ሩሲያ እና ዩክሬን እያደረጉት ባለው ጦርነት የሚጠቀሟቸው ድሮኖች

ድሮን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በሩሲያ ዩክሬን ጦርነት በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰው አልባ አውሮፕላኖች [ድሮኖች] የዩክሬን ሰማይ ላይ ይከንፋሉ።

እነዚህ ድሮኖች የተለያየ ተልዕኮ አላቸው።

አንዳንዶቹ የጠላትን መገኛ እና ይዞታዎችን ይለያሉ። ወታደራዊ ግብዓቶችን ከሚጓጉዙት በተጨማሪ በጠላት ኃይል ላይ ሚሳኤል ለመተኮስ ጥቅም ላይ የሚውሉም አሉ።

በዚህ ጦርነት ተሳታፊ የሆኑት ሁለቱም ወገኖች፤ ለወታደራዊ ዓላማ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን እየተጠቀሙ ነው።

ዩክሬን እና ሩሲያ ምን ዓይነት የጦር ድሮኖች አሏቸው?

የዩክሬን ጦር በዋነኛነት የታጠቀው ቱርክ ሠራሹን ባይራክታር ቲቢ2 ድሮኖች ነው።

ባይራክታር ቲቢ2 ለስለላ ወይም የጥቃት ተልዕኮዎችን እንዲወጣ ተደርጎ የተሰራ ነው። በመጠን አነስተኛ አውሮፕላን ያክላሉ። ካሜራ የተገጠመላቸው ሲሆን በጨረር የሚዘወሩ ቦምቦችን መጣል ይችላሉ።

የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ሲጀመር ዩክሬን “ከ50 ያነሱ” ባይራክታር ቲቢ2 ድሮኖች እንደነበሯት የሚናገሩት የሮያል ዩናይትድ ሰርቪስ ተቋም (ሩሲ) ባልደረባ የሆኑት ዶ/ር ጃክ ዋትሊንግ ናቸው።

ሩሲያ በበኩሏ በመጠን አነስተኛ እና በሚሰጡት አገልግሎትም መሠረታዊ የሚባሉትን ኦርላን-10 ድሮኖችን ትጠቀማለች ይላሉ።

“ሩሲያ በሺዎች በሚቆጠሩ ድሮኖች ነው ጦርነቱን የጀመረችው። አሁን የቀራት በመቶዎች የሚቆጠሩ ይሆናሉ።"

እነዚህ ሩሲያ የምትጠቀማቸው ድሮኖች ካሜራ የተገጠመላቸው ናቸው። ሚሳኤል መተኮስም ይችላሉ።

ባይራክታር ቲቢ2

የጦር ድሮኖች ምን ያህል ውጤታማ ናቸው?

የሁለቱም ወገኖች ድሮኖች የጠላትን መገኛ በመለየት እና ዒላማዎች የተጠበቁ እንዲሆኑ በማደረግ ስኬታማ ናቸው።

“ኦርላን-10 ድሮኖች የጠላትን መገኛ በለዩ ከሦስት እስከ አምስት ደቂቃዎች ውስጥ የሩሲያ ጦር መሣሪያ በጠላት ላይ ጥቃትን ይፈጽማል” ይላሉ ዶ/ር ዋልቲንግ።

ያለ ድሮኖቹ እገዛ ጥቃት ለማድረስ ከ20 እስከ 30 ደቂቃ ሊጠይቅ ይችላል።

ዶ/ር ማርቲና ሚሮን ለንደን በሚገኘው ኪንግስ ኮሌጅ የመከላከያ ተመራማሪ ናቸው። ዩክሬን ያላትን ጦር መሳሪያ በድንብ እንድትጠቀም ድሮኖች ትልቅ ሚና አላቸው ይላሉ።

“በቀደመው ጊዜ የጠላትን ዒላማ ለመለየት ልዩ ኃይል መላክ ያስፈልግ ነበር። ይህ ልዩ ኃይል ሥራውን አከናውኖ ሲመለስ የተወሰኑትን ሊሰዋ ይችላል። አሁን ካጡም የሚያጡት ድሮን እንጂ የሰው ሕይወት አይደለም።”

ድሮኖች

የፎቶው ባለመብት, EPA

በጦርነቱ የመጀመሪያ ሳምንታት ዩክሬን ያሰማራቻቸው ባይራክታር ቲቢ 2 ድሮን ሰፊ ሙገሳን አግኝተው ነበር።

“የጠላትን የመሣሪያ ማከማቻ ሲያወድሙ ታይተዋል። ሞስክቫ የተባለቸው መርከብ እንድትሰጥምም ሚና ነበራቸው” ይላሉ ዶ/ር ሚሮን።

ሆኖም አብዛኛዎቹ ባይራክታር ቲቢ 2 ድሮኖች በሩሲያ የአየር መቃወሚያ ሥርዓት ከጥቅም ውጪ ሆነዋል።

“በመጠን ትልቅ መሆናቸው፣ በከፍተኛ ፍጥነት ለአመብረራቸው፣ የሚመሩበት ከፍታ አነስተኛ መሆኑ ለመመታት ቀላል አድርጓቸዋል” ይላሉ ዶ/ር ዋልቲንግ።

በቀላሉ የሚገኙ ድሮኖችን ለጦርነት መጠቀም

የጦር ድሮኖችን ለመተካት ውድ ናቸው። የአንዱ ባይራክታር ቲቢ 2 ድሮን ዋጋ ሁለት ሚሊዮን ዶላር ገደማ ነው።

ሁለቱም ወገኖች ወደ መደበኛዎቹ ድሮኖች ፊታቸውን እያዞሩ ነው።

በተለይም ዩክሬን ይህን መንገድ መከተል ጀምራለች። 1700 ፓውንድ የሚያወጣው ዲጂአይ ማቪክ 3 ደግሞ ተጠቃሽ ድሮን ነው።

አንድ የዩክሬን የድሮን አምራች የአገሪቱ ጦር ከ6000 በላይ ድሮኖች እንዳሏት ግምቱን አስቀምጧል። ይህን ማረጋገጥ ግን አልተቻለም።

ዲጄአይ ማቪክ 3

ለሌሎች አገለግሎቶች የተሰሩና በቀላሉ በገበያ ላይ ሊገኙ የሚችሉ መደበኛ ድሮኖች ላይ ቦንቦችን መግጠም ይቻላል።

ይሁን እንጂ እነዚህ ድሮኖች በስፋት ጥቅም ላይ እየዋሉ ያሉት የጠላትን መገኛ ለመለየት እና ለተኳሾች አቅጣጫ ለመስጠት ነው።

“ዩክሬን የሩሲያን ያህል መሣሪያ የላትም። ድሮን ተጠቅሞ ዒላማን በመለየት አነጣጥሮ መተኮስ ትልቅ እገዛ አለው” ይላሉ ዶ/ር ሚሮን።

ይሁን እንጂ እንደማንኛውም ሸቀጥ ከመደብር የሚገዙት ድሮኖች፣ ለጦር ዓላማ ተብሎ ከሚፈበረኩት ድሮኖች ጋር የሚስተካከሉ አይደሉም።

ዲጂአይ ማቪክ 30 ኪሎ ሜት ብቻ የሚደርስ ርቀትን በመጓዝ አገለግሎት ይሰጣል። በአየር ላይ መብረር የሚችለውም ለ46 ደቂቃ ብቻ ነው።

ተፋላሚዎቹ ራሳቸውን ከድሮን እንዴት ይከላከላሉ?

ሩሲያ ከጦር ድሮኖች ራሷን ለመከላከል ራዳር ትጠቀማለች። መደበኛ ድሮኖችን ለመከላከል ደግሞ የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎችን ጥቅም ላይ ታውላለች ሲሉ ዶ/ር ሚሮን ይገልጻሉ።

“የሩሲያ ኃይሎች ኤሌክትሮማግኔቲክ አካላትን ለይተው የሚመቱ መሳሪያዎች አሏቸው” ይላሉ። ይህ ደግሞ መደበኛ ድሮኖች ጂፒኤስ ተጠቅመው ቅኝት እንዳያደርጉ ያግዳል።

የሩሲያ ኃይሎች ኤሮስኮፕን የመሳሰሉ የበይነመረብ ዘዴዎችን ተግባራዊ ያደርጋሉ። በዚህ በመደበኛ ድሮኖቹ እና በተቆጣጣሪዎቻቸው መካከል ያለውን ግንኙነት ያቋርጣሉ።

በዚህ ዘዴ ድሮኖቹ እንዲከሰከሱ ወይም ወደ መነሻ ስፈራቸው እንዲመለሱ ያስገድዳሉ። መረጃም እንዳይስተላልፉ ያስተጓጉሏቸዋል።

እንደ ሩሲ ሪፖርት ከሆነ አንድ የዩክሬን ድሮን አማካጥ የአገልግሎት ቆይታ አንድ ሳምንት ብቻ ነው።

ስዊችብሌድ ድሮን

ድሮኖቹን ማን እያቀረበ ነው?

እንደ አሜሪካ መንግሥት ከሆነ ሩሲያ አሁን ሻሂድ የተሰኙ የጦር ድሮኖችን ከኢራን እየገዛች ነው። መቀመጫቸውን የመን ያደረጉት የሁቲ ኃይሎች በሳዑዲ እና በተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ የሚገኙ ዒላማዎቻቸውን ለመምታት እነዚህን ድሮኖች ይጠቀማሉ።

አሜሪካ በበኩሏ 700 የሚጠጉ “ካሚካዚ” የተባሉ የጦር ድሮኖችን ለዩክሬን እያቀረበች ነው።

እነዚህ በፈንጂዎች የተሞሉ ናቸው። ዒላማቸውን እስኪያገኙ ድረስ ሰማይ ላይ ያንዣብባሉ።

የኤሎን መስኩ ስፔስ ኤክስ ኩባንያም ስታርሊንክ የተባሉ የኮሙኒኬሽን ሳተላይቶች ለዩክሬን እያቀረበ ነው። ይህ ደግሞ በመደበኛ ድሮኖች እና በተቆጣጣሪያቸው መካከል ግንኙነት ለመፍጠር ያግዛል።

ዲጂአይ ማቪክ 3 የተባለውን ድሮን አምራች ለዩክሬንም ሆነ ለሩሲያ እነዚህን በራሪዎች ማቅረቡን አቁሟል።

ዩክሬን ለድሮኖቹ እንዴት እየከፈለች ነው?

ዩክሬን 200 የጦር ድሮኖችን ለመግዛት ገንዘብ ከለጋሾች እያሰባሰበች ነው።

“እንደ ባይራክታር ቲቢ2 ካሉ ትልልቅ ድሮኖች በተጨማሪ አነስተኛ እና የማይተጣጠፍ ክንፍ ያላቸውን ድሮኖች እያማተሩ ነው” ይላሉ ዶ/ር ዋልቲንግ።

የዩሮቪዥን የሙዚቃ ውድድር አሸናፊው ካሉሽ ኦርኬስትራ ሽልማቱን በ900 ሺህ ዶላር በመሸጥ የተገኘውን ገንዘብ ለድሮን መግዣ አውሎታል።

ይህ ከሙዚቃ ውድድር ከተበረከተው ሽልማት ሽያጭ የተገኘው ገንዘብ ከሩሲያ ጋር ለወራት በዘለቀ ጦርነት ውስጥ ለሚገኘው ሠራዊት ሦስት ፒዲ-2 ድሮኖችንለመግዛት ያስችላል።