ምዕራባውያን ዩክሬንን ለማስታጠቅ ፈራ ተባ ያሉባቸው ብረት ለበስ የውጊያ ተሽከርካሪዎች

ለዩክሬን ለማስታጠቅ ስታመነታበት የነበረው ማርደር ብረት ለበስ ተሽከርካሪ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, ጀርመን ለዩክሬን ለማስታጠቅ ስታመነታበት የነበረው ማርደር ብረት ለበስ ተሽከርካሪ

ዩክሬን ከሩሲያ ጋር እያደረገችው ባለው ጦርነት በአሸናፊነት እንድትወጣ ምዕራባውያን አገራት ይፈልጋሉ። ለዚህም በቢሊዮኖች ዶላር የሚያወጡ ዘመናዊ የጦር መሣሪያዎችን እያስታጠቋት ነው። በዚህም ተገዳዳሪያቸው የሆነችውን የሩሲያን ወታደራዊ አቅም ክፉኛ እየፈተኑት ነው።

ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ ወዲህ የዩክሬንን የጦር ሜዳ አቅም ለማጠናከር ፈረንሳይ በተለይ ብረት ለበስ ተሽከርካሪዎችን ለማስታጠቅ ወስናለች። አሁን ደግሞ ጀርመን እና አሜሪካም በዚህ በኩል ዩክሬንን ለመደገፍ ከፈረንሳይ ጎን ተሰልፈዋል።

ለወራት ዩክሬን ምዕራባውያን አጋሮቿ ታንኮች እንዲሰጧት ስትጠይቅ የቆየች ሲሆን፣ አሁን ከሦስቱ አገራት የሚቀርቡላት ብረት ለበስ ተሽከርካሩዎች የታንክን ያህል ባይሆንም ወሳኝ ድጋፍ እንደሆኑ ይታመናል።

ፈረንሳይ ኤኤምኤክስ-10 አርሲ የተባሉትን “ቀላል የውጊያ ታንኮችን” ወደ ዩክሬን እንደምትልክ መግለጿን ተከትሎ፣ ጀርመን እና አሜሪካንም በተመሳሳይ ብረት ለበስ የውጊያ ተሽከርካሪዎችን ለመስጠት በመሪዎቻቸው አማካይነት ቃል ገብተዋል።

ዩክሬንን ከፍተኛ ገንዘብ በማውጣት የምትደግፈው አሜሪካ ሦስት ቢሊየን ዶላር መድባ የሚያስፈልጉ አቅርቦቶችን ለመስጠት ቃል መግባቷ ይታወሳል።

ምዕራባውያኑ የሩሲያን ምላሽ በመፍራት አስካሁን እንዲህ አይነቶቹን ከባድ የጦር መሳሪያዎችን ለዩክሬን ከመስጠት ተቆጥበው ቆይተዋል። አሁን ግን በይፋ ዩክሬንን ለማስታጠቅ ቃል ገብተዋል።

ነገር ግን ይህ የምዕራባውያን ውሳኔ ብረት ለበስ ተሽከርካሪዎችን ከመስጠት ባሻገር ዩክሬን እየጠየቀች ያለውን ተዋጊ ጄቶች፣ የጦር መርከቦችን ጨምሮ ሌሎችንም እንድታገኝ በር ይከፍታል ብለዋል የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር።

ብራድሊ የአሜሪካ ከባድ ብረት ለበስ ተሽከርካሪ
የምስሉ መግለጫ, ብራድሊ የአሜሪካ ከባድ ብረት ለበስ ተሽከርካሪ

አሜሪካ የሦስት ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ 50 የሚደርሱ ብራድሊ የውጊያ ተሽከርካሪዎችን የሚጨምር ሲሆን፣ የአሜሪካ የመከላከያ መሥሪያ ቤት ፔንታገን እንዳለው ይህ ተሽከርካሪ ታንክን የሚተካ ባይሆንም “ታንኮችን አድኖ የሚመታ ነው” ብሎታል።

የውጊያ ተሽከርካሪው ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ወደ ዩክሬን እንደሚደርስ የአሜሪካ መንግሥት ገልጿል። በተጨማሪም በእራሳቸው የሚንሳቀሱ ሆዊትዘር መድፎች፣ ፀረ ተሽከርካሪ ፈንጂዎችን የሚቋቋሙ ብረት ለበሶች እና ኢላማቸውን በብቃት የሚመቱ ሮኬቶች ጭምር በምሥራቅ አውሮፓ ላሉ የኔቶ አጋሮች እንደሚሰጥ ተነግሯል።

ጀርመን በበኩሏ ለእግረኛ ውጊያ የሚያገለግሉ ተሽከርካሪዎች እና ፓትሪዮት ፀረ አውሮፕላን የሚሳኤል ሥርዓቶችን በቀጣይ ጥቂት ወራት ውስጥ ለዩክሬን ትልካለች። ለስምንት ሳምንታት የሚቆይ ሥልጠናም ጀርመን ውስጥ እንደሚሰጥ የመንግሥት ቃል አቀባይ አመልክቷል።

እነዚህ ከምዕራባውያን የሚሰጡት ብረት ለበስ የውጊያ ተሽከርካሪዎች የዩክሬን ሠራዊትን የከባድ መሳሪያ፣ የመንቀሳቀስ እና ጥቃት የመቋቋም ብቃትን በማጠናከር፣ ወታደሮች ደኅንታቸው ተጠብቆ በፍጥነት ወደ ውጊያ ግንባሮች በመድረስ ቀልጣፋ ምላሽ ለመስጠት ያስችለዋል ተብሏል።

የፈረንሳይ ኤኤምኤክስ-10 አርሲ የተባለው 105 ሚሊሜትር የውጊያ ተሽከርካሪ፣ መድፍ ካለው ታንክ ጋር ተመሳሳይ ነው። ነገር ግን ባለሰንሰለት ሳይሆን ባለ ጎማ ከባድ ተሽከርካሪ ነው።

ወታደራዊ ባለሙያዎች ይህ ተሽከርካሪ በየትኛውም የመሬት አቀማመጥ ላይ ከብረት ለበስ ተሽከርካሪዎች እና ከእግረኛ ወታደሮች ጋር ተጣምሮ ለመሰማራት የተዋጠለት ነው ሲሉ ይመሰክራሉ።

ኤኤምኤክስ-10 አርሲ
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የአሜሪካው ብራድሊ ብረት ለበስ ተሽከርካሪ ለዩክሬን ጦር ሠራዊት ተጨማሪ የተኩስ አቅምን የሚሰጥ ነው። ተሽከርካሪው ቡሽማስተር የተባለ ባለ 25ሚሊሜትር መድፍ ያለው ሲሆን፣ የሚፈነዱ እና ብረት ለበስ ተሽከርካሪዎችን ጠርምሰው የሚገቡ አረሮችን የሚተኩስ ነው።

የአሜሪካ ሠራዊት ይህንን ተሽከርካሪ ከ1980ዎቹ (እአአ) ጀምሮ በውጊያ ግንባሮች ውስጥ ወታደሮችን ለማጓጓዝ ሲጠቀምበት የቆየ ሲሆን፣ አስከ አስር የሚደርሱ ወታደሮችን ለመጫን ይችላል።

የአሜሪካ የመከላከያ መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ ብርጋዲየር ጄኔራል ፓት ራይደር፣ ተሽከርካሪው ለመከላከል እና ለማጥቃት ዘመቻዎች የሚያግዝ ነው ሲሉ ገልጸውታል።

ሌላኛው ማርደር የተባለው የውጊያ ተሽከርካሪ በጀርመን ሠራዊት ከአውሮፓውያኑ 1070ዎቹ አንስቶ ጥቅም ላይ እየዋለ ነው። 20 ሚሊሜትር ካሊበር መድፍ የታጠቀ ሲሆን፣ ከ1,500 ሜትር ርቀት ላይ ሄሊኮፕተሮችን እና ታንኮችን የመምታት አቅም አለው።

ምንም እንኳን ይህ ማርደር ብረት ለበስ ተሽከርካሪ የ50 ዓመታት ዕድሜ ቢኖረውም፣ በተደጋጋሚ እየተሻሻለ ዘመናዊ ካሜራዎች ተገጥመውለት በጨለማ መንቀሳቀስ የሚችል ሆኗል።

ጀርመን ማርደር የተሰኘውን ብረት ለበስ የውጊያ ተሽከርካሪን ለመስጠት ለረጅም ጊዜ ስታቅማማ ከቆየች በኋላ ነው ውሳኔ ላይ የደረሰችው።

ድጋፉም በዚህ የሚያቆም ሳይሆን በቀጣይነትም ሊዮፓርድ የተሰኘውን ዘመናዊ የውጊያ ተሽከርካሪ ልትሰጥ እንደምትችል ባለሥልጣናት ቃል ገብተዋል።

የጀርመን የውጭ ሚኒስትር አናሌና ቤርቦክ ለዩክሬን የጦር መሳሪያ ድጋፍ መስጠትን በተመለከተ ሲናገሩ “ዩክሬን የተወረሩባትን ቦታዎች እና በሩሲያ በሚፈጸሙ የሽብር ድርጊቶች ምክንያት የሚሰቃየውን ሕዝቧን ነጻ እንድታወጣ መሳሪያ ሊሰጣት ይገባል” ብለዋል።

በተመሳሳይም ዩናይትድ ኪንግደም ቻሌንጀር 2 የተባሉ ታንኮችን ለዩክሬን ለመስጠት መወሰኗን የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ረሺ ሱናክ አሳውቀዋል።

ውሳኔው ዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ለዩክሬን የምታደርገውን ድጋፍ የሚያጠናክር መሆኑን የገለጸው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት፣ ቻሌንጀር 2 የተባሉት 14 ታንኮች ዘመናዊ ታንኮች በቅርቡ ለዩክሬን ሠራዊት እንደሚሰጡ እና ከሩሲያ ጋር በሚደረጉት ውጊያዎች ላይ እንደሚሰማሩ ተገልጿል።

የዩኬ ሠራዊት ዋነኛ የውጊያ ታንክ ሆነው ይህ ቻሌንጀር 2 ታንክ በ1990ዎቹ (እአአ) የተገነባ ሲሆን፣ ዩክሬን ከታጠቀቻቸው ታንኮች ሁሉ ዘመናዊው ይሆናል ተብሏል። ከታንኩ በተጨማሪ የዩክሬን ሠራዊት አጠቃቀሙን በሚመለከት በቀጣይ ቀናት ሥልጠና ይሰጣል ተብሏል።

ቻሌንጀር 2

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ዩናይትድ ኪንግደም ለዩክሬን የምትሰጠው ዘመናዊው ቻሌንጀር 2 ታንክ