56 ኪ.ሜ ተሰልፈው ወደ ዩክሬን የተመሙት የሩሲያ ብረት ለበስ ተሽከርካሪዎች መጨረሻ

ብረት ለበስ ተሽከርካሪዎች

የፎቶው ባለመብት, MAXAR TECHNOLOGIES 2022

ሩሲያ ዩክሬንን በወረረች በሦስት ቀናት ውስጥ 15.5 ኪሎ ሜትር የሚረዝሙ ብረት ለበስ ተሽከርካሪዎች በሳተላይት ታዩ።

በተመሳሳይ ቀን ቀን ጠዋት ከኪዬቭ በስተሰሜን በምትገኘው ቡቻ የሚኖረው የ67 ዓመቱ ቮሎዲሚር ሸርቢንይን ከመቶ የሚበልጡ የሩስያ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች ወደ ከተማው ሲገቡ ሱቁ በር ላይ ቆሞ ይመለከት ነበር።

ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን የዩክሬን ዋና ከተማን ለመቆጣጠር እና መንግሥትን ለማስወገድ ዕቅድ መንደፋቸውን ቮልዲሚር እና ሳተላይቱ ምስሎቹ ምስክሮች ነበሩ። በወታደራዊ አጠራር ደግሞ - አናቱን የመቁረጥ ጥቃት ይባላል።

ሰዓቱ ይነጉዳል። ከ48 ሰዓታት የብረት ለበስ ተሽከርካሪዎቹ የሸፈኑት ወደ 56 ኪሜ አደገ። በፈጣን ድል ታጅቦ ከመጓዝ ይልቅ ለሳምንታት ባለበት ቆመ። ከዚያም ደግሞ በአንድ ሌሊት የጠፋ መሰለ። ለመሆኑ ምን ተከሰተ? ይህን የሚያክለው ግዙፍ ኃይል እንዴት ከኪዬቭ ደጃፍ ተመሰለ?

ቢቢሲ በርካታ ሰዎችን አነጋግሯል። ይህም የመከላከያ ተሽከርካሪ ሠራተኞችን፣ ብሔራዊ እና ዓለም አቀፍ የስለላ አገልግሎቶችን፣ ሲቪሎችን፣ የቀድሞ ወታደሮችን እና የጦር ሠራዊት አባላትን ያካትታል።

በተጨማሪም ብረት ለበስ የጦር ተሽከርካሪዎቹ ዕቅድ ምን እንደሆነ እና ለምን በአስደናቂ ሁኔታ ሳይሳካ እንደቀረ የሚያሳዩ የሩሲያ ካርታዎችን እና ሰነዶችንም ማግኘት ችሏል።

ታሪኩ የሚጀምረው የክሬን በሰሜን አቅጣጫ ከቤላሩስ ጋር በምትዋሰንብት ድንበር ላይ ነው።

የ23 ዓመቱ ቭላዲስላቭ የዩክሬን 80ኛ የአየር ኃይል አባል ነው። የዕለቱን የመጀመሪያ ሲጋራውን ሊያጨስ ሲወጣ በድቅድቁ ሰማይ ላይ ደማቅ መብራቶችን አየ።

“መብራቶቹ ከጫካው ሲወጡ መመልከቴን አስታውሳለሁ። መጀመሪያ ላይ የመኪና መብራቶች ናቸው ብዬ አስቤ ነበር። ግን ከዚያ በኋላ ግራድስ (በራሳቸው የሚንቀሳቀሱ ሚሳኤሎች) እንደሆኑ ተረዳሁ። እየተኩሱብን ነበር” ይላል።

ጥቅጥቅ ባለው በቼርኖቤል ደን ውስጥ ሰፍሮ የነበረው የቭላዲላቭ ቡድን የመጀመሪያዎቹ የሩሲያ የጦር ተሽከርካሪዎች ወደ ዩክሬን ሲሻገሩ በጥበቃ ላይ ነበር።

“ምድር ሁሉ እየተንቀጠቀጠች ነበር። ታንክ ውስጥ ገብተህ ታውቃለህ? እንደ እሱ ያለ ሌላ ድምጽ የትም የለም። በጣም ኃይለኛ ነው።”

ሁሌም እንደሚታቃደው ምንም ዓይነት ጥቃት በሚደርስበት ጊዜ ቭላዲላቭ እና የተቀረው 80ኛው የብርጌድ አባላት ቸርኖቤልን ከኢቫንኪቭ ከተማ ጋር የሚያገናኘውን ድልድይ አፈነዱ።

ሩሲያውያን ተቀያሪ ድልድይ እንዲገነቡ ተገደዱ። ይህም ለቭላዲላቭ እና ባልደረቦቹ ወደ ኪዬቭ መመለሻ ጊዜ ሰጣቸው።

“መጀመሪያ ላይ ለምን እዚያው ቸርኖቤል ላይ አላቆምናቸውም? ስል ተገርሜ ጠይቄ ነበር። ሆኖም ስለ ጠላታችን መማር አለብን። ለዚህም ነው ይህንን ያደረግነው።"

ቦታው ለቤላሩስ ድንበር ቅርብ ነው። ዩክሬናውያን ተኩስ በመክፈት ሌላ ግጭት መጀመር አይችሉም። ቅድሚያ የሰጡት ወታደሮቻቸውን ወደ ግንባር ከመላካቸው በፊት የሩሲያን የውጊያ ዕቅድ መረዳት ነበር።

ቮሎዲሚር ሸርቢንይን

የፎቶው ባለመብት, BBC / CLAIRE JUDE PRESS

የምስሉ መግለጫ, ቮሎዲሚር ሸርቢንይን

የፑቲን ትልቁ ዕቅድ

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ከብዙ የመገናኛ ብዙኃን ዘገባዎች በተቃራኒ 56 ኪሎ ሜትር የሚረዝመው ከአሥር የተለያዩ የሩሲያ የጦር ክፍሎች የተወጣጣ ሠራዊት እንደነበር የዩክሬን ጦር ኃይል ገልጿል።

አንድ ቢቢሲ የተመለከተው የሩሲያ ሰነድ ጥቃቱ የሚፈጽምበትን የጊዜ ሰሌዳ ያሳያል። የመጀመሪያው ጦር የካቲት 17/2014 ዓ.ም. ሌሊት 10፡00 ላይ የዩክሬን ድንበር ካቋረጠ በኋላ 8፡55 ላይ በቀጥታ ኪዬቭ ይደርሳል።

ጥቃቱ ሁለት ቁልፍ ጉዳዮች ላይ የተመሠረተ ነው - ምስጢራዊነት እና ፍጥነት ላይ።

እንደ ሮያል ዩናይትድ ሰርቪስ ኢንስቲትዩት (አርዩኤስአይ) ከሆነ በዋና ከተማዋ ላይ የሚደርሰው ጥቃት እንደታቀደው ቢሳካ የሩሲያ ወታደሮች በኪዬቭ ሰሜናዊ ክፍል በዩክሬን ጦር ላይ ያላቸው የበላይነት 12፡1 ይሆን ነበር።

ሆኖም የፑቲን ምስጢራዊነት ዋጋ አስከፈለ። አብዛኞቹ የጦር አዛዦች እንኳን ትዕዛዝ የደረሳቸው ከወረራው ከ24 ሰዓታት በፊት አልነበረም።

በታክቲክ ደረጃ ከታየ ይህ ለጥቃት ተጋላጭ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። ምግብ፣ ነዳጅ እና ካርታ አልነበራቸውም። ትክክለኛ የመገናኛ መሳሪያዎችም አልያዙም። በቂ ጥይት አልታጠቁም። ለክረምቱ በሚሆን ደረጃ እንኳን በደንብ አልተዘጋጁም።

ትክክለኛ ጎማ ሳይገጥሙ የወጡት የሩሲያውያን የጦር ተሽከርካሪዎች በበረዶ ከመከበብ ባለፈ ጭቃ አላንቀሳቅስ አላቸው። ኢቫንኪቭ አቅራቢያ የነበሩ ገበሬዎች ታንኮቻቸውን ለማውጣት እንዲረዷቸው በሩሲያ ወታደሮች ጥያቄ እንደቀረበላቸው ገልጸዋል።

የሩሲያ ተሽከርካሪዎች በውሃ ከራሰው መሬት ለመራቅ ጥርጊያ መንገዶችን መጠቀም ተገደዋል። ይህም በሺህዎች የሚቆጠሩ መኪኖች በአንድ መስመር ሆነው እንዲጓዙ አስገድዷቸዋል።

በጦር ኃይሎቹ መካከል ያለው ግንኙነት ውስን በመሆኑ የትራፊክ መጨናነቅ መፍጠር ጀመሩ።

አንድ የጦር ኤክስፐርት እንዳስቀመጡት ደግሞ “በረዥም የጦር መኪኖች ወደ ጠላት ግዛት መጓዝ በጭራሽ አይመከርም።”

ከዩክሬን ጦር ሠራዊት በተሰጠ ቃል እና መረጃ መሠረት ከየካቲት 17 እስከ መጋቢት መጨረሻ ባለው ጊዜ ውስጥ የጦር ተሽከርካሪዎቹ የሸፈኑትን መሬት መለየት ችለናል። ከመንገድ ውጪ መጓዝ ባለመቻላቸው ከኪዬቭ በስተሰሜን ባሉት አብዛኞቹ ዋና ዋና መንገዶች ላይ ብቻ የነበሩ ናቸው።

የሩሲያ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች ርዝመት ወደ 56 ኪሎ ሜትር ባደገበት ወቅት 1,000 ታንኮች፣ 2,400 ሜካናይዝድ የእግረኛ ተሽከርካሪዎች እና 10,000 ወታደሮች እንዲሁም ምግብ፣ ነዳጅ እና ጥይቶች የጫኑ በደርዘን የሚቆጠሩ ድጋፍ ሰጪ መኪኖች ተሰልፈው ነበር።

ካርታ

የተባበረ ተቃውሞ

ከኪዬቭ በስተሰሜን የቆሙት እና የምግብ እና የነዳጅ እጥረት የነበረባቸው ሩሲያውያን ጠላታቸውን አቅልለው ነበር የተመለከቱት።

ለሦስት ቀናት ያህል ቮልዲሚር ሼርቢንይን እና አብዛኞቹ ጡረተኛ የሆኑ በጎ ፈቃደኞች የጦር ተሽከርካሪዎቹ ወደ ትውልድ መንደራቸው ቡቻ እንደሚደርሱ በማሰብ በዝግጅት ላይ ነበሩ።

ለ12 አንድ የጦር መሣሪያ የታጠቁ የአካባቢው ነዋሪዎች የመንገድ ምልክቶችን በሙሉ አጠፋፉ። የፍተሻ ኬላዎችን ግንብተው በመቶዎች የሚቆጠሩ የነዳጅ ቦምቦችንም አዘጋጁ።

በመጨረሻም እሑድ ጠዋት የሩሲያ ታንኮች ወደ ከተማው ገቡ።

ለሰላሳ ደቂቃዎች ያህል ቮልዲሚር እና ባልደረቦቹ ታንኮቹን በያዙት ትንሽ ነገር አጠቁ።

“ሁለቱን ተሽከርካሪዎች አቃጥለን ጉዞውን አዘገየን” ብሏል ቮሎዲሚር።

በኋላ ላይ ግን የአጸፋ ምላሽ ተሰጠ።

የ30 ዓመቱ ማክሲም ሽኮሮፓር “የጠርሙስ ቦንቦችን ስንጥል ሲያዩ ተኩስ ከፈቱ። እኔ መጠጥ ቤት ነው እሰራ የነበረው። ምንም ዓይነት ወታደራዊ ሥልጠና አልነበረኝም” ብሏል።

ከግማሽ ሰዓት በኋላ የቮልዲሚር ቡድን አባላት በሙሉ በጥይት ተመትተው ወደ ሆስፒታል ተወሰዱ።

ቮሎዲሚር ግን ውጊያውን ቀጠለ። በኪዬቭ ክልል ውስጥ ካሉ ሲቪሎች የጦር ተሽከርካሪዎችን በመለየት መረጃ ወደ ዩክሬን ባለሥልጣናት መላክ ጀመረ።

በሌላኛው ጫፍ ደግሞ የ23 ዓመቱ የኢርፒን ምክትል አስተዳዳሪ ሮማን ፖሆሪሊል ነበር።

“ለሦስት ቀናት እንቅልፍ አልወሰደንም። እኔና የሥራ ባልደረባዬ የምክር ቤቱን የስልክ መስመር እንቆጣጠር ነበር” ብሏል።

ስለጦር ተሽከርካሪዎቹ እና ለጠላት ምልክት በማድረግ መረጃ ስለሚሰጡ ባንዳዎች መልዕክት ይቀበሉ ነበር።

ቀን ቀን የምክር ቤት አባል የሆነው ሮማን በምሽት ደግሞ የስለላ ባለሙያ ነው። ስመ ገናናው ዲፕ ስቴት የተባለው ድረ ገጽ መሥራች ሲሆን፣ የማኅበራዊ ሚዲያ እና የስለላ ዘገባዎችን በማቀናበር በድረ ገጹ ላይ ይለጥፋል።

“ሩሲያውያኑ ወደ ኪዬቭ ሲጓዙ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ቪዲዮዎችን ይለጥፉ ነበር። ቪዲዮዎቹን በድጋሚ በመለጠፍ እንቅስቃሴያቸውን እናጋለጥ ነበር። እነሱ ለጉራ ያሳዩ ነበር። ይህን ግነ ጎድቷቸዋል።”

በዋና ከተማዋ ኪዬቭ ላይ ጥቃት በተሰነዘረበት ወቅት በጣም አስፈላጊው ነገር የዩክሬናውያን የአንድነት ስሜት ነበር ይላል ሮማን።

“ሁሉም ሰው የበኩሉን እያደረገ ነበር። የመጀመሪያዎቹ ጥቂት ቀናት በጣም ከባድ እንደነበር አምናለሁ። ነገር ግን ሲቪሎችን የሚረዱ የጦር አባላት ነበሩ። ሁሉም ሰው ከተማውን ለመከላከል ፍላጎት ነበረው።”

በኪዬቭ ክልል ባሉ ከተሞች እና መንደሮች ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ ጥቃቶች በጦር ተሽከርካሪዎቹ ላይ ተፈጽመዋል። ይህም የሆነው ቤት ውስጥ የተሠሩ መሳሪያ ከታጠቁ ሰላማዊ ሰዎች እስከ አነስተኛ ሜካናይዝድ እና መድፍ ድረስ በታጠቁ ሰዎች ነው።

ቮሎዲሚር (ከመሃል) እና ወዶ ዘማች ጓዶቹ

የፎቶው ባለመብት, BBC / CLAIRE JUDE PRESS

የምስሉ መግለጫ, ቮሎዲሚር (ከመሃል) እና ወዶ ዘማች ጓዶቹ

ጊዜ ያለፈባቸው ስልቶች

ከዩክሬናውያን በተቃራኒ የሩሲያ ኃይሎች በመሬት ላይ ተለዋዋጭ ውሳኔዎችን ለማድረግ አለመቻላቸውን በተደጋጋሚ አሳይተዋል።

“ሁሉም ሩሲያውያን ‘ምስጢራዊ’ የሚሉ ትልልቅ የብረት ሳጥኖችን ይዘው ነበር። በደፈጣ ጥቃት ወቅት አንዱን ያዝነው። መንገዳቸውን ምልክት ያደረጉበትን ካርታዎች አግኝተናል። ከዚያ በኋላ ሙሉ ስልታቸውን ለማወቅ ችለናል” ሲል የ80ኛው ብርጌድ ባልደረባ ሆነው ቭላዲስላቭ ተናግሯል።

የፑቲን ምስጢራዊነት መሬት ላይ ያሉ የሩሲያ አዛዦች ጭምር ስለ ጦርነቱ ዕቅድ ምንም እንዳያውቁ አድርጓቸዋል።

የመንቀሳቀሻ ካርታዎቻቸውም ጊዜ ያለፈባቸው ነበሩ። ቢቢሲ ከወረራው በኋላ የሩሲያ ወታደሮች ይዘዋቸው የነበሩ ካርታዎችን ተመልክቷል። በዚህም ከ1960ዎቹ እና 70ዎቹ በፊት የነበሩትን ጭምር አግኝቷል።

በዚህም ሳቢያ በሚጠቀሙባቸው ካርታዎች ላይ ቀደም ሲል ያልነበሩ አዳዲስ ከተሞች አሁን ተቆርቁረዋል። በተለያዩ ክፍሎች መካከል የሚግባቡበት እጅግ በጣም ጊዜ ያለፈበት ባንዲራዎችንም አግኝቷል።

ዩክሬን የተሳካላት አንዱ ዘዴ ከጦር ተሽከርካሪዎቹ ቀድመው ድልድዮችን እና ግድቦችን ማፍረሳቸው ነው። ይህም ሩሲያውያን በሌላ አቅጣጫ እንዲጓዙ አስገደዳቸው። ካላቸው አሮጌ ካርታዎች በተጨማሪ ከበላይ አዛዦቻቸው ጋር የነበራቸው የተገደበ ግንኙነት በፈጠረው የውሳኔ እጥረት የሩሲያ ጦር በተደጋጋሚ ተሰናክሏል።

በርካታ የሳተላይት ምስሎችም የሩሲያ የጦር ተሽከርካሪዎች ግራ በመጋባት ሲሸከረከሩ ያሳያሉ።

የወደሙ የሩሲያ የጦር ተሽከርካሪዎች በሆስቶሜል

የፎቶው ባለመብት, BBC / CLAIRE JUDE PRESS

የምስሉ መግለጫ, የወደሙ የሩሲያ የጦር ተሽከርካሪዎች በሆስቶሜል

ህልም

በዩክሬን የአየር ድብደባ እና የመድፍ ጥቃት ግፊት የሩሲያ የጦር ተሽከርካሪዎች ከኪዬቭ ከተማ ደጃፍ ላይ እንዲቆሙ ተደረገ። ይህ ወቅት በተሽከርካሪዎቹ አቅራቢያ ለሚኖሩ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሲቪሎች ያሳለፉት ጊዜ በጣም አሰቃቂ ነበር።

“ሁሉንም ነገር ዘርፈዋል። ሱቆቹን ባዶ አደርገዋል። ሲቪሎችንም እንደ ጋሻ ይጠቀሙ ነበር” ይላል ቭላዲላቭ።

በኪዬቭ ሰሜን እና ምዕራብ አቅጣጫ በሚገኙ መንደሮች እና ከተሞች የተፈጸሙትን ግፎች ለጦር ወንጀል ማስረጃነት አስፈላጊ በመሆናቸው፣ ዓለም አቀፉን የወንጀለኞች ፍርድ ቤትን ጨምሮ በብዙ ባለሥልጣናት እየተጣራ ይገኛል።

“በፍተሻ ጣቢያ ላይ ሳለሁ [የሩሲያ ወታደሮች] ከጀርባ ወደ እኛ መተኮስ ጀመሩ። በመሃል ሲቪሎች መግቢያ መውጫ አጡ። በጣም አሰቃቂ ነበር” ይላል ቭላዲስላቭ።

ከአራት ሳምንታት በኋላ ሩሲያውያን ለቀው መውጣት ጀመሩ።

የቀሩት ትላልቅ ሁለት ሻለቃዎች ሆስቶሜል አውሮፕላን ማረፊያ አቅራቢያ ተሸነፉ። በዚድቪዝሂቭካ መንደር ትተዋቸው የሄዱ 370 የጦር ተሽከርካሪዎች በመድፍ ወድመዋል።

የዩክሬን ጦር እስከ መጋቢት አጋማሽ ድረስ ማጥቃቱን ቀጠለ። በኋላም ሩሲያውያን ከኪዬቭ ዙሪያ ሙሉ በሙሉ አፈገፈጉ።

ኪዬቭ ላይ እንደገና ጥቃት ሊሰነዝር እንደሚችል ቢገመትም፤ እንደብዙ የጦር ባለሙያዎች ከሆነ የሩሲያ ወታደሮች ወደ ቤላሩስ ድንበር ሲሰማሩ ስላልታዩ ይህ ሊሆን እንደማይችል ይስማማሉ።

ሩሲያ ወደ ምሥራቃዊቷ የኢንዱስትሪ ማዕከል ዶንባስ መግፋቷን ከመቀጠል ባለፈ በደቡብ በኩል በኼርሶን፣ ሜሊቶፕል እና ዛፖሪዢያ ክልሎች አቅጣጫም ጥቃቷን ቀጥላለች።

“በቸርኖቤል የነበረኝን ያንን ምሽት ሁልጊዜም አስታውሰዋለሁ። ከጓደኛዬ ጋር ነበር ለማጨስ የወጣሁት። ሲጋራዬን ስጨርስ ጦርነቱ ተጀመረ” ይላል ቭላዲስላቭ።

“ልክ በዚያ ምሽት እንዳደረግነው፣ በፈረቃችን ቀጥለን ሲጋራ ስናጨስ ጦርነቱን አሸንፈን መጠናቀቁን የመስማት ህልም እኔ እና ጓደኛዬ አለን” ብሏል።