።

ሊዮፓርድ 2 ታንክ

ጀርመን እና አሜሪካ ለምን ታንኮችን ለዩክሬን አልሰጡም?

“ሁሉም የምዕራብ አገራት በአንድ ላይ ታንኮችን የመሳሰሉ ጦር መሳሪያዎችን እስካልሰጡ ድረስ ጀርመን በተናጠል ለዩክሬን መስጠት አስጨንቋታል” ይላሉ ዶ/ር ሚሮን።

“ይህንን ብታደርግ ሩሲያ ነጥላ ልትመለከታት እና ‘መስመሩን አልፈሻል፤ አሁን የእጅሽን ታገኛለሽ’ ብላ ትበቀለኛለች የሚል ስጋት አላት።”

አሜሪካን ታንኮቹን አለመስጠቷን በተመለከተ ደግሞ ዶ/ር ዋልቲንግ ሲናገሩ፣ ታንኮቹን ለዩክሬን ያልሰጠችበት ተጨባጭ ምክንያቷች አሏት ይላሉ።

“ታንኮቹ ያላቸው የነዳጅ ፍጆታ ከፍተኛ ነው፣ ዩክሬን ደግሞ የነዳጅ እጥረት አለባት። በተጨማሪም ኤብራምስ ታንኮችን በቋሚነት ጥቅም ላይ ለማዋል ከፍተኛ ክትትል እና ጥገናን ይፈልጋሉ” ብለዋል።

ምናልባትም አሜሪካኖች ዩክሬንን “የጀመርን ሊዮፓርድ እና የዩኬን ቻሌንጀር ታንኮችን እንዴት እየተጠቀማችሁ እንደሆነ ካየን በኋላ የእኛን እንሰጣችኋለን ብለዋቸው ሊሆን ይችላል” ሲሉ ዶ/ር ሚሮን ግምታቸውን አስቀምጠዋል።

ኤም1 ኤብራምስ ታንክ

የምዕራባውያን ታንኮች ዩክሬንን ምን ያህል ያግዟታል?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ዶ/ር ዋትሊንግ እንደሚሉት የምዕራባውያኑ ታንኮች ከሩሲያውያኑ በክብደት ከፍ ያሉ በመሆናቸው በአጠቃቀም ላይ ውስንነት ሊኖራቸው ይችላል።

“ታንኮቹ ዩክሬን ውስጥ ያሉ ድልድዮችን ለመሻገር በጣም ከባድ ናቸው” በማለት ለዚህም መፍትሄው “ከታንኮቹ ጋር ለመሸጋገሪያ የሚሆኑ ድልድዮችን የሚዘረጉ ከባድ ተሽከርካሪዎች አብረው መሰማራት ያስፈልጋቸዋል” ብለዋል።

ይህ ማለት ደግሞ ዩክሬን እነዚህን ግዙፍ ታንኮች በተወሰኑ አካባቢዎች ላይ ብቻ እንድትጠቀምባቸው ያደርጋታል ይላሉ ዶ/ር ሚሮን።

“ስለዚህም ዩክሬናውያን ታንኮቹን መጠቀም የሚችሉት ጥቂት ወንዞች ባሉባቸው የአገሪቱ ክፍሎች እና ከክብደታቸው የተነሳ በጭቃ እንዳይያዙ በጣም ጭቃማ ባልሆኑ አካባቢዎች ላይ ብቻ ነው ማሰማራት የሚችሉት።”

በተጨማሪም ወደ ዩክሬን የሚላክ የትኛውም የምዕራባውያን ታንክ ወዲያውኑ የሩሲያ ኃይሎች ዋነኛ ኢላማ መሆኑ አይቀሬ ነው።

“ሩሲያውያን እነዚህን አዳዲስ ታንኮች ለይተው ቀዳሚ ኢላማቸው በማድረግ ለማውደም ጥረት ያደርጋሉ” ሲሉ ዶ/ር ሚሮን ተናግረዋል።

ይህም ቢሆን ግን ዩክሬን ከፕሬዝዳንቷ ጀምሮ ሁሉም ባለሥልጣናቷ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ታንክ እንዲሰጧቸው ምዕራባውያኑን እየተማጸኑ ነው።

ምዕራባውያኑ ደግሞ በአንድ በኩል ከሩሲያ በኩል የሚመጣው አጸፋ ምን ሊሆን ይችላል የሚለው፣ በሌላ በኩል ደግሞ ታንኮቹ በጦርነቱ ውስጥ በምን ያህል ውጤታማነት ዩክሬንን ሊያግዙ እንደሚችሉ እርግጠኛ ባለመሆናቸው ለውሳኔ ተቸግረዋል።

ሩሲያም በበኩሏ ምዕራባውያን ለዩክሬን ታንኮችን ማስታጠቅን በተመለከተ እያደረጉት ያለውን ንግግር ተከትሎ፣ የጦር መሳሪያውን የሚሰጡ ከሆነ ጦርነቱን ከማባባስ ባሻገር የአጸፋ ምላሽ እንደሚጠብቃቸው እያስጠነቀቀች ነው።